Saturday, 09 November 2019 13:09

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

     ‹‹እውነትን ገልብጦ ማሽሞንሞን ጥበብ እንጂ ፍትህ አይደለም››
                
             ሴትዮዋ አዋቂ ዘንድ ሄዳ፡-
‹‹ባለቤቴ አስቸገረኝ›› ትለዋለች፡፡
‹‹ምነው?››
‹‹መግባባት አልቻልንም፣ ደርሶ ቱግ ይላል፣ አያዳምጠኝም››…
አዋቂውም የሚጠይቁትን ከጠየቁ በኋላ፡-
‹‹ጉዳይሽ ቀላል ነው፣ መድሃኒቱን ሰርቼ እሰጥሻለሁ፡፡ ከዛ በፊት ግን የምታደርጊው ነገር አለ›› አሏት፡፡
‹‹ችግር የለም፡፡ ምን ላድርግ?››
‹‹መድሃኒቱ የሚቀመመው ከአንበሳ ቅንድብ ነው፡፡ መጀመሪያ እሱን አምጪልኝ››
‹‹እ?... ከአንበሳ ቅንድብ?››
‹‹አዎ ልጄ፡፡ ያለሱ አይቻልም››…
ሴትየዋም ባሌን ከማጣ የተባልኩትን ልሞክር ብላ ወደ አያ አንበሶ ዋሻ ትሄዳለች:: እየተመላለሰችም ባህሪውን አጠናች:: የሚወደውን ምግብ እያቀረበችለት፣ ከማይፈልገው ነገር እየራቀች ተዋደዱና ጓደኛሞች ሆኑ፡፡ አንድ ቀን እየደባበሰችውና እያጫወተችው የምትፈልገውን የቅንድብ ፀጉር ቆርጣ ወሰደች፡፡ አዋቂውን ለማግኘትም ተቻኮለች፡፡ እቤቱ ደርሳ ስታየው ግን ከት ብላ ስቃ፣ የያዘችውን ወርውራ ወደ ቤቷ ተመለሰች::… ምን ገጠማት ይሆን?
* * *
አዳዲስ ነገሮችን መሻት፤ ለተሻለ ሰብዕና፣ ለላቀ ሕይወት መዳዳት መልካም ነው፡፡ አንዳንዶች “መክሊትን ፍለጋ›› ይሉታል፡፡… መዳረሻው ባልታወቀ ጎዳና መመላለስ!!
ወዳጄ፡- በዚሁ መንገድ መውጣትና መውረዳችን እስካልቀረ ድረስ እግረ መንገዳችንን ሲያጋጥሙን የነበሩትን፣ ልብ ሳንል ያለፍናቸውን ነገሮች እንደገና በአዲስ ዓይን መመልከት ያስፈልገናል፡፡ ‹ዘ አልኬሚ› መጽሃፍ ላይ እንዳየነው እንደ ወጣቱ ሳንቲያጎ ዞረን፣ ዞረን፣ ተንከራተን፣ ከሕይወት ተምረን፣ በቀኑ መጨረሻ  ያወቅነው፣ ዕድላችን (our treasure box) የተቀበረው ለዘመናት ቁጭ ብለን፣ በግ ስናግድ ከነበርንበት ድንጋይ ስር ሊሆን ይችላል::
ወዳጄ፡- አስፈላጊና ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ ዋናውን ምሰሶ፣ ዋናውን የሀሳብ ማዕከል ሳንነካ፣ ወልካፋዎቹን ማገሮች በመቀየር፣ ትርኪምርኪ ስሞታዎችን በማራገፍ… ጎጇችንን ማነፅ፣ እምነታችንን ማቃናት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የምንጽፈው ባህረ ሃሳብ እንዳለ ሆኖ የምንጽፍበትን ቀለምና ወረቀት መምረጥ ወይም ማሻሻል፤ ባትሪውን ሳይሆን ድንጋዩን ወይም የብርሃኑን ቀለም መቀየር ማለት ነው፡፡ ከለር ስለተቀየረ የምናይበት እንጂ የምናየው ነገር አይለወጥም፡፡ … እንደ ፀሐይ መከላከያ መነጽር ማለት ነው፡፡ ስሜታችን ላይ ግን ተፅዕኖ አለው::
ወዳጄ፡- የስሜት ሕዋሳቶቻችንን ማኮማተርና ማፍታታት፣ ትኩረትንና አመለካከትን የማጉላትና የማደብዘዝ ጉልበት አለው፡፡ ማየትና ማስተዋል፣ ማድመጥና መስማት፣ ልብ ማለትና አለማለት… ልዩነት የሚኖራቸው ለዚህ ነው፡፡ ዲቴክቲቭ ሆልእስ ‹‹ስለተመለከትኩ አየሁ›› እንዳለው፡፡
ምናባዊ አመለካከት ይቅርና በእጅ የምንዳስሳቸውን፣ በዓይን የምናያቸውን ነገሮች እንኳ የምንገልጽበት አቀራረብ፣ ውስጣዊና መንፈሳዊ ፍላጎታችን መገለጫ ናቸው… የሚሉ ምሁራን አሉ:: የግማሽ ብርጭቆውን ውሃ ጉዳይ እንደ ምሳሌ ብንወስድ፡- ጨለምተኝነትን (ፔሲሚዝምን) ወይም ተስፈኝነትን (ኦፕቲሚዝምን) ካማከለ የዕይታ አንፃር ጋር ያያዙታል፡፡ አንዳንዶች ‹በግማሽ የጎደለ› ከማለት ‹ግማሹ የሞላ› ማለት ይሻላል ሲሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ እውነትን ገልብጦ ማሽሞንሞን ‹አርት› እንጂ ‹ፍትህ› አይደለም፤ ጎዶሎውን ጎዶሎ ማለት ተገቢ ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡
እኔ እንደሚመስለኝ አመለካከት (Observation) እንደ ቃላት ትርጉም በተሻለ ሁኔታ የሚገለፀው ወይም የሚብራራው መነሻ ጉዳዩን ወይም የተጠቀሰበትን ዐውድ (Context) መሰረት ሲያደርግ ወይም ባለቤት ሲኖረው ነው:: ውሃ ላስፈለገው ወይም ውሃውን ላስቀመጠው ሰው፤ ብርጭቆው ውስጥ ውሃ መኖሩ ብቻ ጥቅም አለው - መጠኑ ምንም ይሁን ምንም፡፡
ሃሳብም እንዲሁ ነው፡፡ ቁም ነገር እስካለው ድረስ ለሚፈልጉት ትልቅ ነው፡፡ ሀሳብ ከብርጭቆው ውሃ የሚለየው ሲሞላ የሚፈስ ወይም ብርጭቆው ሲሰበር ተደፍቶ የሚባክን አለመሆኑ ነው:: ሀሳብ የመጠንና የወሰን ልክ የለውም፡፡ ሀሳብ የሚመጠነው፤ በየአንዳንዱ ሰው የመረዳት አቅም (Capacity) ሲለካ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ትልቅ ነገር ሁሉ የተሰራው ከትናንሽ ንጥረ ነገሮች መሆኑን አትዘንጋ፡፡ ትንሽ ከሌለ ትልቅ፣ ትልቅ ከሌለ ትንሽ የለም፤ አይነጣጠሉም:: አንድ ነጥብ ባትኖር ትሪያንግል፣ ክብ ወይም ቀጥታ መስመር፤ አንድ ጠብታ ውሃ ባትኖር ውቅያኖስ፣ አንድ ሕዋስ ባትኖር ሕይወት የለም፡፡ እዚህ ጋ ሳይንስና ጥበብ አንድ ይሆናሉ፡፡ በአመለካከት ግን ሳይንስ ከዩኒቨርሳል ወደ ፓርቲኩላር ሲቆፈር… ጥበብ ከተቃራኒው ይጀምራል፡፡… ከፓርቲኩላር ወደ ዩኒቨርሳል፡፡
‹‹The portion is the part of the whole and the whole is the part of the portion››
ወዳጄ፡- በተፈጥሮ ስሌት ‹ብቻ› የሚባል ነገር የለም፡፡ አንድ ‹ቁጥር› እንጂ ‹being › አይደለም:: ‹አንድ እንሁን› ስንል፣ ሁለት፣ ሶስት ቁጥር የማብዛትና የመቀነስ ጉዳይ የለበትም፡፡ የጋራ ህልውና (being) እንገነባ ማለት እንጂ… እንደ ትዳር፣ እንደ አገር!!... ከታላቁ ሎርድ ባይረን ‹‹የፍቅር ፍልስፍና›› (Love’s philosophy) ከተሰኘ ዝነኛ ግጥሙ እንቀንጭብ…
The fountains mingle with the river
 And the rivers with the ocean,
The winds of heaven mix forever
With a sweet emotion;
Nothing in the world is single,
All things by a law divine,
In one spirit meet and mingle,
Why not I within?
እዚህ ጋ ፍቅርና መደመር አንድ ናቸው… ህልውና!!...
እናም ወዳጄ፡- በፈለግኸው አቅጣጫ ተመልከት፡፡ አዲስ ዓይን ይኑርህ ብቻ:: … በፍቅር የአንበሳ ቅንድብ ይቆረጣል፡፡ አይመስልህም?
* * *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሴትየዋ የተባለችውን ይዛ አዋቂው ሰው ዘንድ ደረሰች:: ዓይኑን እንዳየች ባነነች፤ ‹‹አንበሳ አልምደሽ ቅንድቡን የቆረጥሽ ጀግና… ባልሽን መግራት እንዴት ያቅትሻል?›› እንደሚላት ገባት፡፡ እየሳቀች ተመለሰች፡፡ በነገራችን ላይ ‹ዘ ሳይኮይድ› በሚለው ግጥሙ የሚታወቀውና
“I met a man who is not there” በማለት የፃፈልን ማን ነበር?
ወዳጄ፡- የሌለ ነገር ከመፈለግ የአንበሳ ቅንድብ ማምጣት ወይም የነበረውን በአዲስ ዓይን ማየት አይሻልም?
ሠላም!!

Read 1720 times