Monday, 11 November 2019 00:00

ቻይና የኢንተርኔት ነጻነትን በማፈን ዘንድሮም ከአለም አንደኛ ናት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     ሁዋዌ በ5ጂ ኢንተርኔት ፍጥነት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበ

              የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጥና ስለላን ጨምሮ ሌሎች ነጻነትን የሚጋፉ እርምጃዎችን በመውሰድ የዜጎችን የኢንተርኔት ነጻነት በማፈን ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት ከአለም አገራት ቀዳሚነቱን ይዛ የዘለቀችው ቻይና፣ ዘንድሮም በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ ተዘግቧል፡፡
ፍሪደም ሃውስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም በ56 የአለም አገራት ያካሄደውን ጥናት መሰረት በማድረግ ሰሞኑን ያወጣውን አለማቀፍ የኢንተርኔት ሁኔታ አመላካች ሪፖርት ጠቅሶ ዴይሊ ሜይል እንደዘገበው፣ ቻይና በአመቱ እጅግ የከፋውን የኢንተርኔት ነጻነት አፈና በመፈጸም ቀዳሚነቱን ስትይዝ፣ ኢራንና ሶርያ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ይከተላሉ፡፡
በሪፖርቱ የዜጎችን የኢንተርኔት አገልግሎት ነጻነት በማክበር ከአለማችን ቀዳሚዋ አገር ተብላ የተጠቀሰችው አይስላንድ ስትሆን፣ ኢስቶኒያና ካናዳ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ፣ በ5ጂ የሞባይል ኢንተርኔት ፍጥነት አዲስ ክብረ ወሰን ያስመዘገበበትንና በሰከንድ ከ2.92 ጊጋ ባይት በላይ ፍጥነት ያለውን አዲስ ኔትወርክ በስራ ላይ ማዋሉን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ሁዋዌ ከቱርክ ቴሎኮም ኩባንያ ጋር በመተባበር በኢስታምቡል ይፋ ያደረገው ይህ እጅግ ፈጣን የሞባይል ኔትወርክ፣ በሁዋዌ ሜት ኤክስ ስማርት ፎን አማካይነት ተሞክሮ በፍጥነት አዲስ የአለም ክብረወሰን ማስመዝገቡ ታውቋል፡፡
ኩባንያው ይህንን እጅግ ፈጣን ኔትወርክ በስራ ላይ ለማዋል የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሙን ማስታወቁን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ይህ አዲስ እምርታ ኩባንያው ከአሜሪካ መንግስት እየተደረገበት ያለውን ጫና ተቋቁሞ በአለማቀፉ የሞባይል ስልኮች ገበያ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

Read 7808 times