Sunday, 10 November 2019 00:00

ሀገር ስትፈርስ እኛም እንፈርሳለን!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

    ተስፋ በትዝታ መቃብር ላይ የሚተከል አበባን ይመስላል፡፡ የማይመለሰው ትናንት፤ ነገ ላይ ጥቁር ጥላ እንዳይጥል በብሩህ ልብና ዐይን የተሻለውንና በጎውን ማሰብና መተለም ያስፈልጋል፡፡ ለትናንት እያላዘኑ፣ ነገን ከትናንት የባሰ ለማጨለም መባከን ኪሳራ እንጂ ትርፍ  የለውም፡፡   
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንደ ፋሽን የተያዘውና ለአንዳንዶች አትራፊ መስሎ የታያቸው ነገር ቢኖር፤ የትዝታን ልቃቂት እየተረተሩ ማልቀስና ማስቀለስ፣ ደረት ሳይመቱ የሌሎችን ደረት ማስደለቅ ነው:: “የእገሌ ብሔር እገሌ በሚባል ብሔር ግፍ ደርሶበታል” እያሉ ድርሳን እየመዘዙ ህዝብን እርስበርስ ማጋጨት፣ ተጨማሪ እሳት ለኩሶ አገርን ወደባሰ አዘቅት ከማስገባት ውጭ የሚያመጣው ጥቅም የለም፡፡   
ስለ ብሔር ካነሳን አይቀር አደባባይ ላይ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ከሚያላዝኑት ባለፈ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን እንደሚጐዳ ማሰብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞም ሆነ የአማራ ብሔር ዛሬ የሚወራውን ያህል ማዶ ለማዶ የቆሙና ሩቅ አይደሉም፡፡ እውነታው የፖለቲካ ነጋዴዎች  እንደሚያወሩት የሚናናቅም አይደለም፡፡ ለዚህም ደግሞ ሁለቱ ብሔሮች  በጋብቻ መተሳሰራቸውና መዋለዳቸው ብቻውን በቂ ማሳያ ነው፡፡  
ለምሳሌ እኔ ልጅነቴን ያሳለፍኩበት የሲዳማ ሕዝብ፣ በተለይ በከተሞች የነበረው ሁኔታ ዛሬ ከምናስበው የተለየ ነው፡፡ ከተማው ላይ በጣም ብዙ የኦሮሞ ተወላጆች በእህል በጌሾ፣ በቡና --- ንግድ ተሰማርተዋል፣ እነዚህ በወሊሶ አቅጣጫ የመጡ ናቸው፡፡ የእኛ ጐረቤት ከነበሩት የሰላሌ ሰው ጀምሮ የጓደኞቼ አባት አባባ ጃተማን፣ አሁንም ድረስ ቤተሰቤ የሆኑትን የጋሽ ተካን ቤተሰብ ጨምሮ ብዙዎቹ  ባለርስት ሆነው እንደመጡ፣ አንዳንዶቹም በዘመነ ደርግ ጭርታው ውስጥ እንደገቡ ይታወቃል፡፡ የሲዳማና የጌዲኦ ሕዝብ “ነፍጠኛ ወይም አማራ” የሚለው አማራውን ብቻ አይደለም፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የኦሮሞ ተወላጆች በዚያ ክልል ባለርስት ሆነውና በንግድ ስራ ተሠማርተው ኖረዋል፡፡
በሌላ በኩል ወደ ምኒልክ ዘመቻም ብንመለስ፤ ምኒልክ ጦርነት የገጠሙት አማራ ካልሆነው ብሔር ጋር ብቻ አልነበረም፡፡ ከአማራውም ጋር ገጥመዋል፡፡ ከአማራው ጋር ሲገጥሙ ደግሞ የሠራዊታቸው አዛዦች አማራና ኦሮሞ ነበሩ፡፡ ዓላማውም ሀገር አንድ የማድረግ አካሄድ መሆኑን የሁሉም ልብ ያውቀዋል፡፡
የሆኖ ሆኖ ታሪክን ለታሪክ ባለሙያዎች ትተን፣ ዛሬን መኖርና ነገን ተስፋ ማድረግ ነው ያለብን፡፡ ትላንትን መለወጥ አንችልም፤በዚያ ላይ ማንም ላልኖረበት ዘመን ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዛሬው ትውልድም የታሪክ ንትርክና ውዝግብ የሚጠቅመው ነገር የለም:: ለትላንት እያለቀስን ድሃውን ህዝብ፣ በረሃብና በድንቁርና ዕድሜ ዘመኑን እንዲፈጅ ልንፈርድበት  አይገባም፡፡ ቂም ቀስቅሶ መለቃቀስና ሰይፍ መምዘዝ፣ ከድህነትና እልቂት በቀር የሚያመጣው ፋይዳ የለም፡፡
ይልቁንም ጽንፍ የረገጡ ህልሞቻችንን አቀራርበን፣ ዳቦ ከመለመን የምንወጣበትን መላ መዘየድ  የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች፡የሚጋጩ ህልሞች” በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚሉት፤ የኦሮሞ ልሂቃን “ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በጆሮዬ አልሰማም” ከማለት፤ አማራውም የኢትዮጵያዊነት የምስክር ወረቀት ሰጪና ከልካይ አድርጐ ራስን ከመሾም መታቀብ ያስፈልጋል፡፡
አሁን የሚያስፈልገን ጠብ ሳይሆን እርቅ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገን መከፋፈል ሳይሆን አንድነታችንን ማጥበቅና መጠበቅ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገን ለወጣቶች የተሻለ የሥራና የትምህርት ዕድል መፍጠርና ማመቻቸት ነው:: የትላንት በደሎችን እየቆሰቆሱ፣ ትውልዱን ለጥፋት ማነሳሳት አደጋ አለው፡፡  ግጭት ሲፈጠር ዋጋ የሚያስከፍለው አንድን ወገን ብቻ አይደለም፡፡ ተደጋጋሚ ግጭቶችና የጥላቻ ቅስቀሳዎች ጭልጥ ወዳለ ጦርነት ውስጥ ሊያስገቡን እንደሚችሉ ማሰብ ብልህነት ነው:: ከጦርነት ደግሞ ማንም የሚያተርፍ የለም:: ውጤቱ እልቂትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም እንጐዳለን፤ ሁላችንም እንጠፋለን::  በድህነታችን ላይ ሌላ ውርደትና ቅሌት እንጨምራለን፡፡  
አሜሪካ በእርስበርስ ጦርነት ትልቅ ዋጋ ከፍላለች፡፡ በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ከሞተባት ሰው ይልቅ በሰሜኑና በደቡቡ ጦርነት ያለቀባት ይበልጣል፡፡ በአንደኛው የዓለም ጦርነት 117 ሺ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት 400 ሺ ያህል ሰዎችን ያጣች ሲሆን በእርስበርስ ጦርነቱ ደግሞ 620 ሺ ሰዎችን አጥታለች፡፡ ከአንድ ቤት ውስጥ ሶስትና አራት ወጣቶችም ሞተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሀገሪቱ የገባችበት የኢኮኖሚ አዘቅት ቀላል አልነበረም፡፡
ልዩነት ያለብን ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለንም፡፡ ከእኛ በእጅጉ የላቀ ቁጥር ያላቸው ሀገራት በሰላም እየኖሩ ሀገራቸውን ከበለፀጉት ሀገራት ተርታ ለማሳለፍ ደፋ ቀና ሲሉ፣ እኛ በትዝታ ሀውልቶች ሥር ተደፍተን ማልቀስና ጦር መቀስቀስ ለምን እንዳስፈለገን ጨርሶ አይገባኝም፡፡
በዚህ የፈተና ወቅት እንኳ በአገራችን በአርአያነት የሚጠቀሱ የሰላምና የፍቅር ተምሳሌቶች አይተናል፡፡ ባለፈው ዓመት የጋሞ ሽማግሌዎች ያከናወኑት ቅዱስ ተግባር፤ በኢትዮጵያዊነት እንድንኮራና በአገራችን ተስፋ እንዳንቆርጥ አድርጎናል፡፡ ብዙ ያልተነገረለት የወላይታ ህዝብም በእጅጉ መደነቅ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በቅርቡ ወደ ወላይታ ሶዶ ዘልቃ የነበረች ጋዜጠኛ ወዳጄ እንደነገረችኝ፤ የወላይታ ህዝብ የአዲስ ዓመት በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት ለአንድ የቀድሞ መንግስት ባለሥልጣን የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሰውየው ደጃዝማች ወልደሰማያት ገብረወልድ የሚባሉ የንጉሡ ዘመን አውራጃ ገዢ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው በሥልጣን ዘመናቸው እንደ ማንኛውም የፊውዳሉ ሥርዓት ገዢዎች፣ የራሳቸው የሆነ ውስንነትና ችግር ቢኖርባቸውም፣ ለአውራጃው ህዝብ ላበረከቱት የልማት ሥራዎች ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የወላይታን ህዝብ ሥልጡንነትና የዳበረና የዘመነ ባህል ባለቤት  መሆኑን ነው፡፡
በነገራችን ላይ ማፈናቀል በበዛበት ባለፉት ዓመታት፣ በወላይታ ዞን፣ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆችን “መጤ ናችሁ፤ከሀገራችን ውጡ” ብለው የጠላትነትና ጠባብነት ስሜት አላንፀባረቁም፡፡ ልሂቃኖቻቸው ያለፈውን በደል ከመፈለፈልና ሙሾ ከማውረድ ይልቅ አብሮ በመኖርና ተስፋና ፍቅር ላይ በማተኮር አርአያነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ከሰከነና ከሰለጠነ ባህላቸው መማር ያለብን ይመስለኛል፡፡  
የሰው ልጅ ማህበራዊ ፍጡር ነው፤ በማህበር እንዲኖር የተፈጠረና ከማህበራዊ መስተጋብር ውጭ መኖር የማይችል ፍጡር ነው፡፡ በተለይ በተመሳሳይ ሥነ ልቡና በመዋለድ፣ በክርስትናና በጉዲፈቻ የተጣመርን አንድ ህዝብ፤ የጋራ ታሪክና ሥነልቡና እንደሌለው አድርጐ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ለመሆኑ ተጋብቶ ከመዋለድ የበለጠ ዝምድና አለ እንዴ?
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበረው ቶማስ ጀፈርሰን፡- “Man was created for social intercourse but social intercourse cannot be maintained without a sense of justice, then man must have been created with a sense of justice” ያለው በዋዛ አይደለም፡፡
የሰው ልጅ በፍትህ ጠገግ ሥር በነፃነት መኖር እንዲችል፣ የማህበራዊ መስተጋብሩ ቅጥር ከፍ ማለት አለበት፡፡ መንግሥትም የፍትህ ዋልታዎች ተናግተው፣ ህዝቡ እረኛ የሌለው በግ እንዳይሆን መትጋት ይጠበቅበታል:: በየአደባባዩ የሚናገረውን በገቢር ማሳየት አለበት፡፡ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ማድረግ ያልቻለ መንግሥት፣ ዓይኑን በጨው አጥቦ ግብር ለመቀበል ማፍጠጥ አይችልም፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ተቀባይነታቸው ደካማ ቢሆንም፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚከበሩ ግለሰብ ሰባኪዎችና መምህራን፤ በህዝቡ ውስጥ እየተረጨ ያለውን የጥላቻና የመለያየት መርዝ ለማክሸፍ መትጋት አለባቸው፡፡ ፍቅርን ሰላምን አንድነትንና መከባበርን ደጋግመው መስበክና ማስተርም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተረፈ “በጥንቃቄ ይጠብቅሃል፤ ማስተዋል ይጋርድሃል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር  አጽንኦት ቢሰጠው ከመከራ ያድነናል ብዬ አምናለሁ፡፡
በገጣሚ አሌክስ አብርሃም ግጥም ሃሳቤን ልቋጭ፡፡ እነሆ፡-
ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ---ላንድ እውነት ሺህ              ስም መሰየም፣
ፊደል ገደፍክ-- ሥም አሳሳትክ----ባፍ እላፊ          መቀያየም
    በቃል ቁርሾ መቆራቆስ
ወይ አንቀር ወይ አንደርስ
 ጦር መማዘዝ መወጋገዝ
ጠባብ ምኞት፣ ጠባብ ዓለም፣
ስጋ ለብሶ ፈቅ ያረገን
የዘመን ቃል በዚህ የለም!!
እንደው ድከሙ ቢለን ነው ቢጋረድብን ሀቁ፣
ቁመው የካዱት ነው የሚያምኑት እየወደቁ
“ንቁ…ንቁ…ንቁ እንደቆማችሁ
ሰሚ ጆሮ የለም--- የረገጣችሁት ድንጋይ         ከከዳችሁ!!”


Read 8050 times