Sunday, 10 November 2019 00:00

25 ሺህ ደቡብ ኮርያውያን ሳይሞቱ ቀብራቸው ተፈጽሟል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በደቡብ ኮርያ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች በህይወት እያሉ የቀብር ስነስርዓት በተሳካ ሁኔታ የመፈጸም አገልግሎት የሚሰጥ በአይነቱ ለየት ያለ ድርጅት መቋቋሙንና ከ25 ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎች በዚህ ድርጅት አማካይነት ሳይሞቱ ቀብራቸው መፈጸሙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሆዮዎን ሂሊንግ ሴንተር የሚል ስያሜ ያለውና ከሰባት አመታት በፊት የተቋቋመው ድርጅቱ፤ ሰዎች በቁም እያሉ የቀብር ስነስርኣታቸውን በመፈጸም፣ ሞትን እንዲያስታውሱና ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያስችል አገልግሎት የመስጠት ዓላማ እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፣ እስካሁን ድረስም ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎቱን መስጠቱን አመልክቷል፡፡
“እንደምትሞት በቅጡ ከተረዳህና ሞትን በህይወት እያለህ ከተለማመድከው፣ ህይወትህን የምትመራበትን መንገድና አኗኗርህን ትለውጣለህ” ያሉት የ75 አመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ቾ ጃሂ፤ “በጥሩ ሁኔታ መሞት” በተሰኘውና በድርጅቱ በሚሰጠው የጅምላ የቀርብ ስነስርዓት ላይ ቀብራቸውን ማስፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በቅርቡ ባከናወነው የጋራ የቀብር ስነስርኣት ላይ ህጻናትና አረጋውያንን እንዲሁም ቀሳውስትንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደቡብ ኮርያውያን መሳተፋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ሰዎቹ በሬሳ ሳጥን ውስጥ ተጋድመው ለ10 ደቂቃ ያህል በመቆየት ቀብራቸው መፈጸሙንም አመልክቷል፡፡
ድርጅቱ በህይወት እያሉ የቀርብ ስነስርዓታቸውን እንዲያከብሩ በማድረግ ዜጎች ለህይወታቸው ዋጋ እንዲሰጡ፣ የበደሏቸውን ይቅር እንዲሉና ኑሯቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲመሩ የማገዝ ራዕይ ሰንቆ ስራ መጀመሩንና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ዘገባው አስታውቋል፡፡

Read 2775 times