Saturday, 09 November 2019 12:15

ተምሳሌት “ሁላችንም አገራችንን መውደድና ማገልገል አለብን”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   እማሆይ ወለተማርያም ገላው መነኩሲት - የማህበረሰብ መሪ - ገበሬ

                      እዚህ ገዳም ውስጥ እየሰራሁ መኖር የጀመርኩት፣ ፈጣሪ ለመንፈሳዊ ሕይወት ስለጠራኝ ነው፡፡ ብዙ ሴቶችና ወንዶች መንፈሳዊ ፈውስንና እፎይታን ለማግኘት ወደዚህ ስፍራ ይመጣሉ፡፡ ወደ አራት መቶ ሀምሳ ከምንሆነው የገዳሙ መነኩሲቶችና መነኩሴዎች በተጨማሪ የኛን እርዳታና እንክብካቤ የሚሹ በርካታ ወላጅ አልባ ሕጻናት፣ የአካል ጉዳተኞች፣ በእድሜ የገፉ አዛውንቶችና አቅመ ደካማ እናቶች አብረውን ይኖራሉ፡፡ በፀሎትና በአገልግሎት ከመትጋት ጎን ለጎን፣ በፈጣሪ የተመረጠችውን ይህቺን መሬት ለመንከባከብና ለማልማት እንታትራለን:: ራሳችንን ለመደገፍና ለሌሎች ለማካፈል በጋራ እንሰራለን፡፡ የፈጣሪ ቸርነት የተመሰገነ ይሁንና በአካባቢ ጥበቃና በዘላቂ የግብርና አሰራር፣ በዙሪያችን ላሉ መንደርተኞች አርአያ ለመሆን በቅተናል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ማቻከል ወረዳ፣ ኪሻካ ቂርቆስ በሚባል አካባቢ፣ በ1954 ዓ.ም ግድም ከገበሬ ቤተሰብ ነው የተወለድኩት:: ወላጆቼ በእርሻ ሥራ የተዋጣላቸው ትጉህ ገበሬዎች ነበሩ:: እኔም ከልጅነት እድሜዬ አንስቶ በታታሪነት መሥራት ያስደስተኝ ነበር:: ለወላጆቼ አምስተኛ ልጅ ብሆንም፤ እህት ወንድሞቼ በተለያዩ በሽታዎች ሳቢያ በለጋ እድሜያቸው ነበር የሞቱት፡፡ ነፍስ ሳላውቅ በአስር አመቴ ከተዳርኩ በኋላ፣ በጠና እስከታመምኩበት ጊዜ ድረስ ሁለት ልጆችን ወልጃለሁ፡፡ በበሽታ የተያዝኩት 22 ዓመት ሲሆነኝ አካባቢ ነበር፡፡ ክፉኛ በመታመሜ እኔም እንደ እህት ወንድሞቼ በወጣነት እድሜዬ እሞታለሁ ብዬ ብፈራም ተረፍኩ፡፡ ጤናዬ ሲመለስልኝ ‹‹ከቤተሰቤ ጋር ዓለማዊ ሕይወትን እመራ ዘንድ የፈጣሪ ፈቃድ አይደለም፤ እሱን እንዳገለግለው ይፈልጋል›› የሚል አዲስ ሀሳብ በውስጤ ይመላለስብኝ ጀመር፡፡
መጀመሪያ በአካባቢያችን ወደሚገኘው ደብረ መድሃኒት ኪሻካ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል ገባሁና፤ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ለማሳነፅ እያገዝኩ ሰባት ዓመታትን አሳለፍኩ። ከዚያ ግን ከሚያውቁኝ ሰዎች ርቄ ወደ ግሸን ማሪያም ወይም ወደ ላሊበላ ገዳማት መሄድ አሰኘኝ፡፡ ፈጣሪ ያሰበኝ ግን ለሌላ ነበር:: የት ሄጄ ፈጣሪዬን እንደማገለግል ሳስብና ስፀልይ፣ በሕልሜ አንድ ዋሻ ታየኝ፡። ይሄው ዋሻ እየደጋገመ መላልሶ በህልሜ መጣ፡፡ አንድ ክረምት ካለፈ በኋላ፣ እዚህ አሁን ያለሁበት አካባቢ የጊራም ማሪያም ቤተ ክርስቲያን ለማሰራት እንዳግዛቸው ጠሩኝ፡። በአቅራቢያው ለፀሎት የምቀመጥበት ገዳም ይኖር እንደሆነ ስጠይቃቸው፣ ከአንዲት ወራጅ የምንጭ ውሃ ከፍ ብሎ ወደሚገኘው ዋሻ ይዘውኝ መጡ:: ልክ በህልሜ ሲመላለስ ያየሁት አይነት ዋሻ ነበር፡፡ በዚያ የዋሻ ገዳም ውስጥ በዱር እንስሳት መሀል ለሁለት ዓመታት ኖርኩ፡፡ እዚህ መጥቼ የምኖረው በፈጣሪ ፈቃድ ስለሆነ እሱ ይጠብቀኛል ብዬ ስለማምን በጅብ፣ በነብርና በሌላ የአራዊት መንጋ ዙሪያዬ ቢከበብም አልፈራሁም፡፡
በ1986 ዓ.ም የፋሲካ በዓል እንዳለፈ፣ አንድ ሌሊት ላይ ከወዲያ ጫካ ውስጥ ነብር ብቻ ሲቀር፣ ሌላው የአራዊት መንጋ ሁሉ ተጠራርጎ ሄደ፡፡ ያኔ ይህ ስፍራ በፈጣሪ መመረጡ ተገለጠልኝ:: ስሙ እንዲቀደስበትና እንዲወደስበት፣ የሰው ልጆችም ምህረትንና በረከትን እንዲያገኙበት፣ ፈጣሪ ይህን ቦታ እንደመረጠው ገባኝ፡፡ የአገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዘካርያስ ፈቅደውም፣ በአቡነ ተክለሃይማኖትና በቅዱስ ሩፋኤል ላይ ገደም እንዲቆምበት ቦታው ተባርኮ ተቀደሰ። አቡነ ዘካርያስ ባረኩንና ገዳሙንም “ዋሻ አምባ ተክለሃይማኖት አንድነት” ገዳም ብለው ሰየሙት:: እኛም መቀመጫውን አዲስ አበባ ባደረገው የዋሻ አምባ ተክለሃይማኖት ተቋራጭ ኮሚቴ እገዛ፣ ቤተ ክርስቲያኑን ገነባነው፡፡ የኮሚቴው አባላት ላሰባሰቡልን የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
በፈጣሪ ፈቃድ፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ጠበል ለመጠበቅና ምህረት ለመቀበል ሰዎች መምጣት ጀመሩ፡፡ ብዙ ሰዎች ከህመማቸው ተፈውሰዋል፤ ከመከራ ተገላግለዋል። ተዓምራት ያሳያቸውን ፈጣሪ ለማመስገንና የፈጣሪ በረከት ከኛ ጋር እንዲሆን በጉልበታቸውና በገንዘባቸው፣ ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ እርዳታ ሰጥተዋል፡፡
መሬቱንና ዙሪያ ገባውን ለማልማት ደፋ ቀና ማለት የጀመርኩት እግሬ ይህን አካባቢ በረገጠበት በ1984 ዓ.ም ነው፡፡ ከሞላ ጎደል አፈሩ ሁሉ ተራቁቶ፣ ለአይን ማረፊያ አንድም አጽዋት አልነበረውም፡፡ የድሮው ደን ተመንጥሮና ጠፍቶ፣ የወጥ ማማሰያ እንጨት ተፈልጎ የማይገኝበት በረሃ ሆኖ ነበር። የተራቆተው 52 ሄክታር መሬት እንደገና ነፍስ እንዲዘራና ደን ለምቶበት አረንጓዴ እንዲለብስ በማሰብ፣ ለመንግሥት አስተዳደር አመለከትኩ፡፡ ቀንና ሌሊት ዛፍ ለመቁረጥ ተደብቀው የሚመጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ ዛፍ ሲቆርጡ እንዳንሰማቸውና እንዳንይዛቸው በመጋዝ ቢጠቀሙም፣ ዛፎች ተገንድሰው ሲወድቁ መስማታችን አይቀርምና ተከታትለን እንይዛቸዋለን፡፡ ሕግን የሚጥስና አካባቢን የሚያጠፋ ተግባር እየፈፀሙ መሆናቸውን እንነግራቸዋለን፡፡ ሁሌም ስለ አካባቢ ጥበቃ እናስተምራለን፡፡ በመጨረሻ ግን በፈጣሪ ቸርነት ሁሉም ሰው ጫካው መነካት እንደሌለበት ስለተገነዘበ፣ ዛሬ የአካባቢው ነዋሪ ራሱ ደኑን ከጭፍጨፋ ይጠብቃል፡፡ የዱር እንስሳትን መንከባከብ የጀመርኩት ግን ከጊዜ በኋላ ከዋሻው አቅራቢያ ድኩላ ሲገደል አይቼ ነው፡፡ ለድኩላና ለሚዳቋ እንዲሁም ለሌሎች አራዊቶችና ለአእዋፍ ዘሮች መጠለያ እንዲሆናቸው የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን ተክያለሁ፡፡ ዛፎቹ እያደጉ ሲመጡ ጉሬዛ፣ ከርከሮ፣ አቦ ሸማኔዎችና ሌሎች የዱር እስሳት እንዲሁም ሌሎች በርካታ አዕዋፋት በአካባቢው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ይህንን ደን የምንቆጥረው እንደ ሰውነታችን አካል፣ እንደ ሕይወታችን ክፋይ ነው፡፡
መሬቱን ለማልማት በምናደርገው ጥረት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈናል፡፡ የ5 ሺ ብር መነሻ ገንዘብ ከልማት ኮሚሽን ከማግኘታችን በተጨማሪ የተለያዩ አካላትም ድጋፍ አድርገውናል፡፡ ሁሉንም ሥራ ያከናወንነው በራሳችን አቅም ነው፡፡ ወዲህ የሚመጡ መነኩሲቶች፣ መነኩሴዎችና ቤተሰቦች ሲበራከቱ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ማብቀል እንዲሁም እንስሳትን ማርባት ጀመርን፡፡ ባለ አራት ቋት የወፍጮ ማሽን ተክለናል፡፡ ለችግር ሳንገበር እንደምንተጋ ያዩ በጎ ሰዎችም አግዘውናል፡፡ በአቅራቢያችን በሚገኘው አማኑኤል የተባለ ቦታም ባለ አራት ማሽን የዳቦ መጋሪያ አቋቁመናል፡፡ አሁን ደግሞ መንግሥት የማህበራችንን እድገት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ መንደራችንን ከዋናው ጎዳና ጋር የሚያገናኝ የበጋ የክረምት መንገድ በመሥራት ለጥያቄያችን ምላሽ ሰጥቶናል፡፡ ኤሌክትሪክም አስገብቶልናል፡፡ እኛም ሥራችንን ቀጥለናል፡፡ እንደ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቲማቲም፣ ቀይ ስር፣ ቃሪያና ካሮት የመሳሰሉ አትክልቶችን እናመርታለን:: ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሎሚ፣ ትርንጎ፣ ዘይቱን ብርቱካንና ሌሎች ፍራፍሬዎችንም እናለማለን፡፡ ወቅቱን ተከትለን የሸንኮራ አገዳና ሌሎች ተክሎችን እንተክላለን፡፡ ለምግብ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ራሳችንን ለመደገፍና ችግረኞችንም ለመርዳት የገቢ ምንጭ እንዲሆነን ነው የምናመርተው፡፡ ከጀርመን የልማት ተራድኦ ተቋም ጂቲዜድ ባገኘነው ድጋፍም፣ ማገዶ የሚቆጥብና የምግብ ማብሰያ ክፍላችንን በጭስ የማያፍን የኮንክሪት ምድጃ አሰራር አውቀንበታል፡፡ ምድጃ እየሰራን ለአካባቢው ነዋሪዎች እንሸጣለን፡፡ በአንድ ወገንም ለነዋሪዎቹ ጤንነት የሚጠቅም ምድጃ ነው፡፡ አላማችን አብረን እየተደጋገፍን መኖር ነው፡፡ ለወደፊት ትልልቅ እቅዶችም አሉኝ፡፡
ለመነኩሴዎች መኖሪያ ቤት መሥራት፣ የብሉይና የሃዲስ ቅዱሳን መጻሕፍትን አሰባስቦ የሚይዝ ቤተ መጻሕፍትን መገንባት፣ በዜማና በቅኔ የምናደርሳቸውን የአምልኮና የውዳሴ ስርዓቶቻችንን የሚያስጠና የሃይማኖት ትምህርት ቤት መክፈት፣ ሕጻናት እስከ አራተኛ ክፍል የሚማሩበት ዘመናዊ ትምህርት ቤትና የጤና ማዕከል መክፈት፣ የግብርና ምርቶቻችንን ወደ ሰፋፊ ገበያዎች ለማድረስና በጥሩ ዋጋ ለመሸጥ የሚያስችሉንን መኪኖች መግዛት፣ ከፍጆታ እየተረፈ በማጓጓዣ እጦት እየተበላሸ የሚባክንብንን የወተት ምርታችንንም ለገበያ ማቅረብና ለአካባቢያችን ሙሉ አገልግሎት ከሚሰጥ የእንግዳ ማረፊያ ጋር ለኢኮ ቱሪዝም መዳረሻነና ማልማት በመሳሰሉት እቅዶቻችን አማካኝነት ወደፊት ይበልጥ ጠንካራ እንሆናለን::  
በእስካሁኖቹ ጥረቶች ያገኘነው መንገዱ ቀላል ሆኖልን አይደለም፡፡ ስኬታማ የሆንነው እንቅፋቶችን እየተሻገርን ነው:: በየጊዜው የሚያጋጥሙን ችግሮች የሰውን ልጅ እንደሚያጠነክሩትና ወደ በጎ ነገሮች እንደሚመሩት አምናለሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ የአካባቢው ሰዎች ደናችንን እየጨፈጨፉ፣ ለመተዳደርያቸው ሊያውሉት ይፈልጉ ነበር:: በዚህ ሳቢያ ከብዙ ሰዎች ጋር ተቃቅሬ ዛቻና ማስፈራሪያ ሳይቀር ደርሶብኝ ነበር፡፡ ያኔ ሲዝቱብኝ የነበሩ ሰዎች ዛሬ አብረውን ይሰራሉ:: የኛን ፈለግ ተከትለው ዛፎችን ይተክላሉ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ያለማሉ፡፡ ብዙዎቹ በሕይወታቸው ላይ በጎ ለውጥ ለማየትና ኑሯቸውን ለማሻሻል በቅተዋል፡፡
በአካባቢያችን የሚገኝ ሶስት ሄክታር የተራቆተ መሬት በመጨመር፣ ደኑን ያስፋፋነው ሲሆን አሁንም እየተንከባከብነውና መልሰን እያለማነው እንገኛለን፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የምርጥ ዘር ማባዣ ማዕከል በመፍጠር ለአካባቢው ገበሬዎች ለማከፋፈል እንፈልጋለን፡፡ ወደፊት ሥራችንን አስፍተንና አሻሽለን እንድንሰራ እውቀቱ ያላቸው ሰዎች ቢረዱን ደስ ይለናል፡፡ ዛሬ በእግዚአብሔር እርዳታና በራሳችን ጥረት፣ ሥራችንን በክልልና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘትና መከበር ጀምሯል፡፡ ከኢትዮጵያም ሆነ ከባህር ማዶ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ማህበር አማካኝነትም ሆነ በራሳቸው ሃይማኖት በኩል የደገፉንን ሁሉ ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡
ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክት እንዲህ የሚል ነው- አንድ ነገር ስትጀምሩ ጥሩና መጥፎ ነገሮች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ፡፡ ትርፍና ኪሳራ ሁሌም ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ የምታገኙት ትርፍ ትንሽ ሆኖ ቢታያችሁም እንኳ ተስፋ አትቁረጡ፡፡ የበለጠ ትርፋማ የሚያደርግ መንገድ ለማግኘት መርምሩ፡፡ ቅጠላ ቅጠልን ሰብስቦና አድርቆ መሸጥ አልያም ትንሽ የሚመስሉ ሌሎች ሥራዎችም እንኳ ቢሆኑን፣ ከልባችሁ አስባችሁ ከገባችሁበት የሰራችሁት ነገር ትርፋማ ይሆናል፡፡
ወጣቶች፣ ዶሮ ቢያረቡ፣ ከብቶችን ቢያደልቡ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ቢያመርቱ፣ ወይም በሌሎች  መስኮች ተግተው ቢሰሩ፣ ራሳቸውንና አገራቸውን ይጠቅማሉ፡፡
ሴቶች ጠንካራ ለመሆንና ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚያስፈልጋቸው መማር፣ ራሳቸውን መቻልና ከወሲባዊ ግንኙነት በመታቀብ ጤናቸውን መጠበቅ ነው፡፡ ሁልጊዜ ወጣቶችን የምመክራቸው፣ በትምህርታቸው እንዲገፉ፣ በፈጣሪ እንዲያምኑና በሃይማኖታቸው እንዲፀኑ ነው፡፡ ሁላችንም አገራችንን መውደድና ማገልገል አለብን፡፡  

Read 2006 times