Print this page
Saturday, 09 November 2019 11:45

በሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሣኔ ላይ ያለውን ስጋት ኮሚቴው አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  የዎላይታ የሠብአዊ መብት ኮሚቴ፤ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለፌደሬሽን ም/ቤት፣ ለኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለሂውማን ራይትስዎችና ለተባበሩት መንግስታት የሠብአዊ መብት ጥበቃ በፃፈው ደብዳቤ፣ ህዳር 10 ቀን በሚካሄደው የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሣኔ ላይ ያሉትን ስጋቶች አስታውቋል፡፡
ኮሚቴው ከትናንት በስቲያ ባሠራጨው ደብዳቤው፤ ከዚህ በፊት በሐዋሣ ከተማ በወላይታ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት በማስታወስ፤ እንዲህ ያሉ ጥቃቶች በህዝበ ውሣኔው ወቅትም ሆነ ከህዝበ ውሣኔው በኋላ እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡
በተለይ በሁለቱ ዞኖች (ወላይታ እና ሲዳማ) አጐራባች ወረዳዎች የሚካሄዱ ህዝበ ውሣኔዎች በጥንቃቄ እንዲመሩ የጠየቀው ኮሚቴው፤ ከወዲሁ እየታዩ  ያሉ ጽንፈኛ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ አሳስቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሐዋሣና በአካባቢው የወላይታ ተወላጆች እየታሠሩ መሆኑን በመግለጽም የታሠሩ በአስቸኳይ እንዲፈቱና ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥብቃ ይደረግላቸው ዘንድ ጠይቋል፡፡
በክልሉ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና የሚዲያ አካላት የሚሠራጩ መግለጫዎችንም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እየገመገመ ከወዲሁ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድና ሚዲያዎች ሁሉም ዜጐች በፍትሃዊነት ሃሳባቸውን የሚገልፁባቸው መሆኑን እንዲያረጋግጥ አመልክቷል፡፡
በአካባቢው “መጤዎች” እና “ነፍጠኛ” የሚሉ ዘረኛ ቃላትና አመለካከቶች እየተንፀባረቁ መሆኑን የጠቆመው ኮሚቴው፤ ይህ አመለካከት ወደ መጤ ጠልነት ደረጃ አድጐ ችግር እንዳይፈጥር ስጋቱን ገልጿል - በደብዳቤው፡፡
ይህን ስጋቱንም አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲገነዘቡለት ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
የሲዳማ ህዝበ ውሣኔ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ቦርዱ ከ6ሺህ በላይ የምርጫ አስፈፃሚዎችን አሠልጥኖ ማሰማራቱንና ከሐሙስ ጥቅምት 27  ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥም የምርጫ ቅስቀሳ በይፋ እንደሚጀመር ቦርዱ ያሠራጨው መረጃ ይጠቁማል፡፡  

Read 9482 times