Saturday, 09 November 2019 11:39

በኦሮሚያ የተፈጠረው ችግር በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  ‹‹ጉዳዩ ተድበስብሶ መቅረት የለበትም›› - ኢሃን


             በኦሮሚያ፣ በድሬደዋና ሀረር ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ በዜጐች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል ያለው የኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን)፤ ጉዳዩ ከምንጩ ጀምሮ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቋል፡፡
ንቅናቄው ከምርጫ ቦርድ የእውቅና ምዝገባ ሠርተፊኬት ማግኘቱን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ተፈጥሮ የነበረው ችግር ተድበስብሶ መቅረት የለበትም ሲል ጉዳዩ በአስቸኳይ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቋል፡፡
‹‹ማንነትን መሠረት ያደረገ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በዜጐች ላይ ተፈጽሟል” ያለው ንቅናቄው፤ “እንዲህ አይነቱን አስነዋሪ ተግባር አድበስብሶ ማለፍ የሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ብሏል፡፡
‹‹በወቅቱ የተፈፀመው ድርጊት በሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ላይ ትልቅ ዳመና ያዘለ ነው›› በማለት የገለፀው ፓርቲው፤ ‹‹ችግሩን ከምንጩ ጀምሮ ማጥራትና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል›› ሲል አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል፤ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ አንዱ የመታገያ አጀንዳው እንደሆነ የጠቆመው ኢሃን፤ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ምልክታችን ናት፤ የአዲስ አበባ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲጠበቅ እታገላለሁ ብሏል፡፡
“ነፃነት ሳይኖር ምርጫ የለም” ያለው ንቅናቄው፤ ህዝባዊ አስተዳደርን በምርጫ ለመመስረት በቅድሚያ የዜጐችን ነፃነት ማክበርና ማስከበር ያሰፈልጋል ብሏል፡፡ ለህዝቡ የሃሳብ አማራጮች ለማቅረብም የሃሳብ ነፃነት ስለሚያስፈልግ ከምርጫ በፊት የዜጐችን ነፃነት ማክበር ያስፈልጋል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ከአንድ አመት ተኩል በፊት በቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት የተመሠረተ ሲሆን ሰሞኑን የፖለቲካ ድርጅት የምዝገባ እውቅና ማግኘቱን አስታውቋል፡፡


Read 8428 times