Saturday, 09 November 2019 11:37

ኢዜማ በሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ላይ የሚመክር አገራዊ ውይይት ሊያዘጋጅ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  በሀገሪቱ የሠላምና መረጋጋት ጉዳይ ላይ ሁሉንም ባለድርሻዎች የሚያሳትፍ ታላቅ ሀገራዊ የውይይት መድረክ ሊያዘጋጅ መሆኑን ኢዜማ አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ሊያዘጋጀው ስላቀደው ሀገራዊ የውይይት መድረክ ለአዲስ አድማስ ያብራሩት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ናትናኤል ፈለቀ፤ በአሁኑ ወቅት ውይይቱ ሊመራበት የሚያስችል እቅድ (ፕሮፖዛል) ተዘጋጅቶ በባለሙያዎች እየተገመገመ ነው ብለዋል፡፡
ይህን የውይይት መድረክ ኢዜማ ለብቻው ሳይሆን ከሌሎች የሲቪክ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚያዘጋጅ ተጠቁሟል፡፡ መድረኩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ መንግስት፣ የሃይማኖት ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የሚሳተፉበት እንደሚሆንም ገልጿል፡፡
‹‹ሃገሪቱ እንዴት ወደ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ትሸጋገር›› በሚለው ላይ ስምምነትና መግባባት እስኪፈጠር ድረስ ውይይቱ በተከታታይ የሚካሄደ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
“ሠላምና መረጋጋት የሁሉም ሰው ጉዳይ ነው” ያሉት አቶ ናትናኤል፤ ይህ መድረክ ሁሉም ባለድርሻዎች በሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ላይ አንድ አይነት አረዳድ የሚይዙበት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል ብለዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላም የተለያዩ ስምምነቶች ላይ ተደርሶ በቃል ኪዳን ውል ሊታሠር እንደሚችልም ተናግረዋል - የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፡፡
የውይይት መድረኩ ሀገሪቱ በቀጣይ መፍጠር ለምትፈልገው ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሚሆን የተጠቆመ ሲሆን በመንግስት የተቋቋመውን የብሔራዊ እርቅና መግባባት ኮሚሽን ተግባርን ተክቶ የሚሠራ መድረክ ግን እንደማይሆን ተነግሯል፡፡  

Read 8090 times