Saturday, 02 November 2019 13:37

ለልብ ፍቅረኛ የተበረከተ አስደናቂ ስጦታ

Written by  (ታ.ጸ)
Rate this item
(2 votes)

    የሰው ልጅ ለአፈቀረው ሰው አይደለም ሀብቱንና ንብረቱን ይቅርና ሕይወቱን እንደሚሰጥ ከዓለም ታላላቅ የፍቅር ታሪኮች እንረዳለን፡፡ ንጉሥ ሼህ ጃሃንም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ ንጉሡ መላ ንብረቱን፤ ወርቁንና ብሩን፤ ዕንቁውንና አልማዙን አሟጥጦ፣ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ቤተ መንግሥት በስሟ በመሥራት፣ በሕይወት ዘመኑ እጅግ ያፈቅራትና እርሷም ታስደስተው ለነበረቺው ልዕልት ሙምታዝ ማሃል ዘለዓለማዊ ማስታወሻ ይሆናት ዘንድ አበርክቶላታል፡፡
ልዕልት ሙምታዝ ማሃል  በፐርሺያ የሙግሃል ግዛት አስተዳዳሪ ከነበረው ከበርቴ  መስፍን  ከአባቷ ከአቡል ሐሰን አሳፍ ማሃልና ከእናቷ ከዲዋንጂ ቤጉም  የተወለደችው እ.ኤአ አፕሪል 27 ቀን 1593  ጥንት የፐርሺያ ግዛት በነበረ አርጁማንድ ባኑ ሙግሃል አግራ በተባለ ቦታ ነው፡፡ እናቷም እንዲሁ በፐርሺያ የኩዋዝሚን መስፍን የነበረው የክህዋጃ ግያስ አፕዲን ልጅ ነች፡፡ ልዕልት ሙምታዝ ማሃል የተወለደችበት ቦታ አርጁማንድ ባኑ ከጊዜ በኋላ በሕንድ አስተዳደር ውስጥ ተጠቃልሏል፡፡
ልዕልት ሙምታዝ ማሃል  በትምህርቷ በጣም ጎበዝ ተማሪ የነበረች ከመሆኗም ባሻገር በሥነ ምግባር የታነጸች፤ የሰዎችን ሐሳብ የምታከብር፤ ግልጽና ተግባቢ፤ በዐረብኛና በፐርሺያ ቋንቋዎች ከፍተኛ  እውቀት ስለነበራት ሥነ ግጥም ጭምር የምትጽፍና በራሷ የምትተማመን  ወጣት ነበረች፡፡ መልካም ባሕርይዋ ከእውቀትና ከተፈጥሮ ውበቷ ጋር ተዳምሮ በቤተ መንግሥት ሰዎች  ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ትኩረት የምትስብ  እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ብዙ ሚስቶች የማግባት መብት የነበረው የ20 ዓመቱ  ንጉሥ ሼህ ጃሃን፣  በልዕልት ሙምታዝ ፍቅር ተነድፎ  በ19 ዓመቷ እ.ኤአ አፕሪል 30 1632 ዓ.ም  እንደ ሁለተኛ ሚስት አድርጎ ሊያገባት የቻለውም ከዚሁ ባሕርይዋ፤ እውቀቷና የተፈጥሮ ውበቷ የተነሣ ነው:: ጋብቻው ፖለቲካዊ ይዘትም አለው፡፡ የመጀመሪያ ሚስቱ ልዕልት  ካንድሃሪም ቤጉም ስትሆን ፤ከልዕልት ሙምታዝ በኋላ ያገባት  ሦስተኛዋ ሚስቱ ደግሞ ልዕልት ኢዝ  ንሳ ቤጉም ናት፡፡ ንጉሥ ሼህ ጃሃን ለሦስቱም ሚስቶቹ ለቤት ወጭና ለጉዞ አገልግሎት የሚውል ወርኀዊ ደመወዝ ይሰጣቸው ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት ንጉሥ ሼህ ጃሃን  ለልዕልት  ሙምታዝ በዓመት አንድ ሚሊዮን ሩፒ  ይሰጣት እንደነበር በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ከሁለቱም ሚስቶቹና ከአንድ ሺህ ፍቅረኞቹ ውስጥ አብልጦ ያፈቅራት የነበረውም ይህቺኑ ልዕልት ሙምታዝ ማሃልን ነበር፡፡ እንደተጋቡ ሺህ  ጃሃን  «ሙምታዝ ማሃል የሙገሃል ግዛት  የጋብቻ ልዕልት» የሚልና   የፐርሺያ ቤተ መንግሥት ከፍተኛ መጠሪያ የሆነውን ማዕረግ  ሰጥቷታል፡፡ እንደገና እ.ኤ.አ በ1628 ዘውድ የጫነበትን ቀን ምክንያት አድርጎ «ዋነኛዋ ንግሥት  መልካኢ ጃሃን ወይም  የዓለም ንግሥት »  የሚልና «መልካ ኡዝ ዛማኒ ወይም የእድሜ ልክ ንግሥት» የሚል ማዕረግ አቀዳጅቷታል፡፡
በዘመኗ ገጣምያን ስለ ውበቷና ግርማ ሞገሷ፤ የፍቅር ሰው ስለመሆኗ ተጽፎላታል፡፡ የታሪክ ጸሐፍት ደግሞ በተከታታይ  የማርገዟ ነገር ሳይበግራት፣ ንጉሥ ሼህ ጃሃን ለሥልጣኑ ሲል ከአባቱ ጋር ለመዋጋት ሠራዊቱን እየመራ በሄደበት ጦር ሜዳ ሁሉ አብራው ትጓዝና በቤተ መንግሥት ሥራው  ታማክረውና ትረዳውም እንደነበር መዝግበዋል፡፡  የ19 ዓመት የጋብቻ ዘመናቸውም እንደ ብረት ጠንካራ ነበረ ብለው ጽፈዋል፡፡
ሁለቱም ባልና ሚስት በጋብቻ ዘመናቸው 14 ልጆችን ወልደዋል፡፡ ከልጆቻቸው ውስጥ ስምንቱ ወንዶች ሲሆኑ ስድስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ሰባቱ ልጆቻቸው በወጣትነታቸው ሞተውባቸዋል፡፡ ንጉሥ ጃሃን ከልጆቹ ውስጥ ከልቡ የሚወድዳቸው  ጃሃናራ ቤጉምን፤ አልጋ ወራሹን  ዳራ ሺኮህን፤ እ.ኤ.አ በ1658 የሙግሃል ስድስተኛ  ንጉሥ ተብሎ በአባቱ ምትክ የነገሠውን  አውራንግዜብን ነበር፡፡ ልዕልት ሙምታዝ  በ38 ዓመቷ ጁን 17 ቀን 1631 ዓ.ም  ለሞት የተዳረገችው 14ኛዋን ልጇን ጋውኻር አራጉምን በወለደች ጊዜ  ምጥ ስለጠናባት ነበር፡፡ ያረፈችውም  በዚያው በሙግሃል ግዛት  ቡራንፑር ሲሆን  የተቀበረቺው ታጂ ማሃል አግራ በተባለና ለስሟ መታሰቢያ በሆነ  ቦታ ነው፡፡
ሰው ለፍቅር ሲል ያለውን ሁሉ ቢሰጥ አይሰስትምና የሙግሃል ንጉሥ  የነበረው ሼህ  ጃሃን  ከጃንዋሪ  19 ቀን 1628 ጀምሮ እስከ ጁን 1631  ድረስ  ተቀዳሚ ባለቤቱ ለነበረችው ለልዕልት ሙምታዝ ማሃል ማስታወሻና የመቃብር ስፍራዋም  እንዲሆነው በማሰብ፣ በቦምቤይ  ወደብ ከተማ ዳርቻ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስገራሚና አስደናቂ የሆነና ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ቤተ መንግሥት፣ ወጭውን ሙሉ በሙሉ ሸፍኖ  ሰርቶላታል:: ቤተ መንግሥቱም እጅግ ያማረና አስደናቂ ቅርስ ስለሆነ በዓለም መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ማእከል ተመዝግቧል፡፡ አግራ ውስጥ ታጂ መሃል የሚገኘውና የልዕልት ሙምታዝ ማሃል የዐፅሟ ማረፊያ  የሆነው   ቤተ መንግሥት ፤ በየጊዜው በብዙ መቶ ሺህ በሚቆጠሩ የዓለም ቱሪስቶች ይጎበኛል፡፡ ታጂ የሚለው ቃል የሙምታዝን ስም አሳጥሮ ለመጥራት የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ማሃል ደግሞ የአባቷ ስም ነው፡፡
ሼህ ጃሃን ለዘለዓለማዊት ፍቅረኛው  ለልዕልት ሙምታዝ ማሃል ማስታወሻ እንዲሆነው  በቦምቤይ ያሰራው የታጂ መሃል ቤተ መንግሥት፣ ዘመናዊ የሆቴልና የመዝናኛ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የታጂ ማሃል ቤተ መንግሥት በሙምባይና በቦምቤይ  የመዝናኛ አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ የተደራጀው እ.ኤ.አ በ1903 ነው፡፡ በሕንድ  የወደብ አገልግሎት የመጀመሪያ በሆነውና እንደ ልዩ ምልክት ተደርጎ የሚታየው ይህ ሆቴል፣ ለሀገሪቱ እንደ ንግድ ምልክት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ወደ ሕንድ ለመግባትም ዋነኛውና ግርማ ሞገስ ያለው መግቢያ በር ይኸው ነው፡፡ ይህ ምቾት የሚሰጠው የቤተ መንግሥት ሆቴል በአለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ነገሥታትን፤ ታላላቅ ሰዎችን ፤የታወቁ ግለሰቦችን ለማስተናገድ የተለየ ብቃት አለው፡፡
በመስተንግዶ አሰጣጡና በተንከባካቢነቱ በዓለም የታወቀው ሆቴሉ፤285 የመኝታ ክፍሎች፤ የበለጸገ ታሪክና ዘመናዊ የመስተንግዶ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በአካባቢው ታላላቅ ሱቆች፤ የፋይናንስ ተቋማት፣ ፓርላማና ስታዲየም ይገኛሉ፡፡ በውስጡ ሙዚየሞች፤ የሥዕል ጋለሪዎች ፤አብያተ ክርስቲያናት፤ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች፤ የሙዚቃ፤ የተውኔትና የፊልም አዳራሾችም ይዟል፡፡ ልዕልት ሙምታዝና ንጉሥ ሼህ ጃሃን ይኖሩበት የነበረውና በኋላም የተገነባው ቤተ መንግሥት፣ ሙሉ በሙሉ በንጹሕ ወርቅና ብር የተሠራ፤ በከበሩ ደንጋዮች የተለበጠ፤ የሚያንጸባርቅና በውበቱ የሚያማልል በመሆኑ ምንጊዜም በዓለም ቱሪስቶች እንደሚጨናነቅ ይታወቃል፡፡   

Read 2586 times