Saturday, 02 November 2019 13:36

ገጣሚውi

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(5 votes)

  አባቴ ቀን ከሌት ነበር የሚፅፈው፡፡ በልጅነቴ ከጓደኞቼ ጋር ስጫወት ቆይቼ ቤት ስገባ ጠረጴዛና ወንበሩ መሀል አገኘዋለሁ፡፡
ባለቅኔ ነው አባቴ፡፡ ቅኔው ግን ከሰዎች የመረዳት አቅም በላይ ስለሆነ ሰው ሳያውቀው፤ መጽሐፍ ሳይኖረው አለፈ፡፡ ፅፎ… ፅፎ… ፅፎ … ማሳተም ባይችል፤ አንድ ቀን ስራዎቹን ሰብስቦ አቃጠላቸው፡፡ የዛኑ ቀን የመርዝ ብልቃጥ ጎን አስከሬኑ ተገኘ፡፡
የአባቴን ህልም ላሳካ ነው ቆርጬ የተነሳሁት:: አጥንቱ እንዳይከሰኝ፤ መንፈሱም እንዲኮራብኝ ፈለግሁ፡፡ ገጣሚ ሆንኩ፡፡ ያባቴ ዕጣ ደረሰኝ፡፡
ከሰዎች አዕምሮ በላይ በመሆኔ በየአሳታሚ ድርጅቱ ብመላለስም ሥራዎቼን እያነበቡ በንቀት የሚወረውሩብኝ በዙ፡፡ ባይገባቸው እንደሆነ ገባኝ፡፡
ገጣሚ የመሆን ሀሳቤ አልተሰናከለም፡፡ ሰውን ለምን ደስ ይበለው?! … የአባቴ መንፈስ ለምን ቅር ይበለው? … የህዝብ ገጣሚ ሆንኩ:: አንድ መጽሐፍ ባይኖረኝም፣ ጆሮዎች እልፍ እንደሆኑ አወቅሁ፡፡ ንግግሬ ሁሉ በግጥም ሆነ፡፡
‹‹እንደምን አደርክ?›› ሲሉኝ
‹‹እንደምን አደርክ ካላችሁኝ
እንደሰው ተኝቼ አደርኩኝ›› ብዬ እመልሳለሁ::
አውቶብስ ስሳፈር፤ ቲኬት ቆራጯን፤
‹‹ዝም ብለሽ ከምትቀመጪ
ትኬቱን ቁረጪ
የቆረጥሽውን አምጪ፡፡››
እያልኩ ሳንቲም እሰጣታለሁ፡፡
ታክሲ ተሳፍሬ፤ የሚከፈለውን እያወቅኩ፤
‹‹ፒያሳ ለሚሄድ ሰው
ሒሳቡ ስንት ነው?›› ብዬ እጠይቃለሁ፤ ይነግረኛል፡፡ ዝርዝር እያለኝ ድፍን ብር እሰጠውና፤
‹‹ሰው አታታሉ
ይላል ቃሉ
ምንም ሳታስጠጣ
መልሴን አምጣ››
መታጠፊያ ጋ እስኪደርስ ጠብቄም፤
‹‹ወያላ ስማ
ኋላ እንዳትታማ
እጥፍ እንዳለ
ወራጅ አለ፡፡››
ገጣሚነቴን ሀገር እንዲያውቀው ጥሬያለሁ:: ሆኖም ብዙዎች ግር ሲሰኙ አይቼ፤ ይህም ከአቅማቸው በላይ መሆኑን በመረዳት፤
‹‹የሌለው አቅም
ግጥሜ አይገባውም
ተጠቀሙ ያወቁ
ሌሎች ተሳቀቁ
ስላላወቁ …››
ብዬ ገጥሜባቸዋለሁ፡፡
ካፌ እገባለሁ፡፡
ክፍት ቦታ ሊኖር ይችላል፡፡ አልቀመጥም፡፡
ሰው ያለበት እፈልግና እሄዳለሁ፤
‹‹ጤና ይስጥልኝ የኔ ጌታ
ሰው አለው ይሄ ቦታ?››
እንደሌለው ይነግረኛል፡፡
‹‹ሰው ስለሌለው ቦታው
ምስጋናዬ ከልብ ነው፡፡››
እቀመጣለሁ፡፡
አስተናጋጇ ትመጣለች፤ የማዝዘውን እያወቅሁ እጠይቃለሁ፡፡
‹‹ጣጣ የማያመጣ
ምናለ የሚጠጣ?››
ትነግረኛለች …
‹‹የቱን ልታዘዝ?›› ትላለች፡፡
‹‹የኔ ትዕዛዝ … እ…?›› አስባለሁ፤ ገጣሚነቴን የሚያስመሰክሩ ቃላት እየፈለግሁ፡፡ የፈለግሁት ነጣ ያለ ማኪያቶ ነው፡፡ … እናም…
‹‹የኔ ትዕዛዝ
ማኪያቶ ያለ ፍዝዝ…›› እላታለሁ፡፡
እየተጎነጨሁ …
‹‹አቤት ጣዕም
ጣት ሲያስቆረጥም›› ማለቴም የማይቀር ነው::
ስጨርስ እጠራታለሁ፡፡
‹‹ሰው ሲጣራ ስሚ
ማስቲካ ከምትቀሚ
ስንት ነው ማኪያቶ
ከፍዬ ልሂድ መርካቶ››
ከፍዬ እወጣለሁ፡፡
ስወጣ ከሰው ጋር ልጋጭ እችላለሁ፤
‹‹ይቅርታ!...›› ይላል
‹‹ካላዩበቱ
ዐይን ምናባቱ
ሰው እየመቱ
ይቅርታ ከንቱ…››
ባለቤቴ፤
‹‹እራት ይምጣ?›› ትለኛለች
‹‹እራቱ ይምጣ
አታብዢ ጣጣ
እንጀራ እንብላ
ከምንጠጣ ጠላ››
በቃ የህዝብ ገጣሚ ነኝ፡፡ መጽሐፍ ባይኖረኝም፤ የህዝብ ጆሮ አለልኝ፡፡ ለጆሮው የህትመት ዋጋ ማን ይጠይቀኛል?! … ታዲያ አባቴን አልበለጥኩትም?!....
ከአዘጋጁ፡- ይሄ አጭር ልብወለድ ከዚህ ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ለህትመት የበቃ ሲሆን ለትውስታ አድማስ ይመጥናል ብለን ነው በድጋሚ ያወጣነው፡፡ በነገራችን ላይ ጸሃፊው በቅርቡ ያወጣው የአጭር ልብወለድ መድበል ከነገ በስቲያ ይመረቃል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ደራሲውን እንኳን ደስ ያለህ! ብለነዋል፡፡


Read 2503 times