Wednesday, 06 November 2019 00:00

ማይክል ዘንድሮም ከሞቱ ዝነኞች በገቢ ቀዳሚ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ከዚህ አለም በሞት ቢለዩም በስራዎቻቸው እጅግ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ የአለማችን ዝነኞችን ዝርዝር በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ፎርብስ መጽሄት፣ የ2019 ባለ ከፍተኛ ገቢ በህይወት የሌሉ ዝነኞችን ዝርዝር ባለፈው ረቡዕ ያወጣ ሲሆን ላለፉት ስድስት ተከታታይ አመታት በመሪነት የዘለቀው ማይክል ጃክሰን ዘንድሮም በ60 ሚሊዮን ዶላር ቀዳሚነቱን ይዟል::
በወርሃ ሰኔ 2009 ከዚህ አለም በሞት የተለየው እውቁ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ማይክል ጃክሰን፣ የሙዚቃ ስራዎች በአመቱ በአሜሪካ ውስጥ ብቻ በድረገጾች 2.1 ቢሊዮን ጊዜ መታየታቸውንና በዚህም ከፍተኛ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው የፎርብስ መረጃ፣ ምንም አንኳን ገቢው ካለፈው አመት በእጅጉ ቢቀንስም ዘንድሮም ከአንደኛ ደረጃ አለመውረዱን አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1977 በልብ ድካም ህመም ይህቺን አለም የተሰናበተው ሌላኛው እውቅ ሙዚቀኛ ኤልቪስ ፕሪስሊ   በ39 ሚሊዮን ዶላር የሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ ከ19 አመታት በፊት በካንሰር ለሞት የተዳረገው ቻርለስ ሹልዝ በ38 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ሆኗል፡፡
ታዋቂው የጎልፍ ተጫዋች አርኖልድ ፓርመር በ30 ሚሊዮን ዶላር፣ የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌይ በ20 ሚሊዮን ዶላር፣ ዶክተር ሲዩስ በ19 ሚሊዮን ዶላር፣ ድምጸ መራው ጆን ሌነን በ14 ሚሊዮን ዶላር፣ ዘመን አይሽሬዋ ማርሊን ሞንሮ በ13 ሚሊዮን ዶላር፣ ፕሪንስ በ12 ሚሊዮን ዶላር፣ በቅርቡ በወሮበሎች የተኩስ እሩምታ ድንገት ህይወቱ ያለፈው ኤርትራዊው ድምጻዊ ኒፕሲ ሃስል በ11 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት ባለከፍተኛ ገቢ የአለማችን ሟች ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውም ታውቋል፡፡

Read 5476 times