Monday, 04 November 2019 00:00

28 በመቶ አፍሪካውያን ሚስትን መደብደብ ጥሩ ነው ብለው ያምናሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  አፍሮባሮሜትር የተባለው የጥናት ተቋም፣ ከ28 በመቶ በላይ የሚሆኑት አፍሪካውያን፣ አንድ ባል አልፎ አልፎ ወይም በየዕለቱ ሚስቱን ቢደበድብ ጥሩ ነው ብለው እንደሚያምኑ በጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በተለያዩ 34 የአፍሪካ አገራት የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፣ ምንም እንኳን በጥናቱ ከተካተቱት አፍሪካውያን መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት ባሎች፣ በምንም አይነት ሁኔታ ሚስቶቻቸውን ሊደበድቡ አይገባም የሚል አቋም ቢይዙም፣ 28 በመቶ ያህሉ ግን ድብደባው ተገቢ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በጥናቱ ከተካተቱት 46 ሺህ ያህል የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች መካከል ድብደባው ተገቢ ነው የሚል ምላሽ የሰጡት 24 በመቶ ሴቶች እና 31 በመቶ ወንዶች መሆናቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት በጥናቱ ከተካተቱት ሰዎች መካከል እስከ 70 በመቶ የሚደርሱት ድብደባን ጨምሮ በባለትዳር ሴቶች ላይ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተገቢ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ መናገራቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ መሰል አመለካከቶች ስር የሰደዱት ጋቦንና ላይቤሪያን በመሳሰሉ የመካከለኛውና ምዕራባዊ አፍሪካ አገራት ዜጎች ዘንድ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ተቋሙ ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በሰራው በዚህ ጥናት ከተካተቱትና ባሎች ሚስቶቻቸውን መደብደብ አለባቸው ብለው እንደሚያስቡ ከገለጹት ሰዎች መካከል 41 በመቶ ያህሉ ምንም አይነት መደበኛ ትምህርት ያልወሰዱ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

Read 3049 times