Print this page
Saturday, 02 November 2019 12:31

መደመር ወይስ መበተን?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(3 votes)

     ከጥቂት ወራት በፊት በአንድ ጋዜጣ ላይ ዶ/ር መንግስቱ የተባሉ ሰው “ሚኻኤል ጐርባቾቭን በሀገሬ ዳግም ማየት አልፈልግም” ማለታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ “ዶ/ር ዐቢይ ማንን ይመስልብሃል? ኒልሰን ማንዴላን ወይስ ሚኻኤል ጐርቾባን?” የሚል ጥያቄ ቂርቦላቸው ነው ይህን ምላሽ የሰጡት፡፡
እኔም ብሆን ከእሳቸው የተለየ መልስ የለኝም፡፡ ዶ/ር ዐቢይ፣ ሚኻኤል ጐርባቾቭን ሆነው፣ ኢትዮጵያ በእጃቸው ላይ ስትፈራርስ ማየት አልፈልግም፡፡ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ በአንድነቷ  ፀንታ እንድትኖር ነው የምመኘው፡፡ ሆኖም አሁን ያለው ሁኔታ ራስን ደግሞ ደጋግሞ “እውን ኢትዮጵያ አንድ አገር ሆና ልትቀጥል ትችላለችን?” ብሎ መጠየቅን የሚያስገድድ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ፣ ይልቁንም የሚፈርሱት የኢትዮጵያን መፍረስ የሚመኙ ወገኖች እንደሆኑ አረጋግጠውልናል (በቃላቸው!)፡፡ እንደ አፉዎ ያድርግልን ከማለት ውጭ ሌላ አልልም፡፡
በመጋቢት 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን የመጡት የተነሳ በድንገት ያህል በፓርላማ ያቀረቡትም ንግግር ያነሱትም ሃሳብ የ”ድንገቴ” ነበር - ያልተጠበቀ፡፡ በዚህም የተነሳ እኔንም ጨምሮ ብዙዎችን ተአምር አሰኝቷል:: በወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው ቢገልፁትም፤ ዶ/ር ዐቢይ ደግሞ “እኛ ኢትዮጵያዊያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” በማለት ይበልጥ ሃሳቡን መሬት እንዲረግጥ አደረጉት፡፡ ይህ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድም ከፍተኛ መከበርና መወደድ አስገኘላቸው፡፡ ወደ አሜሪካና አውሮፓ በዘለቁ ጊዜም የሞቀ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ ያ የሕዝብ ድጋፍ ዛሬም ከሚኒስትሩ ጋር አለ ወይ ቢባል፣ በድጋፍ ላይ ድጋፍ እየጨመሩ ሳይሆን ከነበራቸው ድጋፍ ላይ እየቀነሱ፣ ኃይላቸውን እየበተኑ ነው የቆዩት፡፡ የኢትዮጵያ ቀጣይነት ጉዳይ አሳሳቢ የሆነውም  ለዚህ ነው፡፡
ሥልጣን ከመያዛቸው በፊትና ከዚያም በኋላ በየአካባቢው በተፈጠሩ ግጭቶች በዜጐች ላይ ጉዳት ያደረሱና ሕይወት ያጠፉ ወገኖች ለሕግ ቀርበው እንዲጠየቁ ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም፣ በተግባር የሚታየው ግን አፍ ሞልቶ የሚያናግር አይደለም፡፡ ቁጥር እየተጠቀሰ “ይህን ያህል ሰው ተጠርጥሮ ተያዘ” ሲባል እንጂ “በማስረጃ ተረጋግጦበት እንዲህ አይነት ቅጣት ተወሰነበት” ሲባል አልተሰማም:: ይህ ደግሞ በመንግሥታቸው ላይ የነበረውን የሕዝብ ተስፋና አመኔታ እንክት አድርጐ በላው::
ከጊዜ ወደ ጊዜ የብዙኃን ማኅበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ጩኸት፤ “መንግሥት የሕግን የበላይነት ያስከብር!” የሚል እየሆነ መጣ፡፡ የታሰሩ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን በይቅርታ የፈቱት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፣ በሕግ ተቆርቋሪነታቸው ላይ የበለጠ መጨመር እንዳልቻሉ ታዝበናል፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን እሳቸውም የኢሕአዴግ ሰው በመሆናቸው “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመረጣል” ወደ ሚል ተረት ብዙዎችን እየገፉ ነው፡፡ እኔም ወደዚያው ነኝ፡፡
ወደ ጥቅምት 12 እና 14 ቀን 2012 ዓ.ም ክስተት እንለፍ፡፡ አቶ ጀዋር እንደሚለው፤ የተመደቡለት የጥበቃ ሰዎች ተነስተው፣ ለሕይወቱ በመሥጋት እርዳታ ይጠይቅ፣ ወይም አንድ የመንግሥት ኃላፊ “የመደብኩትን ጥበቃ በፈለግሁት ጊዜ ባነሳ ምን ችግር አለው ብሎ ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ “ግቢውን ለቃችሁ ውጡ” ይበል፡፡ የፈለገው ቢሆን ግን ድርጊቱ ከሚገባው በላይ መለጠጥ አልነበረበትም፡፡
አቶ ጀዋር የድረሱልኝ ጥሪ ያስተላለፈው ባጋጣሚው፣ ምን ያህል ደጋፊ እንዳለው ለማየትና ለማሳየትም ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ የጦስ ዶሮ ሆነው ሕይወታቸውን ላጡ ሰባ አምስት ዜጐች፣ የአካል ጉዳትም የንብረት መውደምም ለደረሰባቸው ወገኖችና ቤተሰቦቻቸው የተሰማኝን ሀዘን የምገልፀው ምርር ባለ ቃል “ፈጣሪ ደመ ከልብ አያድርጋችሁ፤ እንባችሁን ይቁጠርላችሁ” በማለት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሩሲያ መልስ የመጀመሪያውን ስብሰባቸውን ከኦሮሚያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ከተሰባሰቡ አባ ገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ቄሮዎች ጋር አድርገዋል:: ተመሳሳይ ስብሰባዎችም በሐረርና አምቦ አካሂደዋል፡፡
ሐረር ላይ ያደረጉትን ንግግር ፀጋ መንክር የተባሉ ደጋፊያቸው ተርጉመውት አንብቤዋለሁ፡፡ በፓርላማ ሁለት አገር ስላላቸው ወገኖች ያቀረቡትን ንግግር አንዳንድ ሚዲያዎች እጅግ አውርደው፣  በቃላት አጠቃቀም የተፈጠረ አለመግባባት ለማስመሰል ሞክረዋል:: ፀጋ መንክር ይሁነኝ ብለው ትርጉም ካላሳሳቱና በትክክል ከተረጐሙት፣  ለዶ/ር ዐቢይ ደጋፊ የሚያበዛ ወይም የቀድሞ ደጋፊያቸውን የሚመልስ ሳይሆን የሚበትን  መስሎ ነው የታየኝ፡፡
በጅማ በአሰላና በሌሎችም የኦሮሚያ ከተሞች የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አበቤና ሌሎችም ኃላፊዎች እያደረጉት ያለው ስብሰባ፣ ደጋፊን የማሰባሰብ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም - ከድባቡ በመነሳት:: ዶ/ር ዐቢይ እየተከተሉት ባለው መንገድ ግን  መንግሥት አሸናፊ ሆኖ ይወጣል መልሱ አጭር ነው፡፡ መንግሥት ጥርሱን ነክሶ የሕግን የበላይነት ካስከበረ፣ በየዋህነት ከመሥመር እንዲወጡ ያደረጋቸውን ወደ መስመር እንዲገቡ ካደረገ፤ ያኔ ብቻ ከመበተን ይልቅ መደመር ይሳካል፡፡ አገር የመፍረሷ ስጋትም ሥጋት ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችላል፡፡ ካልሆነ ግን በመበተን መንገድ ላይ ነን ወይም እንመስላለን፡፡

Read 2027 times