Monday, 04 November 2019 00:00

ከውድቀት ዋዜማ እስከ ጥፋት ማግስት

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)


• ‹‹አንድ የዘረኝነት አውራ›› የፈጠረው የጥፋት ዘመቻ፣… ‹‹ለሌላኛው የዘረኝነት አውራ››፣ የመቀስቀሻ ሰበብ ይሆንለታል፣
ዘረኝነትን ለማስፋፋት ይጠቀምበታል።
• የዘረኝነት ጥፋት በተፈፀመ ቁጥር፣ በማግስቱ የተምታታ አስተሳሰብና ግራ መጋባት ይበራከታል። ይሄ አይበጅም። ተጨማሪ የዘረኝነት ጥፋትን ይጋብዛል።
• በዘረኝነት ቅስቀሳ አማካኝነት የተፈፀሙ ጥፋቶችን፣ በሰበብና በማመካኛ አጀብ አለዝቦ ለማሳየት፣ ከዚያም አልፎ ‹‹ለማቆንጀት›› የሚደረግ ሙከራ፣ ክፉ ነው።
             
         በዋዜማው፣ የዘረኝነት ስብከት
የግል ማንነትን የሚያንኳስስ ስብከት፣ የውድቀት ዋዜማ ነው። እውኑ የሰው ማንነት ‹‹የግል ማንነት›› ቢሆንም፣ ከእውነታው በተቃራኒ፣ ‹‹የጋራ ማንነት››፣ ‹‹የብሔር ብሔረሰብ ማንነት›› የሚል የዘረኝነት ቅኝት እንደዋዛ ይሰበካል - በቀሽም ወይም በመጥፎ ምሁራን›› (‹‹በተማሩ መሃይማን››)።
ከግል ማንነት ጋር የግል ሃላፊነትንም ጭምር የሚያጣጥል ስብከት፣ ከእውነታ ጋር መጣላትን ብቻ ሳይሆን፣ ስነ ምግባር አልባነትንም ነው የሚያስፋፋው። እንዴት?
‹‹ይሄኛው ሰውዬ ውሸት ቢናገርም፣ ጥፋት ቢፈፅምም፣ ክፉ ባሕርይ ቢኖረውም፣ ‘ከኛ ጎራ ስለሆነ’፣ ንግግሩን በጭብጨባ እናጽድቅለት፣ ወንጀሉን እንደግፍለት፣ ክፋቱን እንደ ጀግንነት እናድንቅለት›› የሚል የዘረኝነት ቅኝት እንደዘበት ይሰበካል - በውድቀት ዋዜማ። ይሄ ለማን ይመቻል?
ለህሊና ቢስ ውሸታሞች፣ ለወሮበሎችና ለነፍሰገዳዮች  የሚመች ክፉ አስተሳሰብ ነው - የዘረኝነት ቅኝትና ስብከት። ህሊና ቢስ ክፉ ሰዎች ደግሞ፣ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም፣  ሁልጊዜ ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ከመሃል እስከ ጠረፍ ዳር፣ በሁሉም ቦታ ይኖራሉ።
አዎ፣ ጥቂት ናቸው። ከጠቅላላው ሕዝብ፣ 5 በመቶ እንኳ አይሞሉም። የዘረኝነት አውራዎችና አራጋቢዎችማ፣ ከሚሊዮን ሰው አስር ያህሉ እንኳ አይሆኑም። መርዘኛ ቢሆኑም ብዙ አቅም የላቸውም።
ለክፋት የሚመች የዘረኝነት ስብከት ሲስፋፋላቸው ግን፣ በአገር በምድሩ ላይ መግነንና፣ እንዳሻቸው ማተራመስ፣ መዝረፍና ማቃጠል፣ ከኑሮ ነቅሎ ማሳደድና በዘግናኝ የጭካኔ ግድያ ከፍተኛ እልቂትን መፍጠር ይችላሉ። አብዛኛው ሰው ደግሞ፤ በቁጥር እጅግ ብዙ ቢሆንም፤  የዘረኝነት ክፋትን የመግታት አቅም በማጣት የዳር ተመልካች ይሆናል። ለምን?
አብዛኛው ሰው ዘረኝነትን ይቀበላል ማለት አይደለም። እውኑን የግል ማንነት የሚያጣጥል፣ ከእውነታ ጋር የተጣላና ስነ ምግባርን የሚያጠፋ የዘረኝነት ቅኝት ሲስፋፋ፣ ‹‹የጋራ ማንነት››፣ ‹‹የብሔር ማንነት›› እየተባለ ሲሰበክ፣ አብዛኛው ሰው አይዋጥለትም። ቅር ቅር ይለዋል። ይተናነቀዋል፡። ለመከላከልም ይሞክራል… ‹‹አገራዊ ማንነት››፣ ‹‹የአዳምና የሄዋን ልጅነት››፣ ‹‹የተዋለደና የተዋሃደ ሕዝብ›› የሚሉ መከራከሪያዎችም በየጊዜው ይሰነዘራሉ። ነገር ግን፣ ውጤት አላመጡም። መፍትሄ አልሆኑም።
እውኑ ‹‹የግል ማንነት›› እና ‹‹ለሥነ ምግባር የተገዛ የግል ሃላፊነት›› ናቸው፤ ፍቱንና ሁነኛ መፍትሄዎች። ዘረኝነትን ከስረ መሰረቱ ነቅለው የሚያጠፉ እውነተኛ መፍትሄዎች እነዚህ ናቸው።
አሳዛኙ ነገር፣ ሁነኛዎቹ መፍትሄዎች፣ ማለትም እውነት ላይ የተመሰረተ ‹‹የግል ማንነት››፣ እንዲሁም ስነ ምግባርን የሚያስታጥቅ ‹‹የግል ሃላፊነት››፣ ተዘንግተዋል። ብዙ ትኩረት አልተሰጣቸውም።
በዚህም ምክንያት፣ ለህሊና ቢስ፣ ለሥነ ምግባር አልባ፣ ለክፉ ሰዎች የሚመች የዘረኝነት አስተሳሰብ ተስፋፋ። ጥቂት ቢሆኑም አገርን ለማተራመስ፣ ሕይወትን ለማርገፍ፣ ንብረትን ለማውደም አቅም አገኙ። ነገር ግን የዘረኝነት ስብከት በቂ አይደለም። የጥፋት አዝማች ያስፈልጋቸዋል።
በዘር አቧድነው ጥፋትን የሚቀሰቅሱና የሚያዘምቱ ፖለቲከኞች፣ አጋፋሪዎች፣ አራጋቢዎች በየጎራው፣ በየአይነቱ የገነኑ ጊዜ፣ በሰበብ አስባቡ፣ በየጊዜውና በየቦታው፣ ክፉ ድርጊቶችና ጥፋቶች እየተበራከቱ ይመጣሉ።
በዘረኝነት ጥፋት ማግስት
በአንዱ ጎራ፣ አንዱ የዘረኝነት አውራ፣ በዘር እያቧደነ፤ ለጥፋት ዘመቻ ያነሳሳል። በተቀሰቀሰው የጥፋት ዘመቻም፣ የሰዎች ሕይወት ይጠፋል፣ እልፍ አእላፍ ከኑሮ እየተነቀሉ ይሰደዳሉ። ንብረት ሲዘረፍ ውሎ፣ ሲወድም ያድራል።… ብዙ ሰው በሃዘን፣ በስጋትና በቁጣ ይንገበገባል በዚህ የዘረኝነት ጥፋት።
ተቀናቃኝ የዘረኝነት ጎራ ለመፍጠርና ተቀናቃኝ የዘረኝነት አውራ ለመሆን ለሚፈልጉ ክፉ ሰዎች ግን፣ ትርጉሙ ሌላ ነው። እያንዳንዱ የዘረኝነት ጥፋት፣ እንደ መልካም አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። አንድ የዘረኝነት አውራ የፈጠረው የጥፋት ዘመቻ፣ ለሌላኛው የዘረኝነት አውራ፣ የመቀስቀሻ ሰበብ ይሆንለታል። ዘረኝነትን ይበልጥ ለማስፋፋት ይጠቀምበታል። እናም፣ የጥፋቶች ብዛትና ዘግናኝነት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በአመኔነትም እየከፋ ይሄዳል። ይሄ በዘረኝነት ጥፋት ማግስት የሚፈጠር ክስተት ነው።
ሌላኛው ክስተት ደግሞ፣ ግራ ከተጋባና ከተምታታ አስተሳሰብ ጎን ለጎን፣ ዘግናኝ የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ፣ በዘረኝነት ፖለቲካና ቅስቀሳ አማካኝነት የተፈፀሙ የጥፋት ተግባራትን በሰበብና በማመካኛ አጀብ አለዝቦ ለማሳየት፣ ከዚያም አልፎ ለማቆንጀት የሚደረግ ሙከራ ነው።
‹‹ለሕዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ስላልተሰጠ ነው›› የሚል ሰበብ፣ እጅግ የተደጋገመና የተሰላቸ የወንጀል ‹‹ማስዋቢያ›› ሰበብ ነው። ‹‹መንግስት ፈጣን ምላሽ አልሰጠኝም›› ካልኩ፣ ከዚያ በኋላ፣ ጎረቤቴን የምገድልበት፣ የማላውቀው መንገደኛ የምዘርፍበት፣ መንገድ ዘግቼ የእልፍ ዜጎችን ኑሮ የማናጋበት አዲስ ስልጣን ይኖረኛል ማለት ነው?  
የዘረኝነት ጥፋት በተፈፀመ ቁጥር፣ በማግስቱ የተምታታ አስተሳሰብና ግራ መጋባት ይበራከታል። ሰበብና ማመካኛ መደርደር ይበዛል።
‹‹…ለቤቴ የተመደበ የፖሊስ ጥበቃ ስለተቋረጠ፣… ስጋት ስለገባኝ፣… እንደ ቀድሞ ነፃነት እንዳይታፈን ብዙ ወጣቶች ስለሰጉ፣… ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች እነሱን የሚቃወሙ ሌሎች ወጣቶች ስለገጠሟቸው…››
ይሄ ለነገ አይበጅም። ተጨማሪ የዘረኝነት ጥፋትን ይጋብዛል። እያንዳንዱ ፖለቲከኛ ወይም አጋፋሪ፣ በአንዳች ምክንያት ስጋት ሲገባው… ማንኛውም ሰው ጎረቤቱን የመግደል ስልጣን ይኖረዋል? የመዝረፍ፣ የማቃጠል፣ መንገድ የመዝጋት ልዩ ስልጣን ይኖረናል?
‹‹ነፃነት እንዳይታፈን ሰጋሁ›› በማለትስ፣ የማንኛውንም ሰው ሕይወትና ነፃነትን የማጥፋት ስልጣን ይኖረኛል? በጭራሽ! በጭራሽ!
ስለዚህ፣ ነገሮችን አጥርቶና አሟልቶ ማሰብ ተገቢ ነው።
በማንኛውም ሰበብና ማመካኛ… መንገድ መዝጋትና ኑሮን ማናጋት፣ ንብረት መዝረፍና ማቃጠል፣ አፈናቅሎ ማሳደድና መግደል… ወንጀል ነው።
ወንጀል የፈፀመ ማንኛውም ሰው፣ በዘር ወይም በቋንቋ በጅምላ በመፈረጅ ሳይሆን፣ ለግል ድርጊቱ የግል ሃላፊነት እንዳለበት ታውቆ፣ ድርጊቱ ተመርምሮና ተረጋግጦ፣ በሕጋዊ ሥርዓት የሕግ ዳኝነት ማግኘት አለበት። ይሄው ነው ፍትህ። በግል ማንነትና በግል ሃላፊነት ላይ፣ በእውነትና በስነ ምግባር ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ ፍትህ።


Read 8566 times