Print this page
Sunday, 03 November 2019 00:00

በሰሞኑ ግጭት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ምን ይመስላል?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


            ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን ሌሊት አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ በፌስቡክ ገፁ ‹‹ጥበቃዎቼ ሊነሱ ነው፤ የታጠቀ ሃይል ወደ ግቢዬ እየገባ ነው›› የሚል መልዕክት ማስተላለፉን ተከትሎ በኦሮሚያ አካባቢዎችና በአዲስ አበባ ዙሪያ ወደ 80 የሚጠጉ ዜጎች መገደላቸው ተገልጿል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያያዞም፤ በምዕራብ አርሲ ዶዶላ 3500፣ በድሬዳዋ 680፣ በሰበታ 1ሺህ 100፣ በሀረር መቶ ገደማ አባወራዎች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም በቤተ እምነቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው እንሚገኙ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ኮሚሽኑ፣ ቀይ መስቀል ማህበርና ‹‹የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት›› ለተፈናቃዮች እርዳታ እያቀረቡ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ስለሚገኙበት ሁኔታ፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እየተሰበሰበ ስላለው እርዳታ፣ በቀይ መስቀልና  በኮሚሽኑ ስለሚደረጉ የድጋፍ ጥረቶች፣ እና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ የሶስቱን ተቋማትና አንድ የበጐ አድራጐት ድርጅት ኃላፊ አነጋግራ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች፡፡

                  ‹‹ጊዜያዊ እርዳታ ወሳኝ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልጋል››
                       ሊቀ ትጉሃን ገ/መስቀል ኃ/መስቀል
     
ሊቀ ትጉሃን ገ/መስቀል ኃ/መስቀል እባላለሁ የፍኖተ አብርሃም የብዙሃን በጐ አድራጐት ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ነኝ፡፡ ዛሬ እዚህ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ግቢ የተገናኘነው ሰሞኑን በአገራችን በተለይም በኦሮሚያ አካባቢ በተከሰተው ችግር ለተጐዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች መጠነኛ ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ብርድ ልብስ፣ አንሶላና ሳሙና ገዝተን እዚህ ለሚገኙት ለሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት አስረክበናል፡፡ በተከሰተው ግጭትና ሞት በእጅጉ አዝኛለሁ፡፡ በእውነቱ ይህ ተግባር የኢትዮጵያዊነት ባህልም ስርዓትም አይደለም:: በእምነትም አኳያ ካየነው እምነት ማለት ፍቅር፣ ሰላም አንድነት ነው፡፡ በዘመናዊ ህይወት ስንመለከተውም፣ የዘመናዊነት መገለጫ ሌላ ነው፡፡ አንድ ዘመናዊ ነኝ የሚል ሰው ወይም ቡድን በአንድነት፣ በመግባባት በመተባበር ራሱን፣ አገሩንና ወገኑን ያበለጽጋል እንጂ አንዱ አራጅ ሌላው ታራጅ የሚሆንበት ጉዳይ የለም፡፡ ይህ መሆንም የለበትም፤ መቀጠልም አይገባውም፡፡ አሁን እያደረግን ያለነው እርዳታና ድጋፍ ጊዜያዊ ነው የሚያስፈልገው ግን ዘላቂ መፍትሔ ነው:: ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባትና ደህንነተ መጠበቅ አለበት፡፡ ይህንን ዘላቂ ሰላም ማምጣት የአንድና የሁለት ሰው ብቻ ስራ አይደለም፡፡ የመንግስትም፣ የህዝብም፣ የሰራዊቱም የፍትህ አካላትም… የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት፡፡ በአንድነት የህግ የበላይነትንና ሰላምን ማስከበር አለብን፡፡ አንድነት ሲኖር ፍቅር ሰላምና መረጋጋት ይመጣል፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብና የዚህ ድጋፍ አሰባሳቢ ወጣቶችን በአጠቃላይ እግዚአብሔር አምላክ የነፍስ ዋጋ ያድርግላችሁ እላለሁ:: ወደፊት እንዲህ አይነት ችግር ባያጋጥመን ደግሞ እመኛለሁ፡፡ ካጋጠመን በተሻለ ሁኔታ ህዝብም መንግስትም በጐ አድራጊ ተቋማትም የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ ለወገኖቻችን መድረስ አለብን ስል መንፈሳዊ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

“እስከ 10 ሚ. ብር የሚገመት እርዳታ ተሰብስቧል”
     (አርቲስት ያሬድ ሹመቴ፤ የጉዞ አድዋ መስራች)

እርዳታውን ለማሰባሰብ ሃገር ፍቅር ቴአትር የተመረጠው ከ80 ዓመት በፊት ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ አገራችንን ለመውረር ሙከራ ባደረገበት ጊዜ፣ ጀግኖች በዱር በገደል ተሰማርተው ለኢትዮጵያ አንድነት መምጣት መስዋዕትነት በሚከፍሉበት ጊዜ ነው የሀገር ፍቅር ማህበር የተቋቋመው፡፡ ይህ ማህበር የተመሰረተውም በተለያዩ ህዝብን በሚያነቁ የደጀንነት ተግባራት ተሰማርተው በነበሩ ታላላቅ ሰዎች ነው፡፡ ለእነሱ መታሰቢያነት የተቋቋመና 84ኛ ዓመቱን ለመያዝ የተቃረበ ቴአትር ቤት ነው፡፡ ከስያሜው ጀምሮ አሁን ከምናደርገው ተግባር ጋር ተመሳሳይ ስራ ሲሰራ የነበረ ቤት በመሆኑ ነው - ድጋፉን እዚህ የምናሰባስበው፡፡ ከቦታው በላይም ስሙ “የሀገር ፍቅር” ስለሆነ ነው የተመረጠው፡፡ እኛ እርዳታውን የምናሰባስበው ችግር ሲከሰት ድንገት እየተሰባሰብን ነው እንጂ በቋሚነት መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ወይም በሌላ መንገድ ተደራጅተን የተቋቋምን አይደለንም:: ለምን ከተባለ… ሁላችንም ሌላ ስራ አለን፡፡ ነገር ግን ችግር ተከሰተ በተባለ ቁጥር ለወገን መድረስ ያለበት አንድ አካል መኖር አለበት በሚል መዳረሻችንን ይህንን ቦታ አድርገናል፡፡ በዚህ የሚተባበሩንን የሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት ኃላፊዎችን እናመሰግናለን፡፡ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ የምናደርገው የእርዳታ ማሰባሰብ ስራ ነው፡፡ አሁን በዚህ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ 25 አባላትን ነው ያካተትነው፡፡ የ“ቅድሚያ ለሰብአዊነት” የጉዞ አድዋ መሪዎችና አባላት እንዲሁም ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ጨምረን 25 የኮሚቴ አባላት ሆነን ስብሰባ ካደረግን በኋላ ቀኑን ወሰንን፡፡ ቅዳሜ ከስብሰባ በኋላ መግለጫ ሰጥተን፣ ሰኞ ስራውን ጀመርን፡፡ ሰኞ 2፡00 ከመሆኑ በፊት እርዳታ መምጣት ጀምሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ይህ እንቅስቃሴ ‹‹የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት›› ብለነዋል፡፡ ምክንያቱም ከአንድና ከሁለት ኃላፊነት ከሚወስዱ ሰዎች በላይ ከተለያዩ ቡድኖችና ግለሰቦች ጋር በዛ ብለን እየሰራን ስለሆነ ነው፡፡ እስካሁን ከብሔራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽንና ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር ነው የምንሰራው:: ለምን ካልሽኝ የ “ሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት” ስራውን እዚህ ግቢ ነው የሚጨርሰው፡፡ እዚሁ ግቢ የተሰበሰቡት ንብረቶች እንዳሉ ከእኛ እጅ ወጥተው ቀጥታ ለተጐጂዎች በቀይ መስቀል በኩል ተጭነው ይሄዳሉ፡፡ እኛ እስካሁን በጥሬ ገንዘብ ምንም አንቀበልም፡፡ የማይበላሹ ምግቦች፣ ዘይት፣ አልባሳት፣ የመመገቢያ ቁሳቁስ፣ የንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስና ዳይፐር) እና መሰል ድጋፎችን ብቻ ነው የምናሰባስበው:: እነዚህ የሰበሰብናቸውን ለቀይ መስቀል እዚሁ ነው የምናስረክበው፡፡ ዛሬ (ሐሙስ ዕኩለ ቀን ማለት ነው) ቀይ መስቀል ማህበር አንድ ትልቅ መኪና ከእነታሳቢው እዚህ ግቢ ልኳል፣ ወደ ዶዶላ እርዳታው ይላካል፡፡ ቅድሚያ ለዶዶላ የሰጠነው እዛ ያለው ችግር ገዘፍ ያለ ስለሆነ ነው፡፡ ቀይ መስቀል እዚህ ይረከበንና አንድ የእኛ ተወካይ አብሮ ሄዶ ለተረጂዎቹ በትክክል መድረሱን ያረጋግጣል፡፡ እነሱ አስረክበው ለእኛ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ እኛ ደግሞ መልሰን ለህዝቡ በአግባቡ ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ ይህን አይነት እምነትና ግልጽነት ህዝቡ ሲያይ ወገኑን ለመደገፍ ፍላጐቱ እያደገ ይመጣል፡፡ ለእርዳታ ጥያቄው የአዲስ አበባ ህዝብ የሰጠው ምላሽ በጣም ውስጥን የሚነካ ነው፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ማዕከል ናት፡፡ የኢትዮጵያዊነት ሃሳብና ስሜት ትክክለኛ ቦታውን ይዞ የምታገኚው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ የሚገርምሽ የሚረዳው ብቻ ሳይሆን ተረጂውም ጭምር እዚህ ግቢ እየመጣ ነው፡፡ ይሄ የሚያሳየው ችግሩ የደረሰበትም የችግሩም መፍትሔ ማዕከል አዲስ አበባ መሆኗን ነው:: በነገራችን ላይ በጣም ግልጽ መሆን ያለበት፤ ከአዲስ አበባ ውጭ ማለትም በውጭ የሚኖሩ ወገኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ዘመዶቻቸው ገንዘብ በመላክ፣ በዘመዶቻቸው በኩል የሚያስፈልጉ እቃዎችን እያመጡ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችም (ችግሩ ከደረሰበት ቦታም ጭምር ማለቴ ነው::) ለምሳሌ ድሬደዋ ላይ ወደ 680 ተረጅዎች እንዳሉ ከቀይ መስቀል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል:: ድሬደዋ ያሉ ሰዎች እንኳን በፀጥታ ስጋት ምክንያት እዛው ላሉ ተረጂዎች ድጋፍ ለማድረግ ስለተቸገሩ፣ አዲስ አበባ ባሉ ዘመዶቻቸው በኩል እዚህ ድረስ ድጋፍ እየላኩ ነው፡፡ እዚያ እርዳታ ሲሰጡ ከታዩ ችግር  ይደርስብናል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ስታይ ልብ ይነካል፡፡ አንቺም ተዘዋውረሽ እንደተመለከትሽው፣ ዱቄት ሩዝ፣ ማካሮኒ፣ ሴሪፋም ብስኩት፣ ዘይት፣ ብርድ ልብስ፣ አንሶላ፣ በርካታ አይነት አልባሳት፣ ጫማ፣ የቤት ዕቃ - ጀሪካን፣ ሰሀን፣ ብረት ድስት እየመጣ ነው፡፡ እስከ ትላንትና ማታ ድረስ (ረቡዕ ማታ ድረስ) ምን ያህል እርዳታ እንደተሰበሰበ እናውቃለን፡፡ አሁን ከልምዳችንም መጋዘኑ ምን ያህል ይይዛል? ውጭ ያለውስ ምን ያህል ይሆናል የሚለውን እናውቃለን፡፡ ስለዚህ እስከ ረቡዕ ማታ ድረስ ከ8-10 ሚ. ብር የሚገመት ሃብት ተሰብስቧል:: በነገራችን ላይ አሁን የተሰበሰበው ትንሽ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ልንገርሽ፤ ለጌዲኦ 12 ጭነት መኪና እርዳታ ነው የላክነው:: የተፈናቀለው 500ሺህ ህዝብ ነው፡፡ የላክነውን እርዳታ በገንዘብ ተምነሽ ለተፈናቀለው ህዝብ ስታካፍይው፣ የ3 ቀን ምግብ ብቻ ነው የላክነው፡፡ ያንን ሁሉ መኪና ልከን ማለት ነው:: አሁንም የተሰበሰበው ቢሆን ወደ ቤታቸው እስኪመለሱና እስኪረጋጉ ትንሽ ይረዳቸዋል እንጂ በቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛ ከምንም በላይ ትልቅ ነገር የምንለው፣ አሁን እዚህ ከህዝቡ የሚሰበሰበው እርዳታ ለተቸገሩ ወገኖች ተስፋ ይሰጣል፡፡ ወገን አለኝ እንዲሉ ያደርጋል:: ሁሉም ሰብአዊነትን ያስቀድም፤ ለዚህም በየግላችን ኃላፊነታችንን እንወጣ ነው የምለው፡፡ ሰብአዊነት ይከበር፤ እናቶች እንዳይነኩ ህፃናት እንዳይጐዱ፣ ቤተሰብ እንዳይቸገር፣ ከዱላ ከጭካኔ ወጥተን ሰብአዊነትን እናስቀድም፡፡ በዚህ ሰዓት መፍትሔ የሚሆነው ስለ ኢትዮጵያ፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ህብረት፣ ከንግግርና ከስብከት አልፎ ከችግር የሚያወጣ ተግባር ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡

‹‹ወደ ዶዶላ አስፈላጊውን እርዳታ ልከናል፤ ድጋፉ ይቀጥላል››
    ሰለሞን አሊ (ዶ/ር) (በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የኮሙኒኬሽን ኃላፊ)

ሰሞኑንም ሆነ ባለፈውም አመት እያጋጠመ ባለው ችግር የደረሰውን ሰው ሰራሽ መፈናቀልና የህይወት መጥፋት ስመለከት እጅግ በጣም ነው ሀዘን የሚሰማኝ፡፡ እንደ አንድ በሰብአዊነት ሥራ ላይ እንደተሰማራ ተቋም እነዚህ ነገሮች እንዴት ነው በየጊዜው የሚከሰቱት እንዴትስ ነው የሚቆሙትና የሚቋጩት?... የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ምክንያቱም የሰብአዊ ቀውሱ ተጐጂዎችን ብቻ ሳይሆን ጐጂዎቹን፣ ማህበረሰቡንና የአገር ኢኮኖሚን በሙሉ የሚጐዳ ነው፡፡ ጉዳቱ ደግሞ የጐጂውንም የጥቃት አድራሺዎችንም የነገ አገር ተረካቢ ወጣትና ታዳጊ ልጆች የሚነካ ነው፡፡ የጐጂውም የተጐጂውም ልጆች አንድ አገር አንድ አካባቢ ነው የሚኖሩት፡፡ አሁን ላይ አሳዳጅና ተሳዳጅ፣ እያዩ የሚያድጉ ልጆችን ነው የሚያበላሸው፤ ተስፋም ያስቆርጣል፡፡ እንግዲህ እኛ በሰብአዊ ተቋም ውስጥ እንደመስራታችን እንዲህ አይነት ችግሮች እኛንም ይጐዱናል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ሰሞን በቅማንትና አማራ በተነሳ ግጭት ሁለት ሰራተኞቻችን ተጐድተው፣ አንዱ በተዓምር ሳይጐዳ ተርፏል፡፡ ለተፈናቃዮች ድንኳን ሊተክሉ ጐንደር አካባቢ በስራ ላይ እያሉ ነው ጉዳቱ የደረሰባቸው፡፡ አንዱ በሁለት ጥይት ተመትቶ ሆስፒታል ገብቷል፡፡ አንዱ ከጥይት ለማምለጥ ከመኪና ሲወርድ እጁን ተሰብሯል፡፡
ሰብአዊ ቀውሶች የሚያስከፍሉን ዋጋ ብዙ ነው - ስነ ልባናዊ፣ አካላዊ፣ ቁሳዊ፣ ብሎም የህይወት መስዋዕትነትን ጨምሮ ጉዳቱ በርካታ ነው፡፡
‹‹እኛ የተለየን የሰው መገኛ፣ ምድረ ቀደምትና የመቻቻል ባህል ያለን ነን›› እያልን ይሄ ሲከሰት ያሳዝናልም ያሳፍራልም፡፡
በኦሮሚያ ከሚገኙ የተለያዩ የዞን ጽ/ቤቶቻችን በጣም ዝርዝር የሆነ መረጃ እየጠበቅን እንገኛለን፡፡ ‹‹ተባረው ነው፣ ቤት ንብረታቸው ወድሞ ነው›› የሚለውን እየጠበቅን ነው፡፡ ለጊዜው የዶዶላ ተፈናቃዮች ገ/እግዚብሔርና ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ነው ተጠልለው የሚገኙት፡፡ እስከ ትላንትና ባለን መረጃ፤ በዶዶላ ከ3500 በላይ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ ይሄ በምዕራብ አርሲ ዞን (ዶዶላ ብቻ ነው) በአርሲ ደግሞ፣ በጥቅምት 12 እና 13 አስር ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት ተደርጓል፡፡ በአዩ ዱኪና አሰላ ነው ይህ የሞት ሪፖርት የተመዘገበው፡፡ በአሁን ሰዓት ከዶዶላ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ድንኳን ተተክሎ፣ ለቆሰሉ ለደከሙ የአምቡላንስና የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ እየሰጠን ነው፡፡ ትላንትናም (ረቡዕ) የላክነው እርዳታ ደርሷል፡፡ 1ሺህ የፕላስቲክ የመሬት ንጣፎች፣ 1ሺህ የመጠለያ ፕላስቲኮች፣ 1ሺህ የገላ ሳሙና፣ 1ሺህ የልብስ ሳሙና፣ 1700 ያህል ቁሳቁሶች (ጆግ፣ ኩባያ፣ ሳህኖችና ባልዲዎች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ እቃ የሚይዙባቸው የፕላስቲክ ቦርሳዎች፣ እያንዳንዳቸው 10ሺህ ሌትር ውሃ የሚይዙ ሁለት ሮቶዎች፣) ልከናል፡፡ እዛ ያሉ ሰራተኞቻችንና በጐ ፈቃደኞችም አስፈላጊውን ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ ወደ 700ሺህ ብር የሚያወጣ እርዳታ ልከናል፡፡
ድሬደዋን በሚመለከት ከ600 በላይ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ ወለቴም አካባቢ እንደዚሁ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ ህብረተሰቡና መንግስት እርዳታ እያደረገላቸው ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ግቢ ውስጥ እርዳታ እያሰባሰበ የሚገኘው “ሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት” ጋር አብረን ለመስራት ትላንት (ረቡዕ) በሀገር ፍቅር ተገኝተን ተነጋግረናል፡፡ ዛሬ (ሐሙስ) ከካናዳ ያገኘነው ትልቅ ትራክ ለዶዶላ የላክነውን አድርሶ መጥቷል፡፡ አሁንም አልሚ ምግቦችንና ለሎች ቁሳቁሶችን ይዞ ዶዶላ ላሉት ያደርሳል እዛ በጣም ብዙ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ቁጥራቸውም ብዙ ነው፡፡
በአሁን ሰዓት እየተረጋጋ ነው ብለን እናምናለን፤ ነገር ግን ገና መቶ በመቶ ስላልሆነ የሎጂስቲክ ስትራቴጂ እያወጣን ነው፡፡ አሁን ዶዶላ፣ ድሬደዋ፣ ወለቴ፣ ሰበታ… አካባቢ ተፈናቃዮች አሉ፡፡
ከሀረር የእኛ ሰራተኛ ደውሎ በነገረኝ መሰረት፤ ከአጐራባች ቦታዎች ወደ ሀረር ከተማ የመጡ 100 አባ ወራዎች ፖሊስ ጣቢያና ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው ለ90 አባወራ ከዶዶላዎቹ ጋር ተመሳሳይ የሆነ እርዳታ መከፋፈሉን ነግሮኛል፡፡ እንግዲህ አሁን ባለው ሁኔታ የተፈናቃዮቹ ቁጥር ጥርት ባለ ሁኔታ አልታወቀም፡፡ ገና እየተሰራ ነው፡፡ አርሲ የተጠለለ ሰው ባይኖርም አሰላ ላይ 17 ከባድ 30 ቀላል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የአምቡላንስና የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ አድርገናል::  በቀጣይ የተጣራ የተፈናቃዮች ቁጥር ያሉበት ሁኔታ ሪፖርት ሲደረግ በምናወጣው ስትራቴጂ መሰረት፣ በምንችለው አቅም ድጋፍ እንሰጣለን:: ከእኛ አቅም በላይ የሚሆን ከሆነ ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበርን ድጋፍ እንጠይቃለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት፣ በየቦታው ካሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቻችንና በበጐ ፈቃደኞቻችን አማካኝነት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡
በ2011 ዓ.ም ለደረሰው ጉዳትና መፈናቀል፣ እስከ 2 ሚ. ለሚጠጋ ሰው ደርሰናል፡፡ በመደበኛው ስራችን በዓመት ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆን ሰው ቢያንስ የአምቡላንስና የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ሰጥተናል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጀ በ300 ጣቢያዎቻችን በተጠንቀቅ ሆነው ችግር በደረሰ ጊዜ አስቸኳይ እርዳታ የሚሰጡ 480 አምቡላንሶች አሉን፡፡ እነዚህ አምቡላንሶች በ24 ኪ ሜ ራዲየስ ለሚገኙ ነፍሰጡር እናቶች፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለደረሰባቸው፣ ወድቀው ለተገኙ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

    ‹‹5 ሺ ለሚጠጉ ተፈናቃዮች አስፈላጊው እርዳታ ተልኳል››
       (አቶ ደበበ ዘውዴ፤ በብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር)
በብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሰራር መሰረት፣ በአንድ አካባቢ ላይ አደጋ ከደረሰ በኋላ አደጋው የተከሰተበት ክልል ድጋፍ እንድናደርግ በደብዳቤ ሲጠይቀን ነው እርዳታ የምናቀርበው፣ ክልሉ ‹‹በዚህ በዚህ ቦታ ይህን ያህል ሰው ተፈናቅሏል፣ እርዳታ እንፈልጋለን›› ብሎ የተፈናቀለውን ሰው ቁጥር ጭምር በደብዳቤ ሲገልጽ፣ እኛ በዚያ መሰረት አስፈላጊውን እርዳታ እንልካለን፡፡
ከዚያ አኳያ በኦሮሚያ ክልል በሰበታ 300 አባወራና 800 ቤተሰብ፣ በድምሩ 1ሺህ 100 ሰው እንዲሁም በምዕራብ አርሲ ዶዶላ 3ሺህ 366 ሰው መፈናቀሉን የኦሮሚያ ክልል ጠቅሶ እርዳታ እንድናደርግ በደብዳቤ በጠየቀን መሰረት ለሁለቱም ቦታዎች እህል፣ ጥራጥሬ፣ ዘይት ብስኩትና አልሚ ምግብ ልከናል፡፡ አልሚ ምግቡን በተመለከተ አንድ ቦታ አደጋ ተፈጥሮ ሰው ሲፈናቀል፣ ህፃናት፣ አጥቢ እናቶችና ነፍሰጡሮች ይኖራሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ፣ ከተፈናቃዩ ቁጥር 35 በመቶ ለሚሆኑት አልሚ ምግብ ይላካል፡፡ እኛም በዚህ መሰረት ለዶዶላና ለሰበታ ተፈናቃዮች አስፈላጊውን እርዳታ ልከናል፡፡ ከሁለቱ ቦታዎች ውጭ በድሬዳዋና በሀረር ላሉት ተፈናቃዮች ድጋፍ እንድናደርግ አልተጠየቅንም፡፡ እዛም ግን ተፈናቃዮች እንዳሉ ሰምተናል፡፡ እንግዲህ ከከተማ አስተዳደሩ ወይም ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ አደጋ ሲያጋጥም ነው፤ ወደኛ ደብዳቤ የሚልኩት፡፡ የተፈናቃዩ ቁጥር አነስተኛ ከሆነ ክልሉ ተፈናቃዮችን መርዳትና መደገፍ ይችላል፡፡ አሁንም ቢሆን ከድሬደዋም ሆነ ከሌላ ቦታ ደብዳቤ ከተፃፈልን ወዲያውኑ ድጋፉን እናደርጋለን፡፡ በነገራችን ላይ አነስተኛ ተፈናቃይ ሲኖር፤ ከቀበሌ ከወረዳ፣ ከዞን እስከ ክልል ባለ መዋቅር ድጋፍ ስለሚቀርብ ክልሉ ያንን ባቅሙ መወጣት ይችላል፡፡  አሁን ዶዶላ ላይ ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው የሚል ነገር እየሰማን ነው፡፡ መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር የህዝብ ለህዝብ ስራ በመስራት ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ይመለሳሉ፡፡ አደጋው የድርቅ ከሆነ እርዳታው ለ5 ወር ይሰጣል:: ድጋፉን በገንዘብ አናሰላም፤ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ዱቄት፣ 0.45 ሊትር፣ ዘይት 1.5 ኪ.ግ ጥራጥሬ፣ አልሚ ምግብ ደግሞ የተፈናቃዩን 35 በመቶ ይሰጣል፡፡ አንድ ቤተሰብ 5 አባላት ካሉት ከላይ ለአንድ ሰው የተሰጠውን በአምስት ማብዛት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ነው የምንለካው:: በዚህ መሰረት በዶዶላና በሰበታ ለተፈናቀሉት ሰዎች እርዳታውን አድርሰናል፡፡ በቀጣይ ከአቅም በላይ ሆኖባቸው ደብዳቤ የሚጽፉልን ክልሎችም ካሉ በዚሁ መሰረት እርዳታውን በፍጥነት እናደርሳለን ማለት ነው፡፡



Read 3716 times