Saturday, 02 November 2019 12:57

“ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

  • ነዳጅና መለዋወጫ የማይፈልጉ ቀላልና ዘመናዊ ናቸው
      • የአገራችን የአውቶ ተማሪዎች ወደፊት እዚሁ እንዲያመርቷቸው እፈልጋለሁ
      • ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከውጭ ምንዛሬ ማስቀረትና ከስራ እድል ፈጠራ አንፃር ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡

          የህክምና ባለሙያውና ኢንቨስተሩ አቶ ቶማስ ገ/መስቀል የዛሬ 10 ዓመት ግድም ወደ ሀገር ቤት ከመመለሳቸው በፊት ለረጅም ጊዜ የኖሩትና የሰሩት በአሜሪካ ነው፡፡ የኩላሊት እጥበት ነርስም ነበሩ፡፡ በአገራችን የመጀመሪያውን የኩላሊት እጥበት (ዲያሊስስ) ክሊኒክ በአዲስ አበባ የከፈቱት አቶ ቶማስ፤ ለኩላሊት እጥበት ህክምና ወደ ደቡብ አፍሪካና ታይላንድ ይሄዱ የነበሩ የኩላሊት ታማሚዎች አገራቸው ላይ ህክምናውን እንዲያገኙ  ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
የኩላሊት እጥበት ማሽኖትን ወደ አገር ውስጥ ያስገቡም ነበር፡፡ በቅርቡ ደግሞ ከንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ አዲስ ፕሮጀክት ጀምረዋል፡፡ ይህንንም ፕሮጀክታቸውን ባለፈው ሳምንት ለመገናኛ ብዙኃን አስጐብኝተዋል:: አቶ ቶማስ ገ/መስቀል በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የኢንቨስትመንት ሃሳብ አቅርቦ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ያስረዳሉ፡፡ እስካሁን በአገራቸው የሰሯቸውንና ወደፊት ሊሰሩ ያቀዷቸውንም ይናገራሉ:: የአዲስ አድማሷ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ አነጋግሯቸዋለች፡ እነሆ፡-

            እንዴት ነበር ከአሜሪካ ጠቅልለው ወደ አገሩ የመጡበት?
ነፍሳቸውን ይማርና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፣ አሜሪካ መጥተው በነበረ ጊዜ፣ “በኩላሊት ህመም ዙሪያ አገርህ ላይ ብትሰራ” ብለው ለመኑኝ፡፡ እኔ ደግሞ እሳቸውን በጣም ነበር የምወዳቸው፡፡ “እኔ መለመንም የለብኝም፤ ግዴታዬ ነው እመጣለሁ” አልኳቸውና መጣሁ፡፡ ከዚያም የኩላሊት እጥበት ህክምና ጀመርኩኝ፡፡ አሁን ለኩላሊት ህክምና ደቡብ አፍሪካና ታይላንድ (ባንኮክ) መሄድ ቀርቷል፡፡
የሚያሳዝነው ግን የኩላሊት ህክምናን አቅሙ ችሎ የሚታከመው 20 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው፡፡ ሌላው 80 በመቶ ታማሚ እንዴት እየሆነ እንዳለ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ አገሩን በተለያየ መንገድ ሲያገለግል የኖረ ሁሉ በዚህ በሽታ እንደ ውሻ እየሞተ፣ እንደ ተራ ነገር እየወደቀ ነው ያለው፡፡ ይህንን የኩላሊት ህክምና ለመስጠት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን መጀመሪያ ከአሜሪካ አመጣሁ፡፡ በጣም ውድ ነበር፡፡ አውሮፓም ሄድኩኝ፤ እዚያም ውድ ሆነ፡፡ ቀጥዬ ወደ ቻይና ሄድኩኝ፡፡ በጣም በሚገርም ዋጋ አገኘሁ:: ለካስ ቱርኮች ሲሸጡልኝ የነበረው ከቻይና እየገዙ ነው፡፡ ዋጋው በግማሽ ሲቀንስልኝ፣ እኔ ደግሞ የኩላሊት ህክምናውን ዋጋ በዚያው ልክ በግማሽ ቀንሼ፣ አገልግሎት መስጠት ጀመርኩኝ ማለት ነው፡፡
አሁን ከንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በጥምረት የጀመሩት ሥራ ምንድን ነው? ትንሽ ያብራሩልን?
እንግዲህ እነዚህን የህክምና መሳሪያዎች ለማምጣት የዛሬ አምስት አመት ወደ ቻይና በሄድኩ ጊዜ ነው፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች አይቼ፣ ፈዝዤ የቀረሁት፡፡ የት ነው የሚገኙት ብዬ ስጠይቅ፣ “ኤግዚቢሽን ላይ ታገኛቸዋለህ” አሉኝ፡፡ ትልልቅ ኤግዚቢሽኖችን ስከታተል አምራቾቹን አገኘኋቸው፡፡
ምን ዓይነት ተሽከርካሪዎቹ ናቸው?
ባለ ሁለትና ባለ ሶስት እግር ሆነው፣ ባትሪ ቻርጅ ተደርጐ የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ እንደ ፍሪጃችን፣ ላፕቶፖቻችን፣ እንደ እጃችን ስልክና እንደ ማንኛውም እቃዎቻችን በኤሌክትሪክ ቻርጅ አድርገን፣ የምንጠቀምባቸው ቀላልና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ የእጅ ስልካችንን ማታ ቻርጅ አድርገን፣ ቀኑን ሙሉ ስንጠቀምበት እንደምንውለው፣ እነዚህንም ማታ ለአራትና አምስት ሰዓት ቻርጅ አድርገናቸው፣ ቀኑን ሙሉ ስንጠቀምባቸው እንውላለን፡፡ እንደ ባትሪያቸውና እንደ አይነታቸው ዋጋቸው ይለያያል፡፡ ዋጋቸውም በጣም ትንሽ ነው፡፡ በሌላ በኩል በካይ ጭስ የላቸውም፤ ምክንያቱም ነዳጅ አይጠቀሙም፡፡ ሁለተኛ ቀላል ቴክኖሎጂ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ለተለያዩ ችግሮቻችን መፍትሄ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ ለትራንስፖርት፣ ለእቃ ማጓጓዣ፣ ለቆሻሻ ማመላለሻ … ከኋላው ታንከር ያለውን ተሽከርካሪ ውሃ በመሙላት አትክልት ለማጠጣት እንዲሁም መኪና ለማጠብና ለሌሎች በርካታ ነገሮች ያገለግላሉ:: ኑሮንም በእጅጉ ያቀልላሉ፡፡
በጉብኝቱ ላይ “ቶም ኢ ባይክ” እንደሚባሉ ነግረውናል፡፡ እስቲ ስለ አሰራራቸውና አጠቀቀማቸው ይንገሩን?
ለምሣሌ ፓሴንጀር የሚባለው ባጃጅን ተክቶ የሚሰራ ነው፡፡  ስምንት ሰው የመጫን አቅም አለው፡፡ 5 ኪዋት ማታ ጃርጅ አድርጐ፣ 90 ኪ.ሜ እና ከዚያ በላይ ይጓዛል፡፡ 1ኪ ዋት ቻርጅ የኢትዮጵያ 30 ሳንቲም ነው፡፡ 5 ኪዋት ደግሞ 1 ብር ከ50 ሳንቲም ብቻ ነው የኤሌክትሪክ ሃይል የሚጠቀመው፡፡ አሁን 1 ብር ከ50 ሳንቲም ገንዘብ ነው?  ስለዚህ ይህንን የኤሌክትሪክ ኢ-ባይክ የሚያሽከርክር ባጃጅ ሹፌር፣ አንድን ተጓዥ በ50 ሳንቲም ቢያጓጉዝ እንኳን ያዋጣዋል:: የነዳጅ የሞተር ዘይትና መሰል ወጪዎች የሉበትም፡፡ ሌላው ቀርቶ መለዋወጫ እንኳን አይፈልጉም፡፡ እኔ ይህን ምርት አንድ ሰው ሲገዛኝ፣ የሁለት ዓመት ዋስትና እሰጠዋለሁ፡፡ በምርቶቹ ይህን ያህል እተማመንባቸዋለሁ፡፡  
እርሶ ባለሀብት ነዎት፡፡ በመንግስት በኩል ንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አለ፡፡ የእነዚህ ተሽከርካሪዎች አምራቾችም አሉ፡፡ የሶስታችሁን አጋርነት ምን ይመስላል?
ባለሀብትና ሀሳቡን ያፈለቅሁት እኔ ነኝ:: ንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን እንዴት አገኘሁት መሰለሽ? በTVET በኩል ኤግዚቢሽን ልመለከት ሄጄ ነበር፡፡ በተማሪዎቹ ተሰርቶ ለእይታ የቀረበው ነገር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ይሄ ሁሉ ወጣት ተማሪ ሰራው ተብሎ ለእይታ የቀረበውን አይቼ አፈርኩኝ፡፡ “እስኪ ኑና እኔ የምሰራውን ተመልከቱ፤ ይሄንን ነው ሰራን የምትሉት” ስላቸው በንዴት መጥተው አዩልኝ፡፡
የት መጡ? ምንስ ተመለከቱ?
ገርጂ ሮባ ዳቦ ቤት አጠገብ የእነዚህ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ አለኝ - የዛሬ ሁለት ዓመት ያቋቋምኩት፡፡ ነገር ግን ተሳክቶልኝ ሊስፋፋ አልቻለም ነበር:: እናም የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን መጥቶ ካየ በኋላ “እና ምን እናድርግ?” አለኝ፡፡ “በመጀመሪያ በዚህ አዲስ ቴክኖሎጂ ተማሪዎቻችሁን ላሰልጥን፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ላድርግ፣ ሁለተኛ ከሚመረቁት ተማሪዎች 50 በመቶዎቹን ቀጥሬ የስራ እድል ልስጥ” አልኩት:: “ታዲያ ከእኛ የምትጠብቀው ምንድን ነው? ምን ላድርግልህ?” አለኝ - ዲኑ አቶ መለስ፡፡ “እኔ ደግሞ ተማሪዎቻችሁን የማሰለጥንበት የመገጣጠሚያ ቦታ ስጡኝ” አልኳቸው፡፡ ይሄ ፊት ለፊትሽ የምታይው ትልቅ መጋዘን ተሰርቶ ሸረሪት አድርቶበት የተቀመጠ ነበር፡፡ ዲኑ ሳያቅማማ ይህንን አዳራሽ ሰጠኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ አቶ መለስ ቢሮክራሲ የማያውቅ፣ በራስ መተማመን ያለውና የውሳኔ ሰው በመሆኑ ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡ እኔ ይህን ሁሉ የተሽከርካሪ ቦዲ ከውጭ ነው የማስመጣው:: ራሳቸው ተማሪዎቹ ይገጣጥማሉ፡፡ በርካታ ነገሮችን ይማራሉ:: ወደፊት ደግሞ ማጠፊያዎችንና ሌሎች ብረታ ብረት ቦዲዎችን እዚሁ አምርተው የማይገጥሙበት ምክንያት የለም፡፡ “ይሄንንማ እኛም እንሰራዋለን” አሉ፡፡ ት/ቤቱ ከሰራው ደግሞ እኔ ከት/ቤቱ እገዛዋለሁ፡፡
ኮሌጁ ተማሪዎቹን ከማሰልጠን በተጨማሪ ሌላ ምን ጥቅም ያገኛል?
ሶስት ጥቅሞች ያገኛል፡፡ አንደኛ፤ የእኔን ምርቶች አምርቶ ይሸጥልኛል፤ ይሄም የስራ እድል ይፈጥራል፡፡ ሁለተኛ፤ ተማሪዎቹ እስከ ዛሬ ከሚያውቁት የተለየና አዲስ የቴክኖሎጂ ሽግግር ያገኛሉ፡፡ ሶስተኛ፤ ከሰልጣኞቹ 50 በመቶውን እቀጥርለታለሁ፡፡ ስራ አጥነትን በመቀነስ በኩል አስተዋጽኦ አለው፡፡ እኔ 50 በመቶውን እቀጥራለሁ አልኩ እንጂ ወደፊት ሁሉም ተማሪዎች የእኔን የስራ ፈጠራ ተከትለው፤ የስራ እድል እንደሚያገኙ በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ባጃጁም ሞተር ሳይክሉም፣ ከኋላው የእቃ መጫኛ ያለውም… ብቻ ሁሉም ኢ - ባይኮች ታርጋም መንጃ ፈቃድም አያስፈልጋቸውም ስትሉ ሰምቻለሁ፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ታርጋ ሳይኖራቸው፣ አሽከርካሪዎቹ መንጃ ፈቃድ ሳይዙ ሰው ቢገጩ፣ ጥፋት ቢያጠፉ በምን ተይዘው ይጠየቃሉ? ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ከመንገድ ትራንስፖርት ቢሮዎች ጋር ያደረጋችሁት ስምምነት አለ?
ኦህ… በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው:: በእውነቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር ለ6 ወራት ስንጨቃጨቅ ነው የከረምነው፡፡ ቻይና አገር እነዚህ ተሽከርካሪዎች ያለ መንጃ ፈቃድና ያለ ታርጋ በቀላሉ በነፃነት ያሽከረክሯቸዋል፡፡ ምክንያቱም ብዙ አይሮጡም፡፡
በሰዓት ስንት ኪ.ሜ ነው የሚሄዱት?
በሰዓት 30 ኪ.ሜ ብቻ ነው የሚሮጡት:: እዚያ ቻይና እንደሆነው እዚህም መሆን ይችላል ስላቸው “ሊሆን አይችልም፤ ይህንን የምናስተናግድበት ህግ የለም፡፡ በህጋችን ውስጥም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ልናስተናግድህ አንችልም” በሚል እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተን ነበር፡፡ በዚህ መሃል ክብርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ጋር እንደ ምንም እድል አግኝቼ ዘልዬ ስገባ፣ ያልጠበቅኩትን ምላሽ አገኘሁ፡፡
ምን አሉ ሚኒስትሯ?
አሁን በስዕል የምታሳየኝን ተሽከርካሪዎች በሙሉ ቻይና አይቻቸዋለሁ፡፡ መቼ ነው እነዚህን ተሽከርካሪዎች ኢትዮጵያዊ ባለሀብት እዚህ አገር የሚያመጣቸው እያልኩ ስመኝ ነው የመጣኸው አሉኝ፡፡ 6 ወር ሙሉ በዚህ ጉዳይ ሲነታረክ ለቆየ ሰው፣ የሚኒስትሯ ምላሽ ምን ስሜት ሊሰጠው እንደሚችል መገመት አያዳግትም እኔም ለክብርት ሚኒስትሯ፣ ላለፉት ስድስት ወራት የደረሰብኝን እንግልትና መጉላላት አስረዳኋቸው፡፡ “አሁኑኑ ፈቃድ ታገኛለህ፤ ህግ ሲወጣ ይወጣል፤ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ግን ለእድገታችን አጋዥ ስለሆኑ ሞተር ሳይክሎቹ ያለታርጋና ያለ መንጃ ፈቃድ ይነዱ” ተብሏል፡፡ ቅድም ያነሳሽው የተጠያቂነት ጉዳይ በውይይታችንም ግምት ውስጥ የገባና በትኩረት የታየ ጉዳይ ነበር፡፡ እናም ባለ ሁለት እግሮቹ ተሽከርካሪዎች ያለ ታርጋና ያለ መንጃ ፈቃድ ይነዱ፤ ባለ ሶስት እግሮች ግን ታርጋ ያውጡ፡፡ ባጃጅ መሃል ከተማ አይመላለስም የእኛ ባጃጅ ግን ከተማ ውስጥ መመላለስ እንዲችል ተፈቅዷል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገጣጠም በመሆኑ፣ እዚህ አገር በርክቶ ችግር እስኪፈጥር ድረስ መመላለስ ይችላል ተብሏል፡፡
ለምሳሌ የእናንተ ባጃጅ በምን ያህል ብር ለገበያ ይቀርባል?
ነዳጅ የሚጠቀሙ ባጃጆች በአሁን ሰዓት እስከ 180 ሺህ ብር ይሸጣሉ፡፡ የእኛ ባጃጅ ነዳጅ አይፈልግም 2ሺህ ዶላር (70 ወይም 80 ሺህ) ብር ማለት ነው፡፡    
አካባቢ ሳይበክል፣ ነዳጅ ሳይበላ ከሌሎቹ በጣም ይቀንሳል፡፡ ዋጋው ቀደም ሲል እንደነገርኩሽ ሞተርም ሆነ መለዋወጫ አይፈልግም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡ ህንድ ነበረች ባለ ነዳጁን ባጃጅ የምታመርተው፡፡ በ2020 ህንድም ምንም ባጃጅ አላመርትም ብላለች፡፡ ቻይና አገር ባጃጅ በህግ አይነዳም፡፡ አሜሪካማ ጭራሽ የሚያደርሰውም የለም፡፡ እኛ እዚህ እያመጣን የምንገጣጥመውና 8 ሰው የመያዝ አቅም ያለው ባጃጅ ቻይናም ህንድም እየተነዳ ነው፡፡ እኔ ኢትዮጵያ አምጥቼዋለሁ፡፡ በካይነት የለውም፣ ዋጋው ርካሽ ነው መንግስትን ነዳጅ ገዝተህ አምጣ አይልም፡፡ በነዳጅ ማጣትም ስራ አያቆምም፡፡ ቻርጅ ለማድረግ የሚፈጀው 5 ኪ.ዋት፣ 1 ብር ከ50 ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በሁሉም አንፃር ሲታይ፣ ተመራጭነቱ የላቀ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በሌላ በኩል፣ ፕራይቬት ፐብሊክ ፓርትነርሽፕ የተሰኘውን የመንግስትን ፕሮግራም በመተግበርም የበኩላችንን እያደረግን ስለሆነ በዚህ ደስተኞች ነን፡፡
ይህንን ስራ የሚሰራው የእርስዎ ድርጅት ምን ይባላል? አጠቃላይ ኢንቨስትመንቱስ ምን ያህል ነው?
የድርጅቱ ስም “ቶም ታዳሽ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ” ይባላል፣ ኢንቨስትመንቱ ብዙ ነው፡፡ ያው ከውጭዎቹ ባለሀብቶች ጋር ሆነን ነው የምንሰራው፡
አሁን 2 ሚሊዮን ዶላር ነው አጠቃላይ ኢንቨስት ያደረግነው፡፡ ወደ እኛ አገር ገንዘብ ስታመጪው፣ ወደ 60 ሚ. ብር ገደማ ነው፡፡ ሰው እስኪያውቀን በኪሳራ ነው የምንሰራው:: ዞሮ ዞሮ ራዕይ አለኝ፡፡ እዚህ አገር ይህንን ታዳሽ ተሽከርካሪ የማስፋት ራዕይ አለኝ ሰውም እንደሚወደው ጥርጥር የለኝም፡፡
የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪዎችም ሆነ የሌሎቹ ት/ቤት ተማሪዎች የሚሰለጥኑት በትንንሽ ነገር እንደነበርና እርስዎ አዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስገባትዎን ነግረውናል ይህን አዲስ ቴክኖሎጂ ለተማሪዎች የሚያሸጋግር ባለሙያ ከየት አመጣችሁ?  
የረሳሁትን ጉዳይ ነው ያነሳሽው፡፡ እኔ ገና ይህን ስራ ሳስብ በመጀመሪያ ትምህርት ስጡኝ ብዬ ሶስት ኢንጂነሮችን ከሁለት አመት በፊት ውጭ ልኬ አሰለጠንኩኝ፡፡ እነዚህ ሶስት ኢንጂነሮች አሁን 22 ደርሰዋል፡፡ አሁን እንግዲህ ንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ገብተናል፡፡  አንድ ሺህ የአውቶ ተማሪዎች አሉ:: በአንድ አመት ውስጥ አንድ ሺህዎቹንም ለዚህ ላበቃቸው ነው፡፡ ይሀን በማድረጌ ደስ ይለኛል:: እነዚህን ቴክኖሎጂዎች እኮ ነገ ሌላም ሰው ያመጣቸዋል፡፡ የሰው ሃይል ችግር አይኖርም ማለት ነው፡፡ ጥቅሙ ከላይ እንደጠቀስኩልሽ የትየለሌ ነው አካባቢ ጥበቃ  የውጭ ምንዛሬ ማስቀረቱ ቦታ አለመፍጀቱ ጥቂቶቹ ናቸው:: ሁለት በሬ የሚሰራውን የሚተካ ማረሻም መገጣጠም ጀምረናል፡፡ በሁለት ወር ውስጥ ገበያ ላይ ይውላል፡፡ የሁለት በሬ ዋጋ ቀለብ አስቢው… እሱን ሁሉ ያስቀራል፡፡
85 በመቶ አርሶ አደር በገጠርና መብራት በሌለበት የሚኖር ነው፡፡ ማረሻ ማሽኖቹ በመብራት ሃይል ነው የሚሰሩት፡፡ ቻርጅ ለማድረግ አይቸገሩም? ወይስ በፀሐይ ሃይል ቻርጅ ማድረግ ይቻላል?
በፀሐይ ሃይል ቻርጅ ይደረጋሉ ወይ  ላልሽው አይደረጉም ይህንን ቻይናም አላደረገችም፡፡ ነገር ግን እስኪ መጀመሪያ ኤሌክትሪክ የሚያገኙትን አርሶ አደሮች እናዳርስ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ኤሌክትሪክ እየተዳረሰ ነው፡፡ እስኪ ሌሎቹ እስኪያገኙ መብራት ያላቸው ይጠቀሙ፡፡ አሁን አባይ ግድብ ሲያልቅ ደግሞ ሁሉም ኤሌክትሪክ ስለሚያገኝ፡፡ ችግሩ ይፈታል ያኔ ሁሉም አርሶ አደር ይጠቀመዋል፡፡ ለአገራችንም አማራጭ የሌለው ቴክኖሎጂ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡


Read 4753 times