Print this page
Saturday, 02 November 2019 12:51

የአገራችን ዝብርቅርቅ ፖለቲካችን!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

      የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሰዎች እሬሳ እንደ ቄጠማ እየጐዘጐዘ መራመድ ልማዱ ቢሆንም ከዘመን ወደ ዘመን ይህንን ያለማስቀረቱ አሳዛኝነቱን ያጐላዋል፡፡ በንጉሡ ዘመን የተማሪዎች ሬሳ መጐዝጐዝ ሲጀምር፣ ሀገር ያጠፋው አብዮት መጥቶ ምድሪቱን በደም አባላ እንዳጨቀያት አንረሳም፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረውም ትንሽ ይሻል እንደሁ እንጂ ያው ነበር፡፡
አሁን ያለንበት ግን ከዚያ የባሰና በታሪካችንም ውስጥ ወደ አስፀያፊ መጠፋፋት እየተጋፋ ይመስለኛል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የአፍሪካና የኤስያ ሀገራት የተሻለ የታሪክና የእምነት ቁመና አለን ብለን የምንተማመንበት ኩራት ወልቆ እርቃናችንን የቆምንበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ደርግ ሥልጣኑን ሲለቀቅ፣ ያለ ጠባቂ ወታደርና መንግሥት፣ ራሳችንን ጠብቀን ለወያኔ ዙፋኑን ያቆየንበት ጨዋነት እንኳ አፈር በልቶ፣ ወታደር እያለ፣ የውጭ ጠላት ሳይመጣብን፣ መገዳደል መጀመራችን ያምማል፤ ያሳፍራል፡፡ ይሁንና ችግሩ መች የተዘራው የጥላቻ ዘር እንደሆነ ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡
አሁን ሥልጣኑ ላይ ያለውና የቀድሞ ምሥሉን ቀለም የቀባው መንግሥት፤ ለውጡ ሥር ነቀል ስላልሆነ በየደረጃው ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎችም እነዚያው በቀድሞው ቅኝት የተቃኙ ስለሆኑ፤ የራሳቸውን ኪስ ከመሙላት አልፈው፤ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ አልቻሉም:: በወያኔ መራሹ መንግሥት ዘመን ሥልጣን ተጋርተው፣ ሕዝቡን ያሳቀቁትና ያስጨነቁት ሰዎች ዛሬም በየዞኑና ወረዳው ተቀምጠዋል:: ትናንትና ለለውጥ የታገሉ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው ሳይለወጥ ትናንት ላሠሯቸው ሰዎች እየተገዙ ነው፡፡ ይህ በራሱ የፈጠረው ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ አሁን በቅርቡ ሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሄጄ ከሰዎች የሰማሁት ምሬት ሲጠቀለል ሙሉ ሃሳቡ ይኸው ነው፡፡ በአብዛኛው ዘራፊዎች፣ የራሳቸውን ዘመዶች በዙሪያቸው የሚሰበስቡና ሕዝቡን የናቁ ናቸው፡፡ አየር ላይ የተጠንጠለጠሉት ለባህልም ሰዎች፣ አንድ ዓመት አልፏቸውም ሕዝቡን ከኑሮ መወደድና ችግር በቀር ቋቱ ላይ ጠብ ማድረግ የተሳናቸው ለዚያ ይመስለኛል፡፡
የተናገሩትንም ማድረግ ተስኗቸው፣ የህዝብ ቁጣ የተቀሰቀሰው በዚያ ነው ብሎ መጠቅለል ይቻላል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ገና በለውጡ ማግስት ህገወጥ ቤቶችን እያፈረሰ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቅሬታና ተቃውሞ ከሚቀሰቅስ ይልቅ ለለውጡ ለታገሉት ወጣቶች ፕሮጀክቶችን እያዘጋጀ ቦታ ቢያስይዛቸው ኖሮ፣ ዛሬ መያዣ መጨበጫው ባልጠፋው ነበር፡፡
ይህንን ያህል ጊዜ ተኝቶ ሲያንኳርፍ ከርሞ፣ አሁን ዘወር ሲል ቀድሞ በጥቂቱ ያደምጠው የነበረው ወጣት፣ ጆሮውን ደፍኖ ያገኘው ለዚያ ነው ብሎ መገመት ይቀልላል፡፡ መንግሥት ትልቁ ሥራው የህዝብን ሥነ - ልቡና ማወቅ፣ ድምፁን ጠጋ ብሎ መሥማትና በቅድሚያ ጥያቄዎቹን መመለስ ነበር፡፡ ጥሎበት የኛ መንግሥት ዛሬም የሚሰማው የራሱን ካድሬዎች ድምጽ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ተራውን የእሚሰማው እያጣ ነው::
መንግሥታችን ድግሥና ጭብጨባ ላይ ማተኮሩም አንድ ደካማ ጐኑ ነው፤ የሚደገስበት ብር ከየትም ይምጣ ከየት የተወሰኑ ሥራ አጦችን ሥራ ቢያስይዝበት ጠላት መቀነስ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ የመጣውን ገንዘብ ለማግኘት ወጣቶች የሚያዩትን መከራ ተጠግቶ ማስተዋል ያስፈልግ ነበር፡፡ እስቲ ሕዝቡን ማዳመጥ ልመዱ እንበላቸው፡፡ አሁን አሁን ሳየው መሪዎቻችን በራሳቸው ገጽታ ላይ ብዙ የሚደክሙና በትኩረት የሚሠሩ ይመስላሉ:: እኛ ደጋፊዎቻቸው እንኳ ለነገሮች ያለንን ትኩረትና ምጥ ያህል የሚደክሙ አይመስለኝም፡፡
በቅርብ ጊዜ የተቀሰቀሱት አስደንጋጭና አሳፋሪ ግጭቶች የዚህ ቸልተኝነትና ዳተኝነት ውጤቶች ናቸው፡፡ የብዙ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ብዙም የማይደነግጠው መንግሥት የወሰደው እርምጃ፣ ያበጀው መውጫ ቀዳዳም የለም፡፡ የበላይነት ከቃሉ ውጭ መሬት መውረድ አልቻለም፡፡ ሰሞኑንም በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ከወርቅ የጠራ ታሪክ ያለውን የአምቦ ህዝብ ለማነጋገር የሄዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጥያቄ ያለውን ህዝብ መሰብሰብ ሲገባቸው የራሳቸውን ደጋፊዎች ሰብስበው የድሮ ዘፈናቸውን መደጋገማቸው የአምቦን ወጣት አስቆጥቶ የሚያሸማቅቅ ውጤት ላይ አድርሷቸዋል፡፡ እውነት ለመናገር የአምቦ ከተማ ህዝብ ከዚህ ቀደምም ይሁን አሁን በማንም ላይ የብሔር ጥቃት የማይሰነዘር፤ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የፀና አቋም ያለውና በዘመነ ደርግ ወያኔ ሠራዊቱን አግተልትዬ ሲመጣ በዘንግና ዘነዘና፣ በድንጋይና ቢላ የመለስ ጀግና ሕዝብ ነው፡፡ ይህን ሕዝብ ማስቀየምም ማጣትም አያስፈልግም፡፡ እኔ በግሌ በኢትዮጵያዊነቴ እንደ ኩራት የማየው ሕዝብ ነው፡፡
የአምቦ ሕዝብ ችግር የካድሬዎች መሰብሰብና የብሶተኞች መገለል ብቻ ሳይሆን በቅርቡ የተገደሉት የአቶ ሞረዳ ሞሳ ጉዳይም አለበት፡፡ እኒህ ሰውዬ በማህበራዊ ኑሯቸው የታወቁ፣ የራሳቸው ትምህርት ቤት የነበራቸው፣ የሀገር ሽማግሌ ሲሆኑ በማህበረሰቡ ዘንድም የታወቁና የተከበሩ ነበሩ፡፡ ይህ በተፈጠረበት ሁኔታ መንግሥት ነገሩን ለማርገብ በግልግል ተግባር ላይ ሆነው ስለተገደሉት ሰው ሕዝቡን ሳያወያይና ይቅርታ ሳይጠይቅ ወይም ሽምግልና ሳይልክ፣ ካድሬዎቹን ሰብስቦ አዳራሽ ውስጥ የካድሬ ውዳሴ ማድመጥ አልነበረበትም፡፡ እውነት የሚናገሩ፣ የከፋቸውና ያዘኑ ሰዎችን አናግሮ፣ ችግሩን ፊት ለፊት መፍታት ነበር:: ከዚህ ቀደም ቃል ተገብቶላቸው ያልተፈፀመ ነገር ካለም ያንን በፍጥነት መጀመር ይገባ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የዚህ ዓይነት ተደጋጋሚ ስህተቶችን መሥራት በመንግሥታችን የተለመደ ሆኗል፡፡ በሀገር አንድነት ጉዳይ ላይ አንድ አቋም ያላቸውና የአካባቢውን ተወላጅ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናንም ለዚህ መጠቀም ለምን እንደሚፈሩ ግልጽ አይደለም፡፡ መረራ የረዥም ዓመታት የፖለቲካ ልምድ ያላቸው፣ ለህዝብ ነፃነት ብዙ መስዋዕትነት፣ እስራትና እንግልት የቀመሱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ናቸው፡፡ ለበርካታ ዓመታት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አስተምረዋል፤ በተለያዩ ሀገራት ትልልቅና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ተካፍለዋል፡፡ ታዲያ እኒህን ሰው መጠቀም ትቶ ያለ መካሪ መቅረትና ነገርን ሁሉ የልጅ ጨዋታ ማድረግ የሚያዋጣ መንገድ ነው?
ዶክተር ዐቢይ በግላቸው እየተወዛወዙ የሚያመጧት ዶላርና ዩሮስ እስከ መቼ ታዋጣናለች? ዛሬ ወዳጅ ያደረጓቸው ሀገራት ሰዎችስ ሰላም ከሌለ፣ ዘወር ብለውን እንዲያዩን የሚያደርጋቸው ምን ምክንያት ይኖራል? እንደኛ ላለው ደሀ ሀገር የዕድገት መሥመር ውስጥ አንዱ ዋስትና ኢንቨስትመንት ከሆነ፣ ሰላም በሌለበት ሀገር ብሩን የሚረጭ ሞኝ ከየት ይገኛል?
በጥቅሉ ያሁኑ አካሄዳችን ሀገራችንን ወደ ትልቅ ጥፋት እየገፋት ይመስላል፡፡ የምናምነው ፈጣሪም አካሄዳችን በጥበብ የተሞላና ማስተዋል የታከለበት ካልሆነ፣ አንገታችንን ጠምዝዞ ድል ሊሰጠን አይችልም፡፡ እርሱም ባለመርህ አምላክ እንጂ የጠራውን ሁሉ የሚከተል ትልም የለሽ አይደለም፡፡
ይሁንና አሁን መንግሥት ማድረግ ያለበት አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ “ህግ ያስከብር! የሃይል ርምጃ ይውሰድ!” የሚለው ብቻ አያዋጣም:: መጀመሪያ በፖለቲካ ህይወታቸው የበሰሉ፣ ልምድ ያላቸውና አዋቂ ሰዎችን ያማክሩት፤ ዘንድ በዙሪያው ያሰባስብ፡፡ ከዚያ በመቀጠል በየክልሉ ያሉ የሀገር ሽማግሌዎችን ይሰብስብ፤ በዚህ መንገድ የተለያዩ አቋም ያላቸው የህዝብ ተወካዮች ቀርበው ውይይትና እርቅ ይደረግ! የሚያዋጣው መንገድ ይህና ይህ ብቻ ነው:: ችግሩ የአንድና ሁለት ፓርቲ ጉዳይ ቢሆን፣ በሃይልና በእሥር ሊቆም ይችላል፤ ይህ ግን ብዙ የማህበረሰብ አካላት ጥያቄና አመጽ እየሆነ ነው::
አሁን በሀገራችን ላይ የሚታየው ግጭት ወደ ብሔር ግጭት የሚያዘነብሉ ምልክቶች የሚታዩበት እየሆነ ነው፡፡ የዚህ ግጭት መነሻን በሚመለከት “የግጭት አፈታትና አያያዝ ጥበብ” የሚለው መጽሐፍ እንዲህ አሥፍሮታል፡-
ብዙ የብሔር ግጭቶች መነሻቸው ወይም ግጭቱ እንዲቀሰቀስ የሚሆነው ሰዎች አንድ አላማ ወይም መሪ የመሆን ፍላጐታቸውን ለማሳካት ወይም የያዙትን የመሪነት ስልጣን የሚቀናቀናቸውን ግለሰብ ይሁን ቡድን ለማስወገድ በሚያደርጉት ጥረት፣ የተወሰኑ ወገኖችን ከጐናቸው እንዲቆሙ ልዩነትን በማራገብ ጥላቻን ይቀሰቅሳሉ፡፡ ለዚህ እውነት ማስረጃ ማቅረብ ቢያስፈልግ፣ በቅርቡ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው የሁለት ጐሳዎች ግጭት ተጠቃሽ ነው፡፡
ከላይ በመጽሐፉ የረጠቀሰውትና ሌሎችም ምክንያቶች ለግጭቱ መንስዔ ቢሆኑም ችግሩን ለማስወገድ እርቅንና ሽምግልናን መጠቀም ትክክለኛና አዋጪ መንገድ ነው፡፡ ግጭቱ የመጨረሻው ጡዘት (Climax) ላይ ሳይደርስ በአጭሩ ካላስቀሩት የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አይደለም፡፡ የብዙ ሰዎች ህይወትና ሀብት ከማጥፋቱም ባሻገር የማታ ማታ ሀገርንም ያፈርሳል፡፡
የሽምግልና ሥርዓት ከጥንት ጀምሮ በቻይና፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በዐረቡ አለማትና በአይሁድ ባህል ውስጥ አገልግሎት ላይ የዋለ ነው፡፡ በኢትዮጵያም በተለያዩ ብሔረሰቦች ዘንድ የተለያየ ስያሜ ተሰጥቶት አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ በጉራጌ ኪቻ፣ በአኙዋክ አኩሃድ፣ በኦሮሞ ገዳ፣ በአፋር ሚዳ፣ ወዘተ እየተባለ ይከወናል፡፡
በዚህ አሠራርም የመንግሥት አካላት ከማህበረሰቡ ተወካዮች ጋር በመሆን ይሠራሉ፡፡
አሁን ባለው ሁኔታም መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ፣ ሕዝቡ በትክክል ከመረጣቸውና ከወከላቸው ሰዎች ጋር በግንባር የሚነጋገሩ ብቃትና ቅንነት ያላቸውን ሰዎች በማዘጋጀት ፊት ለፊት ተወያይቶ፣ ለችግሮች እልባት መስጠት ያለበት አስገዳጅ ጊዜ ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡
ችግሩ በአንድ አካባቢ ጐልቶ፣ ገንፍሎ በሃይል የተገለጠ ቢሆንም ከዚሁ ችግር ጋር የሚመጣጠንና ምናልባትም ከገነፈለ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን የሚችል ሌላም ጥያቄና ቁጣ በሌላ የአገሪቱ ክልሎች መኖሩን እናውቃለን፡፡ በዚያ ላይ መንግሥት ብቸኛ የስልጣን አካል ሆኖ መምራት የተነሳነው የሚመስልበት ሁኔታ ላይ ስለደረሰ፣ ሕዝቡን ከጐኑ ለማሰለፍና ለሀገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የተሻለ መንገድ ለመምረጥ መደራደርና ከመላው ኢትዮጵያውን ጋር መወያየት ግድ ይለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ አንድነት እንዳለ ሆኖ፣ ከተሞችን ለማልማትና ቤተመንግሥቱንም ከታሪክ መዘክርነት ባሻገር ገቢ ማስገኛ ማድረጋቸው የሰለጠነ አካሄድና የሀገር ፍቅር የሚንፀባረቅበት በመሆኑ ሊደነቅ የሚገባው ነው፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን ሁሉ ህልምና ልማት ለማሳለጥ መጀመሪያ የሕዝብን ልብ ማግኘት ግድ ይላል፡፡ በአንድ በኩል የተገነባው፣ በሌላ በኩል የሚፈርስ ከሆነ ነገሩ ታጥቦ ጭቃ ነው፡፡
የገዛ ፓርቲያቸው ሳይቀር ሁለት አፍ በሚናገርበት ሁኔታ ሀገሪቱንና ህዝቧን አንድ አድርጐ በሰላም ማስቀጠል መሞከር የእምቧይ ካብ ከመካብ አይተናነስም፡፡
ስለዚህ አሁን የሚያስፈልገው ዋና ነገር በሰዎች ልብ ላይ መሥራት፣ የሚበሉትን ዳቦ በፍጥነት ማዘጋጀት፣ ከሬሳ መካከል ሳይቀር ሳንቲም የሚለቅሙትን ጨካኝ ባለሥልጣናት ከአደባባይ ማስወገድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልልቅ ተሞክሮ ያላቸውንና ሁሉንም የሚወክሉ ሰዎች በአማካሪነት ሰብስቦ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
በተለይ ሕዝብ ከሚቀበላቸውና ከሚያደምጣቸው አዋቂ ሰዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት መፍጠር ግጭት በተፈጠረ ጊዜ ህዝብን ለማረጋጋት እንኳ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ለዚህ ለዚህ ሰው ያጣን አይመስለኝም፤ ትልልቆችንና የሚበልጡንን ሸሽተን የሚያጨበጭቡልንን ከሰበሰብን የኮሎኔል መንግሥቱ ዕጣ በደጃችን መኖሩን መዘንጋት የለብንም፡፡ ምናልባትም ከኮሎኔል መንግሥቱ ይልቅ የሀገር መፍረስ ጣጣ ፊታችን ተደቅኗልና - ጆሮ ያለው ይስማ!    
    

Read 1972 times