Print this page
Saturday, 02 November 2019 12:32

“የወንዝ መደፍረስ ለእንቁራሪትም አልበጃት!”

Written by  ሰላም ምኞቴ
Rate this item
(0 votes)

   የሀገራችን ህዝቦች ለበርካታ ዘመናት እርስ በርስ በመከባበርና በመቻቻል የኖሩ በመሆናቸው ለዓለም ህዝቦች ተምሳሌት ናቸው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀያቸው ላሉት ዜጎች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች ባህር ማዶ ተሻግረው ኑሮን ለተያያዙትም በአካል ቢለዩም፣ በሀሳብ ግን የምትናፈቅና ለክፉ ቀንም መሸሸጊያ በመሆኗ ጥቂቶች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት ሳይሆን ብዙሃኑ በነጻነት የሚኖሩበት ስርዓት ማረጋገጥ፣ የኢትዮጵያውያን ግዴታም ኃላፊነትም ነው:: በአሁኑ ሰዓት የግለሰቦችና የቡድኖች ጩኸት አገርን እያደነቆረ ነው፤አንዱ ለሌላው ስጋት የሆነ ይመስላል፡፡ ይህ ስጋት ደግሞ በህዝቦች ላይ ጭንቀትን ፈጥሯል፡፡        
ሀገራችን በሰላም እንድትኖርና ዜጎች በዜግነታቸው ኮርተው እንደፈለጉ ወጥተውና ገብተው ስራቸውን እንዲሰሩ፣ ሁሉም ዜጋ ስለ ሰላም በመዘመር፣ ለህልውናዋ በጽናት መቆም ይገባዋል፡፡ የአንዱ ቁስል ነገ ለሌላው ስለሚሆን የተቆርቋሪነት ስሜት መኖር አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በሀገራችን ላይ የተጋረጠውን ችግር መፍታት አይቻልም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ የኖረውን ህዝብ ማቆሚያ ወደ ሌለው ግጭት ለማስገባት የተለያዩ ሙከራዎች፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በግልጽ እየታዩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በህዝቡ ላይ ስጋትና አለመረጋጋትን በመፍጠር፣ አገርን ለቀውስ እየዳረገ ነው፡፡  ሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህንን ጥሬ ሀቅ ደግሞ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ እየዘገቡት ነው፡፡  
ይሁን እንጂ የሀገሪቱ ዕድገት የማይዋጥላቸው የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ሀይሎች፣ የስልጣንና የጥቅም ጥማታቸውን ለማርካት፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ አገራችን ግን ከራሷ ሰላም አልፋ የጎረቤቶቿ ሰላም እንዳይደፈርስ የምትተጋ  እንጂ ብጥብጥና ሁከትን የምትሻ  አይደለችም፡፡ በአንጻሩ ብልጭ ድርግም እያለ የሚነሳው ሁከትና ብጥብጥ፣ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንቅፋት እየጋረጠ ነው፡፡ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ለወጣቱ የስራ ዕድል በመፍጠር በኩል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ፋብሪካዎች መቃጠላቸው የሀገሪቱን በጎ ገጽታ ከማጠልሸት ባሻገር በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ጫና  መገመት አያዳግትም፡፡
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በዚህ ሁሉ ጥፋት የሚጎዱት ኢትዮጵያና ልጆቿ ናቸው:: ኢትዮጵያና ልጆቿ በመጎዳታቸው የሚጠቀም ሌላ ኢትዮጵያዊ ቀርቶ የሌላ ሀገር ዜጋ አይኖርም:: ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆንና ስትበለጽግ ኢትዮጵያና ልጆቿ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ሀገራትም ይጠቀማሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ታዲያ እናት ኢትዮጵያንና ልጆቿን የሚጠቅሙና የሚያሳድጉ ጉዳዮችን ትተን፣ በጥላቻና መገዳደል እኩይ ተግባር የተጠመድነው ለምን ይሆን? የወንዝ መደፍረስ ለእንቁራሪትም አልበጃት!
ለዚህ ብጥብጥ መነሻዎቹ የትምክህት፣ የጠባብነትና የሃይማኖት አክራሪነት ናቸው:: እነዚህን አመለካከቶች ለመግታት መላው የሃገሪቱ ዜጎች ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ እያሰለሰ በሚነሳው ሁከትና ብጥብጥ፣ ዜጎች ተወልደው ባደጉበት አገር፣ ምንም በማያውቁት ነገር፣ በአረመኔያዊ ጭካኔ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ንብረታቸው ወድሟል፤ አካላቸውም ጎድሏል፡፡ እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በአንድ ሀገር  ታሪክ ውስጥ መተኪያ የሌለው ወጣቱ ትውልድ፣ ለጸረ ሰላም ሀይሎች የሁከትና ብጥብጥ ተግባር መጠቀሚያ መሳሪያ መሆኑ ነው፡፡ አገራችን በትውልዶች ቅብብሎሽ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየተከፈለላት ለዚህ ትውልድ የተላለፈች በመሆኗ፣ ያሁኑ ትውልድም ታሪካዊ አደራውን ተረክቦ፣ ግዴታና ሃላፊነቱን  ሊወጣ ይገባል፡፡  
ዛሬ ወጣቱ የሚያስፈልገው ሁከትና ብጥብጥ ሳይሆን ድህነትን ለማጥፋት የሚያስችል ስንቅና ትጥቅ ነው፡፡ እናም ክፉዎች በሚለኩሱት እሳት ውስጥ ዘሎ ከመግባት ይልቅ እሳቱን በማጥፋት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መትጋት  ይጠበቅበታል፡፡ ቸር ቸሩን  ያሰማን፡፡


Read 910 times