Saturday, 02 November 2019 12:19

በአዳማና በሐረር ውይይቶች የአገር ሽማግሌዎች ምን አሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

  - “እርስ በርስ መሰባበሩ የትም አያደርሰንም” - ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
         - “የታገልነው በወጣቶች ላይ ሞት እንዲቆም ነበር፤ አሁንም ትግላችን ይሄው ነው” - የመከላከያ ሚ/ር ለማ መገርሳ
         - “በወንጀሉ የተሳተፉትን ለቅመን ለህግ እናቀርባለን” - የ ኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መ ስተዳድር

           የአክቲቪስትና ኦ ኤም ኤን ዳይሬክተር ጀዋር መሀመድ ‹‹የግል ጠባቂዬ ሊወሰድብኝ ነው›› የሚል የማህበራዊ ድረ ገጽ መልዕክትን ተከትሎ በተፈጠረው ተቃውሞና ግጭት የሞቱ ዜጎች ቁጥር 78 መድረሱን መንግስት  ሕይወት መግለፁ የሚታወቅ ይህን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ውይይት በኦሮሚያ ዞኖችና ወረዳዎች እየተካሄደ ነው፡፡
በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ሽመልሽ አብዲሳ ከአባ ገዳዎች፣ ሃያ ሲንቆዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር በአዳማና በሃረር ውይይት አድርገዋል፡፡
የአዳማውን ውይይት በንግግር ያስጀመሩት ጠ/ሚ፤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ “ያሉንን ልዩነቶችና ጥያቄዎች በመወያየትና በመነጋገር መፍታት እየተቻለ፣ ባልተገባ አካሄድ የሰው ሕይወትን ወደ ሚያጠፋ ክስተት በመገባቱ በእጅጉ አዝናለሁ” ካሉ በኋላ ይህን ችግር ለመሻገር ምን ማድረግ እንዳለብን እንድትመክሩን እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡
የመጀመሪያውን እድል አግኝተው ሀሳባቸውን ያጋሩት የሃገር ሽማግሌ፤ ‹‹አገራችን ተረጋጋች፤ ወደ ሰላም እየተመለስን ነው ባልንበት በዚህ ወቅት በመካከላችን የሌለን ልዩነት ፈጥረው ጉዟችንን ሊያደናቅፉ የፈለጉ አሳፋሪዎች ናቸው ችግር የፈጠሩት እነሱ ናቸው ማፈር የለባቸው›› ብለዋል፡፡
‹‹ሕዝባችን የራሱ ስነ ምግባርና ባህል አለው›› ያሉት የሃገር ሽማግሌው ህዝባችን ከዚህ በኋላ ‹‹ይሄ አይነቱ ግርግር እንዲቆም ይፈልጋል፤ መቆም አለበት›› ብለዋል፡፡
‹‹ብሄር ብሄረሰቦች በሚኖሩባትና በፈጣሪ በተባረከችና በተመረጠች አገር እንዲህ ያለውን ቀውስ ከእንግዲህ ማየት አንፈልግም፤ መንግስት በቀጥታ ሕግ ማስከበር ካለበት እኛም ጎረቤት ለጎረቤት እየተመካከርን፣ አካባቢያችንን በንቃት መጠበቅ አለብን” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል›› - የአገር ሽማግሌው፡፡
አንዲት የውይይቱ ተሳታፊ እናት በበኩላቸው፤‹‹ይሄን ችግር ለማስቆምና ከእንግዲህ እንዳይደገም ለማድረግ እናቶች ትልቅ ሃላፊነት አለብን፤ ልጆቻችን በጊዜ ወደ ቤት መግባታቸውን፣ አዋዋላቸውን… መቆጣጠር አለብን፡፡ ልጆቻችንን እኩያን በገንዘብ እየገዙና እያታለሉ መጠቀሚያ እንዲያደርጓቸው መፍቀድ የለብንም፤ ቤተሰብ ልጆቻችንን በሚገባ መቆጣጠር አለብን፣ ይሄን የማድረግ መብትም አለን” ሲሉ ለወላጆች ምክርና ማሳሰቢያ አስተላልፈዋል፡፡
ሌላው የአገር ሽማግሌ ደግሞ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹በለውጡ አመራር የኦሮሞ ሕዝብ ያገኘው ድል ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ የኦሮሞ ሕዝብ አገር መምራት እንደሚችል ለአለም እያሳየን ባለንበት በዚህን ወቅት ወደ ኋላ ተመልሰን ራሳችንን በራሳችን ለመስበር ስንታገል ምን ይባላል? ይሄ በመሆኑ በእጅጉ አዝናለሁ›› ብለዋል፡፡
በትግል ሂደት ውስጥ ችግሮች እንደሚፈጠሩ፤ ነገር ግን ከችግር መውጫዎችን ሁሌም መተለም እንደሚያስፈልግ በመግለጽም፣ እንደ መንግስት አመራሩ እርስ በእርስ እንዲፈታተሽና እንዲገማገም፣ አባ ገዳዎችና ሕብረተሰቡም ወደ ራሱ በስክነት እንዲመለከት የአገር ሽማግሌው መክረዋል፡፡
‹‹ሁሉም ተነስቶ አክቲቪስት ልሁን እያለ ነው፤ በዚህ እውነቱን ለመናገር እኛም ሕዝባችንም ግራ ተጋብተናል›› ያሉት የአገር ሽማግሌው፤ ‹‹ሁላችንም በተረጋጋ መልኩ ወደ ውስጣችን እንመልከት፤ የአገር ሽማግሌዎችም ሕዝባችንን መምከር አለብን›› ብለዋል፡፡
በየጊዜው አባገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ተሰማኒት ያላቸው አካላት ሕዝቡን በማወያየት መምከር እንዳለባቸው ያሳሰቡት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የአገር ሽማግሌ ናቸው፡፡
ለውጡ በፈተና የተሞላ መሆኑን በመስቀል አደባባይ የሰኔ 16 ቀን 2010 የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከተወረወረውና ለሰዎች ሞት ምክንያት ከሆነው ጥቃት ጀምሮ በለውጡና በለውጥ ሃይሎች ላይ የተቃጡ ያሏቸውን ጥቃቶች የዘረዘሩት ሌላው የሃይማኖት አባት፤ ለእነዚያ ሙከራዎች ተገቢና አስተማሪ የሕግ ቅጣት ባለመፈፀሙ የሕግ የበላይነት ላልቷል፣ ይህም ለቀውስ ፈጣሪዎች እድል ፈጥሯል ብለዋል። አክለውም፤ “እኛ ሽማግሌዎች ተወልደን ባደግንበትና ባረጀንበት አገር ለምን በየጊዜው እንሳቀቃለን?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
‹‹የለውጥ ሃይሉ የኦሮሞ ሕዝብ ገጽታ ነው›› ያሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የሃይማኖት አባት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማትን ባገኙ ባገኘ ማግስት ለምን ይሄ ተፈጠረ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እኛ አሁንም ቢሆን እርስ በእርስ መከባበርና አንድነታችንን ማጠናከር አለብን›› ሲሉም ምክር ለግሰዋል፡፡
በመንግስት ላይ እስከ ዛሬ ሲሞከሩ በነበሩ የጥቃት መልክ ያላቸው ሙከራዎች ላይ ተገቢው እርምጃ ቢወሰድ ኖሮ፣ ይሄ ችግር ባላጋጠመ ነበር ያሉት ሌላው የአገር ሽማግሌ፤ አሁንም መንግስት ከምንጊዜውም በላይ የሕግ የበላይነትን ማስከበር አለበት” ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ም/ርእሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፤ በኦሮሞ ሕዝብ መካከል ልዩነትን ለመፍጠር የሚሰሩትን አንታገስም፤ እያስተካከልን መሄድ አለብን፤ ከእንዲህ አይነቱ ቀውስ እርስ በርስ መጠፋፋት እንጂ ሌላ ትርፍ የሚያገኝ አካል አይኖርም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡  ከዚህም የባሱ ችግሮችን እየተወያየን ፈትተን እዚህ ደርሰን ነበር፡፡ አሁን የተፈጠረው ችግር በእጅጉ አሳፋሪ ነው” ብለዋል - ም/ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡
‹‹በተለይም ሕዝብን በሃይማኖት በመከፋፈል ለማጫረስ የተደረገው ሙከራ ትልቅ ቁስል ጥሎ ያለፈ ድርጊት ነው›› ያሉት አቶ ሽመልስ፤  በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን እያንዳንዳቸውን ለቅመን ለሕግ እናቀርባለን፣ ይሄን እንደምናደርግ ለሕዝባችን ቃል እንገባለን›› ብለዋል፡፡ የሃገር ሽማግሌዎች የሕዝቡን ልብ ወደነበረበት የመመለስና የማረጋጋት ተግባር እንዲያከናውኑም ጠይቀዋል አቶ ሽመልስ፡፡
የአገር ሽማግሌዎች የተፈጠረውን ችግር በማረጋጋት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና በማቅረብ ንግግራቸውን የጀመሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ፤ “ከምሁራኖችና ከሽማግሌዎች ጋር በሕዝባችን ጉዳይ እየተመካከርን እየተረዳዳን ነበር ስንሰራ የቆየነው፣ በዚህ ሂደትም እስካሁን ያገኘናቸው ውጤቶች ብዙ ናቸው፣ ነገር ግን ይሄን በበጎ የማይመለከቱ ለማደናቀፍ የሚሰሩ በርካቶች ናቸው፤ ይህ በሆነበት ተመካክረን መስራት ሲገባን ወደ መጠላለፍ መሄዳችን ተገቢ አይደለም›› ብለዋል፡፡
‹‹የታገልነው በወጣቶች ላይ ሞት እንዲቆም ነበር፤ ከዚህም በኋላ ትግላችን ይሔው ነው›› ያሉት ለማ መገርሳ፤ ‹‹አሁንም ቢሆን በግልጽ በፊት ለፊት መመካከር አለብን›› ብለዋል፡፡ ‹‹በአመራሩ ላይ ችግር ካለም በግልጽ ሊነገረን ይገባል›› የተነገረንንም ለማስተካከል ዝግጁ ነን፤ ነገር ግን በመገዳደል የሚሆን ነገር የለም” ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
‹‹ከምንናገረው በላይ ለዚህች ሃገርና ሕዝቧ እየሰራን ያለነውን ስራ ፈጣሪ ይገልጥላችሁ ከማለት ውጪ ብዙ ማለት አልፈልግም›› በሚል ንግግራቸውን የጀመሩት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው፤ “ከዚህ በፊት የነበሩ አመራሮች በኛ ትግል ብቻ ከስልጣን የወረዱ የሚመስላቸው  የቀድሞ አመራሮች አሉ፤ ይሄ ስህተት ነው፤ የኛ ትግል ብቻ ሳይሆን የፈጣሪ ስራም በውስጡ እንዳለ ማመን አለብን” ብለዋል፡፡
በቅርቡ ‹‹መደመር›› በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ መቃጠሉ መቀደዱ ተገቢ አለመሆኑን የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ ሀሳብ የሌላቸው ሀሳብ ማቃጠል የለባቸውም፤ ሀሳቡን አይተው ካልተስማማቸው ሌላ ሀሳብ ማምጣት ነበረባቸው” ሲሉ ኮንነዋል፡፡
‹‹በየሄድንበት አለም እናንተ ሀሳብ አላችሁ እያለ እያደነቀን ነው፤ እኛ ግን እርስ በእርስ እየተሰባበርን ነው ያለነው›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “በዚህ መንገድ መሄድ ደግሞ የትም አያደርሰንም፤ ሕዝባችን ከዚህ በፊት የከፈለው መስዋዕትነት ይበቃዋል፤ ለምን ሌላ ዋጋ እንዲከፍል እናደርገዋለን” በማለትም ሁሉም ወደ ቀልቡ እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡
‹‹ይሄን መንግስት በሁለት ቀን አመፅ እናፈርሰዋለን የሚሉ ሰዎችን ሰምቻለሁ፤ እጅግ ነው የማዝነው፤ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለ አቅም ካላቸው ባለፉት 27 ዓመታት ሕዝባችን ሲቸገር የት ነበሩ? ለምን ከአገር ጥለው ጠፉ? ወይስ ኦሮሞ ሲያስተዳድር ነው ነገሩ የተገለጠላቸው፤ ይሄ አይጠቅምም፤ እርስ በእርስ መሰባበር የትም አያደርሰንም፤ መናናቁ የትም አያደርሰንም›› ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ።
‹‹ለጀዋር ባለፈው 1 ዓመት ከ6 ወር ጥበቃ የምናደርግለት እኛ ነን፤ ልንገለው ብንፈልግ ለምን እናስጠብቀዋለን? ልናስረው ብንፈልግ ለምን እናስጠብቀዋለን? መንግስት’ኮ ጀዋርን የመጠበቅ ሃላፊነት የለበትም፤ እንዲህ መታሰብ የለበትም” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
በወለጋ ካለው ችግር ጋር በተያያዘም ለበርካታ ጊዜ ሽማግሌ መላኩን ነገር ግን የታጠቀው ቡድን እምቢ በማለቱ ችግሩ በሰላም ሊፈታ አለመቻሉን አያይዘው ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባገዳዎች፣ ከየአካባቢው ከሚገኙ ቄሮዎችና ቃሬዎች ምሁራን ጋር ውይይት በተከታታይ እንደሚደረግም ገልፀዋል፡፡
ጠ/ሚሩና የመከላከያ ሚኒስትሩ ከአዳማው ውይይት ቀጥሎ ያመሩት በቀውሱ ወቅት ከፍተኛ ጉዳትና ሁከት ወደተከሰተበት ሃረርና አካባቢው ነበር፡፡ በሃረር ጨለንቆ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች በተገኙበት በተደረገው ውይይትም በዋናነት ለቀውሱ መነሻ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሃሳቦች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል፡፡
“በተለይ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሊት ለምን የአክቲቪስት ጀዋር መሃመድን ጥበቃዎች ማንሳት ተፈለገ? ጀዋርን ለመግደል ሙከራ ተደርጓል የሚል ወሬ ነው የሰማነው፤ ለምን ይህ ይሆናል? ከወጣቶቻችን ላይ መቼ ነው ሞት የሚያበቃው” የሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎችም በስፋት ቀርበዋል፡፡
አንድ የሃገር ሽማግሌም፤ ‹‹ነፃነት ካገኘን ሰላም ማግኘት አለብን፤ የነጻነት መገለጫው ሰላም ነው፣ ነፃነት አለን የምንለው ሰላም ስናገኝ ነው ስለዚህ ሁላችሁም ሰላም አውርዱ” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የተፈጠረው ግጭትና ልዩነትም በውይይት እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡
ከተወያዮቹ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በቅድሚያ ማብራሪያ የሰጡት የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ፤ ከአክስቲቪስት ጀዋር መሀመድ ጋር በውይይት በመተራረምና በምክክር ሲሰራ መቆየቱንና ለወደፊትም ይሄኛው የመመካከርና የመተራረም መንገድ የሚቀጥል መሆኑን በመጠቆም፤ ለተፈጠረው ችግር የመጀመሪያ መነሻ በሆኑ አካላት ላይ ተጣርቶ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል፡።
‹‹ሰዎች ሊያውቁት የሚገባው ይሄን ወንድማችንን ልናጠፋው ብንፈልግ፣ ወደዚህ አገር እንዲገባ ባልጋበዝነው ነበር፣ እንዲጠፋ ብንፈልግ ኖሮ እኛ ራሳችን ጥበቃ መድበንለት አናስጠብቀውም ነበር›› ያሉት ለማ መገርሳ፤ “መንግስት ጀዋርን ሊያጠፋው ይፈልጋል የሚባለው ፈጽሞ የማይሆን ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም “ብንሳሳትም መተራረምና መመካከር ይገባናል እንጂ መጠፋፋት የሕዝባችንን ትግል ያዳክመዋል እንጂ አያጠናክረውም፡፡ ለዚህም የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን በጋራ የምንመካከርበት መድረክ ፈጥረን አብረን እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ውስጥ የሚነሱ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ያመላከቱት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ ‹‹ዐቢይ የኦሮሞን ትግል ረስቷል፣ የኦሮሞን ጉዳይ ረስቷል፣ የሚል ወሬ ይነዛል፤ ነገር ግን ይሄን ለወደፊት ፈጣሪ ይፈርደዋል፤ በሌላ ወገንም ዐቢይ የኦሮሞ የበላይነት ሊያመጣ ነው የሚል ቅሬታ ይቀርባል” ብለዋል፡።
አላማቸው ለሁሉም የምትሆን፤ ሁሉንም በእኩል የምታስተናግድ አገርን መገንባት መሆኑንም ጠ/ሚኒስትሩ በዚሁ መድረክ ላይ በአፅንኦት አስገንዝበዋል። ለዚህም የ‹‹መደመር›› ሀሳብን በመጽሐፍ አትመው ለሕዝብ ትችት ማቅረባቸውንና ይሄን መጽሐፍ አንብቦ ሃሣብ ማዋጣት፣ ወይም አይሆንም የሚል የሃሳብ ሙግትን በማምጣት ሀገር መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ሌላው ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው ያነሱት፣ የኢህአዴግ ፈርሶ አዲስ ውህድ ፓርቲ የመመስረት ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ሰዎች ለምን ኦዲፒን ለማፍረስ ፈለጋችሁ እያሉን ነው፤ እነዚህ ሰዎች መገንዘብ ያለባቸው ይሄን ህዝብ ሲጨቁንና ሲገርፍ የኖረን ድርጅት፣ ያ ድርጅት የሚመራበት ሃሳብ፣ አደረጃጀቱን ማፍረስ ትግላችንን ወደፊት የማሻገር ውጤት ነው ያለው›› ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
‹‹ደርግ ፈርሶ ነው ሌላው የራሱን የገነባው፤ እኛም ለኛ የሚሆነውን ሃሳብና አደረጃጀት የነበረውን አፍርሰን ነው የምንገነባው፣ ድርጅቱንና ሃሳቡን የምናፈርሰውም ለዚሁ ነው›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “የነበረውን ድርጅት እናፈርሳለን፣ የራሳችን እንገነባለን፤ የህዝባችንን ጥያቄም እንመልሳለን” ብለዋል፡፡
የአፋን ኦሮሞ የፌደራል የስራ ቋንቋ የመሆን ጉዳይም እየተሰራበት መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
የጃዋር ጉዳይም በተመለከተ “እኛ እንኳን ጃዋርን እኛን ለመግደል ሲሞክሩ የነበሩትንም ለመግደል አልሞከርንም፤ አልፈለግንም” በማለት ጃዋርን ለማጥፋት የተባለው ሃሰተኛ ወሬ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ሰዎች ሲያጠፉም ህግ አለ፤ በህግ ነው የሚጠየቁት እንጂ ሌላ የተንኮል እርምጃ አይወሰድባቸውም ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
ከሀረር በተጨማሪም ጠ/ሚኒስትሩና የመከላከያ ሚኒስትሩ በአምቦ ከተማ ተመሳሳይ ውይይት ከሀገር ሽማግሌዎቻችና የህብረተሰቡ ተወካዮች ጋር ማድረጋቸውም ታውቋል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ መሳተፍ አለብን ያሉ ወጣቶችም በአደባባይ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 12270 times