Print this page
Saturday, 02 November 2019 12:13

ከአስከፊ ግጭትና የዜጐች ሞት ማግስት የተሰጠው ማሳሰቢያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

       ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በሚያጋጩ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰቡ

                  ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ተከስቶ በነበረው ግርግርና ግጭት የሞቱት ቁጥር 78 መድረሱን የገለፀው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፤ እስከ ትላንት በስቲያ ሀሙስ ድረስ 409 ተጠርጣሪዎችን  ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡
የብሔርና የሃይማኖት መልክ ነበረው ለተባለው ግጭትና ሁከት ተጠያቂውን ለይቶ ለሕግ ለማቅረብ ፖሊስ የምርመራ ተግባር እያከናወነ መሆኑን የጠቆሙት የጠ/ሚር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ የመንግስት ባለስልጣንም ሆነ ግለሰብ በሕግ እንደሚጠየቅ አስገንዝበዋል:: ክስተቱ መንግስት በሙሉ ሀይሉ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ወደማረጋገጡ እንዲያተኩር የሚያደርገው መሆኑን የገለፁት ሃላፊው፤ ግጭቱ ተመልሶ እንዳይመጣ መንግስት ይሰራል ብለዋል፡፡
ለዚህም በቅድሚያ ጉዳቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች ውይይት እየተደረገ መሆኑንና በቀጣይም የችግሩን መነሻ፣ መድረሻና መፍትሄ በመገምገም ለሕግ መቅረብ ያለባቸው ለሕግ እየቀረቡ፣ የአገሪቱን ሰላም የማረጋገጥ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
“የቂም በቀልና የጥላቻ ቁርሾን አለማቆም፣ ለሕግ አልገዛም የሚሉና በጫካ ሆኖ የመተዳደር ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች መስተዋል፤ መንግስትን በለውጡ ሂደት ትዕግስቱን እየተፈታተኑ ያሉ ናቸው ብለዋል - አቶ ንጉሱ፡፡
በአሁኑ ወቅት በጠ/ሚኒስትሩ የቀረበው የመደመር እሳቤ ወደ ሕብረተሰቡ እንዳይደርስ የማኮላሸት ድርጊቶች፣ የገዥው ፓርቲ ውህድነትን ባልተገባ መልኩ በመተርጎም የማደነቃቀፍ እንቅስቃሴ እየተስተዋለ መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ ንጉሱ፤ የፌደራል ስርአቱ በአሃዳዊነት ሊተካ ነው፣ የአንድ ወገን የበላይነት መልሶ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው የሚሉ ውዥንብሮች መነዛት ለግጭቱ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ድርጊት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ በየትኛውም ደረጃና ኃላፊነት ላይ ያሉ ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ፤ ነገር ግን ማን ተጠያቂ ነው ማን? አይደለም የሚለውን ሃላፊነት የተሰጠው መንግስታዊ የፍትህ ተቋም ብቻ ለይቶ እርምጃ እንደሚወስድ ኃላፊው አስገንዝበዋል::
ከዚህ ቀደም በሶማሌ ክልል የተፈጠረውን ግጭትና ጥቃት ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተፈፀመው ጥቃትና ግጭት የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት 3221 ያህል ተጠርጣሪዎች መካከል ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑትን መክሰስ  መቻሉንም አቶ ንጉሱ ጠቁመው፤ መንግስት የሕግ ማስከበር ተግባሩን በተገቢው ሁኔታ እየተወጣ መሆኑን ሞግተዋል::
‹‹ይሄን አገር ለማሸጋገር ያለው አንድ መንግስት ነው፤ ደባል መንግስት የለም›› ያሉት አቶ ንጉሱ፤ “መንግስት ከእንግዲህ አጉራ ዘለልነትንና የደባልነት አመለካከትን አይታገስም” ይሄ ወደ ትክክለኛ መስመር እንዲገባ ይሰራል›› ብለዋል፡፡
በመገናኛ ብዙሃንም ብሄርን ከብሄር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የማጋጨት ምልክቶች እየታዩ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ የብሮድካስት ባለሥልጣን ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
‹‹የመንግስት አመራር የተከፋፈለ ለማስመሰል የሚደረጉ ሙከራዎች አሉ›› ያሉት ሃላፊው አመራሩ አልተከፋፈለም ሕብረተሰቡ በዚህ መደናገር የለበትም ብለዋል:: የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ያለመግባባት ጉዳይን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ንጉሱ ኢሕአዴግ ከእንግዲህ ሊግባባ የሚችለው ሲዋሃድ ብቻ ነው›› ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግስት ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ዜጎች ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን እርዳታ እያቀረበ መሆኑን ያስረዱት ሃላፊው የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሕበረተሰቡን በማረጋጋት ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡  

Read 8858 times