Print this page
Saturday, 02 November 2019 12:12

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የሕግ የበላይነት እንዲከበር ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   - አጥፊዎች በአፋጣኝ ለሕግ እንዲቀርቡ ተቋማቱ አሳስበዋል
           - የክልል መንግስታት የአናሳዎች መብት ጥበቃ እንዲያደርጉ ተጠይቋል

              የሰብዓዊ መብት ተቋማት በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲከበር የጠየቁ ሲሆን የክልል መንግሥታት የአናሣዎችን መብት ከሌላው እኩል እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ አሳስበዋል::  
ከሰሞኑ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ዙሪያ በተከሰቱ ቀውስና ግጭቶች ዙሪያ መግለጫ ያወጣው የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ በክስተቱ በዜጎች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት መፈጠሩንና በፀጥታ ሃይሎችና በዜጎች መካከልም ደም አፈሳሽ ግጭት መከሰቱን ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
የግጭቱ  ባህሪም በብሔርና ሃይማኖትን ለይቶ የተፈፀመ ጥቃትን የሚያካትት፣ ለአገሪቱ ሕልውና አደገኛ አዝማሚያ የነበረው እንደሆነም ጠቁሟል - መግለጫው፡፡
በዚህ ግጭት በዋናነት በክልሉ የሚገኙ አናሳ ብሔሮችና አብያተ ክርስቲያናት መጠቃታቸውን፣ በዚህም 67 ያህል ዜጎች ሞተው 200 ያህል መቁሰላቸውን፣ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን፣ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ቤተክርስቲያናት፣ የንግድ ተቋማትና የሕዝብ መሰረተ ልማቶች የጥቃት ኢላማ ተደርገው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው መግለጫው ያትታል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሰማጉ) በበኩሉ፤ ከጥቅምት 11 ቀን 2012 ሌሊት ጀምሮ አክስቲቪስት ጀዋር መሀመድ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ፤ ‹‹ጥበቃ እንዲያደርጉልኝ የተመደቡልኝ የፀጥታ ሀይሎች ሊነሰቡኝ ነው፡፡ ቤቴም በፀጥታ ሀይሎች ተከቧል›› የሚል መልዕክት ማስተላለፉን ተከትሎ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ወደ ግጭት አምርቶ፣ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ በብዙዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ በግጭቱ ግምቱ ያልታወቀ ንብረት ወድሟል፣ የዜጎች ያለ ሥጋት የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቧል፣ መንግስታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ የንግድ ድርጅቶችና ት/ቤቶች ተዘግተዋል ብሏል፡፡
በተነሳው ተቃውሞና በተፈፀመው የብሔር ተኮር ጥቃትም በምስራቅ ሀረርጌ ዞን፣ በሃረር ከተማ፣ በአወዳይ፣ ድሬዳዋ፣ በአዳማ፣ በባሌ ዞን ዶዶላ፣ በአምቦ፣ በአርሲ ዞን ኮፈሌ ሮቤ ከ67 በላይ ሰዎች ስለመገደላቸው መረጃ ማሰባሰቡን ጠቁሞ፤ ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ በድንጋይና በዱላ ተወግረው በዘግናኝ ሁኔታ መገደላቸውን አስታውቋል፡፡
ከዚህም ሌላ ብሔርና ሃይማኖት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶችን የሚያባብሱ መልዕክቶች ሲተላለፉ መሰንበታቸውንም ተቋሙ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በባሌ ዶዶላ ከፋ ከ400 በላይ የሚሆኑ ዜጎች በአብያተ ክርስቲያናት በስጋት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ በሶስት ቀናት ውስጥ በታየው ግጭትና ጥቃት ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች ስለ መገደላቸው አስታውቆ፣ አጣሪ ቡድን ወደ አካባቢው መላኩን ገልጿል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተቋማቱ መንግሥት የማስተካከያ እርምጃ ይውሰድባቸው ያሏቸውን ጉዳዮችም አስቀምጠዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ የክልል መንግስታት የአናሳዎች መብት ጥበቃ እንዲያደርጉ ያሳሰበ ሲሆን የተፈጠረው ችግርም በገለልተኛ አካል እንዲጣራ መንግስት በአለማቀፍ ተቋማት ጥሪ እንዲያቀርብ ጠይቋል::
መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት እንዲያከብርና እንዲያስከብር የጠየው ኢሰመጉ የሚተላለፉ በበኩሉ፤ በአጥፊዎች ላይ የማያወላውል ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ፣ ሕግ የበላይነት ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጥ አሳስቧል፡፡ በተጨማሪም መንግስት በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን እንዲቆጣጠር፣ ኢ-መደበኛ አደረጃጀትን ወደ ሕግ ማዕቀፍ የማስገባት እርምጃ እንዲወስድ፣ ጉዳቱ ተጣርቶም ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፍልም ጠይቋል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንም መንግስት የሕግ የበላይነትን እንዲያስጠብቅና አጥፊዎችን በአፋጣኝ ለሕግ እንዲያቀርብ አሳስቧል፡፡
በአርቲስት ታማኝ በየነ የሚመራው ግሎባል አሊያንስ የተሰኘው ተቋም በበኩሉ፣ ለዚህ ድርጊት መንስኤ ነው ያለውን ቅስቀሳ አድርገዋል ያላቸውን ወገኖች በአለማቀፍ ፍርድ ቤት ለማቆም እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
መደበኛ መገናኛ ብዙኃንና የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም ቅስቀሳ የሚያደርጉ ግለሰቦችን ለአለም አቀፍ ፍርድ እንደሚያቀርብ የገለፀው ድርጅቱ፤ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት ዘመዳዊና ፖለቲካዊ አድልዎ በአስቸኳይ እንዲቆምና የሁሉም ዜጎች መብት በእኩል እንዲጠበቅ ጠይቋል፡፡  

Read 8578 times