Print this page
Saturday, 02 November 2019 12:09

የ‹‹ግዮን›› መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ይግባኝ ሊጠይቅ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ከሰኔ 15ቱ የባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ ከተጠረጠሩት 22ቱ በዋስ ተፈተዋል

               የ‹‹ግዮን›› መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ ከ6 አመት በፊት በ‹‹ዕንቁ›› መጽሔት ምክንያት በቀረበበት ክስ የሰባት አመት ጽኑ እስራት ውሳኔ የተላለፈበት ሲሆን ጋዜጠኛው በጉዳዩ ላይ ይግባኝ ሊጠይቅ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል፤ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም መንግስት ባለሥልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖች ላይ ከተፈፀመው ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ታስረው ከነበሩት መካከል ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩን ጨምሮ የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት አባላትና ፖለቲከኞች ከ4 ወራት እስር በኋላ በዋስ ተለቀዋል፡፡
ከግብር ጋር በተያያዘ ከ6 አመት በፊት በተመሰረተበት ክስ የ7 አመት እስራትና የ7 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ማክሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም የተላለፈበት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ፤ በ15 ቀን ውስጥ ይግባኝ ለመጠየቅ ማቀዱን ቤተሰቦቹ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ጋዜጠኛው ክሱ ተገቢነት እንደሌለውና የፕሬሱን ሕልውና የሚፈታተን እንዲሁም በቀድሞ መንግስት በጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን በመጥቀስ፤ በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርብም ምላሽ አለማግኘቱን ለእስር ከመዳረጉ በፊት ለአዲስ አድማስ ገልጾ ነበር፡፡
ጋዜጠኛው በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል:: የጋዜጠኛውን መታሰር ተከትሎም ለውጡን ተከትሎ በጋዜጠኛው የተመሰረተው ሳምንታዊ የጊዮን መጽሔት ሕትመት መቋረጡንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል ባለፉት 4 ወራት ምንም ክስ ሳይመሰረትባቸው ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር በተያያዘ በ3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የነበሩ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩን ጨምሮ 22 እስረኞች በመታወቂያ ዋስ ብቻ የተፈቱ ሲሆን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ ሌሎች ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡  

Read 994 times