Saturday, 02 November 2019 12:10

ፓርቲዎችና የሃይማኖት ተቋማት በግጭት ቀስቃሾች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ዙሪያ አካባቢ የተፈጠሩ ግጭቶችን ባስነሱና ሕዝቡን ለግጭትና ሁከት በቀሰቀሱ ግለሰቦችና አካላት ላይ መንግስት ጠንካራ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት አሳሰቡ፡፡
በተለይ ጥቅምት 13 እና 14 ለደረሰው ጥፋት መነሻ ከሆነው ‹‹ተከብቤያለሁ›› በሚል ለመንግስት አካል ማሳወቅ ሲገባው ወደ ሕዝቡ ከረጨው ግለሰብ ጀምሮ በየደረጃው በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ ያደረሱ ወገኖች በሙሉ በአፋጣኝ ለፍርድ እንዲቀርቡ የጠየቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በግጭት የሚነግዱ የማህበራዊ ድረ ገፅና የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሕዝብን ለተከታታይ ግጭቶች ከመዳረጋቸው በፊት ስልጣን የተሰጠው አካል የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አስታውቋል፡፡
በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃም ከፖለቲካና ከዘውግ ወገንተኝነት ፈጽሞ የፀዳ እንዲሆንም ኢዜማ ጠይቋል፡፡  የመንግስት ሃላፊነቱን በአግባቡ አለመወጣት ሕዝብን ተደራጅቶ ራስን ወደ መከላከል ደመነፍሳዊ ሁኔታ እየገፋው ይገኛል ያለው ፓርቲው፤ ‹‹ይህም ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት የእርስ በርስ የእልቂት ድግስ ይከተናል›› ሲል አስጠንቅቋል፡፡
መንግስት በአጥፊዎች ላይ ሊወስድ ከሚገባው ሕጋዊ እርምጃ ጎን ለጎን፣ የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስን የመሳሰሉ ሕጋዊ አደረጃጀቶችን እንዲያጠናክር ጠይቋል፡፡
ለአጠቃላይ ለአገር መረጋጋትና ሰላም ሲባል ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት በፍጥነት መጀመር እንዳለበት ያስገነዘበው ኢዜማ፤ በቀጣይም በራሱ አነሳሽነት የተለያዩ የውይይት መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ ገልጿል፡፡
የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ መግለጫ ወቅት፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በግጭትና ግርግር እንደማይመጣ አስገንዝበው፤ ከአሁን በኋላ በሃይል የሚመጣን ፖለቲካ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቀበልም ብለዋል፡፡
በአደባባይ በአገሪቱ ቀውስ እንዲፈጠርና ሕዝብ ወደ ግጭት እንዲገባ የሚቀሰቅሱ ግለሰቦችና አካላት ላይ በቀጥታ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ያሳሰበው መኢአድ በበኩሉ፤ ከዚህ በፊት ለተሰሩ ጥፋቶች በመንግስት አጥፊዎችን ለይቶ ለሕግ በማቅረብና ቅጣቱን በማሳወቅ በኩል ባለመገፋቱ አዳዲስ አጥፊዎችና በማናለብኝነት የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል ብሏል - መኢአድ::
ለዚህም የመንግስት ዳተኝነትን ለሕግ የበላይነት ቁርጠኛ አለመሆንን ኮንኗል - ፓርቲው፡፡ በሰሞኑ ግጭት የተሳተፉ አካላትንም መንግስት በአስቸኳይ ለሕግ እንዲያቀርብ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሕብረተሰቡን በማቀራረብ ሰላም የማስፈን ሥራ እንዲሰሩ ጠይቋል፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶቹ መንግስት የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን፣ በሰሞኑ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ተገቢውን ካሳ እንዲከፍልም ጠይቀዋል፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና ሌሎች ቤተ እምነቶች ባወጧቸው መግለጫዎች፤ ከሰሞኑ የተፈጠረውን ግጭትና አስከፊ የሕይወት ጥፋት በጽኑ አውግዘው፤ መንግስት አጥፊዎችን ለሕግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡     


Read 8657 times