Saturday, 16 June 2012 12:54

የአፍሪካ ሕፃናት ቀን ይከበራል

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ መብት የጠየቁ ሕፃናት በግፍ የተጨፈጨፉበትን ሰኔ 9 ምክንያት (መነሻ) በማድረግ በየዓመቱ የሚከበረው የአፍሪካ ሕፃናት ቀን ትናንት ከጧቱ 2 ሰዓት እስከ ቀኑ 9 ሰዓት በአዲሱ የአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ተከበረ፡፡ አርቲስት ቻቺ ታደሰ በሥራ አስኪያጅነት የምትመራው “ዊንግስ ኢጁኬሽን እና ሚዲያ” እንዳስታወቀው፤ ለሦስት ቀን በሚቆየው ክብረ በዓል ላይ ከጋምቢያ እና ከኬንያ የመጡ ሕፃናት እንዲሁም አንጋፋ እና ወጣት አርቲስቶች የመዝናኛ ዝግጅቶች ያቀርባሉ፡፡ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ሕፃናት የሚገኙበት ክብረ በዓል ጭብጥ የአካል ጉዳተኛ ሕፃናትን መብት እንጠብቅ፣ እንንከባከብ፣ ቃላችንን እናክብር የሚል ነው፡፡

በዚሁ ሂደት ስለ አካል ጉዳተኛ ሕፃናትና መብቶቻቸው ለሕዝቡ ለማስረዳት ጥረት ይደረጋል፡፡በትናንቱ የመክፈቻ ዝግጅት ላይ አርቲስት ቻቺ፣ ከሰበታ መርሃ እውራን ትምህርት ቤት የተወከለ አንድ አካል ጉዳተኛ ሕፃን፤ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ክብርት ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ እና ሌሎች የክብር እንግዶች ንግግር አድርገዋል፡፡ የሲድሃርታ የሕፃናት ሙዚቃ ቡድን ጣእመ ዜማዎችን አስደምጧል፡፡ በሌላም በኩል የአፍሪካ ሕፃናት ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀ የኪነጥበብ ዝግጅት ዛሬ እንደሚያቀርብ ዛጐል ቤተመፃህፍት ከአጋሩ ECYDO ጋር በመሆን አስታወቀ፡፡ አምስተኛው ዝግጅት ዛሬ ከጧቱ 3፡30 በሀገር ፍቅር አዳራሽ የሚቀርብ ሲሆን፤ ግጥሞች፣ ትረካዎች፣ የልጆች መዝሙሮችና ሌሎች ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል፡፡

 

 

 

Read 1817 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 12:59