Saturday, 26 October 2019 12:41

በዓለም ዙሪያ የተቀጣጠለው ተቃውሞ ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(2 votes)


               ሰበብ ምክንያቱም ሆነ አላማና ግቡ ይለያይ እንጂ ከአፍሪካ እስከ እስያ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅ አለማችን በያቅጣጫው በተቃውሞ ስትናጥ መሰንበቷን ነው አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን የዘገቡት፡፡
ቦሊቪያውያን ከሰሞኑ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ የህዝብን ድምጽ አጭበርብረው አሸናፊነታቸውን አውጀዋል ያሏቸውን ፕሬዚደንት ኢቮ ሞራሌስ ለመቃወም ባለፈው ሰኞ ማለዳ ነበር፣ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው፣ አደባባይ በመውጣት ከፖሊስ ጋር የተናነቁት፡፡
ባለፈው ሳምንት በቺሊ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ፣ ጉዳዩ ያስቆጣቸው የአገሪቱ ዜጎች፣ የመዲናዋን ሳንቲያጎ ጎዳናዎች አጥለቀለቋቸው፡፡ በንዴት የጦፉ ቺሊያውያን ተቃውሞ ከማሰማት አልፈው መደብሮችን መዝረፍና አውቶብሶችን ማቃጠላቸውን ተያያዙት፡፡ የህዝቡ ቁጣ ያሳሰበው የአገሪቱ መንግስትም ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማጽደቅ ሁኔታዎችን ለማረጋጋት ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዘው፡፡
ከሳምንታት በፊትም የኢኳዶር መንግስት ለአስርት አመታት ያህል በነዳጅ ዋጋ ላይ ሲያደርግ የዘለቀውን ድጎማ ማንሳቱን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ዜጎች በተቃውሞ ጎዳናዎችን አጥለቅልቀው ነበር፡፡ በሆንግ ኮንግ ለወራት የዘለቀው ተቃውሞ፤ አሁንም መላ ሳይገኝለት ቀጥሏል፡፡ ከሊባኖስ እስከ ባርሴሎና፣ ከእንግሊዝ እስከ ጣሊያን አለማችን ዙሪያ ገባውን በተቃውሞ እየታመሰች ቀጥላለች፡፡
የአለማችን አገራት በተቃውሞ የሚታመሱበት ሰበብ እየቅል ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ ለተቃውሞ ምክንያት ሆነዋል ብሎ ሮይተርስ ከጠቀሳቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው - ኢኮኖሚ፡፡
ኢኳዶር፣ ቤሩት፣ ሃይቲና ኢራቅን ጨምሮ በበርካታ አገራት የተቀሰቀሱት ተቃውሞዎች ዜጎችን ባስቆጡ የመንግስታት ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች ሳቢያ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በአወዛጋቢ የስራ ፈቃድ አዋጅ ተጀምሮ ሌሎች ጥያቄዎችን እያግተለተለ ላለፉት አምስት ወራት የዘለቀውን የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ ጨምሮ በተለያዩ አገራት ዜጎችን ለተቃውሞ ያስወጣ ሌላኛው ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው ደግሞ የፖለቲካዊ ነጻነት ወይም የሉአላዊነት ጥያቄ ነው፡፡
የስፔን መዲና ባርሴሎናን ጎዳናዎች በመቶ ሺዎች በሚጠጉ ካታሎናውያን ያጥለቀለቀው የጋለ የተቃውሞ ሰልፍም ለአመታት ከዘለቀ የመገንጠልና ራሱን የቻለ ሉአላዊ አገር የመፍጠር ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው ሮይተርስ ያስነበበው፡፡
መንግስት በሙስና ተጨማልቋል፤ ሹመት በዝምድናና በውግንና ሁኗል፤ ባለስልጣናት ከዜጎች በሚዘርፉት ሃብት የግል ካዝናዎቻቸውን እየሞሉ ነው የሚሉና መሰል የሙስና ምሬት የወለዷቸው ተቃውሞዎች ከተቀሰቀሱባቸው አገራት መካከልም ሊባኖስ፣ ኢራቅና ግብጽ እንደሚገኙበት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በተለያዩ የአለማችን አገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን አደባባይ ያስወጣው ሌላኛው የሰሞኑ የተቃውሞ ሰበብ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ መንግስታት ለአየር ንብረት ለውጥ በቂ ትኩረት እንዲሰጡ የሚጠይቁ በርካታ ተቃዋሚዎች፤ከአሜሪካ እስከ እንግሊዝ፣ ከጀርመን እስከ ስፔን፣ ከኦስትሪያ እስከ ፈረንሳይና ኒውዚላንድ ጎዳናዎችን አጥለቅልቀው መሰንበታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Read 2906 times