Saturday, 26 October 2019 12:37

ዝክረ- አርቲስት አብርሃም አስመላሽ

Written by  በሥንታየሁ ዓለማየሁ
Rate this item
(0 votes)

መወለድና መሞት በሕይወታችን ውስጥ አይቀሬ እውነታ ቢሆንም ቅሉ፣ አንዳንዱ ጠቢብ የሞተበትን ቀን ከማሰብ ይልቅ የተወለደበትን ዕለት መዘከር ፋይዳ ያለው ይመስለኛል። ምክንያቱም አንድም በሕይወቱ ትልቅ ስራ ሰርቶ የሄደ ሰው፣ በአካለ ስጋ ገለል አለ እንጂ ሞቷል ለማለት ስለማያስደፍር፣ ሁለትም፤ ሰርቶ ያለፈን ሰው ሰርክ የሞተበትን ዕለት ከማውሳት ይልቅ የውልደቱን ቀን ማስታወስ፣ ከስራው እኩል ዳግም በልቦናችን ውስጥ እንዲዘከርና እንዲወለድ ያግዛልና ነው።
እንደውም ለስም አጠራሩ ይመቸን ዘንድ ነው እኮ የሰውን ልጅ ነፍስና ስጋው ሲለያዩ ሞተ የምንለው። እንጂማ አረፈ፣ ከዚህ የግርግር፣ የጥድፊያ፣ የልፋት ዓለም ተገላገለ ነው መባል የነበረበት፡፡
ዛሬ የምናስታውሰው ታላቅ ሰው፤ በዚህ በያዝነው ጥቅምት ወር ያረፈ ድንቅ ከያኒ ነው። ሕይወቱን በሙሉ በፍቅሯ ተጠፍንጎ፣ ጥበብን መስሏት ሳይሆን ኖሯት ያለፈ ድንቅ ጥበበኛ  ነበር - አርቲስት አብርሃም አስመላሽ። በወርሃ ጥቅምት ልክ በዛሬው ቀን፣ ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር ያረፈው።
አብርሃም፤ በአዲስ አበባ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ተወልዶ ቢያድግም፣ ጎጃሜም፣ ወሎዬም፣ ጎንደሬም ሆኖ የኖረ ‹‹ባላገር›› ነው። ገና ከለጋ እድሜው ጀምሮ ከመንዝና ከሰሜን ሸዋ ክፍለ ሃገር በሚመጡ የበግ ነጋዴዎች አንደበት የተማረከው አብርሃም፤ እነሱን እየተከተለ እኩዮቹ ገንዘባቸውን ለመመንተፍ ሲራወጡ፣ እሱ ግን በአማርኛቸው በእጅጉ ስለተደመመ፣ ቋንቋቸውን ሲኮርጅ ነው ያደገው። ይህንንም በተለያዩ ቃለ ምልልሶች ላይ በአንደበቱ ተናግሮታል፡፡
ዛሬ ሁሉም ባይባልም አብዛኛው ከተሜ ቀመስ ማህበረሰባችን፣ የራሱን ባህልና ወግ እያጣጣለ፣ የፈረንጅን ባህል እንደ መልካም ቡራኬ የሚቆጥር በሆነበት ወቅት እንደ አብርሀም አስመላሽ ከተማ ተወልዶ አድጎ፣ ነገር ግን ቱባውን ወግና ለዛ ጠብቆ፣ ለትውልድ ያሸጋገረ ሲገኝ አለማመስገንና አለመዘከር  አይቻልም። እንዲህ ያለውን ሰብዕና መዘንጋትም ይቅርታ የማያሰጥ ትልቅ ወንጀል  ነው፡፡  
አብርሃም ከ20 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ቅዳሜ መዝናኛ ላይ ሰርቷል (ኢቲቪ ግን በወቅቱ ከሚቆርጥለት ሃያ ብር ውጭ ምንም እንዳላደረገለት እራሱ በአንደበቱ ተናግሯል)። የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከሚሸከሙት ዋነኛ ሃላፊነቶች መካከል፣ የሀገርን ወግና ባህል እንዲሁም ቋንቋ መጠበቅና ለትወልድ ማስተላለፍ ተጠቃሽ  ሲሆን አብርሃም ይህንን ሃላፊነት በቅጡ ተወጥቷል፡፡  
‹‹እነ ጋሽ ታከለና እረኛው›› የተሰኙት የኮሜዲ ስራዎቹ ከፍተኛ ተወዳጅነትን እንዳተረፉለት  ይታወቃል።  በተጨማሪም፣ ለቁጥር የሚያታክቱ ልዩ ልዩ ማህበረሰባዊ እሴት ያላቸው መነባንቦችን በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ሲያቀርብ ኖሯል። “የመንግስትንም ሆነ የማህበረሰቡን ህፀፅ በቀልድ እያዋዛህ ነው መንገር” የሚለው አርቲስቱ፤ አብዛኛው ስራዎቹ ኮሜዲ ቢሆኑም፣ እያሳሳቁና እያዝናኑ ማህበረሰባዊ ትችቶችን በመሰንዘርም ይታወቅ ነበር፡፡ እስቲ አንድ መነባነቡን ቀንጭበን እንይለት፡-

 “መፍጃ ፍቃድ
........
እኒህ በጋ ሰማይ መስለው እሚዘወሩ
ሳንቲም ተከፍሏቸው ሰው እሚያሳፍሩ
በተለይ ሚኒባስ ተብለው በስም የሚጠሩ
ምነው ሃይ ባይ የለም
በወግ እንዲበጁ በቅጥ እንዲሰሩ
እንዳይነታቸው እንደብዛታቸው እንዳገልግሎቱ
ለት ተለት ያክላል ያደረሱትም በደል ያመጡት ጉዳቱ
ቀድሞውኑ ሰው መጫን ይችሉ አይችሉ
እንደው ታይተው ሲሰረጁ
ወላልቀው ተጣመው እንኳን ለመመቸት ሆነውስ ሲበጁ
ለጉዳት ለጥፋት ይመስላል አንዳንዶቹ ተምሃል ደርሰው የተዘጋጁ--”
ተመልከቱ! እንግዲህ የታክሲዎችንም ጥራት፥ የዘዋሪውንም ብቃት፥ አነዳዱን፥ አሰራሩንና ሁሉንተናዊ የትራንስፖርት አቀራረቡንና አገልግሎት አሰጣጡን ቀልድ ቀብቶ አቅርቦልናል…ይህን የመሰለ ነው የአብርሃም አስመላሽ ስራ። በንግግር ዘዬአቸው ከመሳቅ ወይም ከመገረም ያለፈ ነገር ለሌለን አብዛኞቻችን ከተሜዎች፤ አብርሃም  ስለ አማርኛቸው ጥልቀትና ገላጭነት እንዲህ ሲል በምሳሌ ያስረዳናል፦ ለምሳሌ ከሀገር ቤት ሃኪም ቤት ይመጡና አለ፦
ምንህን ነው የሚያምህ?
የሰራ ጅስሜን
እንዴት?
እንደ አይነ-ጥላ
እንደ አይነ-ጥላ ስትል እንዴት ነው?
እንግዲህ ኸደ ስለው ይመጣል....መጣ ስለው ደግሞ ይኸዳል....እግሬን ስል ወደ ሆዴ፣ ሆዴን ስል ወደ አናቴ፤ እንደው ሃኪምዋ ምን አታከተዎ ተግር ጥፍሬ እስከራስ ጠጉሬ ይመዘኛል......
እንዴት?
እንዲህ አደል.....ቲያሻውም እንደ ጠፍር እየዘረጋ እያጠፈ፣ እንዴ ማጭድ እየቀነፈ፣ እንዲሁ ሲያቦካ ሲጋግረኝ፣ ሲጠመዝዝ ሲያራግፈኝ ይውልና ያው ማታ እንደ ስጥ መደቤ ላይ ያሰጣኛል፡፡
ጨጓራ አለብህ እንዴ?
ምነው ሃኪምዋ ይሄ ንግግርዎ እንኳን ተሰው ተፈጣሪ አያጣላም ......
እኛን መሰል፥ ሀገሩንና ባህሉን ጠንቅቆ አውቆና አክብሮ፣ የኛኑ ለኛው የሚያቀብል፥ እያዝናና በጥበብ ችሮቱ ትውልዱን የሚያንጽ ባለሙያ ይበዛልን ዘንድ የቀደሙትን ማክበርና ማስታወስ ይገባል። ቸር ሰንብቱልኝ!!

Read 1329 times