Saturday, 26 October 2019 12:28

ለቄሮ ሥራና ተስፋ የሚሰጠው ማን ነው?

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

  ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር ናት እየተባለ ሌት ተቀን በየመገናኛ ብዙኃኑ እስኪታክተን ድረስ ተለፍፎልናል፡፡ ወጣቱ የኢኮኖሚ ግንባታ ሃይል፣ የነገው ሀገር ተስፋ መሆኑ ይታወቃል:: በሌላ በኩል ወጣት ማለት ስሜቱ ስስ፣ አዕምሮውን ለብዙ ሃሳቦች የከፈተ፣ ለደግና ለከፉ ነገር የተጋለጠ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለለውጥ ያለው ጉጉት እንደ እሳት የሚንቦገቦግ ነው፡፡ ወጣቱ በራሱ ስነ ህይወታዊ፣ ስነ ልቡናዊና ማኅበራዊ ህይወት ሳይቀር ለውጥን የሚያስተናግድበት ዕድሜ ላይ ነው፡፡
በዚህም የተነሳ በሀገራችንም ሆነ በሌሎች ሀገራት ወጣቱ በየዘመናቱ ለለውጥ እየተባለ የሚለኮስ ችቦ ሆኗል፡፡ እርሱ ሲነድ፣ ህይወትን ያጣጣሙ ዕድሜ ጠገብ ጐልማሶች እሳቱን እየሞቁ የተድላ ኑሮ ያጣጥማሉ፡፡ ወይም በእርሱ መስዋዕትነት እነርሱ የሚያልሙትን ያሳካሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ወጣቱ ለሌሎች የሚነጠፍ የአውዳመት ቄጠማ፣ የበዓላቸው ማድመቂያ ሻማ ነው፡፡ ይህንን ጠንቅቀው የሚያውቁ ፖለቲከኞች የራሳቸውን ክፉ ሃሳብ በመሙላት ወጣቶችን ለፈለጉት ዓላማ ይጠቀሙባቸዋል:: አርስቶትል ስለ ወጣቶች ሲናገር፤ “ወጣቶች ደስታ ፈላጊዎች፣ ቅኖች፣ ችኩሎች፣ ለስሜት የሚገፋፉ፣ ለሚናገራቸው ሰው እምነት ያላቸው፣ የማይጠራጠሩ፣ የተነገራቸው ነገር እውን እንዲሆን የሚናፈቁ ናቸው…” ይላል፡፡
በታሪክ ውስጥ እንደምንመለከተው፤ በየትኛውም ሀገር አብዮትና ለውጥ ውስጥ መሪ ተዋናይ ሆነው የሚማገዱት ወጣቶች ናቸው፡፡
ሩቅ ሳንሄድ ዛሬ በርካታ መጻሕፍት የተጻፉላት፣ የተቀለበሰውና ደርግ ሥልጣን ላይ የወጣበት አብዮት እንዲመጣና ከመጣም በኋላ ከደርግ እጅ ወደ ህዝብ ለመመለስ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በተደረገው ትግል በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ሞተዋል:: የሞቱትም ለጭቁኑ ህዝብ የተሻለ ኑሮ ለመፍጠር እንጂ ለራሳቸው የኢኮኖሚ ጥቅም አይደለም:: እንዲያውም በዘመኑ የነበሩ ታላላቅ ባለሥልጣናትና ባለሃብት ልጆች በዋነኛነት የተሳተፉበት ነበር፡፡ ወጣቶች አእምሮዋቸው ለለውጥ ክፍት ስለሆነ የተነገራቸውንና ቃል የተገባላቸውን ተቀብለው መቆየት  አይችሉም፤ ወዲያው እንዲፈፀምላቸው ይፈልጋሉ፡፡ በዚያ ላይ ሠፊው የወጣትነት ዘመን ላይ ያሉቱ፣ በመንጋና በቡድን ልምምድ ውስጥ ተሣታፊ ይሆናሉ፡፡ ከቤተሰባቸው ይልቅ ጓደኞቻቸውን ያምናሉ፡፡
መምህራን የሚያስተምሯቸውን የፍልስፍና ሃሳብ ይዘው መነጋገርና ማብሰልሰል፣ ወደ ተግባር ለማምጣትም መሞከር የወጣቶች አንዱ ባህርይ ነው፡፡
ስለዚህ ለእነርሱ የሚነገረውን መምረጥ፣ በቀጣይ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት መገመት በጣም ጥንቃቄ የሚጠይቀውም ለዚህ ነው፡፡ እሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ የመጨረሻ ውጤቱ፣ መቃጠልና መቀጣጠል መሆኑ ይታወቃል፡፡  ወጣት የሚቀበለው እኩይ ነገሮችን ብቻ አይደለም፣ በጐ ሃሳቦችንም ይዞ እስከ ሞት ድረስ በታማኝነት ሊሄድ ይችላል:: በጐ የዘራ በጐውን ሲያጭድ፤ አረም የዘራ አረሙን ያጭድ ዘንድ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዓለምን ሲያውክ የነበረውና የብዙ ንፁሀንን ደም በአደባባይ ያፈሰሰው አይሲስ፣ በብዙ ወጣቶች ደም የታጠበ ድርጅት ነው፡፡ ወጣቶችን በማህበራዊ ሚዲያ በማግባባት፣ ለፈጣሪ የቀናና የቆመ በማስመሰል፣ ብዙ ህይወት እንዲጠፋና ምድራችን በእንባ እንድትታጠብ አድርጓል፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን የክፋት ድግስ የደገሱ ሰዎች መራራውን የሞት ጽዋ አልጠጡም፤ ለሁሉ ነገር ልቡ ክፍት የሆነው፣ ስሜተ ትኩሱ ወጣት በቦምብና በጥይት አረር ረገፈ እንጂ:: የአይሲስ መሪዎች ደግሞ ብራቸውን ዛቁ፤ ተልዕኮዋቸውን ለመፈፀምም ወጣቱን እንደ ፈረስ ጋለቡበት፡፡
የእኛ ሀገር ወጣቶችም ታሪክ ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ በዘመነ ደርግ በየአደባባዩ ሬሣው የተሰጣው ወጣት፣ በወያኔ ተመልምሎ በረሃ ለበረሃ ስኳር እየቃመ የታገለው ሁሉ አለቆቹ የነገሩትን ህልም ተቀብሎ፣ የጓጓውን አዲስ ዓለም ለማየት አልሞ ነበር፡፡
የኢህአፓው ዘመን እንዲሁ ባክኖና ተቃጥሎ ቢቀርም፣ በወያኔ ትግል የሚያልቀው አልቆ የተረፈው ህልሙን የማየት ዕድል ገጥሞት ነበር፤ ህልሙን ግን ተነጥቋል፡፡ ያሰበውን ተከልክሏል፡፡ ለሌሎች ሃብት ማጋበሻና ሥልጣን መፈናጠጫ ሆኗል፡፡ ቤተሰቡም ልጆቹን ከገበረ በኋላ ከድህነትና ጉስቁልና ሊወጣ አልቻለም፡፡ ሁሉን በሆድ ይዘው የሚያልፉት ሲያልፉ፣ ወላጆች የሚጦሯቸው ልጆቻቸውን በጦርነት በማጣታቸው፣ ለማይፈልጉት ልመና ተዳርገዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ ትርዒት በአብዛኛው ታዳጊ ሀገራት ውስጥ የተለመደ የሰቆቃ ቀለበት ነው፡፡ ወጣቱ ‹‹እንታገልልሃለን›› የሚሉትን ያዳምጣል፣ ህልማቸውን ይጋራል፣ ለህልሙ ራሱን ይሰጣል… ይነድዳል፣ ሌሎች ይሞቁታል፡፡ የቅንጦት ኑሮ ይኖሩበታል፡፡
ታዲያ ወጣትን አንድደው እየሞቁ፣ ዐመድ ተሸክሞ፣ ወይም ለአዲስ ነገር ዝግ የሆነ አእምሮ ይዞ ዕድገትና ልማት አይታሰብም፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት መጀመሪያ ላይ እንደ ቀደሙት መንግሥታት ወጣቶች በአደባባይ በተጋነነ መጠን ባይገደሉም፣ በየእሥር ቤቱ ማቅቀዋል:: የወያኔ መራሹ መንግሥት ፍፃሜ ሲቃረብም በአደባባይ ተገድለዋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ኦሮምኛ ተናጋሪዎች የተለየ ሃሳብ ካቀረቡ “ኦነግ” በሚል ሰበብ በሚታሠሩበት ጊዜ በተናጠል ከመሞት ብሎ በአደባባይ ላይ ለትግል የወጣው ቄሮ፤ በእጅጉ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ በ1997 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ወጣት ድንጋይ ይዞ ወጥቶ ከወያኔ ጋር መተናነቁም የሚረሳ አይደለም፡፡ ቄሮ በኢትዮጵያ የለውጥ ጐዳና ላይ ከአማራው ፋኖ ጋር የሚነሳ ጉልህ ታሪክ አለው፡፡ ሥርዓቱ ያንገሸገሸውን ያህል፣ ምናልባትም ቤቱ እንኳ ቢቀመጥ ጐትቶ የሚያወጣውን ግፍ ለመከላከል አደባባይ ላይ እየወጣ ደረቱን ለጥይት ሰጥቷል፡፡
ይሁንና ቄሮ ከወያኔ ጋር ቢፋለምም፣ ብዙ የጥላቻ ትርክቶች የተነገሩት በመሆኑ፣ ከሌሎችም ብሔሮች ጋር በሠላም እንዳይኖር ያው ወያኔ ራሱ ያዘጋጀለት አጥር አለ፡፡ የመቶ አመታት ቂም እየቆፈረ አንጀቱ እንዲቃጠልና በቁጭት እንዲያርር ተደርጓል፡፡ ያ ሁሉ የተደረገው ደግሞ የወያኔ ዙፋን ዘላለማዊ እንዲሆንና ግራና ቀኙን በማባላት፣ የሌሎችን ሀብት ዘርፎ ለመጠቀም  ነበር፡፡
ቄሮ ይህንን የጥላቻ አጥር ዘልሎ ነው ወያኔ ላይ የተከመረበት፡፡ የ‹‹ቲም ለማ›› ቡድን ልዩ ሃይሉ ከለላ ስለሰጠው ሞቱ ውጤት አምጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና የቄሮ አዛዥ ብዙ ነው፡፡ እንደ ራሱ ክብር ዘብ ሊጠቀምበት የማይፈልግ የለም:: መንግሥት ቄሮን ይፈልጋል፤ ጃዋር ቄሮን ይፈልጋል፤ ኦነግ ቄሮን ማሰለፍ ይፈልጋል:: የሚያሳዝነው ግን እስካሁን ቄሮ ምን ያስፈልገዋል? ብሎ ትኩረት የሰጠው የለም፡፡ ቄሮ የማይከፈለው ነፃ ሠራዊት ነው፡፡ በብዙዎቹ አይን ቄሮ ኑሮ የለውም፤ ቄሮ ዳቦ አይበላም፤ ቄሮ አይማርም፣ ቄሮ ህልም የለውም፣ ቄሮ የአደባባይ ላይ አውታታ ነው:: አንዱ ወገን መሣሪያ ሲያደርገው፣ ሌላው ወገን ቄሮን እንደ ሽፍታ ያየዋል፡፡ ግን እስከ ዛሬ ማነው ለቄሮ መቋቋሚያ አስቦ ገንዘብና ድጋፍ የሰጠው? ማነው ስራ ልፍጠርለት ብሎ ፕሮጀክት የነደፈው? ማነው ትምህርት ቤት ገብቶ ተረጋግቶ እንዲማር የጣረው? ቄሮ ለአንዳንዶቹ ግድግዳ ላይ የተጠንጠለጠለ ጠመንጃ ነው:: እኔ እስከማውቀው ድረስ የኦሮሞ ህዝብ ሲፈናቀል፤ የዛሬ “ወዳጆቹ” ሚሊየን ብሮች ላይ ተኝተው ሻራፊ ሣንቲም አልሰጡትም:: ሲታረዝ አላለበሱትም፤ ሲፈናቀል መጠለያ አልቀለሱለትም፡፡ ታዲያ የቄሮ ዘመድ ማነው? በትክክል ለኦሮሞ ህዝብ የሚታገል የቱ ነው? አንጀቱ ታጥፎ ከአመት እስከ ዓመት ከአፈር ጋር ለሚታገለው ምስኪን የኦሮሞ ገበሬ ያዘነለት ማነው? ቀንበሩን ለመሥበር፣ ኑሮውን ለመለወጥ አንድ እርምጃ ወደርሱ የተራመደው የትኛው የኦሮሞ ፓርቲ ነው? የኦሮሞ ሕዝብ፣ የኦሮሞ ወጣትና ቄሮ የሌሎች መሰላል ከመሆን ያለፈ የተጠቀመው ነገር ካለ፣ የምታውቁ ንገሩኝ፡፡ ኪሱ ሞልቶ፣ ሆዱ ጠግቦ የሚፈልገውን አግኝቶ ቢሆን ኖሮ እንዳሻን፣ አደባባይ ላይ እንደ ብቅል አናሰጣውም ነበር?
የቄሮ ህልም ሌላ ሳይሆን ኑሮ ነው፤ መማር፣ ሰርቶ መብላት፣ ለቤተሰቡ መትረፍ… ራሱን መቻል ነው ህልሙ፡፡ ወደዚያ የሚያደርሰውን ትክክለኛ መንገድና አቅጣጫ የሚያሳየውና የሚደግፈው በማጣቱ ግን ወደ ከተማ እየመጣ ቦታ ማጠር፣ መሬት መከለል ጀምሯል፡፡ ያለ ሥራ ተቀምጦ፣ ያገኘው ሁሉ በማህበራዊ ሚዲያ ሲጠራው እንደግሪሳ ወፍ ግርር ብሎ እየወጣ ዘመኑን ማጠናቀቅ፣ ባክኖ መቅረት አይፈልግም፡፡
የቄሮ ዋና ችግሩ የኢኮኖሚ ችግር ነው፡፡ ሰሞኑን በፖለቲካ ጨዋታ መሀል በዚሁ ጉዳይ ላይ ያወራኝ ወዳጄ የነገረኝ ይህንኑ ነው፡፡ ወዳጄ የንግድ ድርጅት ስላለው ወጣቶች ቀጥሮ ያሠራል፡፡ እናም “እነዚህ እኔ ቤት የሚሠሩት ልጆች እዚህ ባይሠሩ ኖሮ፣ ሠልፍና ግርግር ላይ ታገኛቸው ነበር፡፡” ብሎኛል፡፡ እውነቱን ነው:: ስራና ተስፋ የሌለው ወጣት የት ይሄዳል? ዕድል የመሰለውን ሁሉ ይጠቀማል፡፡ ሕይወትን የሚያሳጣ ቢሆንም፡፡
አንዳች ተስፋ ያጫረለት የመሰለውን ሁሉ ያምናል፡፡ “መሬትህ ላይ ያሉትን መጤዎች አስወግደህ፣ አንተው ራስህ በገዛ ሀገርህ እንዳሻህ ትሆናለህ” የሚሉ እብዶች የሚጭሩት እሣት ብርሃን መሆኑን እንጂ ማቃጠሉን አያውቅም፤ ሳያይ ዘው ብሎ ይገባል፡፡
ግን ቄሮን የሚታደገው ማነው? እናንተ ጐልማሳ ፖለቲከኞች ሆይ  ከዳር ቆማችሁ በወጣቱ ህይወት ዳማ መጫወት አቁሙና ለችግሩ መፍትሄ አብጁለት፡፡ የቄሮ ዋነኛ ችግር ነው፡፡ የራሳችሁን እንጀራ አብስላችሁ፣ ጠግባችሁ እየበላችሁ… ወጣቱን  ጦሙን አታንከራትቱት፡፡
ቄሮ ሌላ ሳይሆን ሰው ነው፡፡ ወጣት ነው:: ትኩስ ነው፡፡ እንደ ወዳጅ ቀርበው የነገሩትን በሚያምንበት የዕድሜ አንጓ ላይ የሚገኝ፣ ህልም ፈላጊና ህልም ተከታይ ነው፡፡ የየግል ጥቅማችሁን የሚያስከብርላችሁን ክፉ ህልም አትጫኑበት!!
ቄሮ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ወጣት ዳቦ ይፈልጋል፤ ሥራ ይፈልጋል፣ ትዳር ይፈልጋል፤ ትምህርት ይፈልጋል፡፡ የየራሳችሁን ኑሮ አሟልታችሁ.፣ ሚሊዮኖች ሰብሰባችሁ… ቄሮን ግድግዳ ላይ እንደሰቀላችሁት ጠመንጃ ለጦርነት የምትጠቀሙበት ሁሉ፣ በሕይወቱና በዘመኑ አትቀልዱበት፡፡ እስቲ በህዝብ ስም ከምትሰበስቡት ገንዘብ ትንሽ ትንሽ እያዋጣችሁ ኑሮውን ቀይሩለት፡፡ ሁልጊዜ የናንተ መሣሪያ እንዲሆን የውሸት ታሪክና ህልም እየሰበካችሁ ህይወቱን  አታስገብሩት! ግን ቄሮን የሚታደገው ማነው?

Read 10533 times