Saturday, 26 October 2019 12:25

አስገራሚውን ታሪካዊ ምድር ሸዋን እንዳየሁት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አንዳንዴ በየዓመቱ፣ ሌላ ጊዜ በየሁለት ዓመቱ የሚያዘጋጀው ‹‹ህያው የኪነ ጥበብ ጉዞ››፤ ማህበሩ ከሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ባለፉት ዓመታት ይህን የኪነ ጥበብ ጉዞ፤ ወደ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ አገር፣ ወደ ፍቅር እስከ መቃብር አገር፣ ወደ ፈላስፋው ዘርዓያቆብ አገር፣ ወደ መቀሌ፣ ሐረርና ወደ አባይ ጣና ምድር አምስት አስደናቂ ታሪካዊ ጉዞዎችን አድርጓል፡፡
ዘንድሮም ‹‹ሕያው የኪነ ጥበብ ጉዞ 6 ወደ ታሪካዊቷ ምድር ሸዋ›› የተሰኘውን ጉዞ ከጥር 5-10 ቀን 2012 ዓ.ም አድርጎ ተመልሷል፡፡ በዚህ ጉዞ ላይ የሙዚቀኞች፣ የሰዓሊያንና ቀራጺያን እንዲሁም የቴአትር ባለሙያዎች ማህበራትን ጨምሮ 26 የሙያ ማህበራት ተወካዮች፣ አንጋፋ ፀሀፍትና ገጣሚያን እንዲሁም ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል፡፡
ጉዞው የተጀመረው ረቡዕ ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ረፋድ ላይ ስታዲየም ፊት ለፊት በሚገኘው የማህበሩ ዋና ጽ/ቤት ሲሆን የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ባደረጉት የአሸኛኘት ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡
የተጓዥ ቡድኑ ረፋድ 5፡00 ላይ ጉዞውን የጀመረ ሲሆን አዳሩን በሰሜን ሸዋ ሞላሌ በማድረግ ጓሳ የተባለውን በጣም ቀዝቃዛና ቀይ ቀበሮ የሚገኝበት ሥፍራ ተጎብኝቷል፡፡ በመሃል ሜዳ በአንድ አባት፣ ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራ (ዳግማዊ ላሊበላ) ዳግም ጎልጎታ የተሰኘ ቤተ ክርስቲያን፣ ከየአቅጣጫው ሕዝቡ እየጎረፈ የሚሳለመውና ፈውስ የሚያገኝበት ዘብር ገብርኤል፣ ወደ ውስጥ መግባት ባይፈቀድም እንዲሁም ‹‹አርባሃራ›› የተሰኙ ቤተ ክርስቲያናትና ሌሎችም አጃኢብ የሚያሰኙ ቦታዎች ተጎብኝተዋል፡፡
ተጓዡ ቡድኑ ቅዳሜ ጠዋት ከሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ደብረ ብርሃን ተነስቶ ጉዞውን ያደረገው ወደ አድዋው ፈርጥ ወደ እምዬ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት አንኮበር ነበር:: አንኮበር ከተማ ቁርስ ከቀማመስን በኋላ ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ቤተ መንግሥት አመራን፡፡ ጉልበት የሚሰባብረውን ቁልቁለት ወርደን፣ በጥርብ ድንጋይ የተሰራውን ከ240 በላይ ደረጃ እየቃተትንና ቁና ቁና እየተነፈስን መውጣቱን ተያያዝነው፡፡ ቤተ መንግሥቱ የታነፀበትን ከፍተኛ ተራራ ልብ ያልነው ‹‹እባክዎ እያረፉ ደረጃውን ይውጡ›› የሚለውን ማሳሰቢያ ጽሑፍ ባየን ጊዜ ነበር፡፡
ቤተ መንግሥቱን ያስጎበኘችን ወጣት ብርቱካን አይችሉህም እንደነገረችን፤ ቤተ መንግሥቱ ሁለት በሮች ሲኖሩት ‹‹ፊት በር›› እና ‹‹ሚስጥር በር›› ይባላሉ፡፡ ‹‹ፊት በር›› ንጉሶቹ በግልጽ የሚጠቀሙበትና ሕዝቡም ግብር ለመክፈል የሚጠቀምበት ነው፡፡ ‹‹ምስጢር በር›› 471 ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ምስጢራዊ ሰው የሚገባበትና ለንጉሶቹ መልዕክት በልዩ ሁኔታ የሚገባበት እንደሆነ ተገልጾልናል፡፡ ቤተ መንግሥቱ ባለ አንድ ፎቅ ሲሆን ላይ ቤትና ታች ቤት እየተባለ ይጠራል፡፡ እላይ ቤት ንጉሶቹና ቤተሰቦቻቸው ሲኖሩ፣ ታች ቤት ደግሞ እልፍኝ አስከልካይ፣ አማካሪዎችና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ይኖሩ እንደነበር አስጎብኚዋ ትናገራለች፡፡
በአንኮበር ቤተ መንግሥት ከ25 በላይ የሸዋ ነገስታት እንዳለፉ ታሪክ ይናገራል፡፡ እስከ ንጉስ ይኩኖ አምላክ ዘመን ማለት ነው፡፡ በይኩኖ አምላክ የንግስና ዘመን ግራኝ መሀመድ መጥቶ ቤተ መንግሥቱን አስለቅቋቸው የነበረ ሲሆን በ1733 ዓ.ም በአመሃ ኢየሱስ በድጋሚ ተመስርቷል፡፡ ከአመሃ ኢየሱስ በኋላ አስፋ ወሰን ወሰን ሰገድ ቁንዲ ላይ፣ የአፄ ምኒሊክ አያት - ንጉሥ ሳህለ ስላሴና የአፄ ምኒሊክ አባት ንጉሥ ኃይለ መለኮት እንዲሁም አፄ ምኒሊክ ለመጨረሻ ጊዜ የነገሱበት  ታሪካዊ ቦታ ነው - አንኮበር፡፡ ይህ ቤተ መንግሥት ከአፄ ምኒሊክ በኋላ በኃይለ ሥላሴ ዘመን  በ1928 ዓ.ም ጣሊያን እንደገና አፈራርሶት ነበር፡፡  በ1992 ዓ.ም በኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅ እንደገና የተገነባ ሲሆን ግንባታው ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በሎጅ መልክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በአራቱም ማዕዘን ጅው ባለ ገደል ተከቦ ብቻውን የተጎበረውና ከባህር ጠለል በላይ በ2870 ጫማ ላይ የሚገኘው ይሄው ቤተ መንግሥት፤ አፄ ምኒሊክ የተዋጣላቸው የጦር ስትራቴጂ መሪ እንደነበሩም በግልፅ ይመሰክራል፡፡ ነገስታት ቤተ መንግስታቸውን ተራራዎች ላይ ያንፁ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡
የቤተ መንግሥቱ እልፍኝ አሁን እንደ ሬስቶራንት የሚያገለግለው የአፄው የግብር አዳራሽ ሲሆን መኝታ ቤታቸው ደግሞ ከዋናው አዳራሽ  ውጭ፣ ‹‹ሳህለ ስላሴ እልፍኝ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ከመኝታ ቤታቸው ዝቅ ብሎ ‹‹የሸዋ ነገስታት ፍርድ ቤት›› የሚል ጽሑፍ የተሰቀለበት የሚታይ ሲሆን ንጉሱ ፍርድ የሚሰጡበት እንደነበር ተገልጾልናል፡፡
ቤተ መንግሥቱ በእንቁላልና በኖራ ድብልቅ የተሰራ ሲሆን አፄ ምኒሊክ ማዕከላዊ መንግሥት መስርተው አዲስ አበባ ሲገቡ፣ እንጦጦ ላይም ሆነ አራት ኪሎ የገነቡት ቤተ መንግስት ከአንኮበር ቤተ መንግሥት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁን ሬስቶራንት ሆኖ በሚያገለግለው በቀድሞው የንጉሱ የግብር አዳራሽ ውስጥ እጅግ የሚገርሙ ቅርሶችና የጥንት ታሪካዊ ፎቶዎች ይገኛሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የቦታ ስያሜዎችና ሌሎች ነገሮች ወደ አዲስ አበባ የሄዱት ከዚሁ ከአንኮበር ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹አራዳ›› የሚለው ስም አንኮበር የሚገኝ የአካባቢ ስም ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ንቁ ሕዝብ›› ማለት ነው ትላለች - አስጎብኚዋ፡፡ ፒያሳ የሚለው የጣሊያን ቃል ሲሆን በ1840 ዓ.ም የፈረንሳይ፣ የጣሊያንና የብሪታንያ ኤምባሲዎች በዙሪያው እንደ ነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩ ታሪካዊ ቅርሶች በብዛት በአንኮበር መድሃኒአለም ቤተ ክርስቲያንና በአዲስ አበባ እንጦጦ ሙዚየም የሚገኙ ሲሆን፣ በዚህ ቤተ መንግሥት ዋና አዳራሽ ውስጥ ጥቂት ቅርሶችና በርካታ ታሪካዊ ፎቶዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ንጉሱ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ፣ አንኮበር መድሀኒአለም ቤተ ክርስቲያን ሲጋቡ የተነሱት ፎቶ በአዳራሹ በር ላይ በጉልህ ይታያል፡፡ ፎቶውን አንዲት ፈረንሳዊት አንስታ በስጦታ መልክ እንደሰጠቻቸውም ይነገራል፡፡ ፈረንሳዊቷ አንኮበር አጠገብ በሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ትኖር እንደነበርም ሰምተናል፡፡ በፎቶው ላይ የሚታየው እንደ ካባ የተለበሰ ወርቅ በንጉሱም በንግስቲቱም ላይ ይታያል፡፡ ይህ ሁለቱም የለበሱት ወርቅ የእያንዳንዳቸው 18 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን በአሁኑ ወቅት ይህ የወርቅ ካባ (ሊሻን) እና ዋናው ፎቶ አሁንም በአንኮበር መድሀኒአለም ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ በወቅቱ ከነበሩት 44 ነጋሪቶች አንዱ በዚሁ አዳራሽ ውስጥ በፎቶ ሳይሆን በአካል ይታያል፡፡ ይህን ነጋሪት እየጎሰሙ ነበር አፄ ምኒሊክ የክተት አዋጅ የሚያውጁት፡፡
አፄ ምኒሊክ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም የጣሊያንን ወራሪ ሀይል ድል ለመንሳት፣ ወረኢሉ ላይ እንገናኝ ብለው ጥሪ ያስተላለፉበት ጽሑፍ በብራና ተፅፎ ግድግዳ ላይ ተሰቅሏል፡፡ የፈረሳቸው የአባዳኘው ፎቶም ይታያል፡፡ አፄው በፈረሶቻቸውና በበቅሎዎቻቸው እግር ላይ በጋለ ብረት ‹‹ምጣ›› የሚል ጽሑፍ ምልክት ያደርጉ ነበረ፡፡ ይኼም ምኒሊክና ጣይቱ የሚል የስማቸውን የመጀመሪያ ፊደል የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡ የፊታውራሪ ገበየሁና የባልቻ አባ ነፍሶ ፎቶም ከነጋሪቱ አናት ላይ ተሰቅሎ ይታያል፡፡
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ…  የተባለላቸው ጀግኖች መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ አፄ ምኒሊክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገራችን ያስገቧት እና የመጀመሪያ ሹፌር ሆነው የነዷት መኪና ፎቶ (ታርጋዋ አ.አ 00) እንዲሁም የመጀመሪያውና የተሻሻለው ሁለተኛው ስልክ በዚሁ ግቢ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በአፄ ምኒልክ አያት፣ በንጉስ ሳህለ ስላሴ ዘመን (በ1840 ማለት ነው)  ከቤተ መንግሥቱ በቅርብ ርቀት ላይ አነስተኛ ኢንዱስትሪ ተቋቁሞ የነበረ ሲሆን ወፍጮ፣ ባሩድና ሌሎችም ይመረቱ እንደነበር ተነግሮናል:: ንጉሱ በተጨማሪ የአስመጪነትና ላኪነት ሥራ እንዲሁም የታክስ ክፍያ አልዩ አምባ ላይ ያስጀመሩ ሲሆን የቴክኖሎጂ ልምምድም ይደረግ ነበር ተብሏል፡፡
ሌላው የኢንጂነር ተፈሪ ራስ ወርቅ የቴክኖሎጂ አሻራ ያለበት ቅርስ በዚሁ አዳራሽ መሀል ላይ ይገኛል፡፡ ይህም የአማርኛ ቃላትን በቴሌግራም ለመጻፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂን የሰሩበት ነው፡፡ ኢንጂነሩ በፊት በቴሌግራም መልዕክት ለመለዋወጥ በእንግሊዝኛ ብቻ ይሰራ የነበረውን ማሽን በአማርኛ እንዲጽፍ ያደረጉ ሲሆን በምርቃቱ ዕለት በቴሌግራሙ የተፃፈውና ከአስመራ ለጃንሆይ የተላከው ጽሑፍ ለዕይታ ቀርቧል፡፡
ጽሑፉ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ግርማዊ ሆይ፤ በቀዳማዊነትዎ ዘመነ መንግሥት በዘመናዊ እቅድ የተቋቋመው ቴሌኮሚዩኒኬሽን 15ኛ ዓመት በሚከበርበት በዛሬው ቀን በአማርኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራውን የቴሌኮሙኒኬሽን መገናኛ፣ በዚህ ዕለት በግርማዊነትዎ ተመርቆ የሚከፈት በመሆኑ ይህ ለኢትዮጵያ መገናኛ ከፍተኛ ምዕራፍ መከፈቱ ስለሆነ፣ ለኢትዮጵያ ዕድገትና እርምጃ ከሚያስቡት አንዱ በመሆኑ ከግርማዊነትዎ ጠቅላይ ግዛቶች ይህ የመገናኛ ዕድል በቀደምትነት የደረሰው በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ሕዝብ ስም ሆነ፡፡ በዚህ ሰዓት በዘመነ መንግሥትዎ  ይህን የፍጻሜ እድል ያሳየን አምላክ፣ ለግርማዊነትዎ እረጅም እድሜና ጤና ሰጥቶ፣ የጀመሩትንና ያቀዱትን ሁሉ ፍጻሜ ለማየት እንዲያበቃዎ፣ የማያቋርጥ ፀሎቴ መሆኑን በታላቅ ትህትና እገልጻለሁ፡፡
አስመራ የካቲት 19 ቀን 1960 ዓ.ም
የግርማዊነትዎ ዝቅተኛ አገልጋይ አስራተ ካሳ››    
በነገራችን ላይ ሎጁን የሚያስተዳደሩትና ቴሌግራም ማሽኑ አማርኛ እንዲጽፍ የፈጠራ ስራ የሰሩት የኢ/ር ተፈሪ ራስ ወርቅ ፎቶ ለብቻው እንዲሁም ከጃንሆይ ሽልማት ሲቀበሉ የሚያሳይና መሰል ሌሎች ፎቶዎች ይገኛሉ፡፡
የቤተ መንግሥቱን ጉብኝት ካጠናቀቅን በኋላ ወደ አንኮበር ከተማ ተመለስን፡፡ ከዚያም የከተማው አስተዳዳሪዎች ያዘጋጁትን ምሳ ተመግበንና ተመራርቀን፣ ጉዞ ወደ ማደሪያችን ሆነ - ወደ ደብረ ብርሃን ማለት ነው፡፡ በዚሁ ዕለት (ቅዳሜ ማለት ነው) ከምሽቱ 1፡00 ጀምሮ በጌትቫ ሆቴል የኪነ ጥበብ ምሽት ተሰናድቶ ነበር፡፡ በዚህ ምሽት የድንገቴ እንግዳ መገኘቱ በሁሉም ዘንድ ግርምትን ፈጥሮ ነበር:: የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ነበሩ - የድንገቴ እንግዳው። የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ደራሲና ገጣሚ አበረ አዳሙ በአጠቃላይ ስለ የኪነ ጥበብ ጉዞው አጠር ያለ ሪፖርት - ያቀረቡ ሲሆን ለጉዞው መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉትን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደሪን፣ ኮከብ ሚዲያና ማስታወቂያን፣ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲንና ሌሎችንም አጋሮች አመስግነዋል፡፡
‹‹የሸዋን ትልቅነት ከእናንተ በላይ ለመግለጽ ያስቸግራል›› ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድም አገኝ፤ ስለ ሸዋ ታላቅነት፣ ስለ ንጉሶቿ ጀግንነት ስለታሪካዊ መስህቦቿ… የተመለከታችሁትን እንደየ ሙያ ድርሻችሁ ለሌላው በማካፈልና በመመስከር ሁሉም እንዲጎበኘው መጣር አለባችሁ ሲሉ አደራ ሰጥተዋል።
ገጣሚ ምስራቅ ተረፈና መምህርና ገጣሚ ገዛኸኝ ፀጋው (ዶ/ር) ግጥሞቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ በበኩላቸው፤ ጉዞውን ያዘጋጀውን የደራሲያን ማህበርንና አጋሮቹን አድንቀው፤ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያለውን ሸዋን በመጎብኘታችሁ የታደላችሁ ናችሁ፤ ይህን ታሪክ አጉልታችሁ ለቀሪው ሕዝብ ብሎም ለአለም ለማስተዋወቅ ትልቅ አቅም አላችሁ›› ብለዋል፡፡ በተስፋና በእርግጠኝነት ተሞልተው የኪነ ጥበብ ምሽቱም በእራት ግብዣው ተቋጭቷል፡፡
በነጋታው የእምዬ ምኒሊክ የትውልድ ቀዬ ወደ ሆነው አንጎለላ ለመሄድ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ተሰርዞ ጉዞ ወደ ‹‹ኮረማሽ›› ሆኗል፡፡ ኮረማሽ የአፄ ምኒሊክ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ሲሆን ይህ ግምጃ ቤት ከሸኖ ከተማ በስተምስራቅ በኩል፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ማርያም  ከሰም ልዩ ወረዳ ውስጥ ይገኛል። በአድዋ ድል ማግስት በ1890 ዓ.ም የተገነባው የጦር ግምጃ ቤቱ፤ በእኩል ርቀት ላይ የተሰሩ 14 ቤቶች የነበሩት ሲሆን ሰባቱ ፈርሰው ሰባቱ ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡ ግቢውን ቀልብ የሚስቡ ጥቅጥቅ የጥድ ዛፎች አየሩን ነፋሻማ አድርገውታል - መንፈስ የሚያድስ፡፡ አፄ ምኒሊክ ጣሊያንን ድል ከነሱ በኋላ ዳግመኛ ጠላት ቢመጣ የሚመክቱበትና ጠላት በቀላሉ የማይደርስበት ስትራቴጂካዊ የጦር ግምጃ ቤት ሲያፈላልጉ፣ በቡልጋው ገዥና በአጎታቸው ራስ ዳርጌ ጠቋሚነት ይህንን ቦታ እንደጎበኙ የገለፁልን አስጐብኛችን፤ ‹‹እንዴት እስከ ዛሬ ይቺን ቦታ ሳላያት›› ማለታቸውን ተከትሎም ቦታው ‹‹ሳላይሽ›› የሚል ስም እንደወጣላት ሰምተናል፡፡ እስከ ዛሬም የቦታውና የከተማው ስያሜ ‹‹ሳላይሽ›› በመባል ይታወቃል።
በግምጃ ቤቱ ግንባታ ላይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች - (ከ14ቱም ክፍለ ሀገራት) የተውጣጡ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፈዋል ተብሏል፡፡
ግምጃ ቤቱ ከ1890 እስከ 1928 የጦር ግምጃ ቤት ሆኖ ሲያገለግል፣ ከ1928 እስከ 1933 በጣሊያን ቁጥጥር ስር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከ1933-1966 ዓ.ም የፖሊስ ጦር ሀይል ማሰልጠኛ፣ ከ1966 - 1983 ዓ.ም በቢሮና በአዳራሽነት አገልግሏል፡፡ ከ1983 - 2004 በጽ/ቤትነት ያገለገለ ሲሆን ከ2004 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ስር ሆኖ እየተጠበቀ ለጉብኝት ክፍት ሆኗል። እኛም በጎበኘንበት ጊዜ ወጣቶች በቡድን በቡድን ሆነው ሲጎበኙት ተመልክተናል:: ይህ ታሪካዊ የኪነ ጥበብ ጉዞአችንም በዚሁ ተጠናቋል፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን አካባቢው ትልቅ ታሪክን ይዞ አንኮበርም ሆነ ኮረማሽ ጥሩ የሚባል የጠጠር መንገድ እንኳን የሌላቸው፣ ከመሰረተ ልማት የተፋቱ ኋላ ቀር መሆናቸው የሚያስቆጭ ነው፡፡   

Read 2218 times