Saturday, 26 October 2019 12:24

ትናንሽ በጎ ተግባራት!!

Written by  ሂሮዬ ሹማቡኩሮ
Rate this item
(3 votes)

ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በዚህ ዓመት አያሌ በጎ ተግባራትን ፈጽሜአለሁ ወይም የፈፀምኩ መስሎኛል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከፈፀምኳቸው ከእነዚህ ትናንሽ በጎ ተግባራት መካከል ጥቂቶቹን ለአዲስ አድማስ አንባቢያን ላጋራቸው ወደድኩ፡፡ እስቲ እናንተም የፈፀማችኋቸውን (ትናንሽ ቢሆኑም) በጎ ተግባራት በትዊተር አድራሻዬ ላኩልኝ፡፡ በየቀኑ ትናንሽ በጎ ተግባራትን መፈፀም ይቻላል፡፡
* * *
አንድ ማለዳ ላይ ከባንክ ሰራተኛ ስልክ ተደወለልኝ፡፡ ከአንድ ቀን በፊት ከባንክ ዶላር ዘርዝሬ ነበር፡፡ የባንክ ሠራተኛው በስህተት ትርፍ ገንዘብ እንደሰጠኝ በመግለፅ፣ እንድመልስለት ጠየቀኝ፡፡ እውነት ለመናገር በዕለቱ አንድም ባንኩን በማመን፣ ሁለትም ቸኩዬም ስለነበር ሳልቆጥር ነው ገንዘቡን ወደ ቦርሳዬ የከተትኩት:: እቤት ከገባሁ በኋላም አላየሁትም ነበር፡፡ ገንዘቡን ከቦርሳዬ ውስጥ አውጥቼ ስቆጥረው፣ ትርፍ 2600 ብር አገኘሁ! ይሄ እንዴት ሊሆን እንደቻለ አላውቅም። ወዲያው ለባንኩ ሰራተኛ መልሼ ደወልኩለትና ትርፉን ገንዘብ በባንክ ሂሳቡ አስገባሁለት፡፡ ሠራተኛው በደስታ ጮቤ ረገጠ፡፡ ‹‹እግዚአብሄር ይባርክሽ!›› የሚል ምስጋናም በቴክስት ላከልኝ:: ይሄን የሰሙ ጓደኞቼም፤ ‹‹አንቺ ጎበዝ ነሽ!›› እያሉ ሞራል ሰጡኝ፡፡ ይህቺ ትንሽ ብትሆንም፣ ከመልካም ተግባር ደምሬአታለሁ፡፡
* * *
አሁንም ከገንዘብ አልወጣንም፡፡ ሰው በበዛበት የቦሌ መንገድ ላይ እየተጓዝኩ ነበር፡፡ ከእኔ ፊት በ30 ሜትር ርቀት ላይ ይጓዝ የነበረ አንድ ሰው፣ ከኪሱ ውስጥ ገንዘብ ሲወድቅበት አየሁ፡፡ ወዲያው ከኋላው የነበረ ሌላ ሰው፣ ገንዘቡን ከመቅፅበት ከመሬት ላይ አፈፍ አደረገው፡፡ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ፤ ‹‹ሄሎ ወንድም! ገንዘብ ጥለሃል!›› አልኩት፤ ለባለቤቱ:: ገንዘቡን ያነሳው ሰውዬ ለባለቤቱ ለመመለስ ያስብ አያስብ የማውቀው ነገር አልነበረም:: ለዚህም ነው በማይታመን ፍጥነት፣ ለገንዘቡ ባለቤት ጥቆማ ወይም ጥሪ ያደረግሁት፡፡ በዚህም ጥረቴ ገንዘቡ ለትክክለኛው ባለቤት በመድረሱ ደስ አለኝ፡፡ ይህን ሁኔታ ሲከታተሉ የነበሩ እግረኞችም፤ ‹‹ደግ አድርገሻል!›› በማለት አውራ ጣታቸውን አሳዩኝ - አድናቆታቸውን ለመግለጽ፡፡ አንዳንዴ መፍጠን ይጠቅማል!
* * *
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የሚኖሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር የጨመረ ይመስላል፡፡ እኔ በምኖርበት አካባቢ ከወላጆቻቸው ጋር ሳይሆን ከዘመዶቻቸው ጋር የሚኖሩ  ኤርትራውያን ሕጻናት አሉ::  ዕድሜያቸው ከ6-14 ዓመት ቢሆን ነው፡፡ የሚውሉት ሰፈር ነው::  ትምህርት  ቤት አይሄዱም:: ብዙ ጊዜ ሳቅና ፈገግታ አይታይባቸውም፡፡ ምግብ በቅጡ እንደማይመገቡም ሰምቻለሁ:: ማድረግ የቻልኩት ታዲያ በየሳምንቱ ሀሙስ በአቅራቢያችን ከሚገኘው አነስተኛ ካፌ፣ ምግብ (ቀይ ወጥ) ማዘዝ ብቻ ነው፡፡ ይሄን የምታውቅ አንዲት የካፌው ሰራተኛ፣ ይህቺን ትንሽ በጎ ተግባር፣ ቡና ሊጠጡ ወደ ካፌው ጎራ ለሚሉ ደንበኞቿ ነግራቸው ተደንቀዋል፡፡ ይህን ታሪክ የሰማና ያነበበ ሁሉ፣ ለእነዚህም ሆነ ለሌሎች ችግረኛ ሕጻናት የተቻለውን ያህል ድጋፍ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ትንሽ ብትሆንም ከበጐ ተግባር ትጣፋለች፡፡
* * *
አንዲት የጀበና ቡና እያፈላች መንገድ ላይ የምትሸጥ፣ ጠና ያለች ሴት አውቃለሁ፡፡ ሁልጊዜ በመንገድ ሳልፍ ባየችኝ ቁጥር፣ ‹‹ሃይ ቻይና! ፈረንጅ! ነይ!›› በማለት ትጠራኛለች - በጣም እየጮኸች፡፡ መጀመሪያ ግድም ችላ ብዬአት  ነበር - ትተዋለች በሚል፡፡ ነገር ግን እየባሰባት ሄደች፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ቀረብ አልኳትና ዳግመኛ እንደዚያ ብላ እንዳትጠራኝ ኮስተር ብዬ ነገርኳት። ንዴቴ የመነጨው ጃፓናዊ ሆኜ ሳለሁ ‹‹ቻይና›› እያለች ስለምትጠራኝ አልነበረም:: (ለቻይናውያን ትልቅ አክብሮት አለኝ) ግን ሰው እንዴት በተወለደበት አገር ወይም በዜግነቱ ይጠራል? በስሙ እንጂ፡፡
እሷም እንደ እኔ ሌላ አገር ሄዳ፣ መንገድ ላይ ሰዎች፤ ‹‹ሃይ ኢትዮጵያ!›› ወይም ‹‹ሃይ አማራ!” አሊያም  “ሃይ ትግራይ!” ወይም “ሃይ ኦሮሞ!›› ብለው ቢጠሯት ያስደስታት እንደሆነ ጠየቅኋት:: ያስደስተኛል አላለችም፡፡ ነገሬ ገብቷታል፡፡ ይሄን ጉዳይ በቅጡ ለማስረዳት ጊዜዬን ያጠፋሁት፣ ሌላ የውጭ ዜጋ በዚህ ዓይነት የተለመደ አጠራር  እንዳይናደድ ፈልጌ ነው፡፡  ከዚያን ጊዜ ወዲህ የዚህችን ሴት የጀበና ቡና (ካፌ) ማዘውተር ጀመርኩ:: አንድ ቀን በመንገድ ሳልፍ፣ እሷ ዘንድ ቡና ይጠጣ የነበረ አንድ ሰው፤ ‹‹እህ ፈረንጅ!›› ሲል ጠራኝ፡፡ ወዲያው ሰውየውን ቆጣ ብላ፣ እንደዛ እንደማይባል ነገረችው፡፡ እግዜር ይስጣት፤ እንዴት? ለምን?  ሳይል ያለችውን  ተቀበላት፡፡ እኔም ድካሜ ፍሬ ሲያፈራ፣ በዓይኔ በብሌኑ አየሁት፡፡ የነገርኳትን ከራሷ አልፋ ለሌሎችም አጋራችው፡፡ ከዚህ አንጻር፣ ይህቺንም ከበጎ ተግባር ደመርኳት፡፡
* * *
ከመዲናችን ቱጃር ሴቶች አንዷ የሆነችው ማሳጄ በ50ሺ ብር የእራት ቀሚስ መግዛቷን ሰማሁ፡፡ ሴትየዋ ገንዘብ ካላት ያሻትን ብትገዛ ምን ይገርማል? አንዳንድ ሰዎች በዚህች ሴት እንደቀኑባት ሰምቼ ተገረምኩ፡፡ ግን ይሄ ምኑ ያስቀናል?
መካከለኛ ገቢ ያላት አንድ ወዳጄ ደግሞ በቅርቡ 8ሺ ብር አውጥታ የልጇን ልደት አክብራለች፡፡ የዚህች  ወዳጄ ትንሽ ይለያል:: የልጇን ልደት ያከበረችው በወላጅ አልባ ሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ይሄን የወላጅ አልባ ሕጻናት ማሳደጊያ ጎብኝታ ነበር፡፡ ለሕጻናቱ ምን ልታደርግ እንደምትችል ስታስብም ቆይታለች። እናም ልጇ ከእነዚህ ሕጻናት ጋር ልደቱን እንዲያከብር አደረገች፡፡ ጓደኛዬን አደነቅኋት፡፡ ያደረገችው ነገር ልቤን ነክቶታል፡፡ አሁን ይሄን የወዳጄን በጎ ተግባር በስፋት እያሰራጨሁት ነው - ሌሎችም እንዲነቃቁበት፡፡
***
በአሁኑ ሰዓት ለምኖርበት አካባቢ አዲስ ነኝ:: በዚህ አካባቢ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ናቸው የሚኖሩት፡፡ የመኖሪያ ስፍራውን በጣም እወደዋለሁ፡፡ ትንሽ ቅር ያለኝ መንገዱ ሁሌም ቆሻሻ መሆኑ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ያለ ጭንቀት መንገድ ላይ ቆሻሻ ይጥላሉ፡፡ እኔና የቤት ሠራተኛዬ፣ በየሳምንቱ ለ30 ደቂቃ የአካባቢውን ቆሻሻ መልቀም ያዝን፡፡ በ30 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ትላልቅ የፕላስቲክ ከረጢቶች ሙሉ ቆሻሻ እንሰበስብ ነበር፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ያው ነው፡፡ ቆሻሻው ማቆሚያ ያለው አይመስልም:: ምክንያቱም ጐረቤቶቼ መንገድ ላይ ቆሻሻ መጣሉን ቀጥለውበታል፡፡ በዚያ ላይ በጋራ ወይም በትብብር የማጽዳት ልምድ የላቸውም:: በቅርቡ ታዲያ ጭንቀት የወለደው አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡ ይኸውም ለጎረቤቶቼ… (ለእያንዳንዱ አባወራ ማለት ነው) በአካባቢ ጽዳት ይተባበሩኝ እንደሆነ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፌ በየመኖሪያ ቤታቸው ላኩኝ፡፡ (ደብዳቤው ከዚህ በታች ቀርቧል) ጎረቤቶቼ ይተባበሩኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
* * *
ውድ ጎረቤቶቼ
ሁላችንም በንፅህና እና ውብ በሆነ አካባቢ መኖር እንሻለን  ሆኖም ግን አሁን ላይ ብዙ ቆሻሻ በየመንገዱ ላይ ሲጣል አይተናል፣ በበጎ ፍቃደኝነት ማፅዳት ብንሞክርም ቆሻሻው በመብዛቱ የተነሳ  ለመቋቋም አልቻልንም፡፡
እንደ ጉርብትናችን እባክዎን ይህንን በማድረግ ይተባበሩን፡፡
ልጆችዎንና ሰራተኛዎን በመንገድ ላይ ምንም  አይነት ቆሻሻ እንዳይጥሉ ይምከሩ::
ሌላ ሰውም ቢሆን መንገድ ላይ ቆሻሻ ነገር ሲጥሉ፣ እባካችሁ አትጣሉ ይበሉ፡፡
 በረንዳችንን (ደጃፋችን) ሁልጊዜ በደንብ እናጽዳ፡፡
ይህ ከሆነ ቀስ በቀስ አካባቢያችንን ንፁህ ይሆንና በጋራ ጥሩ ህይወት እንመራለን፡፡
ከጎረቤትዎ

Read 2287 times