Saturday, 26 October 2019 12:18

‹‹ሰዎቹ›› ጉልበት ተፈታተሹ

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(6 votes)

ሰሞኑን ትኩረት ከሳቡ ሀገራዊ ጉዳዮች አንዱ የአቶ ጀዋር ሙሐመድና የፌዴራል ፖሊስ ውዝግብ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎ የተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ስቧል፡፡ የእኔም ብዕር በዚሁ ጉዳይ ላይ አነጣጥራለች፡፡ በዚህ መጣጥፍ በዋናነት ሁለት ጥያቄዎችን በማንሳት ምላሽ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ፤ “ለአቶ ጀዋር የመንግስት የጥበቃ ኃይል መመደብ ተገቢ ነው?” የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ “እነዚህን የጥበቃ ኃይሎች ለማንሳት የተሄደበት አግባብ ትክክል ነው ወይ?” የሚል ነው፡፡
በቅድሚያ ለአቶ ጀዋር የጥበቃ ኃይል መመደብ ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን እንይ፡፡ ከመርህ አኳያ የአንድ መንግስት ዋነኛ ሥራ፤ የሁሉንም ዜጎቹን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ነው፡፡ ይህም በዓለም ላይ ያሉ መንግስታት ሁሉ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአንድ ሀገር መንግስት የራሱን ዜጎች ብቻ ሳይሆን በሀገሩ ውስጥ የሚኖሩ ወይም በእንግድነት የመጡ የየትኛውንም ሀገር ዜጎች ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታም አለበት፡፡
ይህ አጠቃላይ መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት ልዩ ጥበቃ ሊያደርግባቸው የሚገቡ ተቋማትና ግለሰቦች አሉ፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናት በግለሰብ ደረጃ የመንግስት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ከዚህ ሌላ የተለየ (special) ሙያ ላላቸው ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች (ለምሳሌ፡- የኑክሌር ሳይንስ ተመራማሪ ለሆነ ሰው) ከያዘው ምስጢር አኳያ ልዩ ጥበቃ ቢደረግለት አግባብ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
አቶ ጀዋር የመንግስት ባለስልጣን አይደለም:: ልዩ የሆነ ሙያ ያለው ተመራማሪም ሳይንቲስትም አይደለም፡፡ በርግጥ አቶ ጀዋር ተጽእኖ መፍጠር የቻለ አክቲቪስት ነው፡፡ የአክቲቪስትነት እንቅስቃሴውን የሚደግፉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ የሚቃወሙትም ይኖራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ አቶ ጀዋር ለረዥም ጊዜ ወደተለያት ሀገሩ ሲገባ የሚተናኮሉት ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል እሳቤ ብቻ ሳይሆን (ልዩ ችሎታ እንዳላቸው ሳይንቲስቶች) አቶ ጀዋር ለሀገሪቱ ፖለቲካ ካለው አስተዋጽዖ አኳያ ነገሮች እስቲስተካከሉ ድረስ ጥበቃ እንዲደረግለት በመንግስት መወሰኑና ጥበቃ መደረጉ ክፋት የለውም፡፡ ተገቢም አስፈላጊም ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል:: የፖሊስ ኮሚሽነሩ ከሰጡት መግለጫ አኳያ ለአቶ ጀዋር ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ግለሰቦች ጥበቃ እየተደረገላቸው እንደሆነም መገመት ይቻላል፡፡ ይህ ጥበቃ የሚደረገው ግን “የብሔሬ ተወላጅ፣ የወንዜ ልጅ” በሚል መንፈስ ሳይሆን መርህና አሰራር ተቀምጦለት ሊከናወን ይገባዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ወደ ሁለተኛው ጥያቄ እንለፍ፡፡ የአቶ ጀዋርን የጥበቃ ኃይሎች ለማንሳት የተሄደበት አግባብ ትክክል ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ረቡዕ ዕለት የሰጠውን መግለጫና አቶ ጀዋር በፌስቡክ ገጹ የሰጠውን ማብራሪያ አጣምሮ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ፖሊስ የሚለው “… ለውጡን ተከትሎ ወደ ሀገራቸው ለገቡ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች በሚኖሩበት አካባቢና በሚንቀሳቀሱበት ስፍራ ችግር እንዳይገጥማቸው የጥበቃ ከለላ ስናደርግ ነበር፡፡ በሀገሪቱ የነበሩት ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈቱ ሰላማዊ ሁኔታ እየተረጋገጠ በመምጣቱ … የግል ጥበቃዎችን የማንሳት ስራ ስንሰራ ቆይተናል”፤ በጀዋርም ላይ ተመሳሳይ ነገር ነው ያደረግነው የሚል መንፈስ ያለው መግለጫ ነው የሰጠው፡፡ በአቶ ጀዋር በኩል ደግሞ “ቀደም ባሉት ጊዜያት የአጃቢ ለውጥ ያደርጉ የነበረው በስልክ አሳውቀውኝ ነበር፡፡ አሁን ግን በውድቅት ሌሊት በጣም አጠራጣሪ በሆነ መልኩ የተሞከረው ነገር ምን እንደሆነ አልገባኝም” የሚል መንፈስ ያለው ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት በነበረው አሰራር የሀገሪቱ የፀጥታ አካላት በውድቅት ሌሊት ወይም ማለዳ ላይ የሰው ቤት ይገባሉ፣ ይበረብራሉ:: የተበርባሪው ንብረት ያልሆኑ ሰነዶችና የጦር መሣሪያ ጭምር እዚያ ያስቀምጡና ሰውየውን “ይሄ ሁሉ አንተ ቤት የተገኘ ነው፡፡ በል እዚህ ሰነድ ላይ ፈርም” ይሉታል፡፡ አስገድደው ያስፈርማሉ፡፡ አልፈርምም ካለ ደግሞ ለምስክርነት ይዘዋቸው የሄዱ ሰዎችን “ይሄ ሰነድ/መሣሪያ እዚህ ቤት መገኘቱን አይታችኋል” ብለው ያስፈርማሉ፡፡ ወንጀል ተፈበረከ ማለት ነው፡፡ ከዚያም በነዚያ ሰነዶች ላይ የሚታዩ “ወንጀሎችን” የሚያረጋግጡ የወንጀለኛ መቅጫ አንቀፆችን በመጥቀስ ክስ ይመሰርታሉ፡፡ ፍርድ ቤት አቅርበው፣ ያዘጋጇቸውን “እማኞች” አስመስክረው ያስፈርዱበታል፡፡ ይህንን አሰራር የለመዱ የፀጥታ አካላት በመንፈቀ ሌሊት ወደ አቶ ጀዋር ቤት ሄዱ፡፡ (አቶ ጀዋር ለሚዲያ እንደተናገሩት)
ይህ በአቶ ጀዋር ላይ የተፈጸመ ድርጊት ድንገት የተከሰተ አይመስልም፡፡ መለስ ብለን በጊዜ ቅደም ተከተል ስናየው፤ ዶ/ር ዐቢይ ማክሰኞ እለት በፓርላማ ባደረጉት የጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ በቀጥታ የአቶ ጀዋርን ስም ባይጠቅሱም፣ “የውጭ ሃገር ዜጋ የሆናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች፣ እኛ ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሄዱበት ሃገር ያላችሁ ሰዎች፣ ትዕግስት እያደረግን ያለነው አውድ ለማስፋት ነው፡፡ በማንኛውም ሰዓት በኢትዮጵያ ሰላምና ኅልውና ከመጣ አማርኛ ብትናገሩም ኦሮምኛ ብትናገሩም እርምጃ መውሰዳችን አይቀርም” የሚል ሃሳብ ተናገሩ፡፡ አቶ ጀዋር ይህንን ሰማና “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል” የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ማክሰኞ ማታውን ወደ ሞስኮ በረሩ፡፡ እርሳቸው ከሀገር ሲወጡ አንዳች ነገር መከሰቱ እየተለመደ በመምጣቱ “ምን ይፈጠር ይሆን?” ብለን ስንጠብቅ ፌዴራል ፖሊስ የአቶ ጀዋርን ቤት መክበቡ ተሰማ:: አቶ ጀዋር ከተለመደው ሁኔታ ያፈነገጠ ክስተት ሲገጥመው ለደጋፊዎቹና ለተከታዮቹ ባለው የግንኙነት መስመር አሳወቀ፡፡ የጀዋር ደጋፊዎችና ተከታዮች በቁጣ ገንፍለው ወጡ፡፡ የሰው ህይወት ተቀጠፈ፡፡ ንብረት ወደመ፡፡ ሀገር ተበጠበጠ…
እንደሚታወቀው የፀጥታ አካላት የመንግስት ሰራተኞች ናቸው፡፡ የሚመሩበትና የሚተዳደሩበት ህግና ስርዓት አለ፡፡ የመንግስት ተቋማት የሥራ ሰዓት ከጧቱ 2፡30 እስከ 11፡30 ሰዓት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ህጋዊ ሥራ የሚሰራ አካል ስራውን ማከናወን ያለበት በዚህ የጊዜ ክልል ውስጥ ነው፡፡ ታዲያ የፀጥታ አካላቱ ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት አካባቢ ወደ አቶ ጀዋር ቤት የሄዱት ምን ሊያደርጉ ነው? አግባብስ አለው? ሁለት መስመር ደብዳቤ ጽፈው ለአቶ ጀዋር ጥበቃ እንደማያደርጉ መግለጽ ሲችሉ፣ እንዲህ ያለው ጨለማን ተገን ያደረገ ዘመቻ ምን ይባላል? ጀዋር ለዓመታት ሲጮህ የነበረው እንዲህ ያለው ተገቢ ያልሆነ ተግባር እንዲቀር ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬም (ያውም በራሱ ላይ) ሲፈጸም፣ ደጋፊዎቹንና ተከታዮቹን “ድረሱልኝ” ቢል የሚገርም ሆኖ አይታየኝም፡፡ ይሁን እንጂ ጀዋር የተቆጡ ደጋፊዎቹና ተከታዮቹ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ያሰበበት አይመስለኝም፡፡ በብስጭት፣ በንዴትና በመደናገጥ “ሳይቀድሙኝ ልቅደማቸው” በሚል መንፈስ በወሰደው እርምጃ ይሄ ሁሉ አሳዛኝ ሁኔታ ደረሰ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዳሉት፤ በሀገሪቱ የነበሩ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈቱ በመምጣታቸውም ይሁን በሌላ ምክንያት መንግስት ለጀዋርም ሆነ ለሌሎች የሚያደርገውን የጥበቃ አገልግሎት በፈለገው ጊዜ ማንሳት መብቱ ነው፡፡ አስፈላጊነቱን ካላመነበት መንግስት ለእያንዳንዱ ዜጋ ዘበኛ የማቆም ግዴታ የለበትም፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ጀዋርም የራሳቸውን አማራጭ እርምጃ እንዲወስዱና ራሳቸውን እንዲጠብቁ ፌዴራል ፖሊስ የሚያደርገውን ጥበቃ እንደሚያነሳ በመንግስት የስራ ሰዓት ለአቶ ጀዋር በግልጽ መናገርና የጥበቃ ሰራተኞቹን ማንሳት ይችል ነበር፡፡ ትልቁ የፖሊስ ስህተት ይሄ ነው፡፡
ተያያዥነት ያለው አንድ ሃሳብ ልጨምር፡፡ ሰሞኑን ከተከሰተው ሁኔታ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር፣ በኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል የጦፈ “የስልጣን” ሽኩቻ መኖሩን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ ጎላ ያለ ተሰሚነት ያላቸው፣ ስመ ገናና መሪዎች ብቅ ብቅ እያሉ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ከነዚህ ግለሰቦች ውስጥ አንዱ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ናቸው፡፡  በኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን በበርካታ ኢትዮጵያውን ልብ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከዶ/ር ዐቢይ ሌላ አቶ ጀዋር ሙሐመድ፣ አቶ ለማ መገርሣና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አቶ ሽመልስ አብዲሣና አቶ ታከለ ኡማ በብዙኃኑ ኦሮሞ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኙ መሪዎች ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡
እንደሚሰማው ከሆነ የለማ ቡድን፣ የዐቢይ ደጋፊ፣ የጀዋር ተከታይ፣… የሚባሉ ቡድኖች ተፈጥረዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ህጋዊና ተቋማዊ ቅርጽ የሌላቸው አደረጃጀቶች ልንቆጣጠራቸው ስለማንችል በህዝብና በሀገር ላይ አደጋ ለማድረስ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሰሞኑን የታየውም ይኸው ሁኔታ ነው፡፡ የጀዋር ተከታዮች “ዐቢይ ሌባ” ሲሉ የዐቢይ ደጋፊዎች “ጀዋር ሌባ” የሚል መፈክር ሲያስተጋቡ ነበር፡፡ የአንዱ ተከታይ አቃጥላለሁ ሲል የሌላው ደጋፊ አታቃጥሉም ሲልም ታይቷል፡፡ በዚህ መሀል ነፍስ ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ሥራ ተስተጓጉሏል፡፡ ሰዎቹ ግን ጉልበት ተፈታተሹ!
ሁላችንም እንደምናውቀው በአንድ የንብ ቀፎ ውስጥ ሁለት፣ ሦስት አውራ ሊኖር አይችልም:: ሀገሪቱ ያላት የጠቅላይ ሚኒስትርነት የሥራ መደብ አንድ ነው፡፡ የታሪክ አጋጣሚ ይህንን እድል ለዶ/ር ዐቢይ ሰጥቷቸዋል፡፡ ሌሎቻችን የዶ/ር ዐቢይን ጠቅላይ ሚኒስትርነት አምነን መቀበል የውዴታ ግዴታችን ሊሆን ይገባል፡፡ “የኦሮሞ ህዝብ የሚሰማው እኔን ነው” በሚል መንፈስ መታበይና አላስፈላጊ ንቅናቄ መፍጠር ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ “የሚሰማን፣ አምኖ የሚቀበለን፣ መሪዬ ነህ የሚለን” እኛን ነው የምንል ከሆነ፣ በምርጫ አረጋግጠን የምንመኘውን ጠቅላይ ሚኒስተርነትም ይሁን ሌላ ስልጣን መጨበጥ ከሰለጠነ ሰው የሚጠበቅ የሰለጠነ መንገድ ነው:: ልሂቃኑ ይህንን የማይቀበሉ ከሆነ፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን (በዘመነ መሳፍንት) ይደረግ እንደነበረው አንዱን ሰው “ካነገስን” በኋላ ሌሎቹን “ልዑላን አልጋ ወራሾች” ወደ አምባ ግሸን መውሰድ የግድ ሊሆን ነው፡፡
ጽሁፌን የማጠቃልለው በልጅነት እድሜዬ እረኞች ሲያቀነቅኗት በሰማኋት አንዲት ግጥም ነው፡፡ በሰሜን ወሎ፣ በቀድሞው አጠራር በየጁ አውራጃ “አባተ ኃይሉ” የተባለ ሽፍታ ነበር:: የዚህ ሽፍታ ኃይለኛነት በህብረተሰቡ ዘንድ ተጋኖ ይነገር ነበር፡፡ እናም የየጁ እረኞች እንዲህ ብለው ገጠሙ፡-
“እንደ እንጀራው መስሎህ እንደ ቆሪው ፍትፍት፣
እንደ እሳት ይፋጃል ያባተ ኃይሉ ፊት”
ኢትዮጵያን የመምራት ህልም ሊኖረን ይችላል፡፡ ይሄ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን ህዝብ መምራትና ማስተዳደር እንደ “ቆሪው ፍትፍት” በአስር ጣታችን እየዛቅን የምንሰለቅጠው ዓይነት ተራ ነገር አይደለም፡፡ አበው “አታሞ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር” እንዲሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ስልጣን ከርቀት ሲያዩት የሚያማልል፣ ሲጨብጡት ግን የሚያደነጋግር መሆኑን ጭምር ማስተዋሉ መልካም ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል::


Read 8675 times