Print this page
Saturday, 26 October 2019 12:14

አቶ ጃዋር ስለ ሰሞኑ ግጭት ምን ይላሉ?

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

 - ፌደራል ፖሊስን ተጠያቂ አድርገዋል
              - “ለውጥ ያመጣነው ገድለን ሳይሆን ሞተን ነው”

         የጠ/ሚኒስትሩን የፓርላማ ንግግር ተከትሎ ለሊት ላይ የግል የጥበቃ ሀይሎቹ “ግቢውን ለቃችሁ ውጡ” መባላቸውን የሚናገሩት አክቲቪስትና የኦኤም ኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ዳይሬክተር አቶ ጀዋር መሐመድ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ “የፌደራል ፖሊስ አባላት ጠባቂዎቼን አንስቷል፤ ለህይወቴ ያሰጋኛል” ብለው ባስተላለፉት የድረሱልኝ ጥሪ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎችና በአዲስ አበባ በርካታ ወጣቶች ህይወታቸውን አጥተዋል ለጉዳት ተዳርገዋል፤ ንብረቶችም ወድመዋል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሠላም ገረመው ከአቶ ጀዋር ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡

             በተለያዩ ሚዲያዎች የመለሱት ቢሆንም እስቲ ከፌደራል ፖሊስ ጋር ስለተፈጠረው ችግር ያስረዱኝ?
እኩለ ሌሊት ላይ ሁለት የፌደራል ፖሊስ ተሽከርካሪዎች ቤቴ መጡ፡፡ የፌደራል ፖሊሶቹን እናውቃቸዋለን፡፡ ለእኔ የተመደቡትን የጥበቃ አባላት “እቃችሁን ይዛችሁ ውጡ፤ ታዛችኋል” አሏቸው፡፡ እነሱም “አንደኛ፤ በዚህ ለሌሊት ለምን እንወጣለን? ሁለተኛ እኛን የሚተካ ሃይል  የታለ?” ብለው ሲጠይቁ፤ “ይሄ እናንተን አያገባችሁም፤ ልቀቁና ውጡ” ተባሉ፡፡ “እሺ መጀመሪያ ለእሱ እንንገረው” አሉ፤ “ለእሱ መንገር አያስፈልግም፤ ዝም ብላችሁ እቃችሁን ይዛችሁ ውጡ” አሏቸው:: በዚህ ጊዜም በተሽከርካሪ ከመጡት ጋር ቀድሞ ቢተዋወቁም “እውነት ትዕዛዝ ወስደው ነው ወይ” የሚል ጥርጣሬ አደረባቸው፡፡ እናም ለዋናው አዛዥ ደወሉለት፡፡ ኮማንደሩም ትዕዛዙን ደገመላቸው፡፡ “በአስቸኳይ ውጡ” አላቸው፡፡ አሁንም ደግመው በሌላ ስልክ ደወሉለትና በቴፕ ቀዱት፡፡ ቀጥለው እኔን ቀሰቀሱኝ፡፡ መጀመሪያ ላይ እርስ በእርስ ያልተግባቡ ነበር የመሰለኝ፡፡ ነገሩ ሌላ መሆኑን ሳውቅ፣ እኔም ለኮማንደሩ ደወልኩለት፡፡ ለእኔም ያንኑ ደገመልኝ፡፡ “በዚህ ውድቅት ሜሊት ጥበቃ ማንሳት አግባብ ነው ወይ? ስለው አንገራገረ:: “ተተኪ አላካችሁም፤ ጥበቃ ለማንሳት ከሆነ ደግሞ ለምን በቀን አላደረጋችሁትም? ለምን ለእኔ አላሳወቃችሁኝም?” አልኩት፡፡ “እኔ አንድ ደሀ ወታደር ነኝ፤  ከአንድ ሰአት በፊት፤ ኢሳቅ ከሚባል አለቃዬ ነው ትዕዛዝ የደረሰኝ አለኝ:: “እስከ ጠዋት ቢቆዩስ?” ስለው “አይቻልም፤ አሁን ነው መውጣት ያለባቸው” አለ፡፡ በጥያቄ ሳጣድፈው ትንሽ ረገብ አለ፡፡ የሆነ ችግር እንዳለ ተረዳን፡፡ ለተለያዩ የመንግሥት ባለስልጣናትና የሴኩሪቲ ኃላፊዎች ደወልኩ፡፡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርና ምክትሉ አያነሱም:: ስሙን መጥቀስ ለማልፈልገው ባለስልጣን ደወልኩና እንዲደወልላቸው ነገርኩት፡፡ ለም/ኮሚሽነሩ ደወለለት፡፡ ም/ኮሚሽነሩም ትዕዛዝ እንደተሰጠና ጥበቃው እንዲነሳ እንደተወሰነ ነገረው፡፡ በዚህ ሰአት የበለጠ ግር አለኝ፡፡ ጠባቂ አባላቱም “አንሄድም” አሉ፡፡ ለሚኒስትሮችና ለደህንነት ሰዎች ደወልኩ፡፡ በአገሪቱ ላይ ምን እየተካሄደ ነው ብዬ ተጠራጥሬ ብዙ ቦታ ደውያለሁ:: ከዚያም ሦስት አራት ፓትሮል መኪኖች መምጣት ጀመሩ፡፡ ቤተ መንግስት አካባቢ ምንም እንቅስቃሴ እንደሌለ ካጣራሁ በኋላ  ጉዳዩ በሀገር ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን በእኔ ላይ ያነጣጠረ ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ፡፡ የእኛ ልጆች ከመደንገጥና ከመቆጣት የተነሳ በጣም ስሜታዊነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ የመጡትፀም ስናነጋግራቸው የሚሠጡት መልስ ግልጽ አይደለም፡፡ ስለዚህ እንዳይጋጩ ለህዝብ ማሳወቅ አለብኝ ብዬ ፌስቡክ ላይ ፃፍኩ:: በዚህ አካባቢ የኦሮሚያ ፖሊስም ሌሎችም ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡
እርስዎ በፌስቡክ ጥሪ ከማድረግዎ በፊት ቦታው ላይ የደረሱት ወጣቶች መረጃ ከየት አገኙ?
ከተለያየ ቦታ የመጡ፣ እኔ ጋ የሚኖሩ ወጣቶች አሉ፤ እነሱ ይመስሉኛል የተደዋወሉት:: ከዚያም የመጡት ፖሊሶች ወደ ኋላ ተመለሱ፡፡
ጉዳዩ ጠ/ሚኒስትሩ ሰሞኑን በፓርላማ ከተናገሩት ጋር ይያያዛል ብለው ያምናሉ?
ነገሩ ሙሉ በሙሉ እስኪጣራ ድረስ በርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል፡፡ ግን ግንኙነት የለውም ማለት አልችልም፡፡ ምክንያቱም የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ያልተጠበቀ ነበር:: ንግግራቸው ለእኔና ለሚዲያው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ከእሳቸው በፊት የተለያዩ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ስሞታ ሲያቀርቡ ነበር፣ የፓርላማም ጠያቂዋ ያነሱትም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ስለነበር፣ ከተፈጠረው ችግር ጋር ሊያያዝ ይችላል የሚል ጥርጣሬ አለኝ:: መቼም የፌደራል ፖሊስ የሚታዘዘው በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ነው፡፡ ያለ እሳቸው ትዕዛዝ ወደዚህ ይመጣሉ የሚል እምነት የለኝም:: ለምን አደረጉት የሚለው ግልጽ አይደለም:: እሳቸው ሳያውቁ የተደረገ ከሆነም የተሳሳተ ኦፕሬሽን ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ዛቻውን በተጨባጭ እርምጃ ለማስደገፍ ጠ/ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ሰጥተው ሊሆን ይችላል፡፡ አለበለዚያ ደግሞ የደህንነት ሃይሎች በራሳቸው ተነሳስተው ሊሆንም ይችላል፡፡ እርግጠኛ መሆን አልችልም፤ ግን ግንኙነት እንዳለው ይታየኛል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በሰጡት መግለጫ፤ እርስዎ የሚሉት ነገር እንዳልተፈፀመ ተናግረዋል…
ኮሚሽነሩ ዋሽተዋል፡፡ ነጭ ውሸት ነው የዋሹት፡፡ ማስመሰልም አልፈልግም፡፡ አዲስ አይደለሁም፤ አብሬያቸው ስሠራ ነበር::  ከሳቸው በፊት ሁለት ኮሚሽነሮች ነበሩ፤ ከእነሱም ጋ በቅርበት ስሰራ ነበር፡፡ አይደለም ያለውን ጥበቃ ሲለውጡ፣ በከተማ ውስጥ ችግር ሲኖር ይነገሩኛል፡፡
እንኳን የሊሊት ቀርቶ በቀን አዲስ ልጆች ቢቀየሩ መደናገር ይፈጥራል ኮማንደሮቹ እዚህ ድረስ እየመጡ ስለ ሀገር ሁኔታ… ስለ ደህንነት የምናወራበት ጊዜ አለ፡፡ በዚያ ሌሊት እዚህ አገር ውስጥ ተደርጐ የማይታወቅ… ያለ አንዳች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለጃዋር አትንገሩት ብሎ ማዘዝ ብዙ ጥርጣሬ ይፈጥራል፡፡ ኮሚሽነሩ ወይ የሴራው አቀነባባሪ ወይም የሴራው አካል ናቸው ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ የተፈጠውን ችግር ለማሳነስ ሞክረዋል፡፡ በአጠቃላይ ሃላፊነት የጐደለው ሆኖ ነው ያየሁት፡፡ የፌደራል ፖሊስ አንዱ የአገራችን የደህንነት ተቋም ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ቅጥፈት በጣም ነው የሚያሳዝነው፡፡
አሁን ችግሩ መፍትሔ አግኝቷል?
ምንም የተገኘ መፍትሔ የለም፡፡ ጥበቃዎቹም አንሄድም ብለዋል አሉ፡፡ ሁሉም ነገር እንደተንጠለጠለ ነው፡፡ ኮሚሽነሩ ማወቅ ያለባቸው ፖሊስ የግል ሀብት አይደለም:: የህዝብና የመንግስት ነው፡፡ በፈለጉ ጊዜ እናነሳለን የሚሉት አይደለም፡፡ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት አንተ ላይ አለ” ብለው ጥበቃ የመደቡት እነሱ ናቸው፡፡ ኮሚሽነሩ ለህዝብ  “በጃዋር ላይ ምንም የሚያሠጋ ነገር የለም” ማለት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ከሁለት ሳምንት በፊት “በጣም ከፍተኛ ስጋት አለ፤ ተጠንቀቅ ጉዞህን ቀንስ” ብለው መክረውኛል፡፡ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሠማይና ምድር ካልተገለበጠ በስተቀር ጥበቃውን ማንሳት የለባቸውም፡፡
በምርጫ የመሳተፍ ሃሳብ አለዎት እንዴ?
እያሰብኩ ነው፡፡
በሁለት ዜግነት በምርጫ መሳተፍ ይቻላል?
እኔ ወደ እዚህ አገር ስገባ ወስኜ አሜሪካ በቃኝ፣ ሀገሬ ገብቼ ባለኝ እውቀትና በተረፈችኝ ጊዜ ህዝቤን አገለግላለሁ ብዬ ነው፡፡ ለእኔ የፓስፖርት ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ መምጣቱ አስቂኝ ነው፡፡ ተገድጄ ነው ዜግነት የወሰድኩት:: እስከ 2014 እ.ኤ.አ ድረስ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ነው የነበረኝ:: አሳድሱልኝ ብዬ ስልክ ፓስፖርቴን ያዙና “ና” አሉኝ:: እንደ ከማል ካሾጊ ቀብ ሊያደርጉኝ ነበር መሰለኝ! እኔን “ና” ማለት ለምን አስፈለገ ብዬ ጠፋሁባቸው፡፡ በወቅቱ ባለቤቴ አሜሪካዊት ስለነበረች ዜግነት ወሰድኩ፡፡ የተገፈፍኩትን ዜግነት ዛሬ እንደ አጀንዳ ማንሳት ያስቃል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ካሉት ሠራተኞች ከሀምሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት  የውጭ ዜግነት ነው ያላቸው:: የፕሬስ ሴክሬተሪያቷን ጨምሮ አብዛኛው የውጭ ዜግነት የወሰደው የአገሪቱን ዜግነት ጠልቶ አይደለም፡፡ ከዚህ አገር ተገፍተው ተቸግረው የሱማሌያ፣ የሱዳንን የፀኤርትራ ፓስፖርት የወሰዱ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ የዜግነት ጉዳይ ላይ በመጀመሪያ ስጽፍ የነበርኩት እኔ ነኝ:: የዜግነት ጉዳይ መፈታት አለበት፣ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሊታሰብበት ይገባል ብዬ የፃፍኩት ገና እዚህ ሳልመጣ ነው፡፡ እኔ ከእንግዲህ አገሬ ገብቻለሁ፡፡ የውጪ ሀገር ዜግነት አያስፈልገኝም:: ቢብስ ቢብስ ለቪዛ መሠለፍ ነው እንጂ፡፡
“ጀዋር የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ ነው” ተብሎ የተዘገበው አነጋጋሪ ሆኗል…  
ይሄ ውሸት ነው፡፡ እኔ ምክር ለሚፈልግ ሁሉ እመክራለሁ፡፡  ዜናውን ሮይተርስ ነበር የሠራው:: ግን ውሸት ነው ብዬ አስተካክለውታል፡፡
ከእርስዎ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ተቃውሞና ግጭት በርካታ ወጣቶች ሞተዋል፤ ንብረት ወድሟል፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂው ማን ነው?
ሀላፊነቱን የሚወስደው የፌደራል ፖሊስ ነው፡፡ ከመጀመሪያውም ያልታሰበበትና ኃላፊነት የጐደለው እርምጃ ነው ህዝቡን አስቆጥቶ ወደዚህ ያስገባው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ድሮ እኔ ህዝቡን “ታገሉ መንገድ ዝጉ” ስል ከርሜያለሁ፤ ዛሬ ግን ያ የለም፡፡ እኔ እስካሁን መንግስት አደረገው ለማለት ይከብደኛል፡፡ እኔ ወንጀል ከሰራሁና እኔን ማሰር ከፈለጉ ኮሚሽነሩ በቀጥታ ቢጠሩኝ እሄድ ነበር፤ ምንም ችግር የለውም፡፡ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣናት ሲጠሩኝ፤ ልጐርሰው ያዘጋጀሁትን እንጀራ ጥዬ ነው የምሄደው፡፡ ሽፍታ አይደለሁም፡፡ እኔ ጋ ያሉት ደግሞ የመንግስት ፖሊሶች ናቸው፡፡ አምጡት ቢባሉ አፈፍ አድርገው ይወስዱኛል፡፡ ስለዚህ በውድቅት ሌሊት ለማሰርም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ያንን ማድረግ አልነበረባቸውም፡፡ በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ ኃላፊነት የሚወስደው መቶ በመቶ ፌደራል ፖሊስ ነው፡፡
ተቃውሞውን ተከትሎ የተፈጠረውን ግጭትና ሁከት ለማረጋጋት እርስዎ ምን አደረጉ?
ወጣቶች እንዲረጋጉ… የማንም ንብረት እንዳያጠፉ… ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳያደርሱ፣ በብሔርም ሆነ በሃይማኖት ግጭት እንዳይነሳ… ፍፁም ሠላማዊና ጨዋ እንዲሆኑ ስንወተውት ነበር፡፡ ከሽማግሌዎችና ከፖለቲካ መሪዎች ጋር በመሆን የተጐዱትን እንዲረዱ፣ የወደሙ ንብረቶችን እንዲጠግኑ ጥሪ አድርገናል፡፡
“አቶ ጃዋር ግርግር ይወዳሉ፣ በመግደል ለውጥ ይመጣል” ብለው ያምናሉ ይባላል…
እንደዚህ ብለው የሚከሱኝ አብረውኝ ዋሽንግተን የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ሠላማዊ ትግል ካልሆነ ሌላ አይጠቅምም ስላቸው አይሆንም ኤርትራ ሄደን ታጥቀን መገልበጥ አለብን” ሲሉ የነበሩ ናቸው፡፡ የአገራችንን የትግል ሁኔታ በተመለከተ ባላጠናም፣ በህንድና በባልካን አገሮች ሄጄ ባጠናሁት መሰረት፤  ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው የትጥቅ ትግል ሳይሆን ሠላማዊ ትግል ነው፡፡ ይሄንን ለውጥ ያመጣነው ገለን አይደለም፤ ሞተን ነው፡፡ አንድ ሰው መግደል አልፈልግም፡፡ አንድ ሰው እንዲሞት አልፈልግም፡፡ አንድም የእኔ ባላንጣ ሆነ ወዳጅ ከሚሞት፣ እኔ ሞቼ የህዝብን ጥቅም ማስቀደም እፈልጋለሁ፡፡
እኔ ሞቼ ለውጥ ማምጣት እፈልጋለሁ እንጂ ሌላው ሞቶ ለውጥ እንዲመጣ አልፈልግም፡፡ በመግደል ለውጥ ቢመጣ ኖሮ የህወሓት አገዛዝ ይቆይ ነበር፡፡ አሜሪካ ሳለሁ፣ ስለ ሠላማዊ ትግል ሳስተምር፣ መጽሐፍ ሳከፋፍል ስለነበር፣ “ቄሱ” የሚል ቅጽል ስም ነበረኝ፡፡

Read 5570 times