Saturday, 26 October 2019 12:12

“በሃሳብ ላይ የተገነባ ማህበረሰብ ወዴትም ሊፈርስ አይችልም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 ራሱን “እኔ ሰው ነኝ” ብሎ የሚገልፀው የፍልስፍና ምሁሩ ወጣት ዮናስ ዘውዴ፤ በአሁኑ ወቅት በፍልስፍና የዶክትሬት ድግሪውን እየሠራ ይገኛል፡፡ ከደብረብርሃን መምህራን ኮሌጅ በመምህርነት፣ በከፍተኛ ዲፕሎማ የተረመቀው ዮናስ፤ በሶሲዮሎጂና ሶሻል ወርክስ ከጅማ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል:: ከኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂ ኮሌጅ የመጀመሪያ ድግሪ በቲዎሎጂ ያገኘ ሲሆን፤ እዚያው ኮሌጅ ውስጥ በሆልስቲክ ዴቨሎፕመንት ማስተርሱን ይዟል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ሁለተኛ ድግሪውን በፍልስፍና አግኝቷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨሲቲ በፍልስፍና ፔኤችዲውን ለማግኘት እያጠና ያለው ዮናስ፤ በኢትዮጵያን ግራጁዌት ስኩል ኦፍ ቲዎሎጂ በስልታዊ ነገረ መለኮት ሦስተኛ ማስተርሱንም ዘንድሮ ያጠናቅቃል፡፡
ዮናስ በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት አገልግሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ የልዩ ጽ/ቤት ባለሙያ ሆኖ እየሠራ ይገኛል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን “መደመር” መጽሐፍ ከሚተነትኑና እሣቤውን በጥልቀት ከተረዱ ምሁራን አንዱ ነው፡፡ በየመድረኩም ስለ እሣቤው ትንታኔ በመስጠት ይታወቃል:: የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከወጣቱ ምሁር ዮናስ ዘውዴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡   


            “ሔምሎክ” የተሰኘ የፍልስፍና መጽሐፍህ ከሰሞኑ ለንባብ በቅቷል፡፡ መጽሐፉን ለምን “ሔምሎክ” የሚል ርዕስ ሰጠኸው?
ሔምሎክ የተባለበት ዋናው ምክንያት ስቅራጥስ የሞተበትን ምክንያት ለማንሳት ነው:: ሶቅራጥስ የሞተው ሔምሎክ ከተሰኘው መርዛማ ተክል የተቀመመ ሻይ ጠጥቶ ነው። ሞት የተፈረደበት ደግሞ በቀረቡበት ሁለት ክሶች መነሻ ነበር። የመጀመሪያው ክስ አማልክቶቻችንን ወጣቶቹ እንዳያመልኩ አድርገሃል የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የወጣቶችን አስተሳሰብ በርዘሃል በሚል ነው፡፡ ያንን ሁሉ ያደረገው ግን በመጠየቅና በመርመር ነበር፡፡ ሊቅ ነን የሚሉ ሰዎችን “ይሄ ምንድን ነው? ያ ምንድነው?” እያለ ሲጠይቃቸው፣ ለጥያቄው ምላሽ አይሰጡትም ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ሁሉም አለማወቃቸውን አወቀ፡፡ እነሱ አለማወቃቸውን አያውቁም ነበር። እሱ ግን አለማወቁን አወቀ:: አለማወቄን ነው የማውቀው አለ፡፡ ሕይወት መፈተሽ መበርበር አለባት ይላል -  ስቅራጠስ። በተመሰረተበት ክስም ለፍርድ ቀረበ፡፡ አምስት መቶ ዳኞች ፊት ቀረበ፡፡ ሀሳቡን አስረዳ፡፡ “እኔ እየጠየቅሁ ነው፤ መልስ ግን አላገኘሁም” አላቸው፡፡ “በል አሁን ሀሳብህን ቀይር” አሉት፡፡ እሱም በሀሳቡ ፀና፡፡ እውነት እንዳወራ ተወልጃለሁ፤ ሃሳቤን አልቀይርም፤ ጥያቄ እየጠየቅሁ ነው ግን አትመልሱልኝም” አላቸው፡፡ እነሱም የሞት ፍርድ ፈረዱበት ማለት ነው፡፡ ከአምስት መቶዎቹ ዳኞች 280 ያህሉ በድምፅ ብልጫ ወሰኑበት፡፡ ስለዚህ ሀሳብን በሀሳብ ከመሞገት ይልቅ በቁጥር ብልጫ የሚጋተውን መርዝ አቀረቡለት፡፡ ያንን ጽዋ ስቅራጦስ በደስታ  ጨለጠው፡፡ ሞትን አልፈራም፡፡ ሀሳብ ምን ያክል ዋጋ ያስከፍላል? የሚለውን ለማንሳት ፈልጌ ነው መጽሐፌን “ሔምሎክ” ያልኩት፡፡
ሀሳብ ጥሩ ስለሆነ ብቻ አይደለም፤ ማህበረሰቡ ከተቀበለው ነው ዋጋ የሚኖረው:: ምንም ያህል ሀሳቡ ቆንጆ ቢሆን እንኳ ማህበረሰቡ እስካልተቀበለው ድረስ ዋጋ የለውም፡፡ ሀሳባውያን በነበሩበት ዘመን ጭምር አይፈለጉም ነበር፡፡ ካለፉ በኋላ ነው የሚወሱት:: ዛሬ ሶቅራጠስ ካለፈ በኋላ እናወሳዋለን፡፡ ዛሬ ለግሪክ ትልቅ ነው። ትዕምርታቸው ሆኗል:: በወቅቱ ግን አልተቀበሉትም ነበር፡፡ ስለዚህ ሀሳብ ጎሽ ብሎ ሊያጨበጭብላት የሚችል ብቻ ሳይሆን ሊወግራት ድንጋይ የሚያነሳም እንዳለ ለማመላከት ነው፡፡
በአሁን ዘመን ሀሳብና ሀሳባውያን በማህበረሰባችን ውስጥ ያላቸው ቦታ ምን ይመስላል?
በኔ ምልከታ አሁን ብዙ ሀሳባውያን (thinkers) ያሉን አይመስለኝም፡፡ ሀሳባውያን ናቸው የጎደሉን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምንም እንኳ የሰው ልጅ ባዶ ሆኖ ባያውቅም፡፡ ግን ደግሞ ሀሳብ ስንል፤ ሃሳብ በጎም ያልሆነም ውጤት አለው። የሀሳብ ውጤት አይለወጥም፤ ሊለወጥ የሚችለው ሀሳብ ነው፡፡ በኛ አገር ውስጥ ብዙ አይደሉም ግን ሀሳብ ያላቸው ሀሳባውያን እንዳሉ እርግጥ ነው። ግን የሀሳብ ድርቀት እንዳለብን ፖለቲካውን መመልከቱ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡ ኢኮኖሚያችንን፣ ማህበራዊ ትስስራችንንና የማህበራዊ ትስስር ገፆቻችንን መመልከትም በቂ ይመስለኛል፡፡ የሀሳብ ድህነታችን ጥልቅ ስብራታችንም የከፋ መሆኑን ማሳያው ይኸው የፖለቲካ ትኩሳታችን ነው። ታሪካችን ብዙ ጊዜ በተመሳሳይ ነገር የታጠረ ነው፡፡ እኔም ልጄም የኔ አያትም በተመሳሳይ የግብርና ዘዴ ነው የምንጠቀመው፤ ከቀድሞው እልፍ አላልንም፡፡ ከአውሮፓም ሆነ ከአሜሪካ ኮርጀን ያመጣናቸው ርዕዮተ አለሞችም አላሻገሩንም፤ ስለዚህ በጐ በጐውን እንመኛለን ግን አልተሳካልንም፡፡ እኛ ፍሬውን እንጂ ፍሬው የሚበቅልበትን ስሩን አፈሩን አንፈልገውም፤ ውሃውን እንጂ ውሃው የመጣበትን ምንጭ አናማትርም እና የሃሳብ ድርቀት እንዳለብን በግልጽ እያየን ነው፡፡ በሃሳብ ችግራችንን ከመፍታት ይልቅ በጠመንጃ አፈሙዝ በመነጋገር፣ በጉልበት መንገድ የመዝጋት፣ ንብረት በማቃጠል ለመነጋገር እየሞከርን ነው:: የሃሳብ ብርታት ቢገባን ግን የሰው አሸናፊ አይኖርም ነበር፡፡ የሃሳብ አሸናፊነት ቢገባን ኖሮ ተወያይተን ስንጨርስ ተጨባብጠን እንሄድ ነበር፡፡
በኛ ሀገር ግን “ማን አለ” እንጂ “ምን ተባለ” አይባልም፡፡ ይሄም የሃሳብ ድርቀታችንን ማሳያ ነው፡፡ ማንም ይበለው ማንም ጠቃሚና አሻጋሪ ሃሳብ ከሆነ፣ ሃሳቡ ላይ ነው ማተኮር የነበረብን:: አሁን ግን ማን አለው የሚል ጥያቄ ነው የሚቀድመው፡፡ በዚህ ምክንያት ከሃሳብ ሃዲድ ውጪ ወድቀናል ብዬ ነው የማስበው፡፡
ለተናገረው ሳይሆን ለሃሳቡ ትኩረት የማንሰጠው ለምን ይመስልሃል?
ይሄ ብዙ ጥናት ይጠይቃል፤ ነገር ግን እንደ አንድ እዚህ ሀገር ተዘርቶ እንደ በቀለ ሰው ምልከታዎቼ የሚነግሩኝ፤ ሃሳቦቻችን ብቻ ሳይሆን የችግሮቻችን አይነት ብዙዎች ናቸው:: መፍትሔውም ብዙ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ትምህርት ብቻ ነው መፍትሔው ብዬ አላስብም፤ ወይም ፖለቲካው አሊያም ኢኮኖሚው ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ የለኝም፡፡ እያንዳንዳቸው የተጋመዱ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዱ አንዱ ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡
ተጠያቂውም ሁላችንም ነን ብዬ ነው የማምነው፡፡ በዚህ መሃል የአንበሳውን ድርሻም የሚወስዱ ይኖራሉ፡፡ መንግስት አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም መንግስታት ወደ ቤተ መንግስት ሲገቡ ብዙውን ነገር መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ የሃይማኖት ተቋማትና መምህራን፣ ሚዲያዎች፣ ቤተሰብ፣ የትምህርት ፖሊሲዎቻችን፣ ሽማግሌዎች፣ ዳያስፖራዎች ከያንያን ሁሉ የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ይሄን ትውልድ በበጐ በመገንባትም ሆነ በተቃራኒው የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ትልቁ መፍትሔ የሚመጣው ብዙዎቹ እጃቸውና አዕምሮአቸው ሲፈወስ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በዚህ ዘመን ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ሃሳባቸው የነጠረ ኢትዮጵያውያን ወዴት አሉ? ሃሳብና ሃሳባውያን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ምንም ተፅዕኖ አላሳደሩም ማለት ነው?
በኔ ምልከታ ሃሳባውያን ተወግደው ነው የከረሙት ወይም በየራሳቸው ምሽግ ተከተው ነው የሚኖሩት፡፡ ወይም ደግሞ እዚያው በትምህርት አካዳሚያቸው ነው የሚነጋገሩት የሚወያዩት እንጂ ለብዙኃኑ አይደርሱም:: የእነሱን ሃሳብ የሚያውቀው ከእነሱ ጋር የተነጋገረ ወይም በነሱ ደረጃ ያለ ብቻ ነው:: ሃሳባቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ አናየውም፡፡ በርግጥ አሉ ግን ጥቂት ናቸው፤ መጫወቻቸውም ቢሆን በራሳቸው ሜዳ ውስጥ ብቻ ተቀንብቦ ቀርቷል፡፡
ግን እንዴት በቁጥር ጥቂት ሊሆኑ ቻሉ? ሃሳባውያን ያልበረከቱበት ምክንያት ምንድን ነው?
ብዙ ሰዎች ማለትም መሪዎቻቸውን በሃሳብ ፊት ለፊት የሞገቱ ሰዎች ምን ሆኑ? የሚለውን ጥያቄ ማሰብ ነው ወደዚህ መልስ የሚወስደን፡፡ ብዙዎቹ እኮ ተሰደዋል፣ ታስረዋል፣ በአደባባይ ተረሽነዋል፣ አንዳንዶቹ የት እንደደረሱ እንኳ አይታወቁም፡፡ የሃሳብን ጉልበት እኛ ገና አልተረዳነውም፡፡ እከሌን ያየ በእሣት አይጫወትም ስለሚባል ይመስለኛል:: ጥቂት ሃሳባውያን ምሽጐቻቸው ውስጥ ሆነው የሚተኩሱት እንጂ ወደ አደባባይ ላይ ቢመጡና ለሃሳብ ቦታ ቢሰጠው የተሻለ ይሆን ነበር:: በሃሳብ ላይ የተሠራ ማህበረሰብ ወዴትም ሊፈርስ አይችልም፡፡
መጽሐፍት የገነቡትን ማህበረሰብ ማንም አያፈርሰውም፡፡ እነዚህ ሃሳባውያን ሜዳው ቢፈቀድላቸውና ደህንነታቸው ቢረጋገጥላቸው አደባባይ ይወጡ ነበር፡፡ የትኛውም ነገራችን የሃሳብ ውጤት ነው፡፡ ግን ሃሳብን ሊሸከም የማይችል፣ የሚያረግርግ ማህበረሰብ የፈጠርነው እኛው ነን፡፡ ለዘመናት በራሳችን ምህዋር ብቻ ተከበን ስለኖርን ነው ይሄ የሆነው:: ከኛ ሀገር ውጪ ጥሩ አውሮፕላን ማረፊያ ያለ አይመስለንም፤ ከኛ ሀገር ውጪ ሌሎች ጀግኖች እንዳሉ አናውቅም፤ ወደ ውጪ ስንወጣ ነው ይሄ የሚታየን፡፡
በማህበረሰባችን ውስጥ በጐ እሣቤ እንዴት ነው መበልፀግ የሚችለው?
በመጀመሪያ ጥያቄው በጐ እሣቤን እንዴት እናመጣዋለን? ወይም እንዴት እናዳብረዋለን? ሳይሆን እንፈልገዋለን ወይ? የሚለው ነው:: ለሃሳብ ድንጉጦች ነን፡፡ በጐነት በኛ ሀገር አያሸልም፡፡ አሁን አንተ እንደ ጋዜጠኛ በጐ ነገር ብትጽፍ አያሸልምህም፡፡ ለምን ተብሎ ከተጠየቀ አስተሳሰባችንና አመለካከታችን እኩዩን ናፋቂ እንዲሆን ተደርገናል፡፡ አሁን ጥሩ ዜና የሚባለው እኮ መጥፎ ድርጊት ነው፡፡
ሰው ሲብጠለጠል ሲሰደብ ነው ጆሮና ልባችንን የሚነዝረው፡፡ ግን ይሄ አያዋጣም፡፡ በመጀመሪያ ምክክር፣ የሃሳብ ብዙሃነትን የበለጠ ማበራከት ነው የተሻለ ለውጥ የሚያመጣው:: መቼም ስለ ሃሳብና ምክክር አስፈላጊነት ከኛ በላይ የተነገረው የለም፡፡ ግን መልሰን መላልሰን እዚያው ነን፡፡ በኔ ምልከታ፤ ይሄ የሆነው የገነባነው በውሸት ምልከታ በመሆኑ ነው:: ተረቶቻችን አንዳንዶቹ የውሸቶች ናቸው፡፡ ስነቃሎቻችን አንዳንዶቹ ውሸት ናቸው፡፡ እንግዳ ተቀባይ ነን ይባላል ግን ሲፈተሽ አይደለንም፡፡ ጀግኖች ነን ይባላል ግን ሲፈተሽ ጀግንነታችን ለጠላቶቻችን ብቻ ሳይሆን ለገዛ ወንድማችንም ነው ይሄ ደግሞ ገሎ እስከ መፎከር የሚዘልቅ ነው፡፡ የተገነባንበት እነዚህ ትርክቶች በሚገባ መፈተሽ እንዳለባቸው እገነዘባለሁ፡፡ በሌላ በኩል ታሪኮቻችንም መፈተሽ አለባቸው፡፡ የጋራ ግብ የለንም፡፡ በብዙ ነገር ላይ መስማማት ላይጠበቅብን ይችላል፡፡ የጋራ ግብ ካለን ግን በጋራ ግቦቻችን ላይ መስማማት ይቻላል፡፡ አሁን ግን አላማ ያለን አይመስለኝም፡፡
እንዴት ነው በታሪክ ላይ ተግባብተንና የጋራ አላማ ይዘን ወደፊት መቀጠል የምንችለው ትላለህ?
በመጀመሪያ መነጋገር ነው፤ በሃሳብ ላይ መወያየት፡፡ ለሃሳብ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ምህዳሩን ባሠፋነው ቁጥር አንዳንዱ አሁን የያዘውን ነዳጅ ጨርሶ፣ ውስጡ ምንም ላይኖረው ይችላል፡፡ በዚያው ልክ ጥሩ ሰብዕናና ሃሳብ ያለው ሰው ደግሞ ወደፊት ማሻገር ይችላል ማለት ነው፡፡ ትናንትን ማንም መመለስ አይችልም፡፡ እኔ ትናንት አልነበርኩም፤ ዛሬ አለሁ፡፡ እኛ እኮ እንኳን ትናንት፣ ዛሬም እያግባባን አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ሳንግባባ ስለ ትናንትና እንግባባለን ማለት አይቻልም፡፡ በነገ ላይ ራሱ ላንግባባ እንችላለን:: ይሄ የሆነው የሃሳብ ድርቀት ስላለ ነው፡፡ እሱ የሚመጣው ደግሞ በመወያየት በመነጋገር ነው:: ትናንት በጐ የነበሩትን ማስቀጠል፣ ማስፋት፣ ማሰባሰብ፤ ትናንት መጥፎ የነበሩ ነገሮችን ደግሞ ዛሬ እንዳይደገም ማረም መቻል አለብን:: ብዙውን ጊዜ ግን መግባባት ስለማንፈልግ ነው የማንግባባው፤ ንቃተ ህሊናችን እያደገ ሲመጣ እውቀት ሲጐለብት ማሻሻል የምንችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ታሪክ የሚፃፈው ሁሌም በአሸናፊ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ታሪክ በተለያየ መንገድ ሊፃፍ ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ልቦለዶች ናቸው እስክንል ድረስ ልዩ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ አሁን ከእገሌ ጋር ለመጣላት ሲፈለግ የሚመዘዙ የታሪክ ካርዶች አሉ፡፡ እነዚህን ይዘን መቼም ልንግባባ አንችልም፡፡
ብሔራዊ እርቅና መግባባት መፍትሔ ሊሆኑ አይችሉም?
ብሔራዊ እርቅና መግባባት በጐ እሣቤዎች ናቸው፤ አስፈላጊም ናቸው፡፡ ምንጫቸውም በጐ እሣቤ ነው፡፡ ግን እንደምንጠጣው ውሃ ዝም ብለን የምንጠጣቸው ነገሮች አይደሉም፡፡ ብሔራዊ እርቅና መግባባት ሲባል፣ መጀመሪያ ምን ሆነናል ነው ጥያቄው፡፡ የተጣላ የለም፣ ማን ማንን ነው የሚያስታርቀው? ሲባልም ሰምተናል፡፡ ይሄ ለኔ እውነቱን እያወቅነው አስቀድመን እንደካድነው ነው የሚያመላክተኝ:: ስለዚህ መግባባት በመጀመሪያ የሚያስፈልገው በሃገረ መንግስቱ ግንባታ ላይ ነው፤ በሀገር መንግስቱ ቅቡልነት ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምትባለው ሀገር ላይ ራሱ መግባባት መቻል አለብን፡፡ “ተጣልተናል ወይ?” ለኔ መልሱ፤ አዎ! ነው፡፡ “ህዝብ ህዝብን ጨቁናል ወይ” ለእኔ - አይመስለኝም፡፡ ህዝብ ህዝብን መግደሉን ማጥፋቱን አላውቅም፤ ነገር ግን ከዚያ ህዝብ የወጡ ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታወቃል:: ስለዚህ ከዳህጣኑ ተነስቶ ብዙኃኑን መፈረጅ ተገቢ አይሆንም፡፡ እርቁ እንዴት ይመጣል? ከተባለ፤ በዳይ፣ ተበዳይ፣ እውነት፣ ፍትህ፣ ርትዕ የሚባሉት ነገሮች በሚገባ መፈተሽ አለባቸው፡፡ በዳይ “በድዬሃለሁ…ይሄን…ይሄን አድርጌሀለሁ…” ሲል ነው እውነት በመካከሉ የሚወጣው፡፡ እውነቱ ከወጣ በኋላ የተጐዳው ሰው ይቅርታ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ የተበደለው ሰው ራሱ ነው ይቅርታ ማድረግ የሚችለው፡፡ በተበደለው ሰው ስም ይቅርታ ማድረግ ግን አይቻልም የሚል እሣቤ ነው ያለኝ፡፡ ይሄ እስካልሆነ ድረስ ሁሉ ነገር እዚያው ነው የሚሽከረክረው፡፡ በኔ እሣቤ፤ እርቅ የሚባለው ነገር የሚሳካው በዳይ፣ ተበዳይ፣ በደል፣ ካሣ፣ ፍትህና ርትዕ ሲከበር ነው፡፡ ይሄ በሌለበት “ይቅር ብለናችኋል፤ ይቅር በሉን፤ አጥፍተናል ምናምን…” የሚለው ብዙም አያራምደንም፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን በቅርበት እንደሚያውቃቸው ሰው፤ ለሃሳብ የሚሰጡት ቦታ እንዴት ይገለፃ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት አራት መፃሕፍት ጽፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በተለያየ መድረክ ላይ ስናገኛቸው የመፃሕፍት አፍቃሪ ነበሩ፤ የስነ ጽሑፍ ባለሙያም ናቸው፡፡ ስለዚህ ሃሳብን ይወዳሉ ማለት ነው፡፡ በአንደበታቸው የሚናገሩትም ይሄንኑ ነው፡፡ ሃሳብና ሃሳባውያንን ይወዳሉ፡፡ ሃሳብንና ሃሳባውያንን እንደሚወዱ በአካባቢያቸው ያሉ ሃሳባውያን ማሳያ ናቸው:: የቀድሞ መሪዎች፤ ምሁራንንና ሃሳባውያንን በመፈረጅ በመግደል፣ ከዩኒቨርሲቲ በማባረር፣ በአደባባይ በማዋረድ ነበር የሚታወቁት:: እሳቸው ግን በአደባባይ እያከበሩ ነው፡፡ የተባረሩ ምሁራኖችን እየመለሱ፣ ሃሳብ ያስፈልገናል ነው ያሉት፡፡ ሃሳብ ያለውን ሰው “እንኳን ደህና መጣህ” እያሉ እየተቀበሉ ነው፡፡ ይሄ ለኔ መግነጢሳዊ ለውጥ ነው፡፡ ቤተ መንግስት ለዘመናት የታጠረ ማንም የማይገባበት ሥፍራ ነበር፡፡ አሁን ግን አጥሩን ከፍተው “ኑ ሃሳብ ያላችሁ፣ ሃሳብ ፊትሹ” እያሉ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ለሃሳብ ባሪያ  የሆኑ ወይም ሃሳብ ጌታቸው እንዲሆን የፈቀዱ ሰው ናቸው፡፡ ይሄ በተግባርም የሚታይ ነው፡፡
“መደመር” የተሰኘውን መጽሐፍ ጽንሰ ሃሳቦችን በየመድረኩ እየተነተንክ ነው፡፡ የመደመር እሣቤ አዲስ ፈልስፍና ነው ወይስ የነበረው አስፋፍቶ የቀረበ ነው?
አዲስ የተፈጠረ ነገር የለውም፡፡ ለሠሪው ምንም አዲስ ነገር ሊኖረው አይችልም:: ላልሰራው አካል ነው አዲስ የሚሆነው:: መደመር አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በ1964 (እርግጠኛ ባልሆንም) “ኢትዮጵያ በመደመርና በመቀነስ የተሠራች ናት” የሚል ጽሑፍ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ የወጣ ይመስለኛል:: መጽሐፉም መደመር የነበረና የኛው ነው የሚል ነው፡፡ እሣቸውም በተደጋጋሚ የመደመር ባለቤቶቹ እኛው ነን ሲሉ ነው የሚደመጡት:: እኛ ማለት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለንም፤ የሰው ልጅ በሙሉ ማለት ነው፡፡ ከተፈጥሮ ህግና ከዳበረው ባህላዊም ዘመናዊም እሴቶቻችን የመጣ ነው:: በእርግጥ መደመር በኛ ሀገር ሁኔታ የተቃኘ ነው::
ከዚህ ቀደም የነበሩት ከውጭ የመጡ፣ ውጪውን የሚመስሉ ነበሩ፡፡ መደመር ግን ወደ ውስጥ እንመልከት፤ ሀገር በቀል መፍትሔ ያስፈልገናል ነው የሚለው፡፡ ትላንትናዎቻችን ላይ ምንድን ነው ያለን፣ ዛሬ ላይ ምንድን ነው ያለን፣ ነገን እንዴት ነው የምንመለከተው በሚል መነሻ ነው የሚጀምረው፡፡ መደመር የሚነሳው የብቸኝነት ጉድለት አለን ብሎ ነው፡፡ የሰው ልጅ የሚውተረተረው ለምሉዕነት ነው፡፡ ለምሉዕነት ሲውተረተር ደግሞ ብቻውን ምሉዕ መሆን አይችልም፡፡ እያንዳንዳችን ራሳችንን ጠፍጥፈን አልፈጠርንም፡፡ ስንወለድ የመገቡን፣ ያዘሉን፣ ያስተማሩን፣ ያሳደጉን… ወዘተ ሰዎች አሉ፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፡፡ ስሪታችንን (አናቶሚ) እንኳ ስንመለከት፤ ከብዙ ነገሮች መደመር ነው የተገነባነው፡፡ ተፈጥሮ ሁሉ እንደዚያ ነው፡፡ እሣቸው መደመር ብለው ሲያስቡ፡- መሰብሰብ፣ ማከማቸት፣ ማካበት… ከዚያም የብልጽግና ግባችን ላይ መድረስ እንችላለን ነው የሚሉት፡፡ የምንሰበስበው ምንድን ነው? እውቀት፣ ክህሎት፣ ገንዘብ… ያሉንን ነገሮች ነው የምንሰበስበው፡፡ ይህ ማለት ገንዘባችሁን ሰብስባችሁ ለኔ ስጡኝ ማለታቸው አይደለም:: ግን እውቀታችንን እናሰባስብ፣ የየራሳችንን ልዩ ልዩ ክህሎቶች እናሰባስብ ነው የሚሉት:: ለምሣሌ እርቅ በየማህበረሰቡ አለ፡፡ ያንን የእርቅ እሴት ለምን አንሰበስበውም፡፡ ብልጽግና ላይ እንድንደርስ የተሰበሰበ ነገር ያስፈልገናል፡፡ እኔ ብቻ ሳይሆን አንተም ጋ እውቀት፣ ክህሎት፣ ገንዘብ አለ… በጋራ እናዋጣው የሚል እሳቤ ነው፡፡ በኛ ሀገር ቤተ መንግስት የገባ ሰው ነገሮችን ከዜሮ ነው የሚጀምረው፡፡ ይሄ ግን አልጠቀመንም፡፡ ከዜሮ ለምን እንጀምራለን፣ ከዜሮ ከምንጀምር ለምን ያሉንን በጐ ወረቶች አንጠቀምም? የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ… ሁሉም አይነት ወረቶች አሉን፡፡ እነዚያን ወረቶች ለምን አንሰበስብም? ሰብስበን ለምን አናከማችም፡፡ የምንፈልገው ብልጽግና ላይ ለመድረስ መንገዱ ይሄ ነው የሚል ነው መደመር፡፡  በሌላ ቋንቋ፣ አሁን የተበታተነ እውቀት አለን፤ ግን አሁንም ድሆች ነን፡፡ ስለዚህ ችግርና ችጋርን ለመሻር፣ ወረቶቻችን መሰብሰብ፣ ማከማቸት፣ ማካበት… ከዚያም ወደ ብልጽግና መሻገር አለብን ከሚል ሃሳብ ነው የሚነሳው፡፡
የመደመር ቀይ መስመሩ ምንድነው?
መደመር አሃዳዊነት አይደለም፡፡ ያንንም ቀይ መስመሩ አድርጐ ይወስደዋል፡፡ መደመር መጨፍለቅ ማለት አይደለም፡፡ መደመር… ነገሮች የተንሰላሰሉ የተጋመዱ ናቸው፤ ስለዚህ ህብር አላቸው ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ችግሯ ኢኮኖሚ  ወይም ፖለቲካ ብቻ ወይም ትምህርት ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም ነገሮች ሲነካኩ… ሲፈወሱ ነው መላ አካሏ ጤነኛ መሆን የሚችለው ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ስለዚህ እንደ ሀገር የሚያስፈልገን ሁለንተናዊ ለውጥ ነው፤ መታከክ የለብንም ይላል፡፡ መድረስ የምንፈልገው የጋራ ብልጽግና ላይ ነው፡፡ ሌላው ህብረ ብሔራዊ አንድነት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የዜጐች ክብር ነው፡፡ ዜጐች በየትኛውም የአለም ጥግ ላይ ሲንቀሳቀሱ፣ ክብራቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱ ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ በአረብ ሀገር ያሉ እህቶቻችን ብዙ እንግልት ይደርስባቸዋል፡፡ ከፎቅ ላይ ይወረወራሉ፤ ደሞዛቸው አይሰጣቸውም፤ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እኔ ለምሣሌ ሶስተኛ ድግሪዬን ለመስራት በትላልቅ ዩኒቨርስቲዎች የትምህርት እድሎች አግኝቼ ነበር፡፡ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ኒውካስትል ዩኒቨርስቲዎች ትልልቅ እድሎች አግኝቻለሁ፤ ግን መያዣ ንብረት ስለሌለኝና ከድሃ ሀገር ስለሆንኩ ተከልክያለሁ፡፡ የእውቀት ችግር አይደለም፡፡ መያዣ የሚሆን መኪና፣ ቤትና ንብረት ስለሌለኝ ነው ዕድሉን ልጠቀምበት ያልቻልኩት፡፡ ይሄ አይነቱ ችግር እንዳይኖር፣ ዜጐቻችን በየትኛውም ሀገር የተከበሩ ሆነው እንዲሠሩ… እንዲኖሩ ማድረግ መድረሻው ግቡ ነው፡፡ በመደመር ውስጥ የምንፈልገው ብልጽግና፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና የዜጐች ክብር ላይ ለመድረስ ስንታገል… የሚገጥሙን መደናቀፎች፣ ቀይ መስመሮች አሉ፡፡
እነዚያ ቀይ መስመሮች ምንድን ናቸው?
አንደኛው የአስተሳሰብ ሳንካ ነው፡፡ ሌላኛው የሞራል (የግብር) ችግር ነው፡፡ የአስተሳሰብ የምንለው ዋልታ ረገጥነትን ነው፡፡ አንደኛው ወገን፤ “የኔ ብቻ ነው ልክ?” ሲል፤ ሌላኛውም “የኔ ብቻ ነው ልክ” ይላል፤ መሃከል የላቸውም:: አሁን እኮ በዚህ ምክንያት ሀገር ዥዋዥዌ ላይ ናት፡፡ አንዱ ወደዚህ ይጐትታል፤ ሌላው ወደዚያ ይጐትታል፡፡ ሁለቱም ወደ መነጋገር፣ ወደ መካከል እስካልመጡ ድረስ ሀገር ዥዋዥዌ ላይ የምትሆነው፡፡ በእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ደግሞ የምንፈልገው ላይ መድረስ አንችልም:: ሌላኛው አቅላይነት ነው፡፡ አቅላይነት ማለት ለምሳሌ የኢትዮጵያ ችግር ፖለቲካ ብቻ ነው ወይም ኢኮኖሚ ብቻ ነው ብሎ ማቅለል ነው ይሄን የተበጣጠሰ እይታ ነው ይለዋል - መደመር::
ሌላኛው ጊዜ ታካኪነት ነው፡፡ ትላንትናን በመደመር ሃሳብ ውስጥ ስንመለከት፣ ድሎች አሉን፣ መጥፎም ታሪክ አለን፡፡ እነዚያን ድሎች ማስቀጠል፣ መጥፎዎቹንም ማረም አለብን፡፡
እንዴት ነው ጥፋቶችን የምናርመው?
ዛሬ እንዳይደገም ማድረግ ነዋ! እንጂ ትናንት የሆነውን ወይም የፈሰሰውን ደም ከየትም አምጥተን ልንተካው አንችልም፡፡ በጊዜ ታካኪነት ውስጥ “ትናንት እንደዚህ ተደርገን፣ እንደዚህ አድርገናቸው” የሚሉ አሉ፡፡ እነዚህን ትተን፣ ትናንትን በልኬት ማየት አለብን ይላል -መደመር፡፡ ዛሬያችንን ደግሞ መጠቀም አለብን:: በሌላ በኩል፤ ዛሬ ላይ ትናንት ያልተሠሩ ውዝፍ ስራዎች አሉብን፡፡ እነዚያን መስራት አለብን:: ለምሣሌ ታሪክ ላይ በውይይት - መግባባት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገን ደግሞ ስናስብ ተስፋ ስጋት አለ፡፡ ስለዚህ ስጋቶችን እየቀነስን፣ ተስፋዎቻችንን እያበዛን መሄድ ነው ያለበን:: እንደዚህ ነው አዕምሮአችን መቃኘት ያለበት:: ነው፡፡ ሌላኛው አድርባይነት ነው፡፡ ዛሬን ብቻ ልኑር ብሎ አለ፤ ለመደሰት ነገሮችን በሙሉ መዋጥ ማለት ነው፤ እሱ አይጠቅምም፡፡ የራስንም ሃሳብ ማሰብ፣ ማቅረብ፣ መወያየት መቻልን ያበረታታል፡፡ ሃሳብ ደግሞ ጥያቄው ማን አለ ሳይሆን፣ ምን ተባለ መሆን አለበት፡፡ ግን መደመር ሰዎችን አይፈርጅም በእሣቤው ምክንያት ሰውን መፈረጅ ለመደመር ቀይ መስመሩ ነው፡፡
ሌላኛው ህሊና ቢስነት ነው - ቀይ መስመሩ፡፡ እንደምናውቀው እኛ ሀገር ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተበልተው ቀርተዋል፡፡ ይሄ ህሊና ቢስነት ነው:: ከዚህ በኋላ ይሄ አይደገምም፡፡ ተጠያቂነት ይኖራል ማለት ነው፡፡ ሌላው ልግመኛነት ነው:: ልግመኛነት፡- አንዱ ወደፊት ሲራመድ፣ ሌላው ወደ ኋላ የመጐተት አካሄድ ነው፡፡ ስራን በሚጠበቀው ጥራትና ጊዜ፣ በትጋት መስራት እየተቻለ፣ መለገም ለምን ብሎ ነው ቀይ መስመር የሚያደርገው፡፡ መደመር የሚሳካው ሙያና ሙያተኛ ሲገናኝ እንዲሁም፣ በሃሳብ ልዕልናው ከፍ ያለ ማህበረሰብ ሲኖር ነው፡፡
መደመር ተቃዋሚዎቹን የት ነው የሚያስቀምጣቸው?  
ተቃዋሚዎች ቦታ አላቸው፡፡ ተቃዋሚ የሆነ ነገር አለው ብሎ ነው መደመር የሚያስበው:: ለምሣሌ ኢህአዴግ  በምርጫው ቢሸነፍ ያሸነፈው አካል እኮ መደመር ይጠቅመኛል ካለ ይዞት ሊሄድ ይችላል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆነ ሃሳቡ አይጠቅምም አይልም፡፡ ሃሳቡ ምን ይጠቅማል ነው እንጂ ሃሳቡ የማን ነው ብሎ አይነሳም - መደመር፡፡ እንትናን ጥሎ፣ እንትናን አንጠልጥሎ የሚል አካሄድ የለውም - መደመር:: በራሱ ምሽግ ውስጥ በቻ የሚንቀሳቀስ አይደለም፡፡ ለዚያ ነው የመደመር መጽሐፍን ሁላችሁም አግኙት፤ አብጠልጥሉት፤ ተቹት ከእነመፍትሔው ችግሩን ግለጡት ተብሎ በአደባባይ የተበተነው፡፡
መደመር የፖለቲካ ርዕዮት አለም ነው ወይስ ፍልስፍና?
መደመር ራሱን ሲገልፅ፤ ርዕዮተ አለም (አይዲዮሎጂ) አይደለሁም ይላል፡፡ መንገዱም እውነቱም ይሄ ብቻ ነው ብዬ አላምንም ማለቱ ነው፡፡ የመቀየር የመዋስ፣ የመስፋት እድሉ አለን ይላል፡፡ ይሄ ልክ አይደለም ከተባልኩ፣ መርምሬ እቀበላለሁ ነው የሚለው፡፡ በዚህ መንገድ ካየነው፣ ርዕዮተ አለም ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ምንድን ነው ከተባለ ደግሞ እሣቤ ነኝ ይላል፡፡ አለማቀፍ እሣቤ ነው፡፡ ፖለቲካውን የምንመለከተው በዚህ መነጽር ነው፣ ኢኮኖሚውን የምመለከተው በዚህ መነጽር ነው ወዘተ… ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር መደመር ይሄ ሪፎርም የሚመራበት እሣቤ ነው ማለት ነው፡፡


Read 3523 times