Saturday, 26 October 2019 12:07

በውጥረትና በግጭት በሰነበተው ኦሮሚያ የበርካቶች ህይወት አለፈ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

 ከሰሞኑ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ዙሪያ በተፈጠረው ግጭትና ሁከት ከ27 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ በርካታ ንብረት ወድሟል፡፡ በመንገድ መዘጋጋት የዜጐች እንቅስቃሴ ተደናቅፏል፡፡
አክቲቪስትና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ዳይሬክተር ጃዋር መሐመድ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ ሌሊት ‹‹ጥበቃዎቼን መንግስት ሊወስድብኝ ነው›› የሚል መልዕክት ማስተላለፉን ተከትሎ፣ ኦሮሚያና የአዲስ አበባ ዙሪያ በግጭት ሁከት ተወጥሮ ሰንብቷል፡፡
ሌሊት 9 ሰዓት አካባቢ ጃዋር በፌስቡክ ገፁ “ጉዳዩ ለሚመለከተው ሁሉ” በሚል ባስተላለፈው መልዕክቱ፤ “በመኖሪያዬ አካባቢ በቁጥር በርካታ ታጣቂ እየተሠማራ እንደሆነ እያስተዋልን ነው፡፡ ይህ የታጠቀ ሃይል ከህግ አግባብ ውጪ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ተቆጥቦ ወደ ኋላ እንዲመለስ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡ ማንኛውም ታጥቆ በዚህ ጭለማ ወደ መኖሪያ ግቢያችን ለጥቃት የሚንቀሳቀስ ግለሰብም ሆነ ቡድን ላይ የጥበቃ አካሉ ህጋዊ መብቱን ተጠቅሞ የመከላከል እርምጃ እንደሚወስድ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይኸን ከህግ አግባብ ውጪ የሚደረግን እንቅስቃሴ ለመከላከል በሚደርሰው ግጭትና ጉዳት ሙሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው ያለምንም ተጨባጭ ምክንያትና ማሳሰቢያ ኃይል ያሠማራው አካል መሆኑን ህዝቡ እንዲያውቅልን እንጠይቃለን” ብሏል:: ከዚህ መልዕክት ቀደም ብሎ በአፋን ኦሮሞ ባስተላለፋቸው መልዕክቶችም “የፓርላማው ማስፈራራት ወደ ቤቴ ተሸጋግሯል፡፡ በዚህ ሌሊት ጠባቂዎቼ ግቢውን ለቃችሁ ውጡ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል” የሚል እንዲሁም ጠባቂዎቹና ትዕዛዙን ያስተላለፉት ኮማንደር አደረጉት ያለውን የስልክ ልውውጥም ይፋ አድርጓል፡፡
እነዚህን መልዕክቶች ተከትሎም፣ ከጠዋቱ 11 ሰዓት ገደማ ጀምሮ የአክቲቪስቱ ደጋፊ ወጣቶች ቦሌ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ መሰባሰባቸውን የአይን እማኞች ያስረዳሉ፡፡
ወደ ንጋት እየተቃረበ ሲመጣም በቤቱ ዙሪያ የተሰባሰቡ ወጣቶች (ቄሮዎች) ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱንና ከፀጥታ ሃይሎች ጋርም ውጥረት መፈጠሩን፤ ነገር ግን አክቲቪስቱ ከመኖሪያ ቤቱ በመውጣት ወጣቶችን ለማረጋጋት መሞከሩን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎችም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ገደማ ጀምሮ ዋና አውራ ጐዳናዎች በድንጋይ መዘጋጋታቸውን፣ ወጣቶች በቡድን እየሆኑ ዱላ ይዘው የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የጐዳና ላይ አመፁ አይሎ ከታየባቸው አካባቢዎች መካከልም አዳማ፣ አምቦ፣ ሻሸመኔ፣ ሀረር፣ ድሬዳዋ፣ ዶዶላ ተጠቃሽ ሲሆኑ ከተፈጠረው ተቃውሞና ግርግር ጋር ተያይዞም የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡
በአምቦ በጥይት ከተመቱ 14 ሰዎች አምስቱ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ በአዳማም አመፁ በተነሳ በሰአታት ውስጥ የሁለት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን አለማቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል:: በባሌ ዶዶላ ደግሞ ረቡዕ በነበረ ተቃውሞ 4 ሰዎች፣ ሐሙስ 2 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል:: በምስራቅ ሀረርጌ በሁለቱ ቀናት (ረቡዕ እና ሐሙስ) 6 ሰዎች መሞታቸውን፣ በሀረር ከተማ ረቡዕ እለት 3 ሰዎች መሞታቸውን፣ በድሬደዋ ረቡዕ 1 ሰው፣ ሐሙስ ደግሞ 4 ሰዎች መሞታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ተመሳሳይ ውጥረትና ግጭት የአዲስ አበባ መግቢያ በሆኑት አቃቂ ቃሊቲ፣ ጀሞና ካራ ቆሬ አካባቢዎች ረቡዕ ከረፋዱ 3 ሰዓት ገደማ ጀምሮ መከሰቱን፣ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች ወደ ከተማዋ ለመግባት የሚያደርጉትን ጥረት ፖሊስ ማገዱን፣ ይህን ተከትሎም ድንጋይ ውርወራና ግጭት መፈጠሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአዳማ ከተማ ከረቡዕ ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ ግጭትና ውጥረት ተባብሶ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ረቡዕ ጠዋት 2 ሰዓት ገደማ ለከተማዋ እንግዳ የሆኑ ወጣቶች በቡድን በቡድን ሆነውና ዱላ ይዘው በከተማዋ አውራ ጐዳና ላይ እየተዘዋወሩ ተቃውሞ ማሠማታቸውን፣ ትንሽ ቆይቶም ውስጥ ለውስጥ ባሉ መንደሮች በመግባት ተቃውሞአቸውን መቀጠላቸውን፣ በዚህ ሂደትም በወጣቶቹ ድርጊት የተቆጡ የከተማዋ ወጣቶች ተሰባስበው ከሌላ ቦታ ከመጡት ተቃዋሚ ወጣቶች ጋር ግጭት መፍጠራቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ግጭቱ ረፋድ ላይ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ በመዛመትም፣ ግርግር መፈጠሩን በዚህም የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ ታውቋል፡፡
ሌላኛው የአዲስ አበባ መግቢያ በሆነው በጀሞ አካባቢም ረቡዕ ጠዋት ላይ ተመሳሳይ ውጥረት መከሰቱን፣ ፖሊስም ወደ ከተማዋ እንገባለን የሚሉ ወጣቶችን በአስለቃሽ ጭስ መበተኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ መንገድ በድንጋይ መዘጋጋትና ጐማ የማቃጠል ድርጊት መፈፀሙንም ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በጀሞ፣ ቂሊንጦ፣ ካራ ቆሬ አካባቢዎች ወጣቶቹ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ወጣት ጋር መጠነኛ ግጭት መፍጠራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ውጥረቱና አለመረጋጋቱ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ መቀጠሉም ታውቋል፡፡
ግጭቱና አለመረጋጋቱ በድሬዳዋና ሀረር ከ10 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ምንጮች ለአዲስ አድማስ ያስረዱ ሲሆን፤ በባሌ ዶዶላ ደግሞ ሐሙስ እለት አራት ሰዎች መሞታቸውን  ገልፀዋል፡፡
በደብረ ዘይት፣ ሻሸመኔ፣ አሠላ፣ ኢተያ፣ ሃረማያ፣ ነቀምት፣ አምቦ፣ ባሌ ጐባና በሌሎች የኦሮሚያ ከተሞችም ግጭቱና አመፁ እስከ ትናንት በስቲያ መቀጠሉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ረቡዕ ረፋድ ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ አቶ ጃዋር ላይ የተፈጠረ ችግር የለም፤ የጠባቂዎች መነሳት ጉዳይ የሀገሪቱ ሠላምና ፀጥታ አስተማማኝ እየሆነ በመምጣቱ ለሌሎችም አካላት የተመደቡ የፀጥታ ሃይሎችና ጠባቂዎች መነሳትን ተከትሎ የመጣ ነው›› ብለዋል፡፡
አመሻሽ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሣ በበኩላቸው፤ ‹‹በአክቲቪስት ጃዋር መኖሪያ ቤት በሌሊት የተፈፀመው ድርጊት ስህተት ነው፤ መሆን አልነበረበትም” ብለዋል፡፡
የተፈጠረው ስህተት በማን እንደተፈጠረና ለምን እኩለ ሌሊት ላይ ማድረግ እንደተፈለገ እናጣራለን ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ለአቶ ጃዋርም የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌደራል መንግስቱ ደህንነቱን እንደሚያስጠብቁም አስታውቀዋል፡፡
የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አባ ገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ በመላ ኦሮሚያ የተጀመረው የቄሮ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መንግስትም የፖለቲካ ማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወስድ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች አሳስበዋል፡፡  
በትላንትናው እለትም በአብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች አንፃራዊ መረጋጋት የተስተዋለ  ሲሆን በአዳማ፣ ሀረርና ባሌ አካባቢዎች ግን አልፎ አልፎ ውጥረቱና አለመረጋጋቱ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡    

Read 10750 times