Saturday, 26 October 2019 12:03

ቅዱስ ሲኖዶስ የጐሣና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶች መስፋፋት አሳስቦኛል አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

               - የፀጥታ ሃይሎች ቅድመ ግጭት መከላከል ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቋል
               - በግጭቱ ምክንያት መደበኛ ስብሰባውን አቋርጧል

              የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ጥፋት የሚዳርጉ ጐሣና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እየተስፋፉ መሆኑን በመግለፅ ዜጐች ለሀገር አንድነትና ሠላም እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የፀጥታ ሃይሎችም ቅድመ መከላከል ላይ እንዲያተኩሩ አሳስቧል፡፡ በኦሮሚያ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎም ቅዱስ ሲኖዶሱ ‹‹ልጆቻችን እየሞቱ አንሰበሰብም›› በሚል መደበኛ ጉባኤውን አቋርጧል፡፡  
ቅዱስ ሲኖዶሱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫው፤ በሃገሪቱ ሊደረጉ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጐሣንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ መጠነ ሰፊ ግጭቶች በተለያዩ ክልሎች እየተስፋፉ መሆኑ በእጅጉ እንዳሳሰበው አስታውቋል፡፡
የበርካቶች ህይወት ከጠፋባቸውና ንብረት ከወደመባቸው፣ ዜጐች ለከፋ እንግልትና እርዛት ከተዳረጉባቸው የቀደሙ ግጭቶች ባለመማር፣ አሁንም በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞች እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች ከፍተኛ ጥፋትና ድህነትን የሚያደርሱ ግጭቶች ተበራክተዋል ብሏል፡፡
ከእነዚህ አሳሳቢ ግጭቶች መካከልም የአማራ እና የቅማንት፣ የአማራና ጉምዝ፣ የአማራና ትግራይ፣ የሶማሌና አፋር፣ የኦሮሞና አማራ እየተባሉ የተደረጉ ግጭቶች ሁሉ ምክንያታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች መነሻ የተከሰቱ ናቸው ብሏል - ቅዱስ ሲኖዶሱ፡፡
የግጭቶቹ ዝንባሌም የህዝብን አንድነትና አብሮነት ባህል የሚጐዱ መሆናቸውን የጠቆመው የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ፤ የህብረተሰቡን አንድነትና አብሮነት የሚያፋልሱ ሐሰተኛ ትርክቶች ከወዲሁ ሊታረሙ ይገባል ብሏል፡፡
ሃሰተኛ ትርክቶችን በትክክለኛ ታሪክ በማምከን በኩል ምሁራን ድርሻቸውን እንዲወጡ፤ የፖለቲካ ሃይሎች፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ምሁራንም ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ካደረጉ የትንኮሳ ቃላት ተቆጥበው፣ ከልዩነትና ግጭት ይልቅ ለሀገራዊ አንድነትና መግባባት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል - ቅዱስ ሲኖዶሱ።
የፀጥታ አካላትም ግጭቶች እና አለመግባባቶች ከመከሰታቸው በፊት ቅድመ መከላከልን መሠረት ያደረገ የፀጥታ ተግባር እንዲያከናውኑም በመግለጫሙ ተጠይቋል፡፡
የተለያየ አመለካከት ያላቸው አካላት የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት ባማከለ መልኩ ልዩነቶቻቸውን በሰከነ መንገድ በውይይት እንዲፈቱም ያሳሰበ ሲሆን፤ የነገዋ ኢትዮጵያ መፃኢ እድል በእጃቸው ላይ ያለው ወጣቶችም የሀገሪቱን የወደፊት ተስፋ ለማለምለምና እጣ ፈንታዋን ለመወሰን በሰከነ መልኩ የድርሻቸውን እንዲወጡ መክሯል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደየ እምነቱና ስርአቱ ከሐሙስ ጥቅምት 13 ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም የምህላ ፀሎት እንዲያደርግም ቅዱስ ሲኖዶስ አውጇል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 12 በተከፈተው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓርትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ በቀጣይነት እየደረሰ ያለውን ተፅዕኖና ጥቃት ለማስቆም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት ድምፃቸውን በአለም ዙሪያ በአንድነት ለማሠማትና እስከ ሞት ድረስ መስዋዕትነት ለመክፈል እንዲዘጋጁ ማሳሰባቸው ታውቋል፡፡
‹‹በመንግስት የበታች መዋቅርና ባለስልጣናት አማካይነት በቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ላይ እየደረሰ የሚገኘው ግፍ ቤተ ክርስቲያን ከምትታገሰው በላይ ሆኗል›› ያሉት ፓትሪያርኩ፤ ‹‹መንግስት ህግና መብት እንዲያስከብር በተደጋጋሚ ቢጠየቅም የተጠበቀውን ያህል ምላሽ አልሰጠም›› ብለዋል፡፡ ነባር የቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታዎች ስልጣንን መከታ ባደረጉ ባለስልጣናት እየተነጠቁ መሆኑን፣ ምዕመናንም በሚደርስባቸው ተፅዕኖ የተነሳ ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉና እየተሳደዱ ነው ብለዋል - ፓትሪያሪኩ፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱንና ምዕመናኑን መብት ለማስጠበቅም መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ ሐሙስ ጠዋት መግለጫውን ከሰጠ በኋላ በዕለቱ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ከተፈጠረው ግርግርና ግጭት ጋር ተያይዞ ‹‹በአብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮች ላይ ጥቃት እየተፈፀመ ስብሰባ መቀመጡ አያስፈልግም›› በሚል ስብሰባው መቋረጡ ታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊቃነ ጳጳሳትም ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ምዕመኑን ለማረጋጋት ውሳኔ መተላለፉ የታወቀ ሲሆን ትናንት ከም/ጠቅላይ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ከሌሎች የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ቤተ ክርስቲያኒቱ እየገጠማት ስላለው ተግዳሮትና ጥቃት መወያያታቸው ታውቋል:: የዚህን ውይይት ፍሬ ሀሳብ በተመለከተም ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡   

Read 10124 times