Saturday, 26 October 2019 11:57

ኢኒሽዬቲቭ አፍሪካና የሳይንስን ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ የሰላም ኮንፍረንስ ያካሂዳሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ኢኒሽዬቲቭ አፍሪካ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ‹‹በዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መፍጠር›› በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ 6፡00 የሰላም ኮንፍረንስ ያካሄዳሉ፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና የተማሪ ተወካዮች የሚታደሙ ሲሆን የኮንፍረንሱ ዋና አላማ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታዩ የሰላም መደፍረሶችና የመቻቻል ማነስን ለመቅረፍ፣ የዩኒቨርሲቲ አስተዳደርንና የተማሪ አመራሮችን ሚና ከፍ ለማድረግ እንደሆነ አዘጋጆቹ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ካለፉት አመታት ጋር ሲነጻጸር በዩኒቨርሲቲዎቹ ታሪክ ውስጥ ዓመቱ የተለየ የሰላም እጦት የነበረበት መሆኑን የገለፁት ተቋማቱ፣ በአገሪቱ ከሚገኙት 50 የሕዝብ ዩኒቨርሲቲዎች በአንድ ሶስተኛው የተለያየ መጠንና አይነት ያላቸው የተማሪዎች ሁከትና ብጥብጦች ማጋጠማቸውን ጠቁመዋል፡፡
አሸናፊና ተሸናፊ በሌለባቸው በነዚህ የጎሳና የሀይማኖት ቡድኖች የሚከሰቱ አለመግባባቶች ወደ ከፍተኛ ብጥብጥና ግጭት ማደጋቸውን የገለፁት የሰላም ኮንፍረንሱ አዘጋጆች፤ በእነዚህም ከፍተኛ ብጥብጦች ተማሪዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ጠቁመዋል፡፡ ብጥብጦቹ በአብዛኛው የተከሰቱት በማህበራዊ ሚዲያው የጎሳና የሀይማኖት ቅስቀሳዎች መስፋፋት እንደሆኑ የተገለፀ ሲሆን የሞራል ዕሴቶችን ማበልፀግ፣ አንዱ ሌላውን ለመረዳት የሚያስችል የውይይት ባህል አለመዳበርና የሌሎችን ባህሎች ለመቀበል መቸገር እንዲሁም የክርክር ባህል አለመዳበር የችግሮቹ ዋነኛ መንስኤዎች እንደሆኑ ተገልፆ፣ የተጀመረው የትምህርት ዘመን ከግጭት የራቀና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን የዩኒቨርሲቲ አመራሮችና የተማሪ ተወካዮች ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ ከእነሱ ጋር መወያየትና የችግሮችን ቅድመ መከላከል አቅጣጫዎች ለማስቀመጥ የታለመ የሰላም ኮንፍረንስ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ለግማሽ ቀን በሚቆየው በዚህ ኮንፍረንስ፣ ከዚህ ቀደም ግጭት ያልተከሰተባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ፣ የሚቀርብ ሲሆን ችግር ቢከሰት የአመራሮቹ ዋና ተግባራትና ግጭትን የመፍታት ሂደቶችን በተመለከተ ውይይትና ምክክር ይደረጋልም ተብሏል፡፡  


Read 431 times