Saturday, 19 October 2019 13:48

“ዘላን ግጥም”

Written by  በእሱባለው አበራ ንጉሴ
Rate this item
(1 Vote)

  “--እያንዳንዱ ገጣሚ ውስጥ ያለ ራስን ለማግኘት የመጣር ልምምድ አለ፡፡ ቅርጽ መቀያየር፥ ሙከራ ማድረግ ኪነትን ያበለጽጋል:: ወደ ተሻለውና ራስን ወደ መኾንም ያሳድጋል፡፡ ለመድረኩም የተለያየ ቀለም ይፈጥራል፡፡--”
              
            1* ከዚህ በታች የምታነቡት ግጥም [?] ርዕስ የለውም፡፡ ኾኖም ግን ጀምሮ የጀመረ ነው፡፡ ርዕስ ስለሌለው ያመለጣችሁ [ወይም የሚያመልጣችሁ] ነገር አይኖርም፡፡ ተጽፎ የቀረበውም ቀጥሎ ለምንወያይበት ሐሳብ ለመፈከሪያነት እንዲያገለግለን ያህል ነው፡፡ እነሆ:-

ፈ ገ ግ ታ ሽ : ም ን ድ ር : ነ ው?
ፈገግታሽማ እንደ አደይ፥ ፍካት ነው
ቢጫ ቀለም ያለው፥ ከሕይወት የሚደምቅ
ከጷግሜ ሰማይ ስር፥ ያለን ራቁት ገላ
እንደ ክረምት ውሃ፥ ወርዶ የሚያጠምቅ፡፡
ፈገግ በይ ግድ የለም፥ ያወጣል ከንፈርሽ
ለረቂቅ ሙዚቃ፥ ኖታ የተገባ
ዓይንሽን ባናይም፥ ድምጽሽን ሰምተናል
ብርሃን ዳሰናል፥ ስንል ፈራ ተባ፡፡
ቅ ኔ ሽ : ግን : ም ን ድ ር : ነ ው?
አሁን በቀደም ዕለት፥ ከሳቅሽው ሳቅ
የወጣው ምንድር ነው? ደስታ ወይስ ስላቅ?
ከዓይንሽ የሐዘን ውሃ፥ እንደ ጀምበር ቢጠልቅ
ቀና አንልምና፥ ለዝንተዓለም አናውቅ
አሳበብን እንጂ፥ እኛስ ጆሮዎች ነን
ሰምና ወርቅሽን፥ እንጠረጥራለን፡፡
ከድፍን ግንባር ላይ፥ እንትፍ እንትፍ ብሎ
መሲሁ ኢየሱስ፥ ዓይንን ቢሰራልን፥ አንገት ቢያበጅልን
ዛሬሽን አናይም፡፡
ነገሽ ፊት አንቀርብምም፡፡
ከማናውቀው እውነት፥ የምናውቀው ምናብ
ከማናውቀው መላዕክ፥ የምናውቀው ሰይጣን
ያኖረናል ሲያጠግብ፡፡
እ ው ነ ት : ም ን : ያ ደ ር ጋ ል?
ም ና ብ ስ : ነ ጻ ነ ት : ይ ሰ ጣ ል፡፡
እ ው ነ ት : ሲ መ ረ መ ር : ም ና ብ : የ ት: ነ በ ረ ?
ጲ ላ ጦ ስ : ያ ው ቃ ል : ወ ይ ?
እናም እንናገራለን. . .
ዓይንሽ ዕንባ ቢያዝልም፥ የለም የሚባባ
ፍጥረት ቅኔና ወይን ነው፥ አይፈልግም ዕንባ::
ም ና ብ : ግ ን : ም ን ድ ር : ነ ው ?
ግ ጥ ም ስ : ም ን ድ ር : ነ ው ?
ም ን : አ ይ ነ ት : መ ል ክ : አ ለ ው ?
የ እ ው ነ ት : መ ል ክ : ኢ የ ሱ ስ
የ ግ ጥ ም : መ ል ክ : ሕ ጉ  
አ ይ ጣ ረ ስ ም : ወ ይ ?
[ ዱ ር : አ ደ ር : ከ ሚ ሆ ን፤ ቤ ት : ስ ጡ ት : ለ ግ ጥ ሙ፡፡
ወ ይ ስ : ም ና ባ ች ሁ : ቸ ር : አ ይ ደ ለ ም ? ]

ግጥም ስለ ገጣሚው ስሜት ወይስ ስለ ስነ ግጥም ሕግ?
ግጥም ራሱን በራሱ መተረክ አለበት – ሐቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ በቀረበው፤ ርዕስ አልባ ግጥም ላይ የቀረ ሐሳብ አለ፡፡ ወይም ቦልድ ያልኾነ፡፡
አዳም ረታ “የስንብት ቀለማት” መጽሐፉ ውስጥ አንድ ገጸባህርይ አለው – ወርቁ የሚባል::  ወርቁ በሙያው ሠዓሊና ገጣሚ ነው፡፡ ወርቁና ኢዛና [ጓደኛው] “የሮሃ ኢማጂኔሽን” የሠዓሊያን ቡድን አባላት ናቸው፡፡ እንደ ዮሐንስ ወላይሶ እኔም “የምመለከተው የወርቁን ጉዳይ ስለኾነ በእሱ ብቻ ልቀጥል፡፡”
ወርቁ የዛሬ ልጅ ነው፡፡ “የዛሬ ልጅነቱ” የዚህ ዘመን ከያኒነቱን ሊያንጸባርቅ ይችላል፡፡ ውክልናው፣ ዘመኑና ሥራው ለድህረ ዘመናዊነት ይቀርባል፡፡ ለግጥምም፥ ለሥነ ሥዕልም የተሰጠ ሰው ነውና - እዚያና እዚህ መቀመጣቸው ሰላም ይነሳዋል፡፡ ራሱን ለማግኘት በሚያደርገው ፍለጋ ውስጥ ሁለቱን ድካዎች ያገናኘ – አንድ አከያየን [Genre] ይቀምራል፡፡ እንደ ሠዓሊነቱ ሸራው ላይ ይስላል፡፡ እንደ ገጣሚነቱም የሸራው ጅራት ላይ አጭር ግጥም ያሰፍራል፡፡ ልክ እንደ ጭራ፡፡
በሌላ አማርኛ/በእኔ መረዳት፦  
በብሩሽ ቀለም ነክሮ ውሻ ስሎ ስሎ፥ ጭራው ጋር ሲደርስ [ጭራውን] በግጥም እንደ መጨረስ ማለት ነው፡፡ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ‘ባላለቀው’ መግቢያው፤ “ቃላት በግጥም ተቀርፀው በሚቀርቡበት ጊዜ ከትርጉማቸው በላይ አልፈው ተርፈው ይሄዳሉ” ይላል:: በገጣሚውና በተደራሲው አማካይ ያለው መስመር “መረዳት/መገነዛዘብ” ነው፡፡ ተደራሲው የገጣሚውን ግጥም ሲረዳ፥ ሲገባው ያኔ ገጣሚውና ተደራሲው አንድ መስመር ይሆናሉ፥ ይገናኛሉ:: ሥዕልስ?
ሥዕል ሸራው የስፔስ ፍሬም አለው፡፡ በፍሬሙ ውስጥ የቀረበው ሥዕል የተጠናቀቀ ይሁን? አልያም የተገደበ? እውነታውን የሚያውቀው ፈጣሪና ሠዓሊው ብቻ ናቸው:: እንደ ተመልካች አልቋል ብለን የምናየው ሥዕል የተፈታ ሳይሆን የታሰረ፤ የሠዓሊው ህሊና ውስጥ በአንዳች መንገድ የቀጠለ፥ አውላላ መልክአ ምድር [Vast - landscape] ሊኾን ይችላል፡፡ ማለት እንደ ተደራሲ አናውቅም፡፡ መልክአ ምድሩ ከሸራው ያፈንግጥ? አያፈንግጥ:: ሠዓሊው እየሳለ ሸራው ቢያልቅበት? ሥዕሉ ያልቃል ወይ? ትርፉን የት ይስለዋል? ለትርፉ ብሎ የሳለውን ይተወዋል? ትርፉን ለማካተት አዲስ ቆዳ ይፍቃል? ሌላ ሸራ ይወጥራል? ወይስ እንዳለ ያቀርበዋል?
ወደ ግጥም ስንመጣስ? . . . ግጥም እንደ ሥዕል “ስፔስ” የለውም፡፡ በተለምዶ የሚታይ ሳይኾን የሚሰማ ነው፡፡ ለዓይን ሳይሆን ለጆሮ ነው፡፡ የግጥም ፍሬም ስፔስ ሳይኾን . . . ስንኙ ነው – ቤት መድፊያው፡፡ ሰንጎ መገን፥ የወል ቤት፥ ቡሔ በሉ. . . . ሌላም ሌላም የፍሬም አይነቶች ናቸው፡፡ ተረክ መመጠኛዎች፡፡ ማሰሪያዎች፡፡ መቋጠሪያዎች፡፡ ቤቶች፡፡ ማሰሪያ የሆኑት እኛ ታስረንባቸው ከቀረንባቸው፤ አዲስ ተጨማሪ ድካ ለማግኘት መፈለግ፥ መመርመር ካቆምንበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ማሰሪያዎች አልነበሩም፡፡  
ለምሳሌ...
አንድ ገጣሚ ስንኞች ሲያናብብ . . . ስሜቱ የመረጠለት አቻ ቃል ቢኖር? ነገር ግን ከላይኛው ቤት መድፊያ ጋር በሆሄዬ መልክም ኾነ በምት ድምጸት ባይገጥም? ግጥሙ ስለገጣሚው ስሜት ነው? ወይስ ስለነባር የግጥም ሕግ ነው ተገዝቶ ማለፍ ያለበት? እንዴት ቢጻፍ ግጥሙ ያልቃል? እንዴት ቢጻፍስ አያልቅም ይባላል? ገጣሚው አዲስ ድካን ካልቀደደ ለነባሩ ሕግ ብቻ ተገዝቶ ካለፈ፣ በሕጉ ታሰረበት እንጂ መች ተጠቀመበት ይባላል?

የግጥም ሕይወትና መልክ ምንድር ነው?
ወደ ርዕስ አልባ ግጥሜ ስመለስ፥ የጻፍኩት “ግጥም” መሰለኝ እንጂ [?] ግጥም ያልኾነበት ቦታ አለ፡፡ የኾነበት፥ የፈረሰበትም ቦታ አለ፡፡ ግጥሜ እስከ የት ድረስ ግጥም፤ እስከ የት ድረስ ደግሞ ዝርው ወይም ፈራሽ እንደኾነ ‘ርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን የፈረሰበት ቦታ፥ “ቤት” እንደነበረ መዘንጋት አይቻልም፡፡ ግጥም ሲፈርስ “ፍርስራሹ” ምንድር ነው? የግጥም ፍርስራሽ እንዴት “ዝርው” ብቻ ተብሎ ይታለፋል? ዝርውነት ውስጥ ግጥምነት ሊገኝ አይችልም? [የፈረሰ፥ “የከሸፈ” ግጥም] በራሱ? ግጥም ሊሆንስ አይችልም ወይ?
ገጣሚ ረድኤት አሠፋ “በዘልማድ ግጥም ይኼ ነው እንላለን፥ እንጠረጥራለን እንጂ የሥነ ግጥም ዋነኛ ኤለመንቱ፥ አከርካሪ አጥንቱ የቱ ጋር እንደሚገኝ እስከ ዛሬ አናውቅም” ይላል፡፡ ሐሳቡን እጋራለሁ፡፡ የት ጋ ግጥም ይሰበራል? የት ጋ ግጥም - ግጥም መሆን እንደሚጀምርና እንደሚያበቃ? የት ጋ ግጥም እንደሚከሽፍ? የት ጋ ግጥም እንደሚሞት? በጥልቀት ወርደን አልመረመርንም፡፡
ምሳሌ...
አዳም ረታ በ “ማኅሌት [ሥዕል በብጥስጣሽ ጨርቆች ላይ]” በተሰኘ ሥራው እስጢፋኖስ የሚባል ሠዓሊ ገጸ ባሕርይ አለው፡፡ እስጢፋኖስ የዘመነን [የጓደኛውን] እንደ ገረድም እንደ ሚስትም የኾነች ሴት፤ ማለትም ማኅሌትን በራቁት ሞዴልነት አስቀምጦ፥ በምናቡ ካጨው ሌላ ወንድ ጋር  እንደምትሳሳም አድርጎ ይስላታል፡፡ ማኅሌት በተረኩ ውስጥ ከአንድም ሁለቴ የመደፈር ታሪክ ያጋጠማት ሴት ኾና የተሳለች ናት፡፡ እስጢፋኖስ ስሎ ሲጨርሳት ሥዕሉን ታየዋለች፡፡ አብሯት የተሳለው ወንድ የደፈሯት ሰዎች ጡንቻ፥ ነጭ ካናቴራና ትናንሽ አይኖች አሉት፡፡ ወይም ያየችው ያንን ነው:: ሥዕሉን ከተደገፈበት ትጥለዋለች፡፡ በዚህ ሒደት የስዕሉ ሸራ እስከ ተያያዘበት የጣውላ ጠርዝ መኻሉ ድረስ በአንድ ስንዘራ ይሸረከታል:: ሌላም ሌላም ቦታ ይቀዳደዳል፡፡
የእስጢፋኖስ ሥዕል እዚህ ጋ ሊከሽፍ፥ እዚህ ጋ ሊሞት፥ እዚህ ጋ ሊቀበር ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን የሥዕሉ ሕይወት የጀመረው ሲከሽፍ ነው:: እስጢፋኖስ የተቀዳደደውን ሥዕል እግሩን አንድ ቦታ፥ ከናፍሯን አውጥቶ... ተረከዙ ጋር ያደርገዋል፡፡ “ሥዕል በብጥስጣሽ ጨርቆች ላይ” ሲልም ርዕስ ይሰጠዋል፡፡
በአንጻሩ...
በመክሸፍ ያበቡ ግጥሞች አሉ ወይ? ከእነ መዘባረቃቸው? ከነ ቤት አለመምታታቸው የቀረቡ? የገጣሚውን ስሜት እንጂ የሥነ-ግጥምን ሕግ ያላከበሩ ደፋር ግጥሞች አሉ ወይ? መ’ሰበሩ መጠገን የሆነለት ግጥም አለ? መድረክ ላይ የሚቀርቡ ግጥሞች ተሰምተው ጠፊ ናቸው? ወይስ አገጣጠማቸው ያመራምራል? ወይስ ማመራመር ያለበት ግጥሙ የሚናገረው ሐሳብ ብቻ ነው?
በዝርው አንቀጽ ውስጥ ስናነብ ግጥማዊ ዐ. ነገሮች አጋጥመውን አያውቁምን? አንድ ደራሲ ግጥም እያሰበ ስንኝ ሳይኾን ዐ. ነገር ቢመሰርት ምን ይፈጠራል? . . . በቅርቡ በዮናስ አ. በተጻፈው “ስለ ትናንሽ አለላዎች” ቤሳ ልብ ወለድ ሥራ ውስጥ ያጋጠሙኝ ግጥማዊ አንቀፆች አሉ፡፡ አንዱን በምሳሌነት አቀርባለሁ፡፡
“. . .በየመስኮታችን፣ በየጓዳችን፣ በየሥርቻው፣ በየታዛው፣ በየጥጋጥጉ፣ በየእንቅባችንና በየዳታናችን ሥር፣ በየሙዳይና መሶባችን ሥር፣ በየአልጋችንና በየወንበሮቻችን ሥር፣ በየመብራታችንና በየራታችን ውስጥ፣ እንደ ሻጋታ ተጋግረው፣ እንደ ሐረግ ተንጠላጥለው፣ እንደ ሸረሪት ድር ተደርተው፣ እንደ ንፋስ ብር፣ እንደ ወናፍ ፍር፣ እንደ ዥምል ግር፣ እንደ ዥረት ህር፣ እንደ ጦር ዥር፣ እንደ መንጋ ትር ብለው፣ አድበው እየጠበቁ፣ ተንጠላጥለው እየሰለሉ፣ መሽገው እየጠበቁ፣ ተቆርረው እየተለሙ፣ ተደብቀው እየወጠኑ፣ ተሸሽገው እያደኑ፣ በወርዋሪ እየቀለቡ፣ በነጋሪ እየበለቱ፣ በሯጭ እየተረሩ፣ በተቀማጭ እያቀለሙ፣ ጊዜ እየጠበቁ፣ ቀን እየቆጠሩ፣ ስሜት እየዘረዘሩ፣ ግንባርና ዐይን፣ ፊትና ጉንጭ እየመተሩ የሚያደቡ ሰይጣኖች አሉን። የተዘናጋን ቀን በፊት ለፊት በር በርኖሳቸውን ለብሰው ከተፍ ይላሉ።. . .”
ግጥማዊነትን በዚህ አንቀጽ ውስጥ ሲርመሰመስ አላገኛችሁትምን? ግጥም ዝርው ኾኖ ላይፈርስም ይችላል፡፡ ወደ “ዝርው ግጥም” ነት [Prose poem] ይሻገራል፡፡ ይህን ቸል ብንል ስንኳ መዝሙረ ዳዊትንና መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞንን ከምን እንፈርጃቸዋለን? ቢ’ጠና የምንደርስበት ሐቅ አለ፡፡
የስንብት ቀለማት ውስጥ ወርቁ የጻፋት አንዲት ግጥም እንዲህ ትነበባለች:-
‘ሰማያዊ’
“ቢነጋ ባይነጋም
የተፈቀረ አይዘነጋም፡፡
ከመቶ ዓመት በፊት ተወልደሽ፣ ከመቶ ዓመት በፊት ብትሞቺም
እንደ ጉም እኖራለሁ ሳልተኛ፣ የማይቀር ትንሣኤሽን ሳልም፡፡
ያልተፈጠረ ጉንጭሽን
እንደ ሰማያዊ ስጦታ ስስም”
እስኪ የሐገርህን ባለቅኔ ጥራ ስባል፣ አዳም ረታን ቶኮ [Tokko] የማልለው ለምንድር ነው?
ከርዕስ አልባው ግጥም ሐሳቤ ቢበተን ይጎላል ብዬ የምለው መስመር፦
ም ና ብ : ግ ን : ም ን ድ ር : ነ ው ?
ግ ጥ ም ስ : ም ን ድ ር : ነ ው ?
ም ን : አ ይ ነ ት : መ ል ክ : አ ለ ው ?
የ እ ው ነ ት: መ ል ክ : ኢ የ ሱ ስ
የ ግ ጥ ም : መ ል ክ : ሕ ጉ  
አ ይ ጣ ረ ስ ም : ወ ይ ?  – የሚለውን ነው፡፡
እነኾ፥ ማብራሪያ...
የእውነት መልክ በክርስትናው ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በተመሳሳዩ የግጥም መልኩ ካልን?  መኾን ያለበት “ሕጉ” አይደለም የሚል ነው ማጠንጠኛዬ፡፡ እንግዲያውስ የግጥም መልክ ማን ነው? ምንድር ነውስ? ከተባልኩ ... “ገጣሚው ነው” ብዬ መመለስን እመርጣለሁ፡፡
ኦስካር ዋይልድ “Every portrait that is painted with feelings is a portrait of the artist“ ይላል፡፡ አፈሩ ይቅለለውና፡፡ Basil የተባለ ሰዓሊ ገጸባህርዩ፥ Dorian Gray የተባለ ሥዕሉን ለምን ለአስተርዮ እንደማያበቃው ሲናገር “I am afraid that I have shown in it the secret of my own soul.“ ይላል፤ ፍቅር ይብዛለትና፡፡
ለገጣሚም ይኼው ፐዝል ነው የሚሠራው:: ግጥም – የሌላም አይደለ፡፡ ይልቁንም የገዛ ገጣሚው ምስል ነው፡፡ ግጥም የባለቅኔው የነፍሱ መልክ እንጂ የተጫነበት ሕግ አምሳያና መታያ ሊኾን አይገባም፡፡ ግጥም መግለጽ ያለበት ገጣሚውን ነው፡፡
ገጣሚ ስሜቱንና ሐሳቡን ይዞ በየትኛው የትወራ መንገድ ይዝለቅ?
ምናብ የሚጨበጥ መልክ አይደለም፡፡ ግጥም ከምናባዊ ገምቦ ውስጥ የሚቀዳ ወይን ነው፡፡ ገጣሚ በዕውቀቱ ሥዩም “[ሥነ - ግጥም] ምናባዊ መገለጥ እንደ ኾነ እናምናለን” ይላል፡፡ ስለዚህም እንደ እውነት በቦታ፥ በጊዜ፥ በመልክ፥ በቀለም፥ በአገጣጠም፥ በስንኝ አደራደር፥ በአለባበስ፥ በአነባበብና በአቀራረብ ወዘተ. . . የተገደበ [rigid] ሊኾን አይገባም፡፡ ሥነ-ግጥም ሐይማኖት አይደለም፡፡ ቀኖና የለውም፡፡ ሥነ-ግጥም ራስህን ከምትገልጽበት የጥበብ መንገዶች አንዱ ነው፡፡ በሥነ-ግጥም ውስጥ የአገጣጠም ክርስቶሳዊ ራስ የለም፡፡
የነበረውን ሳያጣጥሉ በቤትም ባይሆን በአመታት፥ በአደራደር የራስን ጎዳና መቀየስ ይቻላል፡፡  ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን በዚህ ረገድ ሳናነሳቸው ማለፍ አንችልም፡፡ ጸ.ገ.መ በምሁራን ዘንድ “የጸጋዬ ቤት” የሚል ስያሜ ያሰጣቸው የአገጣጠም ቴክኒክ አላቸው፡፡ ጸ.ገ.መ የባለ ስምንትዮሽ የሥነ-ግጥም ምት አስተዋውቀው አልፈዋል፡፡ በአጻጻፍ ብቻም አይደለም፤ በአቀራረባቸውም ስኬታማ ነበሩ፡፡ በድምጽ ሥራቸውን ተቀድተው ሰምተናቸዋል:: ያደመጥነው. . .የትም የማናገኘውን የራሳቸውን ውብ ቀለም ነው፡፡
ግጥም ታሥሯል ወይ? የግጥምስ ነጻ አውጪዎች እነማን ናቸው? የትግል መንገዱስ?
ግጥም በዚህ ዘመን ራሱን አግልሏል፡፡ ወይም አካታችነትን አጥቷል፡፡ ‘እዚያው በዚያውነት’ ይታይበታል፡፡ ከዚህ ለመውጣት ግጥም ዘላን ሊኾን ይገባል፡፡ እግሩን በሙዚቃው፥ በስዕሉ፥ በቴአትሩ፥ በውዝዋዜው፥ በዳንሱ. . . በሌሎችም የጥበባት ዘርፎች ውስጥ ሊተክል፥ ሊንሠራፋ ያስፈልጋል፡፡ ወደ አንድ ቦታ መሰበሰብን ሳይኾን ወደ ብዙ ቦታና ፎርም መበተንን መንገዱ ማድረግ አለበት፡፡ በርግጥ ጅማሬዎች አሉ፡፡ የስነ ግጥም መድረክ አለ፡፡ ጃዝ በኹሉ ባይወደድም:: ግጥምን በጃዝ አለ፡፡ በብዛት እንጂ በጥራት ገና ቢኾኑም፤ የግጥም መድበሎች በየጊዜው እየታተሙ ነው፡፡ ነገር ግን የመድረኩ - በአቀራረብ አይነት፥ የመጽሐፉ ደግሞ - በይዘት በቂ ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡ ተመሳሳይ ቅርጽ ይታያል፡፡ ግጥም ከዚያ ነጻ መውጣት አለበት:: ግጥምን ነጻ የማውጣት ኃላፊነት ያለበት ራሱ ገጣሚው ነው፡፡ ገጣሚ እንዴት ነው ግጥምን ነጻ የሚያወጣው? ራሱንና ራሱን ብቻ በመኾን!
እያንዳንዱ ገጣሚ ውስጥ ያለ ራስን ለማግኘት የመጣር ልምምድ አለ፡፡ ቅርጽ መቀያየር፥ ሙከራ ማድረግ ኪነትን ያበለጽጋል:: ወደ ተሻለውና ራስን ወደ መኾንም ያሳድጋል:: ለመድረኩም የተለያየ ቀለም ይፈጥራል፡፡ ከታዳሚ ግምትና ጥበቃ ዘወር ያሉ ሥራዎች ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ሕይወት ዘርፈ ብዙ ናት፡፡ ዘወትር አንድ አይነት አቀራረብ|/አገጣጠም፥ አንድ አይነት የሥነ-ግጥም አጀንዳም ‘ሴት’ ማድረግ አያራምድም፡፡ በታዳሚው የሚያስወድድህ ግጥም እንዲህና እንዲያ ያለው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ [issue] ላይ ብትጽፍ ትታወቃለህ፥ ሰው ልብ ውስጥ ትገባለህ እያሉ የሚሸነግሉ፣ እኚያ የገጣሚን ምናብ አሣሪዎች ናቸው፡፡
ጸ.ገ.መ በ”እሳት ወይ አበባ” መግቢያ፣ ሥነ-ግጥምን እንደባለ ድንጋጌ ታሪክ ሲል ካቀረበው ሐቲት ላይ ጥቂት እንቀንጭብ፡-
“[...] የሥነ - ግጥምን ድንጋጌ ይኼኛው ዓይነት ብቻ መኾን አለበት፤ ወይም ደግሞ ከዚህኛው የቋንቋ መሠረተ ድንጋጌ በተወረሰው ዓይነት ብቻ መመራት አለብን ብሎ መወሰን፤ ያው ከተወሰነ አእምሮ የሚወጣ ድፍረት ነው ብንልም፤ በሌላው መልክ ደግሞ፤ ቁጥሩን (ሚተሩን ወይም ‘ምቱን’) የተመደበ የስንኝ ስልትና ቤት ባልደነገገው የቃላት መረን አሂዶ እነሆ ሥነ - ግጥም ማለቱም ጸያፍ ማለቱ ሳይሳነን፤ ከላይ እንደጠቀስኩት እንደ ምእመኑ ሃይማኖት አይነት፤ ባለቅኔም የሥነ - ግጥሞችን ድንጋጌ ከማተቱ ይልቅ ቅኔውን (ተቀኝቶ) ደርሶ ማበርከቱ ይበልጥበት ይመስለኛል” – ይላል::  ጸ.ገ.መ. በኹለቱ ጉድባዎች አማካይ ያለውን ኪነት [ስም ሳያወጣለት]የሚተወው ለከያኒው ነው፡፡
ሠዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታም እንዲሁ ‘ባላለቀ መግቢያው’ “ደራሲ የኾነ ሁሉ ብዙ መጽሐፍትን በማንበብና በማጥናት፥ እንዲሁም ራሱ ከአካባቢውና ከኑሮው የሚቀምሰውን  ዕውቀት ልብ አድርጎ በመመርመር፥ ሁለቱን እያስተያየ፥ ግን አንድ የግሉ የኾነ የአጻጻፍና የአስተሳሰብ ዘዴ መፍጠር እንዳለበት መገንዘቡ አይቀርም፡፡ እንደዚህ ያለው ሥራ ደግሞ ጊዜና ድካምን ይጠይቃል” – ይላል፡፡ ገ.ክ.ደ እንደ ጸ.ገ.መ ለከያኒው የራስን ፍለጋ የቤት ሥራ ይሰጣል፡፡
እንደ ጸ.ገ.መ ሐተታ፤ ሥነ - ግጥም ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ “[...] ግጥሙ[ም] ቤት የሚመታ  ወይም የማይመታን እንቆቅልሽ የኾነ ምሳሌና ተረት፤ እንዲሁም፤ በቃለ-ውበቱና በቃለ-ኃይሉ፤ ወይም በድቀቱ ሥምረት ለአእምሮና ለልቦና፥ ለስሜት የሚጥምን ባለ ስልትና ባለ ድንጋጌ የቋንቋ አደራደር ሁሉ፥ ሥነ-ግጥም (ፖኤትሪ) ይሉታል፡፡ ”
ግጥም፥ እውነታና የማኅበረሰብ ሁኔታ ይናበባሉን?
በተረጋጋ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለፈው ስነ ግጥም ሲወርድ፥ ሲደረጅ፥ የአሁኑ ዘመን የትውልድ እጅ ላይ ቅርጽ ከያዘ መልኩ (ከ’ነ Metrical Structure) ጋር፥ ከነፈርጣማ ሕጉ ዱብ አለ፡፡ ቀደም ብለው የነበሩት እነ ጸጋዬ፥ ሰሎሞን፥ ገብረ ክርስቶስ . . . Structural Variety ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በተለይም ሰሎሞን ደሬሳ በክርክርና በፖለቲካ እየተለያየ የመጣውን ማኅበረሰብ ሊያሰባስብ የሚችል ድካ ሲያስስ ነበር ወለሎን ለመሥራት ግድ ኾኖ የተሰማው [ዜጋ አራተኛ ዓመት/ ቁጥር 3/ የጥር 1995/ ገጽ 21 ን ተመልከት]፡፡ ይህም የግጥም ቅርጽ ከማኅበረሰቡ መንፈስ ጋር ያለውን ተናባቢነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ብዬ አምናለሁ፡፡  የሰሎሞን ደሬሳ ወለሎ የተወለደው ከማሕበረሰቡ ያለመርጋት ማሕጸን ውስጥ ነበር፡፡ በርግጥ ሰሎሞን ወለሎ ሲል በሰየመው ልጁ ምክንያት የተቀበለው ኂሳዊ - ዱላ ቀላል አይደለም፡፡ በጊዜው እንደ ኀሳዊና እንደ ሰነፍ ገጣሚም ያዩት አልጠፉም፡፡
አሁን ባለንበት ዘመን እንደ ሐገር እንዴት ነን? እንደ ማሕበረሰብስ የተረጋጋ ሁኔታ ላይ ነን ወይ? ግራ መጋባት አይታይብንም? አንድ ደርዝ የያዝን ነን? ቅጥ አለን? Structured ነን? ታዲያ እንዴት ስነ ግጥማችን አልፎ አልፎ እንኳን የ Unstructuredነት ጠባይ አልታየበትም?  ዘመኑ እንዴት ለUnmetrical verse አልጋበዘንም? እንዴት ፈለገ ሰሎሞን ደሬሳውያንንስ ልናፈራ አልቻልንም? ወይስ መሬት ላይ ያለው እውነታ በግጥም ውስጥ የሚተላለፈውን መልዕክት እንጂ የአጻጻፍ ቅርጽ፥ የአቀራረብ መንገድ ሊቀይረው አይችልም?
ዘላን ግጥም [Nomadic poems] እሳቤና የነጻ ስንኝ ነገር
ዘላን የሚለውን ቃል “ስ 1. አንድ ቦታ ላይ ቋሚ መኖሪያ ቤት የሌለው ለከብቶቹ ሣርና ውሃ ለማግኘት ሲል እንደየወቅቱ ሁኔታ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ የሚኖር ሕዝብ [*ግጥም]:: 2. (ዘይ.) ተቆጣጣሪና ቋሚ አድራሻ የሌለው ሰው [*ግጥም]፡፡” ሲል የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ይፈታዋል፡፡ **በቅንፍ [*ግጥም]  ተብለው የተቀመጡት ቃላት በእኔ የተጨመሩ ናቸው፡፡
ዘላን ግጥም [Nomadic poems] ስል የግጥም ስልት በአንድ ድንጋጌ፥ በአንድ ትርጉም፥ በአንድ ጉባዔ፥ በአንድ ዘርፍ ብቻ አይከፈል፥ አይፈከር እያልኩ ነው፡፡ ግጥም በአንድ መልክአ ምድር የሚወሰን ጥበብ አይደለም:: ግጥም ዘላን ነው፡፡ ዘዋሪ ነው፡፡ አንድ መልክ የለውም፡፡  ማንነተ ብዙ ነው፡፡ ተተርጉሞ፥ በአንድ የአከያየን መንገድና ብያኔ Define ተደርጎ አያልቅም፡፡ የግጥም እግሮች ረዣዥም ናቸው፡፡ አንድ ብቻም አይደሉም፡፡ ግጥም በንግግር (Dialogue poems)፥ በሙዚቃው፥ በመዝሙር፥ በመንዙማው፥ በቴአትሩ፥ በዝርው ስነ ጽሑፉ፥ በስነ ስዕሉ . . . በሌሎች ... አያሌ የጥበብ መስኮች ውስጥም ተሰማርቷል፡፡ አሻራው አለ፡፡
የጠነከረ ባይኾንም ለምሳሌ በቀረበው ርዕስ አልባ ግጥም ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የነጻ ስንኝነት ጠባይ ተመላክተዋል፡፡ በተለምዷዊው የሥነ-ግጥም ድንጋጌ መታሰር የማይችሉ ስሜቶቼን “በነጻ ስንኝነት” ተይቤ አቅርቤያቸዋለሁ፡፡ በርግጥ ሙሉ በሙሉ በነጻ ስንኝ ትወራ የተጻፈ ግጥም፣ ባሕላዊውን የስነ ግጥም ቅርጽ [Traditional forms of poetry] አይቀበልም፡፡ የስነ ግጥም ሕግጋት ላይ ያምጻል፥ ይጥሳል፥ ያልፋል፡፡ ኾኖም በቃለ-ውበቱና በቃለ-ኃይሉ፤ በድቀቱ ሥምረት ከያኒውን ነጻ አውጥቶ፣ ተደራሲውንም ለማረስረስ በር ከፋች ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ የ “ነጻ ስንኝ” እሳቤ እንደ አንድ አማራጭ መንገድ እንጂ እንደ ግብ ወይም እንደ መድረሻ ትወራ በሐሳብነት አልቀረበም፡፡ እኔም እንደ ጸጋዬ፤ “...ቁጥሩን (ሚተሩን ወይም ‘ምቱን’) የተመደበ የስንኝ ስልትና ቤት ባልደነገገው የቃላት መረን አሂዶ እነሆ ሥነ - ግጥም ማለቱም ጸያፍ...”  እንደኾነ ይሰማኛልና፡፡
እንደ  መደምደሚያ
የዚህ በጥያቄዎች የተሞላ ጽሑፍ ዓላማ ስለስነ ግጥም እንድንነጋገር፥ እንድንወያይ፤ አንድም ቆምና ዘወር ብለን የመጣነውን መንገድ እንድናይ፥ ወደ ፊትም የሚጠብቀንን የስነ ግጥም ነጋችንን እንድናጤን የሚያስችል ስሜት መጫር ነው፡፡ መልዕክቱም ያለንን ይዘን [ሳንጥል]፥ አዲስ ፍለጋዎችንና ሙከራዎችን ልናደርግ እንደሚገባ፥ እንደ “ወርቁ” ከያኒዎች ስነ ግጥምን ከሥዕል፥ ከረቂቅ ሙዚቃ፥ ከተውኔት፥ ከውዝዋዜ፥ ከዳንስ፥ ከኪነ ሕንጻ፥ ከመልክአ ምድር ጋር . . . የማገናኘት [የተገናኘውንም የማጠንከር] የቤት ሥራን በ.ተ.ጠ.ና መንገድ መወጣት እንደሚገባቸው፣ እንደ አንድ የስነ ግጥም አፍቃሪ ማስታወስ፥ መጠቆም ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2062 times