Print this page
Saturday, 19 October 2019 13:46

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

 “በሌለ ጠላት ላይ ጦር መስበቅ፣ የቅዠት ፊልም ተዋናይ መሆን ነው”
                   
              በጥንት ዘመን ሰዎችና መላዕክቶች አንድ ላይ ይኖሩ ነበር አሉ፡፡ ይጋባሉ፣ አብረው ይጫወታሉ፣ ይዘፍናሉ፣ ያማሉ፡፡ የባህሪ መወራረስም አለ፡፡ አንድ ቀን አንድ መልአክና አንድ ሰውዬ  በሴት ተጣሉ፡፡ ጥፋቱ የመልአኩ ነው፡፡ ሴትየዋ ወደ ሰውየው ስላደላች መልአኩ ቀና፡፡ ሰውየውን ለመበደል የሆነ ያልሆነውን፣ የተደረገ ያልተደረገውን ሁሉ ወደ ሰማይ ቤት ሪፖርት ማድረግ ጀመረ፡፡
ጊዜው ሳይደርስ ሰውየው ተጠራ፡፡ መዝገቡ ሲነበብ ሃጢአቱ ተቆልሏል፡፡ እግዜር እየተገረመ ሰውዬውን መመርመር ጀመረ፡-
“ይህን ሁሉ ሃጢአት በሰው ዕድሜ መፈፀም አይከብድም?”
“ምንም አይከብድም”
“መልሼ ወደ ምድር ብልክህ ትታረማለህ?”
“አልመለስም፡፡ ብመለስም የበለጠ አጠፋለሁ”..
እግዜር “ምን ዓይነት ትዕቢተኛ ገጠመኝ” እያለ በሆዱ፡-
“እሽ ይቅርታ ትጠይቃለህ? ትፀፀታለህ?”
“አልጠይቅም፣ አልፀፀትምም፡፡” …እግዜር ትዕግስቱ እያለቀ መጣ፡፡ ቁጣውን ተቆጣጥሮ፡-
“ድፍረትህ ስላስደሰተኝ ይቅርታ ላደርግልህ’ኮ ነው፣ ገነት እንድትገባ” አለ በስላቅ::
“ገነት መግባት አልፈልግም” አለ ሰውየው፤ ቁርጥ አድርጐ፡፡ እግዜር መጠራጠር ጀመረ፡፡
 “ሰው በራሱ ላይ ከጨከነ መራራ ዕውነት በውስጡ አለ” የተባለውን ቃል አስታወሰና በረጋ ቃና፡-
“ለምን?” ሲል ጠየቀ፡፡
“ምክንያቱም በምድር ዕድሜዬ ስቃዬን ካሳዩኝ፣ ላንተ ቅርብ ነን ከሚሉ ዋሾዎች ጋር “ዘላለሜን” መኖር አልፈልግም” በማለት መለሰ፤ ሰውየው፡፡ እግዜርም ነፍሱን ተመልክቶ፣ ሰውየው ብሶት እንዳለበት አወቀ:: “አንዴ ጠብቀኝ” አለውና ፋይሎቹን ከስር ጀምሮ መረመረ፡፡ መንፈሱንም ወደ ምድር ልኮ ሁሉንም ነገር አጣራ፡፡ ከዛም ቀና ብሎ በእምነት ታሪክ “ታላቅ” የሚባለውን ፍርድ ሰጠ፡፡ ምን ይሆን  ፍርዱ?
***
ወዳጄ፡- በቀን አንድ ጊዜ እንኳ መብላት ስቃይ የሆነብን ድሆች ነን፡፡ ግን ተስፋ አለን፣ ነፃነት አለን፡፡ ተግተን፣ ለፍተን ራሳችንንም፣ አገራችንንም፣ ዓለማችንንም እንቀይራለን:: ጐሰኝነት የተጠናወታቸው ፖለቲከኞች ግን አላወቁንም፡፡ ድህነትን ለማሸነፍ ማድረግ ስለሚገባን ጥረት ሳይሆን እንዴት በሌሎች ወንድሞቻችን ላይ ችግር እንደምንፈጥር ይቀሰቅሱናል፡፡ የእምነት አባቶቻችንም አላወቁንም፡፡ “አይዟችሁ የተሻለ ጊዜ ይመጣል” በማለት ፈንታ “መጨረሻ ሰዓት ላይ ደርሰናል፣ የገሃነብ በር ተበርግዷል፣ ወዮላችሁ” እያሉ ያስፈራሩናል፡፡ ወደ ተስፋ ማጣት፣ ወደ ጭለማ ይገፈትሩናል፡፡
ወዳጄ፡- አንዳንድ ሰዎች ምድር “የኛ” ብቻ ትመስላቸዋለች፡፡ ሌሎቹን ሰባት ቢሊዮን ህዝቦች ይዘነጋሉ፡፡ እኛ ስላዘንን ሌላ ቦታ ሳቅ እንደሌለ፣ እኛ ስለተቸገርን ሌላ ቦታ በረከት እንደሌለ፣ እኛ ስለምንጨቃጨቅ ሌላ ቦታ ፍቅርና መግባባት እንደሌለ ያስባሉ፡፡ ፅድቅና ኩነኔ፣ አልፋና ኦሜጋ፣ የመኖር አለመኖር ግብ ግብ፤ የኛ የመቶ ሚሊዮኖቹ ዕጣ ፈንታ ብቻ አድርገው ይሰብካሉ፡፡
ወዳጄ፡- ተስፋ የሚያሳጡ ሃሳቦች፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ ሰዎችና ሁኔታዎች ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ሀገራትና ማህበረሰቦች ውስጥ እንደነበሩ፣ በታሪክና በቅዱሳን መፃሕፍት ተከትቧል፡፡ አሁን አሁን ግን የእነዚህ ሀገራት ህዝቦች በሳይንስና በጥበብ ዕድገት ሁኔታዎችን ቀይረው ጨለማው ታሪካቸው ላይ የስልጣኔ መብራት አብርተዋል፡፡ ከኛ በኋላ “እንደ ሀገር” በታወቁ ቦታዎች እንኳ ስለ ምግብና መጠለያ የሚያስብ የለም፡፡ ድህነት ታሪክ ሆኗል፡፡
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ መሪው፤ “ዓላማችን ህዝባችን በቀን ሦስት ጊዜ እንዲበላ ማድረግ ነው” ብለው ነበር፡፡ አልተሳካም፡፡ “ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” እንደሚባለው በቀን አንድ ጊዜም ተበልቶ በሰላምና በነፃነት መኖር ቢቻል ጥሩ ነበር፡፡ አልተቻለም፡፡ ድርጅቱን ወደ ውድቀቱ እንዲያሽቆለቁል ያደረገው በሁሉም መንገድ ኢ-ፍትሃዊ መሆኑ እንጂ ጦም አሳዳሪነቱ ብቻ አይደለም፡፡ አድሏዊነቱ፣ ዘራፊነቱ፣ አፈናቃይነቱ፣ ከፋፋይነቱ፣ የዴሞክራሲና የነፃ አስተሳሰብ መርሆዎች ፀር መሆኑ --- ከብዙዎቹ የሚጠቀሱ ጥቂት ድርጊቶቹ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚከፋው በዚህ በሰለጠነ ዘመን ግለሰብዓዊ ነፃነትን የሚያፍን ስርዓት በህዝቦች ላይ ሊጭን መሞከሩ ነው፡፡ ዩታሊቴሪያኒዝምን:: ዩታሊቴሪያኒዝም- ሌላው ስሙ “ፋሽዝም” ነው::
ወዳጄ፡- አለምን የቀየሯት በጊዜያቸው ማንም ሊረዳቸው ያልቻሉ ሰዎች ናቸው:: የተሻለውን መንገድ ለማሳየት፣ አማራጭ ለመፍጠር እንደ ሻማ በርተው የቀለጡ ጥቂት ዕፁባውያን (genuis) በነሱ የሃሳብ መስታወት እራሳችንንም ዓለምንም እንመለከታለን፣ የሚጠቅመንና የማይጠቅመንን እንለያለን፣ ስንዴን ከእንክርዳዱ፣ ፍሬን ከገለባ እናበጥራለን:: ዳርዊን፣ ፍሮይድ፣ ማርክስ፣ አንስታይን፣ በርናርድ ሾ፣ ደስቶቭይስኪና የመሳሰሉት የጥበብና የሳይንስ ሊቆች አእምሯችንን በማነጽ፣ ምድራችን የተሻለች መኖሪያ እንድትሆነን በማገዝ፣ በስልጣኔ መዝገብ ላይ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል፡፡
ወዳጄ፡- የፍላጎትና አቅርቦት መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የአንድ ቁስ ዋጋ የሚጨምረውና የሚቀንሰው፣ የሚሰጠው ጥቅም በጊዜና በቦታው ሲለካና የአስፈላጊነቱ ምክንያት በማህበረሰቡ ባህል ሲመዘን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሃሳብም እንደዚሁ ነው፡፡ ቀደም ሲል ዓለምን የነቀነቁ፣ ታላላቅ ጦርነቶችን የቀሰቀሱ የዕምነት፣ የቅኝ ግዛት፣ የርዕዮተ ዓለም ወዘተ አስተሳሰቦች ዛሬ ዋጋቸው ቀንሷል፡፡ የዓለም ህዝቦች የሚያተርፉት አብሮ ከመኖር፣ ከመተጋገዝ፣ በነጻነት ከማሰብ፣ በህግና በዴሞክራሲ በመተዳደር እንደሆነ ተረድተዋል:: ባልኖሩበትና በሌሉበት “ነበር” በተባለ ተረት፣ ተረት መታወር ዛሬን አለመኖር፣ ነገን አለማሰብ መሆኑን አውቀውታል፡፡ በሌለ ጠላት ላይ ጦር መስበቅ፣ የቅዠት ፊልም ተዋናይ መሆን ነው ይላሉ - እንደ ዶን ኪሾት!!
ወደኛ ጉዳይ ስንመጣ፣ አዲሱ ዓመት ብሩህ ተስፋ የሚታይበት እንደሆነ፣ ገና ከመጀመሪያው በታላላቅ ክንዋኔዎች መታጀቡ ይመሰክራል፡፡ ለ300 ሺህ ተማሪዎች ዩኒፎርም፣ የትምህርት ቁሳቁስና ምግብ በማቅረብ ኑሮ ያደቀቃቸውን ቤተሰቦች ማገዝና ለብዙ ሺ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደ ተዓምር የሚቆጠር ክስተት ነው:: ለውጥ በተግባር ሲታይ “Bravo” ያሰኛል፡፡
ሌላው የአዲሱ ዓመት በረከታችን፣ የብዙ ታላላቆች ህልም የሆነውን ታላቁን ሽልማት ሀገራችን “ጀባ!” መባሏ ነው፡፡ Nobel Price!! የኖቤል ሽልማት የሚሰጣቸው የላቀ አስተሳሰብ ላላቸው የሰላም፣ የጥበብና የሳይንስ ሰዎች ነው፡፡ ኖቤል ሽልማት ማሸነፍ ዕፁብነት ነው፡፡ ኖቤል ሽልማት መሸለም ማለት፣ አገራችን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለመላቀቅና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ለምታደርገው ትግል፣ ዕውቅናና እገዛ መስጠት ነው፡፡ የኖቤል ሽልማት ማለት ሃሳብን በነፃነት ማስተጋባትንና ተከራክሮ ማሸነፍን ማበረታቻና ሃሜትና አሉባልታን “ኩም!” ማድረጊያ ነው፡፡ Shame the devil! እንዲሉ፡፡
“አንድ ዕፁብ ሥራ ከሚሊዮን ፍሬክርስኪ ሃሳቦች የበለጠ አቅም አለው” (One work of genuis is better than millions of commentaries) ይለናል፤ ታላቁ ኮፐን ሃወር!
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- የእግዜር ፍርድ “ከዛሬ ጀምሮ መላዕክትና ሰው አብረው እንዳይኖሩ፣ መላዕክት ለሰው እንዳይታዩ የሚከለክል ሲሆን እሱም በክፉም ሆነ በበጐ የማንንም አማላጅነት እንደማይቀበል የሚገልጽ ነበር፡፡ ወዳጄ፡- እዚህ ጋ አንድ ጐበዝ፣ እውነት እስካለው ድረስ፣ ታሪክን መቀየር እንደሚችል አያሳይምን? በነገራችን ላይ፡- “Masses not, but genuises change the world” በማለት የጻፈልን ድንቅ የዓለማችን ጠቢብ ማን ነበር??
ሠላም!!


Read 1170 times