Print this page
Saturday, 19 October 2019 13:32

ጐንደር በልዩ ክልከላ መመሪያ ስር ውላለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 - በግጭት የተሳተፉ እስከ ጥቅምት 30 የምህረት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል
              - በከተማዋ መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ላልተወሰነ ጊዜ ተከልክሏል
                         
                የአማራ ክልል የፀጥታና ደህንነት ካውንስል በማዕከላዊና ምዕራብ ጐንደር፣ በቅማንት ብሔረሰብ አስተዳደርና በጐንደር ከተማ ልዩ ክልከላ ተግባራዊ ማድረጉ ታውቋል፡፡
ከመስከረም 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በእነዚህ አካባቢዎች የቅማንት የራስ አስተዳደር ኮሚቴ የተከተለው በሃይል ምላሽ ለማግኘት የመሞከር ሂደት አካባቢውን አለመረጋጋት ውስጥ መክተቱንና በዚህም በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የገለፀው የአማራ ክልላዊ መንግስት ፀጥታና ደህንነት ም/ቤት ይህን አለመረጋጋትና ግጭት ለመቀልበስ ልዩ ክልከላና ውሣኔ ለማውጣት መገደዱን አስታውቋል፡፡
ይህን ልዩ የክልከላ ውሣኔ ተግባራዊ ለማድረግም የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ፀጥታ ሃይል፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት በጥምረት እንደሚሠማሩና እንደሚሠሩም ም/ቤቱ አስገንዝቧል፡፡
ም/ቤቱ በ11 ነጥቦች የተዘረዘሩ ክልከላዎችንና ውሣኔዎችን ነው ይፋ ያደረገው፡፡  በዚህ መሠረት፤ ማንኛውንም የሃይል እንቅስቃሴና እርምጃ በመውሰድ የሰው ህይወትና ንብረትን ከአደጋ መታደግ፣ በወንጀል ድርጊቱ ላይ የተሳተፉትን ወገኖች በቁጥጥር ስር በማዋል፤  ለህግ በማቅረብ፣ እንዲሁም ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ፣ የዓመፅ ተግባርን እንዳይቀጥል የማድረግ ተልዕኮ ለፀጥታ ሃይሉ ተሰጥቶታል፡፡
በተለያየ ምክንያት ወደ ግጭት የገቡ ቡድኖችና ግለሰቦች በአስቸኳይ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በመመለስ ያላቸውን ልዩነቶች እንዲፈቱ ጥሪ ያቀረበው ም/ቤቱ፤ ከእንግዲህ በሃይል እርምጃ መብቴን አስከብራለሁ ብሎ የሚንቀሳቀስ ወገን የአፀፋ እርምጃ እንደሚወሰድበት አስጠንቅቋል፡፡
ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን በቀጠናው ላይ ለሚደረግ የፀጥታ ሃይል ስምሪት የመተባበር፣ ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠትና ድጋፍ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ያሳወቀው መመሪያው፤ ይህን የሚያደናቅፍ ማንኛውም ተግባር ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበት ብሏል፡፡
መንግስት ለክልሉ ደህንነት ባሰማራቸው የፀጥታ ሃይሎች ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች ውጪ በተጠቀሱት የክልሉ ዞኖች ላልተወሰነ ጊዜ ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን ይዞ የተገኘም የሚወረስበት መሆኑ በዚሁ መመሪያ ተደንግጓል፡፡
የቅማንት ብሔረሰብ አስተዳደር ከዚህ ቀደም በተወሰነው ህጋዊ ውሣኔ መሠረት በአፋጣኝ በህዝብ ይሁንታ የሚደራጅ የራስ አስተዳደርን በማቋቋም፣ ሁሉም አገልግሎት እንዲጀምር ማድረግ ይገባል ያለው መግለጫው፤ ይህን የሚያደናቅፍ የሃይል እርምጃ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡
በተለያየ ምክንያትና ሰበብ ፍላጐትን በሃይል ለማሳካት በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ የነበረው ቡድንና ግለሰብ እስከ ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሠላማዊ ሁኔታ እንዲመለስና የክልሉ መንግስትም በድጋሚ ይቅርታ እንዳደረገለት መግለጫው አትቷል፡፡ ሆኖም በሰው ግድያ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች ጉዳይ በህግ ይታያል፡፡
በየዞኑ በየወረዳውና በየቀበሌ ውስጥ ለሚፈጠሩ ወንጀሎችና ፀረ ሠላም እንቅስቃሴዎች በየደረጃው ያለው አመራር፣ ነዋሪና ዜጋ የመቆጣጠር፣ የማሳወቅ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ኃላፊነት አለበት ያለው መግለጫው፤ ይህ ካልሆነ ግን ተጠያቂነትን ከማስከተሉም በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኝ ማንኛውም መሳሪያና ትጥቅ ሙሉ በሙሉ ተራግፎ ለመንግስት ገቢ ይሆናል ብሏል፡፡
በኢ-መደበኛ አደረጃጀትና ከክልሉ መንግስት ባልተሠጠ ኃላፊነት ህግን ለማስከበር በሚል ሰበብ የሚከናወን ማንኛውም እንቅስቃሴ የተከለከለ ሲሆን ተጠያቂም ያደርጋል፡፡
ከጐንደር - መተማ፣ ከጐንደር-ሁመራ፣ ከጐንደር-ባህር ዳር፣ ከጐንደር - ደባርቅ የሚወስዱ መንገዶች  ክፍት መሆናቸውን የጠቆመው መመሪያው፤ ይሄን ለማደናቀፍ የሚደረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ያስጠነቅቃል፡፡
እነዚህ ክልከላዎችና ውሣኔዎች ላልተወሰነ ጊዜ ተግባራዊ ሲደረጉም ህግና ስርአትን ተከትለው እንደሚሆን ም/ቤቱ አስገንዝቧል፡፡
በሌላ በኩል በጐንደርና አካባቢዋ እስከ ትናንት በስቲያ ሃሙስ ድረስ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ምንጮች ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን፤ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው፤ ከሁለት ሣምንታት በላይ በቆየው አለመረጋጋት በርካቶች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውንና መሞታቸውን እንዲሁም መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ምንጮችን ጠቅሰው ዘግበዋል፡፡    

Read 1579 times