Saturday, 19 October 2019 13:23

እነሆ “የመደመር” እሳቤዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

 የዶ/ር ዐቢይ ‹‹መደመር›› ዛሬ ይመረቃል
                      

            ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በይፋ መቀንቀን የጀመረውን የ“መደመር” እሳቤ የሚተነትነውና በሦስት ቋንቋዎች፡- በአማርኛ፣ ኦሮምኛና እንግሊዝኛ  የተዘጋጀው “መደመር” የተሰኘ መጽሐፍ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባን ጨምሮ በ20 የአለም ከተሞች ይመረቃል፡፡
በአንድ ሚሊዮን ቅጂዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ማተሚያ ቤቶች ደረጃውን ጠብቆ እንደታተመ የተነገረለት መጽሐፉ፤ በ278 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ዋጋው በ300 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡
ዛሬ የሚመረቀው መጽሐፍ የ‹‹መደመር›› እሣቤን ከአጠቃላይ መሠረታዊ ሃሳቡ ጀምሮ የሚያብራራ የእሣቤው ማጥመቂያ ነው ተብሏል፡፡
የቀድሞውን መልካም ነገር ይዞ ዛሬ ላይ በህብረት በመስራት፣ የነገን ህይወት ብሩህ ማድረግ የሚል ጥልቅ እሣቤ የሚያንፀባርቀው መደመር፤ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት የመፍጠር፣ የዜጐችን ክብር የማረጋገጥና ብልጽግናን እውን የማድረግ ግቦች እንዳሉት በመጽሐፉ ተብራርቷል፡፡
አዲሱ መጽሐፍ፤ የቀድሞ መንግስታት ሲመሩባቸው የነበሩ የፖለቲካ ርዕዮተ አለሞችና እሣቤዎችን የሚገመግም ሲሆን ኢህአዴግ ሲመራበት የቆየውን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ አለምን ከመደመር እሣቤ ጋር እያነፃፀረ ይተነትናል፡፡  
አብዮታዊ ዲሞክራሲ የነበረውን ጥንካሬና ጉድለት በስፋት የሚያስቃኘው “መደመር”፤ ከዚህ በኋላ ሀገሪቱ እንደ ፖለቲካ እሳቤ ብትከተለው መልካም ይሆናል የሚለውን “መደመር”በስፋት የሚያስቃኝ “መደመር”፤ ከፖለቲካ እሣቤው አኳያ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ቢሆንም ከዓለማቀፍ ተሞክሮዎች ግብአትን የወሰደ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በእኩል ማገልገል የሚቻልባቸውን መንገዶች የሚያሳይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
መደመር በፖለቲካ እሣቤው ውግንናው ለአንድ የህብረሰብ ክፍል ሳይሆን ለአርሶ አደሩ፣ ለከተሜው፣ ለአርብቶ አደሩ… እኩል የወገነ ነው፡፡
“መደመር” በፖለቲካ አተያዩ ቀድሞ የተገኙ ድሎችንና ውጤቶችን የበለጠ የሚያሰፋ፣ ያለፉ ኢትዮጵያውያንን ስኬቶችን የሚያከብርም ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ስብራት ጭቆና መሆኑን የሚገልፀው መጽሐፉ፤ ምን አይነት ጭቆናዎች የሚሉትን በምልአት ይተነትናል:: በሀገሪቱ የነበሩ፣ ያሉና ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ የፖለቲካ ጥያቄዎችንና ባህሪያቸውንም ይተነብያል፤ ያቀርባል፡፡
አሁን የተጀመረው ለውጥ የመጨረሻ ግብም ሀገሪቱን ከጭቆናና ከአመጽ አዙሪት የሚያስወጣ፣ ዲሞክራሲን መገንባት መሆኑን በመጠቆም፤ ዲሞክራሲ የሚገነባባቸውን አማራጮች በመደመር እሣቤ ያስቀምጣል፡፡
የመደመር እሣቤ በፖለቲካዊ እይታው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲን ለመገንባት አዳጋች ይሆናሉ የሚላቸውን ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸውን ይጠቁማል፡፡
ሌላኛው የመጽሐፉ ክፍል ኢኮኖሚን በመደመር እሣቤ የሚተነተነው ሲሆን፤ በዚህ ክፍል የእስከዛሬው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጉዞ ያስገኘው ጥቅምና ውስንነቶች እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች ተዳስሰዋል፡፡
ባለፉት አመታት በነበረው የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ክፍተት ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖር፣ የስራ አጥነት መንሰራፋት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የሌብነት መበራከት ይገኙበታል፡፡ የእነዚህን ባህሪና መገለጫቸውን፣ የጉዳታቸውንም መጠን  መጽሐፉ ይተነትናል፡፡ ኢትዮጵያ 50 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ የውጭ እዳ እንዳለባትና ይህም እያንዳንዱ ሰው በነፍስ ወከይ የ15ሺህ ብር እዳ አለበት ማለት እንደሆነ የየድርሻችን አካፍሎ ይነገርናል፡፡
ኢኮኖሚው አሁን ካለበት ችግር ማላቀቅ የሚቻልበትን የመፍትሔ ሃሳብ እንዲሁም የመደመር እሣቤ በማይክሮና ማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ የሚያንፀባርቃቸው አዳዲስ እሣቤዎችም በመጽሐፉ ተንፀባርቀዋል፡፡ የነፃ ገበያ ስርአትን የሚደግፈው “መደመር”፤ የኢንዱስትሪው ክፍለ የኢኮኖሚ ምሰሶ መሆኑን ይተነትናል፡፡
መደመር ከውጭ ግንኙነት አንፃር ደግሞ አዎንታዊ አለማቀፍ አዝማሚያዎችን፣ አሉታዊ ክስተቶችንና ነባራዊ ሁኔታዎችንና በአለም ላይ ያሉ ወቅታዊ ፉክክሮችን በስፋት የሚተነትን ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያን ሚና ያስቃኛል፡፡
በመጽሐፉ የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታም በስፋት ተመልክቷል፡፡ የውጭ ግንኙነት በ‹‹መደመር›› እሣቤ፡፡ ቀድሞ የተገኘን መልካም ሁኔታ የማሳደግ መርህ ላይ የተመሠረተ፣ መግባባትና ትብብርን ያስቀደመ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር፣ ጐረቤት ሀገራትን የሚያቅፍ ግንኙነት መመስረት የሚሉት ተጠቃሽ ትልሞቹ ናቸው፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ክብርና መብት ማረጋገጥ ላይ “መደመር” ጽኑ አቋም እንዳለው በመጠቆም፤ እንዴት ማስከበር ይቻላል የሚለውንም ይተነትናል፡፡
ሀገራዊ ክብርን በማሳደግ እንዴት ተሰሚነትንና ተጽእኖ ፈጣሪነትን ማሳደግ እንደሚቻል፤ ኢትዮጵያ በአለማቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ሊኖራት የሚችለውን የወደፊት ሚና በተመለከተም በውጭ ጉዳዩ የመደመር እሣቤ በስፋት ተቃኝቷል፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት በ“መደመር” እሣቤዎች ዙሪያ ከ10ሺህ በላይ የኢህአዴግ አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደተሰጣቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በቀጣይ የ “መደመር” እሣቤ ለውጡ የሚመራበት የፍኖተ ካርታ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡      


Read 8162 times