Saturday, 19 October 2019 13:20

በተስፋ የተሞላ ማነቃቂያ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ‹‹ትችላላችሁ፤ እንደምትችሉ አምናለሁ››


            እኔ ከአባቴና ከእናቴ ቤት ስወጣ 13 ዓመቴ ነው፡፡ ያሳደገኝ እግዚአብሔር ነው፡፡ እናንተንም እግዚአብሔር ያሳድጋችኋል፡፡ (አሜን ይላሉ ልጆቹ) ግን የእምነት ሰው መሆን አለባችሁ:: እንደምታድጉ እንደምትለወጡ ካመናችሁ… በጣም ብዙ ወጣቶች በጣም ብዙ ታዳጊዎች አላችሁ መለወጥ ማደግ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ሃይስኩል የጨረስኩት፣ መጨረስ ከሚገባኝ ጊዜ በስድስት በሰባት ዓመት ዘግይቼ ነው:: ይቻላል ከወሰናችሁ፡፡ ዋናው የናንተ ውሳኔ ነው፡፡ በኛ በኩል ዛሬ እንድትመጡና እንድታዩ የፈለግነው በኋላ በክፍያ ሲሆን፣ ፕሮቶኮል ሲበዛ፣ እንደናንተ ዓይነት ሰዎች፣ እውነተኛ አገር የሚወዱ፣ አገር የሚጠብቁ፣ ለጊዜው ብቻ እጅ ያጠራቸው ሰዎች የማይገቡበት ሥፍራ እንዳይሆን ነው፡፡ እናንተን ካላካተተ የኢትዮጵያ ሃብት መሆን አይችልም፡፡ እናንተም ኢትዮጵያው ናችሁ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሚያማምሩ የሃብታሞች ብቻ ሳይሆን የሌላቸውም ጭምር ስለሆነች…፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ቢያንስ ከ4ሺ እስከ 5ሺ የሚጠጉ የጐዳና ልጆችን ከጐዳና በማንሳት ማደሪያ ቦታ እንዲኖራቸው እየሰራን እንገኛለን፡፡ እስካሁን ተናግረን አናውቅም፤ ምክንየቱም ሁሉም ሲያልቅ ስለሚያምር ነው፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ እንጨርሳለነ:: አልጋ፣ ፍራሽ፣ አንሶላ የሚያግዙን ሰዎች ካገኘን በኋላ በዚህ ዓመት ከ4ሺ -5ሺ የጐዳና ልጆች እናነሳለን፡፡ በሚቀጥለው ዓመት እያልን ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ብዙ አይደላችሁም፡፡ 30ሺ -40ሺ የሚሆን ነው አዲስ አበባ ያለው:: ማደሪያ ካገኛችሁ ትናንሽ ሥራ ሰርታችሁ፤ ራሳችሁን የምትመግቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እናንተ አካባቢ ክሊኒክ ኖሮ፣ ቢያማችሁ እንኳን የምትታከሙበት ቢያንስ ማታ ማታም ቢሆን የምትማሩበት ነገር እንዲመቻች የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ እናንተ ግን በመደራጀት አሁን ከተማ ውስጥ አበባ ዛፍ እየተከልን ስለሆነ ያንን በመንከባከብ ብቻ… ውሃ በማጠጣት… በመኮትኮት የዕለት ምግባችሁን የምትሸፍኑበትን መንገድ ማመቻቸት የከተማውም የመንግስትም ሥራ ይሆናል፡፡ ከናንተ የሚፈለገው ሱስን መጠየፍ፣ ሌብነትን መጠየፍ፣ ጥላቻን መጠየፍ… ወስኖ መቀየርና ለአገር ኩራት መሆን ነው፡፡ ያንን ደግሞ ትችላላችሁ፡፡ እኛ ከጐናችሁ ነን፡፡ ትችላላችሁ… አምናለሁ እንደምትችሉ!!...››
(ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት የጎዳና ልጆች አንድነት ፓርክን በጎበኙበት ወቅት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ)  


Read 1539 times