Print this page
Saturday, 19 October 2019 13:15

ያልተዘመረላቸው የቤተ መጻሕፍት ባለሙያ!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 - ከ300 በላይ ቤተ መጻሕፍትን አደራጅተዋል
                - በ68 ዓመታቸው ከቤተ መፃሕፍት አልተለዩም


              በሰሜን ሸዋ ቆባስጥል በተባለ አካባቢ በ1934 ዓ.ም ነው የተወለዱት - ከአባታቸው መምህር ተክለሃይማኖት አዝብጤና ከእናታቸው ወለተሚካኤል ኃ/ሚካኤል፡፡ ላለፉት 53 አመታት፣ በኢትዮጵያ በሚገኙ ዋና ዋና የትምህርት ተቋማት ውስጥ በቤተ መጻሕፍት ባለሙያነት አገልግለዋል፡፡ ከ300 በላይ ቤተ መጻሕፍትን በመላ ሀገሪቱ አደራጅተዋል - አቶ ስምኦን ተ/ኃይማኖት፡፡ የ“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ባለቤትና መስራች በነበረው አሰፋ ጐሳዬ ስም የተቋቋመውን ‹‹ዕውቀትና ትጋት አሠፋ ጐሣዬ መታሰቢያ ቤተ መጽሐፍ” ያደራጁትም እኒሁ ጐምቱ ባለሙያ ናቸው፡፡ ባህር ማዶ ተሻግረውም በአገረ አሜሪካ አንድ ቤተ
መጽሐፍ አደራጅተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኑሮአቸውን በአሜሪካ ያደረጉትና ‹‹የመጻሕፍት ወዳጅ›› በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት አቶ ስምኦን፤ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት አጋጣሚ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተገናኝተው በሕይወታቸው፣ በሙያቸውና በወደፊት ዕቅዳቸው ዙሪያ እንዲህ አውግተዋል፡፡ እኒህን ያልተዘመረላቸውን የቤተ መፃሕፍት ባለሙያ ተዋወቋቸው፡፡ ዛሬም በ68 ዓመት ዕድሜያቸው ጡረታ ወጥተው አልተቀመጡም፡፡


              መደበኛ ትምህርት የጀመሩት ዘግይተው ነበር… በ16 ዓመትዎ…?
ያው እንግዲህ ተወልጄ ያደግሁት በገጠር ነው፡፡ የመጀመሪያ ህይወቴን የፈተንኩት በግብርናና በእረኝነት ነበር፡፡ በወቅቱ መደበኛ ትምህርት ቤት ባልገባም፣ የቤተ ክህነት ትምህርት ተምሬአለሁ፤ ድቁና፡፡ እኔ ከተወለድኩበት 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው መዘዝ፣ እስከ 4ኛ ክፍል የሚያስተምር ት/ቤት ሲከፈት፣ በቀጥታ 3ኛ ክፍል ነው የገባሁት፡፡ 3ኛ እና 4ኛን እዚያ ከተማርኩ በኋላ 5ኛ ክፍል ለመማር ደብረሲና ሄድኩ፡፡ 5ኛ ክፍል ትምህርቱ በጣም ስለቀለለኝ፣ ወደ 6ኛ ክፍል እንዲያሳልፉኝ ጠየቅናቸው፡፡ ‹‹ቆይ የመጀመሪያ ሴምስተር ውጤትህን እንይ›› አሉኝ፡፡ በመጀመሪያው ሴሚስተር 1ኛ ወጣሁ፤ ነገር ግን ቃላቸውን አልጠበቁልኝም፡፡ በኋላ ወደ ሞላሌ ሄጄ 6ኛ ክፍል ገባሁ፡፡ 7ኛ ክፍልም እዚያው ተማርኩ:: ነገር ግን 7ኛ ሳልጨርስ፣ ወደ 8ኛ እንዳልፍ ተደረግሁ፡፡ ምን አለፋህ ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን ትምህርት አራት ዓመት እንኳ ሳይፈጅብኝ ነው ያጠናቀቅሁት:: ከዚያ ሃይስኩል ደብረብርሃን ገባሁ፡፡ በኋላ ወንድሜ አዲስ አበባ ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ያስተምር ስለነበር እዚያ አስገባኝ፡፡ ባዶ እግሬን ቦላሌ ታጣቂ ሆኜ ነበር የገባሁት፡፡ እዚያ የሚማሩት ደግሞ የዘመነ አለባበስም አነጋገርም ያላቸው ነበሩ፡፡ በእንግሊዝኛዬ ዘዬ በጣም ይስቁ ነበር፡፡ ተማሪዎች እንደዚያ ሲስቁብኝ ‹‹ለምን እማራለሁ›› ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ከዚያም አንድ ቀን ቁጭ ብዬ ለራሴ እጣ አወጣሁ:: ‹‹ግብርና ወይስ የመንግስት ስራ›› የሚል:: “ግብርና” የሚል እጣ ሲወጣልኝ በቀጥታ፣ ከትምህርት ቤት ጠፍቼ፣ ወደ ሀገር ቤት ሄድኩ::
ትምህርቱን ትተውት…?
አዎ ሄድኩ፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ትውልድ ቦታዬ በእግሬ ተጉዤ ስደርስ፣ አባቴ እህል እያጨዱ አገኘኋቸው፡፡ ‹‹ና በል እጨድ›› አሉኝ፡፡ በጣም እስኪደክመኝ ድረስ አሠሩኝ:: በመጨረሻም ከባድ ሸክም አሸክመውኝ ወደ ቤት ሄድን፡፡ ለካንስ ነገሩ ቅጣት ነበር:: አባቴ ተናደው ስለነበር፤ እቤት ከገባን በኋላ ሊገርፉኝ ዳዳቸው፤ ግን አላደረጉትም፡፡ በንዴት እራታቸውን እንኳን ሳይበሉ ነው ያደሩት:: ጠዋት ‹‹ምን ልታደርግ መጣህ? እኔ እዚህ መርፌ የለኝ ክር የለኝ፤ በእናንተ ያልፍልኛል ብዬ ሳስብ፣ ጭራሽ አንተ ትመጣልህ›› ብለው ገሰፁኝ ተቆጡኝ፡፡ እየመከሩኝ ወደ አዲስ አበባ ይዘውኝ ተመለሱ፡፡ በኋላ ከቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ወጥቼ፣ ጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ወንድሜ እንድገባ አደረገ፡፡ በራሴ ምርጫ ማለት ነው፡፡ ከ10ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ጀነራል ዊንጌት ነው የተማርኩት፡፡ የ12ኛ ክፍል ውጤቴ ለምመኘው የህክምና ትምህርት የሚያበቃ አልነበረም፡፡ በዚህ አዝኜ እያለ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር፣ እዚያው ቀርቼ የቤተ መጽሐፍት ባለሙያ (ላይብረሪያን) እንድሆን ጠየቁኝ፡፡
እንዴት ሊጠይቅዎት ቻሉ?
በወቅቱ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያሉ ስድስት የተለያዩ ክበቦች አባልና መሪ ነበርኩ፡፡ በዚያ ያውቁኝ ነበርና፣ ‹‹የምትወደውን ሳታገኝ ስትቀር ያገኘኸውን ውደድ›› ብለው መክረው፣ የላይብረሪው ኃላፊ አደረጉኝ፡፡ ከቤተመፃሕፍት ጋር የተገናኘነው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ይኸው እስካሁንም እኔና ቤተመፃሕፍት አልተለያየንም:: ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 53 አመታት በዚህ ስራ ውስጥ እገኛለሁ፡፡
በወቅቱ ስለ ቤተመጽሐፍት ሙያ ሥልጠና ይሰጥ ነበር?
አዎ፡፡ ጀነራል ዊንጌት ቤተ መፃሕፍት ውስጥ እያለሁ፣ ወደ 200 የሚሆኑ ተማሪዎችን ስለ ላይብረሪ ሳይንስ አስተምሬ፣ ስለ ቤተ መጽሐፍት ግንዛቤ አስጨብጬ፣ በፈረቃ እንዲያገለግሉ አድርጌአለሁ፡፡ እኔ መጽሐፍት ፍለጋ ስወጣ፣ ተማሪዎቹ ነበሩ እኔን ተክተው የሚሠሩት፡፡ ቤተ መፃህሐፍቱ በሦስት አመታት ውስጥ በጣም ነበር ያደገው፡፡
በወቅቱ ሚስስ ፓንክረስት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቤተ መጽሐፍት ኃላፊ ነበረች፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 4 ኪሎ እንድመደብ አደረገች:: እዚያ እየሠራሁ ላይብረሪ ሳይንስ አጥንቼ ዲፕሎማዬን አገኘሁ፡፡ ከሁለት አመት በኋላ ደግሞ ወደ ኬኔዲ ላይብረሪ ተዛወርኩ፡፡ እዚያ እየሠራሁ የእድገት በህብረት ዘመቻ መጣ፡፡ በዚያ ዘመቻ ላይ ቤተ መፃህፍትን የማሰራጨት ስራ እንድሠራ ተጠየቅሁ፡፡ እውነት ለመናገር፣ ይሄን ስራ በፍቅር ደስ ብሎኝ ነበር የሠራሁት፡፡
ያኔ በጣም ብዙ መፃህፍት ነበር በየክፍለ ሀገሩ የተሠራጨው፡፡ ግን ዛሬ ያ ሁሉ መፃህፍት የት እንደገባ አላውቅም፡፡ ከዚያ በኋላ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቢኤ ድግሪዬን አግኝቼ፣ በትርፍ ጊዜዬ ዩኒቨርስቲ አስተምርም ነበር፡፡
እስቲ በኬኔዲ ቤተ መጽሐፍት ስለነበርዎት የሥራ ጊዜ ያጫውቱኝ…?
እዚያ ሳገለግል ከተማሪዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረኝ፡፡ ማታ ማታ ሙዝና የሚበሉ ነገሮች ሁሉ ያመጡልኝ ነበር፡፡ በአጋጣሚ እኔ ዊንጌት ላይብረሪያን ሆኜ ስሰራ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 9ኛ ክፍል ነበሩ፡፡
ያኔ ያውቋቸው ነበር?
በቅርብ አላውቃቸውም፡፡ ነገር ግን ሁሌ ተማሪዎችን ስብሰባ እየጠሩ ያነጋግሩ ስለነበር በመልክ በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ ሁልጊዜ ከእራት በፊት ባለችው ጊዜ ተማሪዎችን ይሰበስቡ ነበር፡፡ ምን እንደሚማከሩ ግን አላውቅም፡፡ ምናልባት የወደፊቱን መንገድ እያዘጋጁ ነበር ይሆን?
በቤተመፃሐፍት ባለሙያነት ጥሩ ልምድ የቀሰሙት የት ነበር?
የላይብረሪ ባለሙያነትን የተማርኩት ኬኔዲ ቤተ መፃህፍት ነው፡፡ በእውነቱ ግሩም ቤተ መፃህፍት ነበር፡፡
የኢሠፓ አደራጅ ኮሚሽን ሲመሰረትም በቤተ መጻሕፍት ባለሙያነት ሠርተዋል፡፡ እስቲ ስለሱ ይንገሩን…
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እያለሁ ነበር በዝውውር ወደ ኢሠፓአኮ ላይብረሪ የሄድኩት:: ቤተ መጻሕፍቱ 30 ያህል ሠራተኞች ነበሩት:: ከጓድ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ጋር ጥሩ ቅርበት ነበረን፤ እኔ “አንተ” ስለው፤  እሱ “አንቱ” ነበር የሚለኝ፡፡ ቤተ መጽሐፍት መምጣት ያዘወትራል፡፡ እኔ ወንበር ጋ ቁጭ ብሎ፣ ሻይ እየጠጣን ብዙ እናወጋ ነበር፡፡
ከፕሬዚዳንቱ ጋር ምን ጉዳዮችን ነበር የምታወጉት?
ብዙ ነገሮችን… የግሉን ጉዳይ ሳይቀር ያወጋኛል፡፡ ለምሣሌ ‹‹እኔ የማልፈልገው ነገር ነው የሚደረግልኝ፤ ወደ አንድ ቦታ ስሄድ ቀይ ምንጣፍ የሚነጠፍልኝን ነገር አልወደውም… አሁን ለኔ ቀይ ምንጣፍ ማንጠፍ ለምን ያስፈልጋል?›› እያለ ያወጋኝ ነበር፡፡ ለኃላፊዎቼ ስለኔ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ‹‹ስሞኦን የሃይማኖት ሰው ስለሆነ የፓርቲ አባል እንዲሆን አታስጨንቁት››
ሌላው ደግሞ ‹‹ስሞኦን ይገዛ ያለው መጽሐፍ በሙሉ ያለ ምንም ውጣ ውረድ እንዲገዛ›› የሚል መመሪያም ሰጥቶልኝ ነበር፡፡ በተረፈ ኮሎኔል መንግስቱን በየቀኑ እያገኘሁ ሲያወጋኝ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር፣ በጣም ጨዋ ሰው መሆኑን ነው፡፡ በእጅጉ ስነ ምግባር ያለው ጨዋ ሰው ነበር፡፡ ነገር ግን በዙሪያው ያሉ ሰዎች ብልሹ እንደነበሩ ተገንዝቤአለሁ፡፡ በዙሪያው ጥሩ ጥሩ ሰው ቢኖር ኖሮ፣ እሱም እንደዚያ አይሆንም ነበር፡፡
ኢሠፓአኮ ተመድበው ምን የተለየ ተግባር አከናወኑ?
ኢሠፓአኮ ለሦስት ወር ያህል ያልዞርኩበት የኢትዮጵያ ክፍል አልነበረም፡፡ በየቦታው እየተዘዋወርኩ ቤተመፃህፍት በሚቋቋምበት ሁኔታ ላይ መክሬያለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ፤ በኔ አስተባባሪነት 300 ቤተ መጽሐፍት በመላ ሀገሪቱ ተከፍተው ነበር፡፡
በየፓርቲው ጽ/ቤት ነበር ቤተ መፃህፍቱ የተቋቋሙት፡፡ መፃህፍት ከውጪ ነበር የምናስመጣው፡፡ እነዚያን ሁሉ መፃህፍት በዘርፍ መለየት፣ መለያ መለጠፍ፣ ማህተም ማድረግ… በጣም ከባድና አድካሚ ስራ ነበር፡፡ በዚህ ስራ ላይ 500 ያህል ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡
ምን አይነት መፃህፍት ነበሩ? ብዛታቸውስ ምን ያህል ይሆናል?
 ከፖለቲካ ውጪ ያሉ ልብ ወለዶች፣ ዲክሽነሪዎች፣ ኢንሳይክሎፒዲያዎች… ነበሩ:: ብዛታቸው ቢያንስ 4 ሚሊዮን መጽሐፍት ይገመታሉ፡፡
አሁን ቤተ መጽሐፍቱ ያሉበት ሁኔታ ይታወቃል?
የኔም ጥያቄ እሱ ነው፡፡ እነዚያ ሁሉ ቤተመጽሐፍትና መፃህፍት የት እንደደረሱ አላውቅም፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ አብዛኛው ቤተመጽሐፍት ተዳክሞ መዘጋቱን ሰምቻለሁ:: ፕሮጀክቱ እንደወጣ የቀረ አይነት ነው፡፡ እኔ እነዚያን 300 ቤተ መጻሕፍት ካቋቋምኩ በኋላ ወደ ኢሠፓ የካድሬ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ቤተመጽሐፍት ተዛወርኩ፡፡ ቤተ መጽሐፉቱ ሙሉ ለሙሉ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም መጽሐፍት የተሞላ ነበር፡፡ ይህ የካድሬ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሲዘጋ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር፣ የኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ተብሎ ቤተ መጽሐፍቱ ዳግም ተደራጀ፡፡ እዚያ ለሁለት አመት ሰርቻለሁ፡፡ ኢህአዴግ ከገባ በኋላ ነገሩ ሁሉ አበቃ፡፡ በሽግግሩ ወቅት የማስታውሰው፣ ለ3 ወር ያህል ያለ ደመወዝ መስራቴን ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት እንዴት ለቀቁ?
እኔ ሙሉ ህይወቴን እንደ አይነ ስውራን የምጨነቅበት ጉዳይ የለኝም፡፡ ላለፉት 20 አመታት እኔም በግላኮማ ምክንያት አንድ አይኔ ማየት አይችልም፡፡ የዩኒቨርሲቲው አይነ ስውራን ጉዳይ በጣም ያስጨንቀኝ ስለነበር፣ ባልቻ ሆስፒታል የነፃ ህክምና አስፈቅጄላቸው ይታከሙ ነበር፡፡ በዚህም አለቃዬ ‹‹አንተ ለአይነ ስውራን ታዳላለህ››  በሚል ይቆጣኝ ነበር፡፡ አንድ ቀን የመልቀቂያ ደብዳቤ ጽፌ፣ በፍቃዴ ጡረታ እንድወጣ ጠየቅሁኝ፡፡ ከዚያም ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፡፡
የዩኒቲ ዩኒቲን ዩኒቨርሲቲን ቤተ መጻሕፍት ያደራጁት እርስዎ ነዎት?   
ሙሉ ለሙሉ እኔ ነኝ ያደራጀሁት፡፡ ዩኒቲ ስገባ እኔ ብቻ ነበርኩ በላይብረሪያንነት የተቀጠርኩት፡፡ ምንም መፃህፍትም ሆነ መደርደሪያ አልነበረውም - ቤተመፃህፍቱ፡፡ የዩኒቲ ቤተ መጽሐፍትን ሳደራጅ፣ ከመጽሐፍ አሳታሚዎች፣ ከፈርኒቸር ቤቶች ጋር በሚገባ ተዋውቄያለሁ፡፡ በሰባት አመት ውስጥ ሰባት ትልልቅ ቤተ መጻሕፍትን በተለያዩ የዩኒቨርስቲው ቅርንጫፎች አቁቋቁሜያለሁ:: በተለይ ናዝሬት በግል ትራንስፖርቴ እየመላለስኩ ነበር ቤተመፃህፍቱን ያደራጀሁት:: ከዩኒቲ የለቀቅሁት ፕሬዚዳንቱ በአንድ የሴኔት ስብሰባ ላይ ‹‹ላይብረሪው ራዕይ የለውም›› ብሎ ሲናገር ተናድጄ ነው፡፡ “እንዲህ እየለፋሁ እንዴት እንዲህ ይህገራል” ብዬ ተናደድኩ፡፡ በእርግጥ ይቅርታ ጠይቆኛል፡፡
ለመሆኑ ስንት ነበር የሚከፈልዎት ደመወዝዎን ማለቴ ነው?
የሚገርመው… ማስተርስ ቢኖርህ 5 ሺህ ብር እንከፍልህ ነበር፤ አንተ ግን ያለህ የመጀመሪያ ድግሪ ስለሆነ 3 ሺህ ብር እንከፍልሃለን አሉኝና በዚያ ደሞዝ ነበር የምሰራው፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ስሰራ፣ በዋናነት ጉዳዬ ገንዘቡ አልነበረም፡፡ እርካታውን ነበር የምፈልገው፡፡
ከዩኒቲ በኋላስ የት ሠሩ?
አልፋ ዩኒቨርስቲ ገባ፡፡ እዚያም በተመሳሳይ፣ መደርደሪያው ቢኖርም፣ መጽሐፍት አልነበሩም:: መደርደሪያውም ቢሆን ደስ የማይል ነበር:: ስለዚህ በራሴ ተፍጨርጭሬ ነው እንደገና ላይብረሪውን ያደራጀሁት፡፡ ስራው አድካሚ ነበር፡፡ አደራጅቼ ከጨረስኩ በኋላ በየሁለት አመቱ ነበር ኮንትራቴ መታደስ የነበረበት፤ እነሱም እንደተለመደው ድካሜን አላሰቡትም:: በቃላት ጭምር ያስቀይሙኛል፡፡ የበዓል ቦነስ ይከለክሉኝ ነበር፡፡ በኋላ ለምን አልተወውም ብዬ ወሰንኩ፡፡ ከዚያም ብዙ ጊዜ የአይነ ስውራን ጉዳይ ያሳስበኝ ስለነበር፣ አንድ ነገር ባደርግ ብዬ ‹‹ዋልታ የአይነስውራን ማህበር››ን አቋቋምኩ፡፡ ዘጠኝ የቦርድ አባላት ነበርን፤ ኋላ ግን መንግስት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በተመለከተ አዲስ መመሪያ ሲያዘጋጅ እሱም ቀረ፡፡ ነገር ግን ለህሊናዬ እርካታ ለ6 ወር ያህል አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በር ላይ በየቀኑ በመቀመጥ፣ አይነስውራን ተማሪዎችን አስፓልት አሻግር ነበር፡፡ አሜሪካ ያሉት ልጆቼ ይሄን ሰምተው፣ “በል ቶሎ ና” ብለው ቪዛ ላኩልኝ፡፡ ምንም የምሰራው ስራ ስላልነበረኝ ባልወድም የግዴን ሄድኩ፡፡
አሜሪካም ገብተው ከቤተ መፃሕፍት አልራቁም ልበል?
እውነቱን ለመናገር አሜሪካ የሄድኩት ለመደበቅ ነበር፡፡ እዚህ ካለው ነገር ሁሉ ለመደበቅ ብዬ ነው የሄድኩት፡፡ እዚያ በሄድኩ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ቤታችን አጠገብ ወዳለ ‹‹አውሮራ ሴንትራል›› ጐበኘሁ፡፡ ከዚያም “በበጐ ፍቃድ ላገለግል” ብዬ ጠየቅኋቸው፤ ተቀበሉኝና ወዲያው በሳምንት ሦስትና አራት ሰአት በነፃ ማገልገል ጀመርኩ፡፡
ላይብረሪው በባህሪው መጠነኛ የሚባል ነበር፡፡ ትንሽ እንደቆየሁ ‹‹ለምን አናስፋፋውም›› አልኳቸው ‹‹እንዴት?›› አሉኝ፡፡ ‹‹በቃ ኃላፊነቱን ስጡኝ›› ብያቸው፣ ኀላፊነቱን ተቀብዬ በ8 ወራት ውስጥ ቀንና ሌት ሳልተኛ - በአንድ ዲፓርትመንት ብቻ ተደራጅቶ የነበረውን ላይብረሪ ወደ ስምንት አደረስኩትና አዘመንኩት፡፡ የሚገርመው ግን እነሱ አመስጋኝ ናቸው፤ (አሜሪካኖቹን ማለቴ ነው) እንደኛ አገር አይደሉም፡፡ የአድናቆትና የምስጋና ደብዳቤ አበርክተውልኛል፡፡ በነገራችን ላይ ያኔ የዊንጌት ኃላፊም የውጭ ሀገር ሰው ነበሩ፡፡ እሳቸውም የምስክር ወረቀት ሰጥተውኛል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ስምኦንን የመሳሰሉ ሰዎችን ትፈልጋለች›› የሚል አድናቆት የያዘ የምስክር ወረቀት ነው ያበረከቱልኝ፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሁለቱንም ዕውቅና የሰጡኝ የውጭ ሀገር ሰዎች ናቸው፡፡ የኛዎቹ በአንፃሩ አስከፍተው ነው የገፉኝ፡፡ ይሄን ሁሌም ሳስበው ይገርመኛል፡፡
በአሜሪካ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡበት ቤተመጽሐፍ ውስጥ ኢትዮጵያውያን  ይጠቁሙበታል?
አልፎ አልፎ ነው እንጂ ብዙም ልማዱ የለም፡፡ እንደውም በአካባቢው ኢትዮጵያውያን የሚሰባሰቡበት እኔም የማስቀድስበት፣ ዳግማዊ ግሸን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡ በየሣምንቱ እሁድ፤ በትንሹ 400 ሰው ይታደማል፡፡ አንድ ቀን የአውሮ ሴንትራል ቤተመጽሐፍ ኃላፊን ይዠው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሄድኩና ‹‹እባክህ ቤተመጽሐፉን እንዲጠቀሙበት ቀስቅስልኝ›› አልኩት፡፡ እሱም ቅስቀሳውን አደረገ፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ አውሮራ ላይብረሪ፣ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ቤተመፃሕፍት እስኪመስል ድረስ ኢትዮጵያውያን እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ አሁን ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ቤተመፃሕፍቱ እየሄዱ ነው፡፡ በስምንት ወር ውስጥ ያንን ቤተመፃሕፍት አስፍቼ ሳዘምነው፣ እዚያ ውስጥ የሚሠሩ ጥቁሮች ሳይቀሩ ‹‹አኮራኸን›› ብለውኛል፡፡
በአሜሪካ እድር እንዳቋቋሙም ሰምተናል…?
አዎ፡፡ ሁሌ ሰው በሞተ ቁጥር ገንዘብ አዋጡ እየተባለ ነበር አስከሬን ወደ ሀገር ቤት የሚላከው፡፡ ይሄ እንዴት ያሳፍራል መሰለህ፡፡ በተለይ እድርን የመሰለ ማህበራዊ መሰባሰቢያና መረዳጃ እያለን፣ ለዚህ መፍትሄ አለመዋሉ ያሳፍራል፡፡ የሚገርመው በኮሎራዶ ግዛት ብቻ 40 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ፡፡ እናም ‹‹እድር ለምን አናቋቁምም?›› በሚል ተመካክረን ነው ያቋቋምነው፡፡  እኔ የእድሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሆኜ እየሠራሁ ነው፡፡ ፕሬዚዳንታችን የአለማያ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የነበረው ዶ/ር ደጀኔ መኮንን ነበር፡፡ እድሩ ከተመሰረተ ሁለት አመት ሆኖታል፡፡ እኔም በአብዛኛው በአውቶቡስ ስለሆነ፣ አውቶቡስ ላይ ያገኘሁትን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ስለ እድሩ እያስረዳሁ፣ በርካታ አባላትን መልምያለሁ፡፡ አሁን ዕድራችን 550 አባላት አሉት፡፡
እድሩ ሰው ሲሞት 10 ሺህ ዶላር የአስከሬን መላኪያ ይሰጣል፡፡ ያስተዛዝናል፡፡ ማህበራዊ ግንኙነቱን ያጠናክራል፡፡ በስልክም ቢሆን እርስ በእርስ እናስተዛዝናለን፡፡ በቦርሳዬ የእድር አባል ፎርም ይዤ ነው የምዞረው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ሳገኛቸው፣ የእድሩ አባል እንዲሆኑ ፎርሙን አስሞላለሁ፤ የእድር ክፍያ እቀበላለሁ:: የምኖርበት አፓርታማም እየመጡ አባል የሚሆኑ ሰዎችም አሉ፡፡ በዚህ ሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ሰዎች ሞተውብን አስተዛዝነናል፡፡
በአሜሪካ ቆይታዬ ሌላው ደስ ብሎኝ የሠራሁት በጐ ተግባር፣ የአዛውንቶች ተንከባካቢ ድርጅቶችንና ኢትዮጵያውያን አዛውንቶችን ማገናኘት መቻሌ ነው፡፡ አሁን አዛውንቶቹ በድርጅቶቹ ውስጥ ደስ ብሏቸው እየዋሉ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡
ወደፊትስ ምን ዕቅድ አለዎት? ...አርፈው እንደማይቀመጡ ወይም ጡረታ እንደማይወጡ ስለተገነዘብኩ ነው ይሄን የምጠይቅዎት…ተሳስቻለሁ”?
ኢትዮጵያ ውስጥ የካበተ ልምድ ያለን ፕሮፌሽናል ላይብረሪያን ከ10 የምንበልጥ አይመስለኝም፡፡ ለወደፊት መንግስት የሚፈቅድ ከሆነ፣ በአንድ ማዕከላዊ እዝ ስር የሚተዳደር፣ ነገር ግን በመላ ሀገሪቱ ቅርንጫፎች ያሉት የቤተ መጽሐፍ ድርጅት ለማቋቋም እፈልጋለሁ:: ያ ድርጅት፣ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ቤተ መፃህፍትን የሚቆጣጠር ነው፡፡ የትምህርት ቤት ቤተ መጻሕፍት፣ ልዩ ቤተ መጻሕፍትና የህዝብ ቤተመጻሕፍትን… የሚቆጣጠርና የሚያደራጅ ይሆናል - ድርጅቱ፡፡ እግዚአብሔር ከፈቀደልኝ ይሄን እውን እውን ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡

Read 1071 times