Print this page
Saturday, 19 October 2019 13:00

በልፋት የተገኘ ተወዳጅነት

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

 ጋሽ አሰፋ ጫቦ፤ ለዛ ያለው ብዕር፤ እውነትን የሙጢኝ ያለ ሃሳብ ያለው ሰው ነው። ስለ ጥበብ ሲያወራ እንደ ጥንቅሽ ልጦ፣ ስለ ፖለቲካ ሲተርክ ከሥሩ ገሽልጦ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በቀር ህልም የለውም፡፡ የጋሞዋ ጨንቻ የትዝታ ስንቁ፣ የልጅነት ቀለሙ ናት፡፡ የህይወት ማንፀሪያ ዘንጉ፣ ፍቅርን መለኪያ ቱምቢውም ትመስላለች፡፡
ለዛሬው መጣጥፌ አንዲት ዘለላ ሃሳብ ከ “ትዝታ ፈለግ” መጽሐፉ እዋሣለሁ፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“ሀ ብዬ ሥራ የጀመርኩት ጐጃም ነበር:: የመጀመሪያ ልጄ የተወለደው ጐጃም ነው:: ኃይለሥላሴና ንግሥት ኤልሳቤጥ መጥተው የጢስ አባይ ግድብ ሲመረቅ የአይን ምስክርና ግብርም የበላሁ ነኝ፡፡ የባህር ዳር ከተማ ሲመሠረት “መጤ” ቁልፍ የከተማ ቦታ እየተመራ ጐጃሜው በገዛ አገሩ ተመልካች ስለሆነ “ጐጃሜ ተነቀስ” በሚል በ “ፖሊስና ርምጃው” ጋዜጣ ላይ ጽፌ ተባርሬ ጠፍቼ የወጣሁት ከጐጃም ነበር፡፡”
ጋሽ አሰፋ ሀገሩ ኢትዮጵያ ናት፡፡ “ጋሞነቴ ከኢትዮጵያዊነቴ ጋር ተጣልቶ እርቅ አልተቀመጥኩም” የሚል ሰው ነው - ጋሽ አሰፋ::
ሰው ሀገሩን ከጐጡ እኩል ሲያይ፡ ለሠፈሩ ብቻ ሳይሆን ለመላው ወገኑ ይሟገታል፡፡
ዛሬ የሽግግር ዘመኗ አዲስ አበባ ምጥም መልኩ ዥንጉርጉር ነው፡፡ በዚህ ዥንጉርጉር ቀለም ውስጥ መተወን ደግሞ ሥቃይና ዋጋ አስከፋይ ይመስለኛል፡፡ ከግራና ከቀኝ መጓተት፣ ሚዛንን ለመጠበቅ መድከም በእጅጉ ከባድ ነው፡፡ የዮሴፍንና የጶፋራን ሚስት ትግል ያህል ያስምጣል፤ ኮት ያስጥላል የሚል እምነት አለኝ:: ብርቱ መንፈስና የፀና አቋም ግን ይጠይቃል፡፡
ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የተናፈሰው የኢንጂነር ታከለ ዑማ ጉዳይ አንዳንዶቹን ወደተሳሳተ ግምት ወስዷቸው እንደነበርም አይተናል፡፡ ምናልባት “የንጉሥ ወዳጅ” የሚለውን የበለው ገበየሁን ግጥም መዥርጠው ያነበነቡም አልጠፉም፡፡ የኛ አገር ጥሎብን “ያልተጠረጠረ ተመነጠረ፣ ውደደው እንጂ አትመነው” በሚል እሾሃማ አጥር፣ ሳማ ተጐዝጉዞ አድገን እንቸገራለን፡፡ ግጥሙ እንዲህ ይላል፡-
የንጉሠ ነገሥት - ሆኜ ባልንጀራ
ያሻኝን ስነቅል - ያሻኝን ስዘራ
አንዱ ላይ ስተኩስ አንዱን ሳስፈራራ
ከፊል እየጠቀምኩ ከፊል ስንገላታ
ገሚሱን ስደቁስ ገሚሱን ስመታ
አሸኑን ስቋጥር አሸኑን ስፈታ
አንድ ምስጢር አወቅሁ የማታ የማታ
ንጉሥ ከተቆጣ ሕይወት ከመረረው
ሰይፉ ከጐኑ ነው መቁረጥ ሚጀምረው፡፡
ሰሞኑን “የዶክተር ዐቢይ የቁጣ ሰይፍ ወዳጃቸውን ከመቁረጥ ሊጀምር ነው” የሚል ስጋት የፈጠረብን ወገኖች ሁሉ ነበርን፡፡ የኢህአዴግ መንግስት እንደለመደው ሹማምንት ሊቀያይር ነው ብለን ብዙ ተቧጨቅን፡፡ ይሁንና ኢንጂነር ታከለ ባለፈው አንድ ዓመት ከምናምን ገደማ በአዲስ አበቤው ልብ በፍቅር መተከሉን ገመገምንባት - እግረ መንገድ፡፡
ከንቲባው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን በሚሉት መንገድ በሚገባ ተጠቅመዋል፡፡ መሪዎች በመገናኛ ብዙኃን በወጥነት ከተጠቀሙ ዐላማቸውን ከግብ ለማድረስ፣ ህዝብን የራሳቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለበጐም ይሁን ለእኩይ ተግባር ብዙዎች ይህንን ተጠቅመዋል:: አዶልፍ ሂትለር ህፃናትን ካጠመደበት መንገድ አንዱ ይህ ነው፡፡ ጆን ኤፍ ኬኔዲ አሜሪካውያንን የሃይማኖት ልዩነታቸውን እርግፍ አድርገው ክንፍ እንዲያወጡ ያደረጓቸው በዚህ ነው:: ሮናልድ ሬገንም እንደዚሁ በጥሩ የተግባቦት አቅማቸው ነው፡፡
ታከለ ዑማ በብዙ ነገራቸው ዶክተር ዐቢይን ይመስላሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በቅልጥፍናና በጥበባዊ አቀራረብ በተለይ በዘይቤያዊ አገላለጽ በታጀበ ንግግራቸው ህዝባቸው እንደ ሻማ ቢያቀልጡም፤ ታከለ ዑማ ደግሞ በሰከነ መንፈስ፣ በጥንቃቄ በተመረጠ፣ በሚያግባባና በሚያስታርቅ ሃሳብ ልብ ውስጥ ይሰጥማሉ:: በተግባቦት ሳይንስ በእጅጉ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በአካል እንቅስቃሴ ሳይቀር የሰውን ልብ የመማረክ ብቃት አላቸው፡፡ የቀኝ እጃቸውን መዳፍ በልባቸው ትይዩ ባለ ደረታቸው ላይ አድርገው “እወዳችኋለሁ” በሚል ከወገባቸው እጥፍ ሲሉ ሆዱ የማይባባና ነፍሱ በፍቅር የማትለከፍበት ብዙ አይደለም፡፡
ከንቲባው ያለ እረፍት በመሥራትና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ይዘው ብቅ በማለት ይታወቃሉ:: በየቴሌቪዥኑ ብቅ ባሉ ጊዜ ሁሉ አንዳች ሥራ፣ አንዳች ተስፋ አያጡም፡፡ ለወደፊት ህልም አልመው፣ ሌሎች የጀመሩትን አጠናቅቀው ስለሚመጡ ምሥላቸው ብቻ ሳይሆን ትውስታቸውም ከፊታችንና ከልባችን አይርቅም፡፡ እንደገመትነው፤ ስሜታቸው የሚንተከተክ ቀላል ሚዛን አይደሉም፡፡ ስሜታቸው ከዕድሜያቸው ጣሪያ ወጥቶ የሰከነ፣ ንግግራቸው ፍሬ ያለውና በእውነተኛ ድምፀት የተሞላ ነው፡፡ የአደባባይ ንግግር ምሁራን እንደሚሉት፤ ልባዊነት፣ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የማሳመን አቅሙ የትየለሌ ነው፡፡
ሰውየው በተደጋጋሚ እንደታዩት፤ ከህፃናትና አረጋዊያን ጋር፤ ከሌጣው ነዋሪና ከሃይማኖት መሪው ጋር የሚፈጥሩት መስተጋብር የተለየ፣ የሌሎችን ሞራል የማይነካ፤ በፍቅር የተከበበ ነው፡፡ ትህትናቸው ከአንድ ፖለቲከኛ ሳይሆን ከአንድ ፈጣሪውን የሙጢኝ ካለ የእምነት አባት ጋር የሚነፃፀር ነው፡፡
በተለይ በሀገራችን ባህልና እምነት በእጅጉ የሚወደሰውንና እንደ ብፅዕና ማሳያ ተደርጐ የሚቆጠረውን ድሆችን መርዳት፣ ደሀ አደጐችን ማገዝ፣ መበለቶችን መጐብኘትና ህፃናትን ማገዝ እንደ መሣሪያ ስለተጠቀሙበት (ተፈጥራዊ ደግነትንም ይጠይቃልና) በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አልከበዳቸውም፡፡ ቀደም ሲል ሁለመናቸውን በጥርጣሬ አይተው፣ ብዕር የመዘዙባቸው በጥላቻ ሰሌዳ በየማህበራዊ ድረ-ገፁ ያንጓጠጣቸው ሁሉ ሰብሰብ ብለው ሥራቸውን ወደማስተዋል እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡
በተለያዩ ሁነቶች (Events) ላይ ሲገኙም የሚያሳዩት ትህትና፣ የሚናገሩት በፍቅር የተሞላና አስታራቂ ሃሳብ፣ የተስፋ ሥዕልና የነገው አድማስ ብሩህነት “እኒህ ከንቲባ ህይወታችንን ሊለውጡ ይችላሉ” ወደሚል እምነት ብዙዎችን ስቧል፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት “የጋሞው ተወላጅ “ለጐጃሙ ገበሬ ምኑ ነው” በሚሉት ዐይን ሳይሆን አንድ ሰው ሀገሩን አርግዞ ጐጡን ብቻ አይወልድም፤ ኦሮሞም አማራም ትግራይም የኛ ነው” በሚሉት ዘንድ ሞገስ ማግኘታቸው ግድ ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ ንግግራቸው ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ በማህበራዊ ድረ ገፆች ለሚደርስባቸው የጥላቻ ሃሳብና የፖለቲካ ባላንጣነት ግምት ሳይሰጡ ሥራቸውን በትጋት በማከናወናቸው ብዙ ድልድዮች በድል እንዲሻገሩና እንዲገነቡም አድርጓቸዋል፡፡
የሥነ አመራር ሳይንሱ ዶክተር ጆን ሲ ማክስዌልር እንደሚሉት፤ ‹‹ትችትን ምንም ባለመመለስ ምንም ባለማድረግ፣ ምንም ባለመሆን በቀላሉ ልታስወግደው ትችላለህ›› ያሉ ይመስላል፡፡ አንድም ሥራ ሳይስተጓጎልባቸው ቀኑን እየገፉ፣ አዝመራውን እያፈሱ ነው፡፡
በኪነ ጥበቡ ሰፈር ውስጥም ያልተለመደ ቅርብነት በመፍጠር፣ ለጥበቡ ሰዎች በጥበብ ቃል በመቅረብና ለቦታው የሚስማማ ሀሳብ በማንፀባረቅ መጋረጃውን ገልጠው፣ የከያንያኑን ወንበር ተጋርተዋል፡፡
በዐውዳመቱ የችቦ በዓል የቡሄን ጅራፍ አስጩኸው ለዜጋው ባህልና ኢትዮጵያዊነት ያሳዩት ፍቅር፤ በሕዝብ ሥነ ልቡና ውስጥ ያስቀመጠው መሰረትና የደረደረው ጡብ ቀላል አይደለም፡፡
ሰዎችን ቀለል ብሎ መቅረብ፣ አባቶችን ማክበር፣ ለዝቅተኛው የማህብረሰብ ክፍል ከበሬታን ማሳየት… የዓለማችን ተደናቂ መሪዎች ባህርይ ሲሆን ከንቲባ ታከለም እኒህን ፈለጐች በመከተል ተወዳጅነትን ማትረፍ ብቻ ሳይሆን የለውጡ ቀኝ እጅ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡
የአሜሪካው አብርሃም ሊንከን እስከ ዛሬ ድረስ በገዛ ዜጎቹና በመላው ዓለም ብርቅዬ ሆኖ የቆየው፣ በእነማርቲን ሉተር ኪንግ አንደበት በአለማችን ስድስት ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው የተባለው በዚህ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል:: እንደ ፍራንክሊን ሩዝቬልት ለአገርና ለወገን ፋሲካ መሆን፣ ቁም ነገር ብቻ ሳይሆን በፈገግታና በአክብሮት እያቀፉ መቅረብ ዋጋው የትየለሌ  ነው፡፡ እንደ ቀደሙት ሹሞች ተቆልሎና ሕዝብን አርቆ መቆም በስተመጨረሻ የሚያደምጣቸውን እስኪያጡ ማድረሱን ከኋላም ታሪክ የተማርን ይመስለኛል፡፡ ዛሬም በየወረዳውና ዞኑ ያሉ ሰማይን በእጃቸው ያቆሙ የሚመስላቸው ሰነፎች፤ ትህትናን ከትሁታን ሊማሩ ይገባል፡። የሰማይና የምድር ጌታ የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበው አቅም ስለሌለው አልነበረም፤ ዓለምን በፍቅር ለማስታረቅና በመግባባት ሕይወት ለመሙላት ነው፡፡  
በአጋጣሚ ባለፈው ሳምንት ኢንጂነር ታከለ ኡማንም የአውቶቡስ ተርሚናል ሲያስመርቁ! ተመሳሳይ የሕይወትና የፍልስፍና መንገድ ያለን ሰዎች በአንድ ቦታ ታድመን ቴሌቪዥን እየተመለከትን ነበር፡፡ በዚያ ሥፍራ ደራስያን፣ ጋዜጠኞች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሌሎችም ሸንጎው ውስጥ ነበሩ፡፡
ታዲያ ከንቲባው ሁላችንንም የሚያስደንቅ ንግግር አደረጉ፡፡ ስለ ተሰራው ስራ ሲናገሩ፤ እንደተለመደው የሌሎችን ምሥጋና አልነጠቁም:: የሌሎች ላብ ላይ አቧራ አልደፉም፡፡ ይልቅስ “እኛ ብንጨርሰውም የጀመሩት ሌሎች ናቸው” ብለው የአክብሮት ምሥጋና አቀረቡ፡፡ ሁላችንም ተደመምን፡፡ ወደ ኋላ ሄደው የታሪክን መስመር በመከተል፣ ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ ለተሰሩ ስራዎች ዕውቅና ሰጥተው ተናገሩ፡፡ ይህ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንግዳ ነገር ነው፡፡ ከራሳችን በስተቀር ማንም እንዲመሰገን አንፈልግም፤ ምናልባትም ያንን ማድረጉ ራስን ማሳነስ ይመስለናል፡፡ ኢንጂነር ታከለ በዚህ ተግባራቸው የተለየ ቀለምና የሚያስቀና ባህርይ አላቸው ብለን መናገር የሚያስችለን በጎነት አላቸው፡፡
ፍቅርና የተሞላው ንግግራቸው፤ አንዳንዴ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ወንጌል የመስማት ያህል ልብን ይማርካል፡፡ ከአንደበታቸው አንዲት ፀያፍና አስከፊ ቃል አምልጣ እንኳ አትወጣም፡፡ በዚህ ቁጣ በሚፈጥርና የስሜትን ልጓም ለመበጠስ በሚያስገድድ ነውጥ ውስጥ አንደበትን ማረቅ ምን ያህል ጥበብ እንደሚጠይቅ አስተውሉ፡፡ “አንደበት እሳት ነው።
ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል” በገሃነምም ይጥላል›› እንደሚል፣ በጥንቃቄ መራመዳቸውን ማየት ይቻላል። “ታኬን እወደዋለሁ፡፡ ከኦነግ ጋር እግር የሚለካካውን ኦዴፓ እጠረጥረዋለሁ” የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ከአክራሪዎች ፍላፃ ተጠብቆ፣ አደራ ለተሰጣቸው ሕዝብ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም እንዲሰሩ ምኞቴ ነው፡፡ በአዲስ አበቤዎቹ ልብ ላይ የተሰጣቸውን ወንበር፣ በእውነተኛ ፍትህና ርትዕ ላይ ቆመው እውን እንደሚያደርጉት አስባለሁ፡፡  
በታሪክና በትውልድ ውስጥ ለአገራቸው ኢትዮጵያ ለመስራት ቆርጠው የተነሱትንና ፈተናቸው ቢበዛም በፅናት የቆሙትን መሪ ምስልም የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም፡፡ ፈተናው ከባድና ውስብስብ ቢሆንም በቀና ዐይን ለሚያዩ፣ የሚመጣው ዘመን አድማስ ብሩህ እንጂ ጨለማ አይደለም። የቱንም በጥርጣሬ ብሞላ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ኢትዮጵያን ለጥፋትና ለዘረኝነት ይሰጣሉ ብዬ ማሰብ ለምናቤ ሩቅ ነው። ኢንጂነር ታከለ ኡማም በዚሁ በጀመሩት የቅንነት ሀዲድ ይጓዙ ዘንድ መንገዳቸውን እሾህ ከሚነሰንሱ ፈጣሪ ይጠብቅላቸው ዘንድ እመኛለሁ፡፡

Read 1630 times