Saturday, 19 October 2019 12:45

ግልፅ ደብዳቤ ለተወካዮች ምክር ቤት

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)


           የምክር ቤቱ አባላት ራሳቸውን የሚያዩት፣ በሕዝብ እንደተመረጠና የሕዝብ ውክልና እንዳለው ሰው ነው? ወይስ እያንዳንዳቸውን እጩ አድርጐ ያቀረባቸውና በሕዝብ እንዲመረጡ ያደረጋቸው የፖለቲካ ድርጅታቸው በመሆኑ እንደ ፓርቲ ተወካይና የፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚ ነው?
አሥራ ሁለተኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሰሞኑን ተከብሯል፡፡ የተከበረው ግን ሲጀመር እንደነበረውና እንደቀጠለው በአዲስ አበባ ስታዲየም ሳይሆን በምክር ቤቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ባለው የሪፑብሊኩ መንግሥት አርማ (ትምህርተ መንግሥት) ላይ በአሁኑ ጊዜ የጋራ መግባባት ስለሌለና ተጨማሪ ችግር ላለመፍጠር በማሰብ እንደሆነ ምክትል አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ሽታዬ ምን አለ በሥነ ሥርዓቱ ላይ አብራርተዋል፡፡
ለእኔ ግን ሌላ ነው፡፡ ኮከቡ ከዚህ ቀደም ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም ፍልስፍና ጋር የተዋወቅነው ምልክት ቢሆንም፣ ዛሬ ይወክላል የተባለውን የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦችና የሃይማኖቶች እኩልነት በመወከሉ ብዙም የሚከፋ ያለ አይመስለኝም፡፡ እስካሁንም፣ የእኔ ብሔረሰብ ወይም ሃይማኖት ከሌሎች ይበልጣል በሚል “እንዴት እኩል ታደርጉኛላችሁ” ብሎ የተነሳም አላጋጠመም፡፡
ስለዚህም የሌለ ችግር እንዳለ ተደርጐ መቅረብ አልነበረበትም፡፡ ችግሩ የቆየ ሥርዓት የመፍረሱ፣ የነበረ ልማድ የመጣሱ ነው:: ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት ቀደም ባሉ ዘመናት፣ ሰንደቅ ዓላማ እንደነበራት፣ ክርስትናን ከተቀበለች በኋላ ከቀስተ ደመና ተወስዶ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ እንደተደረገ፣ መርስኤ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ ባልታተመ ጽሑፋቸው ይገልጻሉ::
ይህን ሃሳብ የማይቀበሉ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሁን ያለውን አሰዳደር ማለትም ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ፣ ከታች አረንጓዴ ሆኖ የተዋቀረው በአፄ ምኒልክ ዘመን እንደሆነ የሚያስረዱም አሉ፡፡
ምኒልክ እንደ አፄ ቴዎድሮስና እንደ አፄ ዮሐንስ ሁሉ፣ የመንግሥታቸው መለያ (ትምህርት መንግሥት) አንበሳ ነበር፡፡ ከአድዋ ድል በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ምስል በአንድ ፊት መጨመሩንና ኃይለማርያም ሰርባዬ የተባሉ ሰዓሊ፣ ዘውዱንና ዙፋኑን ያስተባበረ አርማ አዘጋጅተው እንደነበር መርሴ ኃዘን ጠቁሟል፡፡ የምኒልክ ሰንደቅ ዓላማ እንዲህ እንደ አሁኑ ጊዜ በየአደባባዩ የሚሰቀል ሳይሆን የንጉሡ ሰንደቅ ዓላማ ያዥ ደርግ ማሰሬው ይዞት ከንጉሡ ፊት ይቆም እንደነበር ይታወቃል፡፡ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን የተለየ ነገር አልታየም›፡፡  
ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በታላቁ ቤተ መንግሥት ግቢ ብቻ እሳቸው አዲስ አበባ በሚኖሩበት ጊዜ የሚወጣና የሚወርድ፣ በአንድ በኩል ዘውድ የደፋ ሰንደቅ ዓላማ የያዘ አንበሳ፣ በሌላ በኩል፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕል ያለበት ሰንደቅ ዓላማ እንደነበራቸው የሚናገሩ ብዙ እማኞች አሉ፡፡ ብዙዎችም ጽፈዋል፡፡ በንጉሡ ዘመን፣ ከክብር ዘበኛ ጀምሮ ልዩ ልዩ የጦር ክፍሎች፣ የየራሳቸውን አርማ ከሰንደቅ ዓላማው አንድ ጫፍ ላይ እያደረጉ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ አላማ ይጠቁሙ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አዋጅ ቁጥር 654/2001 ከመጽደቁ በፊት የተወካዮች ምክር ቤት በጠራው የሕዝብ አስተያየት የመሰብሰቢያ መድረክ፣ ከመከላከያ የመጡ ሰዎች፣ የአርማውንና የሰንደቅ ዓላማውን መዋሐድ የተቃወሙት፣ በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ሁለት አርማ ማስቀመጥ አይቻልም፣ አዋጁ የጦሩን መብት ይጋፋል በማለት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
እኔና የእኔ አይነት ሰዎች፣ ሰንደቅ አላማ የሕዝብና የሀገር ጉዳይ በመሆኑ፣ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማውንና አርማውን ማለትም የመንግሥት ምልክቱን ሊያደባልቅ አይገባውም ብለን ተሟግተናል፡፡ ሰሚ ግን አልተገኘም፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ዲሞክራሲ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ፣ የፌደራሉ መንግሥት አርማ ተለይቶ ከታወቀ በኋላ የወጡት ሁለት አዋጆች፤ አዋጅ ቁጥር 16/1988 እና አዋጅ ቁጥር 48/1989 የሰንደቅ ዓላማውንና የመንግሥቱን ምልክት (ትምህርተ መንግሥት) እራሳቸውን የቻሉ አድርገው ተቀብለው ያፀደቁ አዋጆች ናቸው፡፡  በአጭርና ግልጽ አማርኛ አላዋሃዷቸውም፡፡
ሁለቱም አዋጆች ሰንደቅ ዓላማው በሰማያዊ ክብ መደብ ላይ ያረፈ ባለ ጨረር ኮከብ እንዳለ ቢያረጋግጡም፣ አርማ ያላረፈበት አረንጓዴና ቢጫ ቀዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሕገ ወጥ ነው አላሉም፡፡ ይህ ማለት ሁለቱም ጐን ለጐን ሕጋዊ ሆነዋል ማለት ነው፡፡
በዘመነ ደርግ፣ ሰንደቅ ዓላማና ትምህርተ መንግሥት (አርማ) ተለያይተው እንደ ቆየት ሁሉ፣ በግንቦት 1983 የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ኢሕአዴግም ተቀብሎትና ተስማምቶበት ሲሠራበት ቆይቷል፤ለአሥራ ስምንት ዓመት፡፡
አዋጅ ቁጥር 654/2001 ለምን አርማ የሌለውን ሰንደቅ ዓላማ ሕገ ወጥ አደረገው? ስለ ምንስ በሌሎች ቀዳሚ አዋጆች ያልነበረ፣ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 23 ላይ ልዩ ልዩ የቅጣት እርምጃዎች ደነገገ? ስለ ምንስ በአንቀጽ 4 በየዓመቱ የሚከበር የሰንደቅ ዓላማ ቀን አወጀ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱ ለምክር ቤቱ ይደበቅበታል ብዬ አላምንም፡፡ ቢሆንም ዋናዎቹ ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው፤ ፀረ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መሆኑ እየተተነተነ ቅስቀሳ የተካሄደበት ኢሕአዴግ፤ አፍቃሪ ሰንደቅ አላማ ነኝ ብሎ ሕዝብን ማሳመን ስለፈለገ ሲሆን፣ ሁለተኛው ሰንደቅ ዓላማው ላይ የመንግሥቱን አርማ የማይነጠል አድርጐ በመጫን፣ ተቃዋሚዎቹ ሰንደቅ ዓላማውን ይዘው በቆሙ ቁጥር የእሱን መንግሥታዊ ምልክት ማሳወቅ ስለሚሆንባቸው ከእጃቸው እንዲወጣ ለማድረግ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ምን መደረግ አለበት? ቀላሉ ነገሮችን ወደነበሩበት መመለስ ነው፤ ማለትም፡- ከ1882 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ እንደነበረው መንግሥት የራሱን አርማ በቤተ መንግሥቱና በመንግሥታዊ ተቋማት እየተገለገለ፣ ሕዝብ የራሱን ትምህርተ መንግሥት የሌለበትን፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እንዲጠቀም መፍቀድ፡፡
ይህን ሲያደርግ ደግሞ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሆነው የተሠሩት የመቶ፣ የሃምሳና የአስር ብር ኖቶቻችን የበሰሉ ሰዎች የፈጠራ ሥራ ሆነው ይዘልቃሉ፡፡ የብሔራዊ እግር ኳሳችን ትጥቅ አረንጓዴ ሹራብ፣ ቢጫ ቁምጣና ቀይ ካልሲ  ባለበት ይቀጥላል፡፡ እናቶች በኩታና ቀሚሳቸው፣ አባቶች በነጠላቸው ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለት በመጣል እንደ ልብ ያጌጣሉ፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያሏቸውን ዛጐሎች፣ በልጆቻቸው ፀጉር በመሰካት፣ እናቶች ያለ ችግር የሰንደቅ ዓላማን ፍቅር ለልጆቻቸው ያስተምራሉ - ኧረ ብዙ ማለት  ይቻላል፡፡  
ምክር ቤቱ፤ሌሎችን ህጐችን ያሻሻለበትን መንገድ ተከትሎ፣ ይህንንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሻሽላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
ከሁሉም በላይ ለአባላቱ ማስገንዘብ የምፈልገው አርበኞቻችን  አምስቱን ዓመት ሙሉ ሲዋደቁ፣ እንዳይማረክባቸው ቀፎ ውስጥ ከተው ሲደብቁ የኖሩት፣ ጥና ሲልም ሕይወታቸውን ሲሰጡ የነበረው ለአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ መሆኑን ነው፡፡
ምክር ቤቱ፤ ሌሎችን ህጐችን ያሻሻለበትን መንገድ ተከትሎ፣ ይህንንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሻሽላል አርማ ያለውንም የሌለውንም እንደከዚህ ቀደሙ ሕጋዊ ያደርጋል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን!!

Read 1643 times