Saturday, 19 October 2019 12:24

በአፋር ክልል የተፈፀመውን ጥቃት የሚያወግዙ ሠልፎች ተደረጉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

  ሠላም ሚኒስቴር ጥቃቱን የሚያጣራ ግብረ ሃይል መላኩን አስታውቋል

            በአፋር ክልል ለ17 ንፁሃን ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነውን ሰሞነኛ የታጣቂዎች ጥቃት የሚያወግዙ ሠላማዊ ሠልፎች ባለፈው ረቡዕና ሐሙስ መካሄዳቸውን አዲስ አድማስ ከክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ያገኘው መረጃ የሚጠቁም ሲሆን፤ ጥቃቱ የተፈፀመው በውጪ አክራሪ ሃይሎች እንደሆነ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ የሠላም ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ወደ አካባቢው ማሠማራቱን አስታውቋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መዲና ሠመራን ጨምሮ በሎጊያና በሌሎች ከተሞችና አካባቢዎች በተካሄዱ ሠላማዊ ሠልፎች፤ መንግስት በአፋር ህዝብ ላይ በውጭ ሃይሎች የተከፈተውን የሽብር ጥቃት እንዲከላከል ጥሪ መቅረቡንም ቢሮው አስረድቷል፡፡
ጥቃቱን አስመልክቶ መከላከያ ሠራዊት የውጭ ሃይሎች እጅ የለበትም›› ማለቱን ሰልፈኞች በመቃወም መግለጫው መረጃን ያላገናዘበ እንደሆነ በሠልፈኞቹ ከተንፀባረቁት መፈክሮች ‹‹ሞት ይብቃ፤ በሶስት መንግስታት በሚታገዘው የአሸባሪ ቡድን ለሚሞቱ የአፋር ንፁሃን ህዝቦች ፍትህ እንሻለን፤ በዚያድ ባሬ ያልተሳካው ግዛት የማስፋፋትና ታላቋ ሶማሊያ የመመስረት ህልም በማስቀጠል የሚረባረቡ የውጭ ወራሪዎች ጥምር ሃይሎች እቅድ ቅዠት ሆኖ ይቀራል፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት ቢያስደስተንም በህፃናትና እናቶች ሞት ልባችን ተሰብሯል፤ Yes for peace, no for terrorism” የሚሉና ሌሎች እንደሚገኙባቸው የኮሚኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡
ጥቃቱን የፈፀሙት ወገኖች የአልሸባብን አላማ ያነገቡ መሆናቸውን ህብረተሰቡ ለመንግሥት እየገለፀ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል፡፡ የሠላም ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ጥቃቱን የሚያጣራ ግብረ ሃይል አቋቁሞ ወደ አካባቢው መላኩን ጠቁሟል፡፡
በአፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ ኮስኖ ቀበሌ ባለፈው ሰኞ ማንነታቸው እስካሁን በይፋ ባልታወቁ ታጣቂዎች በተከተፈ ተኩስ ህፃናትና ሴቶችን ጨምሮ 17 ኢትዮጵያውያን አርብቶ አደሮች መገደላቸው ታውቋል፡፡ 

Read 8046 times