Saturday, 16 June 2012 12:45

“ቅዥቢ“ ኪነ-ጥበብ

Written by  ዶ/ር ፍቃዱ አየለ
Rate this item
(0 votes)

አመድ የላሰች ኪነት

ዛሬ በ “ኪነ-ጥበብ “ ዙሪያ ጥቂት ነገር ልል ወደድኩ፡፡ አትኩሮቴ ደግሞ ቅዥቢነትን በልክነት በሰደረው ህመምተኛ የኪነጥበብ አንጃ ላይ ነው፡፡ ኪነ-ጥበብ የየትኛውንም ጎራ የህይወት ጉድባና ስርጓጉ በብዙ ጥፍጥናና ጥበባዊ ለዛ፣ ለህይወት ተዋናዩ ሰብአዊ ፍጥረት እንዲደርሱ የማድረግ ዘርፈ ብዙ ክወና  መሆኑ ግልጥ ነው፡፡  ታዲያ ይህች ኪነ-ጥበብ የጥበብ ምንጭ የሆነችውን ህይወት ከሚተውኑት ከብዙዎች ይልቅ ተጠባቢዎቿ በሚበዛው የህይወት አውታር ላይ ረቅቀው መገኘት ክህሎታዊ ግዴታቸው ነው፡፡ የዚህ ክህሎታዊ ግዴታ ምንጭ ደግሞ ኪነ ጥበብ በክህሎተኞች የምትቀሰምና የምትቀናበር በመሆኗ ሰበብ ነው፡፡ ዳሩ ግን ግለሰብአዊነት ንጥር ብሎ የማይወጣበት ኪነ-ጥበብ፣ ኪነታዊ  ህብረተሰባዊነትን ተላብሶ እጅግ መኮሰሱ አይቀሬ ነው፡፡

በእንዲህ  አይነቱ ምስስሎሽ ባጠላበት ክየና፣ በልክ በልክ ተሰብጥራ እየተመጠነች ልትቀምም የሚገባት፣ ህይወት ያልሆነችውን እንደሆነች ተደርጋ በቀዠበረ ብዕር ተንጋዳ መሳሏ ባይገርመን ይሻለናል፡፡ ግለወጥነትን ደፍጥጠው ሲያበቁ የከያኒውን “ፈጣሪነት “ በመካዱ መስማማትም ራሱ ቅዢቢነት ነው፡፡ ቅዥቢነት በዚህ ፍካሬው ሲበየን ውል አልባ ኪነታዊ ማነጥነጥ ሲሆን ከየቦታው የተቃረመ እኩይና ሰናይ እውቀት ተደበላልቀው፣ ኪነጥበብን ለቅዥብርብሮሽ መጫወቻነት ማደላደልና ከያኒነትንም ከንቱነትን እንዲከንት ማድረግ ነው፡፡

እርግጥ ነው ይህች ኪነ-ጥበብ በህይወት ፍሰት ውስጥ የፍሰቱን ጅረት የሚያጎለምሱትን ውርዘቶች፣ ነጠብጣቦችና ጭርጭርታዎች አንዱንም ሳይቀር የመመልከት ጥልቅ እይታ ባለቤት የሆኑ ክህሎተኞችን መሻቷ ግድ ነው፡፡ ኪነ-ጥበብ ከህይወት ተዋናዩ ውስጥ የራሷ የሆነውን ወደ ጉያዋ የምትስብበት የፍቅር ገመድ አላት፡፡ ዳሩ ግን የኪነጥበባዊውን ፈረስ ልጓም ከጨበጠ በኋላ ጀርባን ለህይወት ሰጥቶ ከያኒነት በህይወት ላይ በጎ ተጽኖ የማትፈጥር ሆና እንድትከሰት በመዛቆን የኋሊት መፈርጠጡ ነው የቅዠቢነቱ ጡዘት፡፡  “የኪነ ጥበብ ድርሻ ህብረተሰብን መለወጥ ሳይሆን ህብረተሰብን ማሳየት ነው“ በምትል መናኛ ሰበብ ራሱን በዝቅጠት አረንቋ ወትፎ በከንቱነት ማለትለት ነው ቅዥቢነት፡፡ ለኪነጥበብ ህይወትን እስከመሰዋት ድረስ ሊዘልቅ በሚገባ ኪነጥበባዊ ፍቅር ልትብራራ የሚገባትን ውድ ህይወት በተልኮሽኳሽ ማንነት ማዳፈን - ቅዥቢነት እሱ ነው፡፡

ህይወትን በኪነ-ጥበባዊ ልዩ ልዩ ዜማ፣ በተለያዩ ስልቶች መቃኘቱና መዝረፉ፤ ከያኒው ቢሻውም ባያሻውም ሲፈጠር በውስጡ ተመስጥሮ የሚገኝ ቱርፋቱ ነው፤ እናም ከያኒ ሆኖ መገኘት  “ውበት ለበስ “ ሆኖ ከመገኘት ብዙም መለየቱ ያጠራጥረኛል፡፡ ባለውበት ውበትን ባይጠነቀቅላትና ለውበት በማይመጥን ጉራንጉር ውስጥ ቢደነጉራት፣ በውበት ጠላቶች ተፈርፍሮና ተፈነካክቶ ከንፈር ለሚመጠጥለት የህይወት ትወና መዳረጉ አይቀሬ እንደመሆኑ፣ ከያኒነትም ምጥቁነቱንና ሃያልነቱን ከጥንቃቄ እጥረትና ከአቅጣጫ መሳት የተነሳ በቅዥቢነት ሊደመደም ይችላል፡፡ ሊንከባከባትና ከብዙ አስተውሎት በኋላ “እንዲያ እና እንዲህ“ መሆኗን ሊያፍታታላት የሚገባውን ያችን ህይወት  “እኔም አካሏ ነኝ “ ብሎ ስጦታውን ቆልምሞ፣ ራሱ ተተራኪ መሆኑን በልክነት መደምደምና ኪነጥበብን የናወዙ ከያንያን እድር ማድረግ የቅዥቢ ኪነት ሸፍጥ ነው፡ ይህ ደግሞ ጥበብን ከተጠያቂነት ማፋታቱ አይቀሬ ነው፡፡

ኪነ-ጥበብ የከያኔው የህይወት እይታ ምንጭ ባትሆንም ህይወት ግን በኪነጥበብ ተፅዕኖ ሊደረግባት መቻሉ ምንም አይገርምም፡፡ እናም ከያኒ ልክነትና ልክአልባነትን ባደበላለቀ መጠን በከያኒያዊ ተሰጥኦ በኩል እየተንኳለለ ወደ ህይወት ጅረት የሚንጠበጠበው ልክነት ወይም ልክአልባነት በውስጡ በተቀረቀረው ኪነታዊ የህይወት ትንታኔ ብቃት እየተረጨ ህይወትን መፈወሱ አሊያም መበከሉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ጠብታ መርዝ እንደመርዙ ጥንካሬ ጅረቱን የሞት ጅረት የማድረግ ብቃቱ ግን አሳሳቢው ሃቅ ነው፡፡ መርዝ የተሞሉ የኪነት ብልቃጦች መርዛቸውን ማርከስ ብቻ ሳይሆን መርዛቸው መድፋት የሚገባበት ሰአት አሁን መሆኑን ቀጣዩ የኪነጥበብ ትውልድ ሊገነዘብ ይገባል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ የኛ ሃገር ኪነጥበብ ላለፉት 40 እና 50 አመታት  “ቅዥቢነትን “ በኪነታዊ ለዛ እያሞናሞኑ ወደ ህይወት ጅረት በሚቀይጡ ልክአልባውያን ቁጥጥር ስር ውላ፣ የኪነት መንደሩ ህይወት ልክአልባዊነትን ከህይወት ትወናው ውስጥ ለመቀለጣጠም ብቃት ያጠረው፣ የተቸረቸፈ መጥረቢያ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ስለሆነም የዚህች ሃገር ኪነት ስነምግባር ሳይሆን ዋልጌነት የህይወት አንዱ ስርጓጥ መሆኑን ማሳየት ሲገባ፣ ልክአልባነትን ከሁሉ በላይ ለማንቋለጥ ውላ በተቀበዣዠረ ስብዕናዎች የተሞላች ጥበብ የሌለባት ኪነት ሆና ስትፍገመገም ይኸው እዚህ ደረሰች፡፡ ይህችን አይነቷን ከያኔነት “ዋልጌነት“ እስኪመስል ድረስ በስድነት የተላቆጠችና ከደደረ ልቦና በሚፈተለኩ ውድ ቃላት እና በጥረት አልባ ተፈጥሯዊ ብቃት መቸክቸክ፣ ኪነ-ጥበብ ተደርጎ እንዲተረጎም የምድሪቱን ውድ ስጦታ ያልኮሰኮሰች ኪነትን ነው “ቅዥቢ“ ያልኳት፡፡ አመድ የላሰች ኪነት፡፡

ተጠያቂያዊነትን በአፍጢሙ ደፍታ እብድ መሰልነትን በብርቅርቅ ቃላቶች እየቀባቡ ያልሆነውን እንደሆነ አድርጎ መሳል ኪነት  “ቅዥቢነት“ ሲጣባት ከሚስተዋልባት የጥበብ በሽታ መገለጫነት ሊያልፍ አይችልም፡፡ የኪነ-ጥበብ መንደሩ  “ቅዥቢነትን “ እስከ መጨረሻው እየጨለጠ፣ ልክአልባነትንና የህይወትን ጉድፍ ባይነቅሰው እንኳ አጉልቶ ማሳየትን እንዴት ይቻላል በዚህ ቅዥብርብር አከያየን ብቃታቸውን ካስዳመጡና ካስደፈጠጡ በኋላ፣ በሃገራችን የኪነት ሃቀኝነት ላይ በሁሉም አይነት የኪነጥበብ አውታሮች ለቅዥቢነት ትውልድ መስዋእት ሲደረግለትና ሃውልት ሲቆምለት አይተናል፡፡ ኪነጥበብ “ስታብድ“ እብደትን በክህሎቷ ማሞጋገሷና ማወዳደሷ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ እናም ራሱን በቅዥቢነት የደመሰሰ ከያኒ ኪነትን ለመከነት ሲነሳ፣ ምልከታውን ሊያጣምም በሚችል ልክአልባ በሆኑ መገልገያዎች ተሰቅዞ በመሆኑ ምክንያት ኪነ ጥበባዊ እይታው፣ ጥርት ካለ ስብዕናውና ከፍጥረታዊ ማንነቱ ውስጥ መፍሰሱ ያበቃለታል፡፡ የገዛ ራሱ ለራሱ ሰልችቶት የሚናውዝ ማንነት ፍለጋውን ትቶ፣ ክህሎቱን በመናዎዣዎች ጉም ጠቅልሎ ቢንሳፈፍ ምን ይገርማል?

እንግዲህ በራሳቸው መንደር እንደተዘከረው ህይወት  “የካርቶን“ ፊልም እስክትመስል ድረስ ልክነት ያጣችው፣ ኪነታዊ ክህሎት ውል ጠፍቶባት አቅጣጫ ስትስት መሆኑን በትልቁ ማሳሰብ እሻለሁ፡፡  “የካርቶን ፊልም“ ብርጭቆም ካርቶን ለሚመስላቸው ጨቅሎች አደብ መግዣ ይሆን ዘንድ ለልጆች የሚዘጋጅ ቧልት ነው፡፡ ነገር ግን የህይወትን ቁምነገርነትና ጣፋጭነት በንቀት አንጓጦ ቅልጥ ያለ ቧልትነቷን ለማግነን አምርሮ የሚታክር ከያኒነት  “ቅዥቢ ኪነ-ጥበብነቱ“ አያከራክርም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን ኪነ-ጥበብ ከቅዥብርብርነት እስር ቤቱ ለመዋጀት  “ለቅዥቢነት “ የማጫፈር ኪነ-ጥበባዊው አድማ የመበተኛው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ኪነጥበባዊው ውድማ ለደቦ ውቅያ የማይመች መሆኑንን መገንዘብ ለቅዥቢነት ቅብብሎሽ ማክተም ወሳኝ ነው፡፡ እኛም ሃገር ቢሆን ህይወት ካልተበጠበጠ ስብዕና በሚወጣ እይታ፣ በመልካም በሚከትብ ከያኒ፤ በሃቅና ባልተቀበዠረ ማንነት ስትፃፍና ባልተቀያየጠ እውነት ተውባ በአዲስነቷ ማየት እንናፍቃለን፡፡ ተጠያቂነት የጎደለው ኪነ-ጥበብ በብቃት ስጦታና ክህሎት አሳቦ ትውልድን ሲበክል ማየት እንዴት ይሰለቻል!!

ኪነ-ጥበብ የሁሉም ናት፤ ምክንያቱም ህይወት ስለሁሉም ናትና! ስለዚህ  “የራሴ ብቻ “ ነኝ ብላ የምትፍላላ ኪነት-ነገር ቅዥቤ መባሏ በዚህ ትርጉም ውስጥ ለተጠቀለሉት ብቻ ነው ልክነቱ፡፡ አለመቀዥበር የህይወት ዋናው መገለጫ ነውና ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ለዛሬው ተፈጸመ፡፡ እግዚአብሄር  ለሌላ ወግ ያብቃን እያልኩ ልሰናበት፡፡

 

 

Read 1728 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 12:50