Saturday, 19 October 2019 12:22

71 ፓርቲዎች በአራት ኪሎ አደባባይ የረሃብ አድማ ያደርጋሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሃኪሞች እንዲመድብ ተጠይቋል

             አዲስ የወጣውን የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅን የሚቃወሙ 71 የፖለቲካ ድርጅቶች በጥቅምት መጨረሻ በአራት ኪሎ የድል ሃውልት አደባባይ ላይ ተሰባስበው ለሁለት ቀናት የረሃብ አድማ ለማድረግ መዘጋጀታቸው አስታወቁ፡፡
አዋጅን በመቃወም በተደጋጋሚ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለምርጫ ቦርድ፣ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ደብዳቤ ቢጽፉም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን የገለፁት 71ዱ የፖለቲካ ድርጅቶች በቀጣይ በአዋጁ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ ተከታታይ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማድረግ መሰወናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ካወጧቸው እቅዶች መካከል የረሃብ አድማ ዋነኛው ሲሆን ይህን አድማ ጥቅምት 5 እና 6 ለማድረግ አቅደው የነበረውን ወደ ጥቅምት 25 እና 26 ማሸጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡
የረሃብ አድማውን ወደ ጥቅምት መጨረሻ ለማሸጋገር የወሰኑትም በጥቅምት መጀመሪያ  በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠሩ አለመረጋጋትና ሁከት ምክንያት በየክልሉ ያሉ የክልል ፓርቲዎች በተያዘለት ቀን ወደ አዲስ አበባ ለመግባት መንገዶች ዝግ በመሆናቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አድማውን ከቤት ውስጥ ይልቅ በአደባባይ በማድረግ በፓርቲዎቹ መወሰኑ ይሄን ውሣኔ አዲስ አበባ አስተዳደር ማሳወቅ ማስፈለጉም የረሃብ አድማውን ለማራዘም ምክንያት ከሆኑት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በተጨማሪም በረሃብ አድማው ወቅት ተሳታፊዎች ላይ ሊፈጠር የሚችል የጤና ችግርና ድንገተኛ አደጋዎችን ታሳቢ ያደረጉ ሰፊ ዝግጅቶች ማድረግ በማስፈለጉ ፓርቲዎቹ አድማውን ወደ ጥቅምት 25 ለማዘዋወር መወሰናቸውን አስረድተዋል፡፡  የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚ/ር ጥቅምት 25 እና 26 ቀን 2012 ዓ.ም በአራት ኪሎ በሚካሄደው የረሃብ አድማ ላይ የጤና ባለሙያዎች በመመደብ ተገቢውን ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና በጐ ፍቃደኛ የጤና ድጋፍ አድራጊዎች ባለሙያዎች በመመደብ ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በእለቱ ፓርቲዎቹ በመፈክርም ሆነ በድምጽ የሚያቀርቡት ተቃውሞ አለመኖሩን፣ መንገድ መዝጋት፣ ጩኸት ማሰማት የመሳሰሉትን እንደማይፈጽሙ ያስታወቁ ሲሆን የመንግስት አካላት ችግሩን ለመርዳት ከመጡ በጽሑፍ ጥያቄዎችን በዝርዝር እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
የረሃብ አድማውም ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓትና በማግስቱም በተመሳሳይ ሰዓት አድማው የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ የረሃብ አድማ ፓርቲዎቹ ቀና ምላሽ ካላገኙ ምላሽ እስኪያገኙ በቀጣይ የተቃውሞ የድጋፍ ፊርማ ማሠባሰብን ጨምሮ የተለያዩ ሠላማዊ ሰልፎችን በማዘጋጀት ተቃውሞአቸውን እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡ በቀጣዩ ምርጫ የመሳተፍ አለመሳተፍ ጉዳይም የየፓርቲዎቹ የተናጠል ውሣኔን የሚጠይቅ መሆኑንም ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል::  

Read 7754 times