Saturday, 19 October 2019 12:14

“ኢትዮጵያ በየዓመቱ 55.5 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ምግብ ታባክናለች”

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)


           - አገሪቱ በየዓመቱ ከምታመርተው ምርት ጥቅም ላይ የሚውለው ከግማሽ በታች ነው
          - ከእርሻ እስከ ጉርሻ ባለው ሂደት የሚባክነው ምርት 52 በመቶ ይሆናል
             
               የምግብ ብክነትና ያለአግባብ ምግብን ጥቅም ላይ ማዋል አገሪቱን በየዓመቱ ለ55.5 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚዳርጋት ተገለጸ፡፡ ባለፈው የፈረንጆች 2017 እና 2018 ብቻ አገሪቱ 282 ቢሊየን ብር የሚያወጣ ምግብ ማባከኗም ተገልጿል፡፡
የአለም የምግብ ቀን ሰሞኑን በተከበረበት ወቅት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁርና በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት ፕሮፌሰር አሊ መሐመድ እንደተናገሩት፤ ምግብን ያለ አግባብ በማባከንና ባልተመጣጠነ ሁኔታ ጥቅም ላይ በማዋል አገሪቱ በየዓመቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ኪሳራ እየደረሰባት ይገኛል ብለዋል፡፡
አግሮ ፕሮፎከስ ኢትዮጵያ በተሰኘ ድርጅት በተዘጋጀውና ሰሞኑን በተከበረው አለም አቀፍ የምግብ ቀን ላይ ምግብን ከመጠን በላይና በተዛባ ሁኔታ መመገብ እንዲሁም ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን አለመከተል በአገሪቱ 42 በመቶ የሚሆነውን ሞት እያስከተለ  እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፎርፉድ ሴክዩሪቲ በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚሁ አለም አቀፍ የምግብ ቀን ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የጅማ ዩኒቨርስቲ ጥናትና ምርምር ክፍል ፕሮፌሰር አሊ መሐመድ እንደተናገሩት፤ ከእርሻ እስከ ጉርሻ ባለው ሂደት ውስጥ የሚባክነው ምግብ ከተመረተው 52 በመቶ ያህሉን ይሆናል፡፡ በዚህም አገሪቱ በየዓመቱ ከ55.5 ቢሊየን ብር በላይ ኪሣራ እንዲያጋጥማት ያደርጋል ብለዋል:: በድህነት አቅማችን ያመረትነውን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ሲገባን በከንቱ እንዲባክን በማድረጋችን አገራችን በየዓመቱ ከፍተኛ ኪሣራ እያጋጠማት ሲሆን የምንጥለውን ቆሻሻ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምረዋል፤ ይህ ደግሞ ለአገሪቱ ሌላ ተጨማሪ ወጪን ያስከትልባታል ብለዋል፡፡
የምግብ ብክነቱ በከፍተኛ መጠን የሚታየው ገበሬው/አርሶአደሩ ጋ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር አሊ፤ በተለይም  የፍራፍሬና አትክልት ምርቶች በአብዛኛው የሚባክኑት እዛው እርሻ ማሳ ላይ ነው ብለዋል፡፡
የኒውትርሽናል ፕሮዳክት ኤንድ ሰርቪስ ፒኤልሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብነት ተክሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በምግብ እጥረትና የተመጣጣነ አለመሆን ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ሳቢያ የሚሞቱና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚዳረጉ ዜጐች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ ኢትዮጵያ፣ በ2040 ዓ.ም ከአፍሪካ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የተጠቁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሚገኙባት አገር ትሆናለች፡፡
የምግብ ብክነትን በመቀነስ የምግብ እጥረት ችግርን መከላከል ይቻላል ያሉት አቶ አብነ፤ የምግብ ምርቶችን በአግባቡ በመጠበቅና በጥቅም ላይ በማዋል፣ በየጊዜው የሚያጋጥመንን የምግብ እጥረት ችግር በዘላቂነት ማስወገድ እንችላለን ብለዋል፡፡
አግሪ ፕሮፎከስ የተባበሩት መንግስታት መረጃዎችን ዋቢ አድርጐ እንደገለፀው፤ የምግብ እጥረትና አለመመጣጠን በየአመቱ ኢትዮጵያን ለ55.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚዳርጋት ሲሆን ይህም በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለው ተፅዕኖ በመቶዎች ሲሰላ፣ 16.5 በመቶ አመታዊ የብሔራዊ ምርት ገቢን ሊያሟጥጥ ይችላል፡፡   

Read 7431 times