Print this page
Saturday, 19 October 2019 12:14

ኦዴፓ ‹‹የመደመር እሳቤ›› የፖለቲካ መስመሩ እንዲሆን ተስማማ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


                         “አብዮታዊ ዲሞክራሲ የአገሪቱን ወቅታዊ ችግሮች አይፈታም”

                 የኢሕአዴግ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የአገሪቱን ወቅታዊ ችግሮች መፍታት እንደማይችል መገንዘቡን የገለፀው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ፤ (ኦዴፓ) የ“መደመር” እሳቤ የፓርቲው መርህ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በሐዋሳ በተካሄደው 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ላይ የኢሕአዴግ የወደፊት እጣ ፈንታ እንዲጠና በተቀመጠው መርህ መሰረት ባለፉት ጊዜያት በኢሕአዴግ ዙሪያ ጥናቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን የገለፀው የኦዲፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ፤ ኢሕአዴግ ከአፈጣጠሩና ከአደረጃጀቱ አገርን በአንድነት ማስቀጠል የማይቻል መሆኑ ተረጋግጧል ብሏል፡፡
ኢሕአዴግ የሚከተለው አስተሳሰብም አሁን ለውጡ የሚፈልገው ትግል የደረሰበትን ደረጃ የሚመጥን አለመሆኑን የገለፀው ኦዴፓ፤ ኢሕአዴግ መለወጥ እንዳለበት ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
የኢሕአዴግ መዋቅር ባለፉት ጊዜያት ለሌብነት፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰትና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ለሆኑ ድርጊቶች እንዲፈፀሙ ምቹ መደላደል የፈጠረ መሆኑም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
በብዙ ውስብስብ ውስንነቶች የታጠረው የኢሕአዴግ አወቃቀር ከዚህ በኋላ የኦሮሞ ሕዝብንም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብን ጥያቄ መመለስ የማይቻል መሆኑን የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ መወሰኑን መግለጫው አትቷል፡፡
በዚህም ኢሕአዴግን የሚተካ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ለመፍጠር ምክክር በመድረግ ላይ መሆኑን መግለጫው አስገንዝቧል፡፡ የዚህ አዲስ ድርጅት የፖለቲካ መርህ የመደመር እሳቤ እንዲሆን መታሰቡንም አስገንዝቧል፡፡
የመደመር እሳቤ እውነተኛ የፌደራል ሥርዓትን በማጠናከር የብሄረሰቦች እኩልነትን የሚያረጋግጥና የአገርን አንድነት የሚያስጠብቅ ነው ያለው መግለጫው የመደመር እሳቤ አገሪቱን ወደፊት የሚያሻግር መሆኑን የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ መገንዘቡንና እሳቤውን መቀበሉን አረጋግጧል፡፡
ኦዴፓ በዚህ መግለጫው ከዚህ ቀደም ፌዴራሊዝም ስር እንዳይሰድ ስልጠናቸውን ተጠቅመው ደባ የፈፀሙ አካላት ስለወጡ በተፃራሪ መቆማቸውን አስታውቆ እነዚህን ሀይሎች በፅናት እንደሚታገልም አስታውቋል፡፡  

Read 1498 times