Saturday, 12 October 2019 11:57

ተወርዋሪ ደስታ

Written by  በሚፍታ ዘለቀ
Rate this item
(11 votes)

  እንደ ሰው ልጅ በብዛት፤ እንደ ሃገር ደግሞ የተጋነነ በሚመስል መልኩ ያዳበርነው ባሕርይ አለ፡፡ መርሳት፡ መዘንጋት፡፡ ብዙ የህልውናችን መሰረት የሆኑ ጉዳዮችን እንረሳለን፡ እንዘነጋለን:: ታሪክ እንረሳለን፡፡ የሃገር ባለውለቶችን እንረሳለን:: መልካም ሰብዕናዎችን ቸል እንላለን፡፡ በእንዲህ መሰል ዝንጋኤዎች እየተዘፈቅን፣ ጥራት በጎደለው ሕይወት እንንጎዳጎዳለን፡፡ በዚህም ይደክመናል፤ ስልቹዎች እንሆናለን፡፡ እሴቶችን ማዳበር እየተዘነጋንና እየረሳን የአለመቻል ሚዛን ላይ እየወደቅን ማቃት ያሳድደናል፡፡ እናም በስራችን መቃወምና መታገል ከሚገቡን ጉዳዮች ዋነኛዎቹ መርሳትና ዝንጋኤ መሆናቸውንም እንረሳለን፡፡ መርሳትን መቃወም ደግሞ ያለፈው ስለ መዘንጋቱ መቆጨትን ብቻ ሳይሆን እየኖርን እየሰራን ያለነው ነገርን ሁሉ በተቻለ ጥራት እንዲሆንና ፋይዳ እንዲኖረው እንዲስተዋል መንገድ ለመጥረግም መሆን ይኖርበታል፡፡
በችግሮች ላይ ችግሮች የተተበተቡባት እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሃገር ያፈራቻቸው ጥቂት ብቁ ሰዎችን በተለያዩ ምክንያቶች ስታጣ እንደ ማየት የሚያሳዝን ሁነት የለም፡፡ ዘመናቸውን በስራቸው እንዲሁም በሰብዕናቸው የዋጁና መጪውንም ጊዜ የተሻለ ሊያደርጉ የሚችሉ ወጣቶችን በሞት ማጣት ጉዳቱ የሚሰማውን ሁሉ ያሳምማል፡፡ የእነዚህ አይነት ሰዎች እጦት፣ የሃገር እጦት መሆኑ የሚገባን ሰዎቹ በብቃት ሊወጡት የሚችሉት ታላቅ ሃገራዊ፣ አህጉራዊ አሊያም ዓለም-አቀፋዊ ግዘፍ የሚነሱ ስራዎችን ለማሰብና ለመከወን ስንሻ የሚኖረንን ጉድለት ስናስተናግድ ይሆናል፡፡ ሰሞኑን በድንገት ሕይወቱን ያጣነው ደስታ ማሕደረ ደስታ (ፓፒ) የተሰኘ ተወርዋሪ ኮከብ፣ ለዚህ አይነቱ እጦት ምሳሌ ይሆነናል፡፡ እንዴት?
የግራፊክስ ዲዛይን ‘ሀ ሁ’ በኢትዮጵያና
ደስታ ማሕደረ
በሃገራችን ሠዓሊ መሆንና ሠዓሊ ሆኖ ለመኖር መሞከር፣ ማማጥና ምጥ ውስጥ እንደ መኖር ነው፡፡ ሠዓሊ ለመሆን ማዋለጃው በአብዛኛው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት (አርት ስኩል) ነው፡፡ የት/ቤቱ በር በዓመት ቢበዛ ለ15 ከፍ ሲል ለ20 ተማሪዎች ነበር ክፍት ይሆን የነበረው፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡ አሁን ጊዜ ተሻሽሎ እስከ 30 እና 40 ተማሪዎችን ይቀበላል፤ መቶ አስር ሚሊዮን ህዝብ ካሏት ኢትዮጵያችን ማለት ነው፡፡ በ1980ዎቹ መጨረሻ ደስታና ጓደኞቹ እጅግ ተፈላጊው የአርት ስኩል የቀን ፕሮግራም በር ቢዘጋባቸው፣ የማታውን ት/ት በመከታተል ጠበል ጠዲቁን ተቋድሰው ነበር፡፡ በ1990 ዓ.ም. ደስታ፣ ኢዛናና ፍቅር ከተባሉ ጓደኞቹ ጋር “ፍርግርግታ” ወይም Harmony የተሰኘ የሠዓልያን ስብስብ ስቱዲዮ መስርተው፣ ሥዕል መሳያ ጎጆ ቀልሰው (ተከራይተው ነው) ተሞሸሩ:: የልጅነት የወጣትነት መነሳሳታቸውን ለጥበብ መስዋዕትነት ሰጡ፡፡ ሥራዎቻቸውን በሥዕል ትርዒት ለማቅረብ፣ ለመሸጥና ጉዞአቸውን ለማስቀጠል ተፍጨረጨሩም፡፡ ምጡ አይቀሬ ቢሆንም ተግዳሮቱ የሚቻል አልሆን ሲላቸው እንደ አመጽ ነገር ይሞካክሩ ጀመር፡፡ ማመጽ ተስኖአቸው የከሸፉ ብዙ እንዳሉም እነ ፓፒ ጠንቅቀው ያውቃሉና የሃገራችን ዘመንኛ ሥነ-ጥበብ እንዳከሸፋቸው ሠዓልያን ላለመሆን አመጻቸውን ገፉበት፡፡ ችስታነትን ነበር እምቢኝ ለማለት የሞከሩት፡፡
አንድ አጋጣሚ ነገሮችን የመቀያየር ሚና ተጫወተች፡፡ እሷም የደስታ(ፓፒ) እህት የምትማርበት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አመታዊ መጽሄት እንዲሰራላቸው ሰው ሲያፈላልጉ ደስታና ጓደኞቹ እድሉን ያገኛሉ፡፡ መጽሄቱን ኮምፒውተር ላይ ሰርተውት ታተመ፡፡ የሥዕል ስራቸው ሳይቆም ገቢ የሚያገኙበት መንገድም ተፈጠረ፡፡ ሆኖም በጊዜው Graphics Design በሚባል ደረጃም ባይሆን ስራውን የሚሰሩ ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ በመሆናቸው ስራዎች ይከታተሉባቸው ጀመር፡፡ ሥዕል የሚሰሩበት ጊዜም እያነሰ መጣ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ ፓፒ ኮምፒውተር ላይ የመስራት ችሎታው እየጨመረ በመምጣቱ ወደ Graphics Design ይበልጥ ማዘንበል ጀመሩ፡፡ ይህ አይነቱ ወንዝ ምንም እንኳ ክፋት የሌለውና አስፈላጊ የሆነ ቢሆንም ብዙዎችን እያሳሳቀ ወስዷል:: እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት፤ ነገር ግን አንድ የምንዘነጋው ጉዳይ ቢኖር የGraphics Design ሙያ እንዲስፋፋ የሠዓልያን መስዋዕትነት የበዛ መሆኑን ነው፡፡ ሙያው በሃገራችን ባላፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ቢስፋፋም ሥነ-ጥበባዊ የፈጠራ ዋጋው እየመነመነ ቆርጦ በመስፋት (Cut ወይም Copy እና Paste) ላይ ሙጥኝ ብሎ ከተማችንን ለዕይታዊ ብክለት መዳረጉም አይዘነጋም፡፡
ደስታ ከ17 ዓመታት በፊት ከፍርግርግታ ስቱዲዮ በኋላ ከተዛማጅ ሙያ ሙያተኞች ጋር በመሆን አፍሮ ሊንክ ዲዛይን ስቱዲዮን በመመስረት፣ ሙያውን ወደ ተሻለ ከፍታ የማሸጋገር ሚናውን ጀመረ፡፡ የደንበኛን ፍላጎት ማርካት ብቻ ሳይሆን የስራው ግብ መሆን የሚገባውን በሚያሳምን የፕሮፌሽናል ከፍታ መድረስና አብረውት የሚሰሩትንም የማድረስ ጉዞውን ተያያዘው፡፡ በሂደቱም ራሱን የማነጽ፣ የማንበብ፣ ምርምሮችን የማካሄድ፣ ቀለል ባለ የሃሳብ መስመር፣ አቀራረብና አሰራርን ተከትሎ ውጤታማ በመሆን የስራውን ተጠቃሚዎችም (ደንበኞችን) ስኬታማ የማድረግ ልምድ አካበተ:: ከአምስት ዓመታት በኋላም ድርጅቱን Designlab (የግራፊክስ ዲዛይን ላቦራቶሪ በሚል እሳቤ) በሚል ስያሜ ቀይሮ ሌላ የከፍታ ጉዞ ጀመረ፡፡ Designlab በሃገራችን የግራፊክስ ዲዛይን ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ብቻም ሳይሆን ሙያውን እዚያው ‘ሀ’ ብለው የጀመሩም ሆኑ ሌላ ቦታ ሰርተው የተቀላቀሉ ሙያተኞች፣ ከደስታ ጋር በመስራት ያዳበሩትን ልምድ ተጠቅመው ሌሎች የዘርፉ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን የቻሉ ድርጅቶችን አቋቁመዋል፤ እራሳቸውም ሆነዋል፡፡ ይህን የፓፒ የመልካምነት እውነት ለሌሎች እንዲደርስና ይህ አይነት በጎነት እንዲበዛ ማድረግን መርሳት የለብንም፡፡
ደስታ ማንኛውም ኮሜርሺያል የግራፊክስ ዲዛይን ስራ ሲሰራ፣ ታሪካዊና ሃሳባዊ ዳራዎችና አውዶችን ያጠናል፤ ይህ እንዲሆንም ያዛል፡፡ ጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎች፣ ጽሁፎች፣ ቪድዮዎች፣ ምስሎች፣ መጽሃፍትን ያማክራል፤ ይበረብራል:: ከምርምሩ ያበለጸገውን እሳቤ ወደ ምስልና ዲዛይን በሚቀይርበት ጊዜም ውሱን ነገር ግን አሳማኝ አማራጮችን ይዞ ብቅ ይላል:: የመጨረሻ የዲዛይን ውጤቶቹም ቁጥብ (minimal) እና ነገርን ባጭሩ የሚገልጹ ናቸው:: ብዙ ሃሳቦችን ቀለል ባለ ምስል ያስቀምጣል እንጂ ጥቂት ሃሳቦችን ተረት-ተረት በሚመስል የተወሳሰበ ምስል አያግበሰብስም፡፡ ሃሳቡን ሲያስረዳም ባጭሩ ነው፡፡
ፓፒ፤ ፕሮጀክቶች መለያ ምስል ወይም አርማ ወይም ብራንዲንግ ሲሰራ ለፕሮጀክቱ እሴት መጨመርና የራሱ እንደሆነ ሁሉ አድርጎ መጠበብ፣ በፈጠራ ልዕልናው ላይ የተጨመረለት ጸጋ ነበር፡፡ ይህንንም አብረውት ለሰሩት ሁሉ የሚያወርስና የሚያጎናጽፍም ደግ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር ለግዕዝ ፊደላት በተለይ፣  ለታይፖግራፊ ባጠቃላይ፣ ልዩ ፍቅርና አትኩሮት ነበረው፡፡ የግዕዝ ፊደላት ባሕሪያትን ማጥናት ብቻም ሳይሆን ራሱ የፈጠራቸውና ተግባራዊ ሊያደርጋቸው ሲሰራባቸው የነበሩ አራት የፎንት አይነቶችን ሙሉ የፊደል ገበታ አዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ “ደስታ” በሚል ስያሜ የፈጠረው ፎንት የማጠናቀቂያ ስራ ሲቀረው ብቻ ነበር  ፓፒ ይህችን ዓለም የተሰናበታት፡፡
የደስታ ሕልም Designlab በሙከራ ላይ የተመሰረተ ሥነ-ጥበባዊ የግራፊክ ዲዛይን ላቦራቶሪ እንዲሆን ያደረጋቸው ጥረቶች ስኬት እያመጡ አብረውት የሚሰሩ የዲዛይን ቡድን አባላትም ወደዚሁ ደረጃ ማሻገር ችሎም ነበር:: እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ለምን? ሲባል ደግሞ በይደር ወዳቆየው ሥነ-ጥበብ በተለይም ሥዕል፣ ፎቶግራፍ፣ ዲጂታል ሥዕል፣ የግራፊክ ፖስተር የመስራት ፍቅሩ ላይ ለመመለስ የነበረው ናፍቆት ነው፡፡
ደስታ፤ ሥነ-ጥበብ እና ሥነ-ጥበብን መደገፍ (Patronage)
የቀለም ቅብ ሥዕል (Painting) የደስታ የመጀመሪያ ፍቅረኛ ነች፡፡ የሥነ-ጥበብ ቁስ ጥበባትን በማሰስ ደግሞ የተዋጣለት ፎቶግራፈር፣ ዲጂታል ሥዕል፣ የግራፊክ አርት ባለ-እጅ እንደነበር ለማሳወቅ ህልፈቱን መጠበቅ ነበረብን፡፡ ምክንያቱም ጋለሪዎችና የሥነ-ጥበብ አጋፋሪዎች፣ ስራዎቹን በትርዒት እንዲያቀርብ ቢወተውቱትም በጄ አላለም ነበር፡፡ የሰለጠነ የጥበብ ልቦና እንደነበረው የሚያመላክቱ አንድ ሁለት አብነቶችን እናንሳ፡፡ ከሃያ አመታት በፊት ገና ፍርግርግታ ስቱዲዮ ሳሉ በተለያዩ ጽንሰ-ሃሳቦች ላይ ለመስራት የቤት ስራ ይወስዳሉ:: ፓፒ ስሎ የመጣው ራስን በራስ የማጥፊያ ወይም የመታነቂያ ገመድ ነበር፡፡ የሳለው ገመድ ሲጥ እንደሚያደርግ ጥርጥር እንደሌለው ያስታውቃል፡፡ ሆኖም የገመዱ ቀለማት ብሩህና በመላእክት ክንፎች የተለበጡ ነበሩ፡፡ ይህን ያደረገበት ምክንያት ደግሞ ሞት ምንም ያህል ጽልመት ቢሆንም ራሱን የማጥፋት ቁርጥ ሃሳብ ያደረገ ሰው በመሞቱ የተሻለ ብሩህነት ቢያይ ሊሆን እንደሚችልና ከሞት በኋላ ያለውን ዓለም ማንም ያላየው በመሆኑ ጽልመቱን ብቻ ማሰቡ ልክ ላይሆን እንደሚችል ያለውን ግምት ያንጸባረቀበት ነበር፡፡
ሌላው በ2011 ዓ.ም. መጀመሪያ በጉራምዓይኔ የሥነ-ጥበብ ማዕከል በቀረበው “ነጋሪ/MANIFESTO” ትርዒት እንዲሳተፍ የትርዒቱ አጋፋሪ ግብዣ ያቀርብለታል፡፡ ትርዒቱ በወቅቱ የሃገራችን ፖለቲካ ምክንያት፣ በታሪካችን የቆለልናቸውን የቤት ስራዎች የሚዳስስ ነበር:: ፓፒ ላስብበት በማለት በሳምንት ቀጠሮ ይለያያሉ፡፡ ከቀጠሮአቸው ሶስት ቀናት ቀደም ብለው ለሌላ ጉዳይ ሲገናኙ ያነሳሱታል፡፡ ፓፒ ጅምር ያለውን ያሳየዋል፡፡
ስራው በግራፊክስ ኮምፒውተር ላይ የተሰራ ጥቁር  ደም የያዘ ጉሉኮስ (I.V. አይ ቪ) ሲሆን እላዩ ላይ ያለው A, B, O... ወዘተ በሚል መጻፍ የነበረበትን የደም አይነት መግለጫ፣ በግዕዝ ፊደላት የተጻፉ የሃገራችን ብሄሮች በአጭር የተጻፈበት ነበር፡፡ ስራው፤ ብሄርና ሰውነት የተምታታብን ደረጃ ላይ መድረሳችንን የሚያሄስ ነበር፡፡ መቼስ የፓፒ ስራዎች ለፍጹምነት (Perfection) ምን ያህል የተሰጡ መሆናቸውን ለማወቅ ማየት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ፓፒ ግን ስራውን በትርዒቱ ለማቅረብ አሻፈረኝ እንዳለ ጸና፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሰራው ስራ “ነጋሪ/MANIFESTO” ለተሰኘው ሃሳብ ይመጥናል የሚል እምነት እንደሌለው በመግለጽ ነበር፡፡ ውስጠ-ወይራው ግን መታወቅን መሸሹ ነበር፡፡
ደስታ የተዳፈነ የሥነ-ጥበብ ፍቅሩን፣ ትኩረቱንና ናፍቆቱን የሚያስታግሰው ለሠዓልያንና ለሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡ ቅርብና አጋዥ በመሆን ነበር፡፡ ሥዕሎችን ይገዛል፤ ይሰበስባል፡፡ በሥነ-ጥበብ ትርዒቶች ላይ በመገኘት ሃሳቦችን ያቀብላል፤ ያበረታታል። ሠዓልያንና ጋለሪዎች ለሚሿቸው የዲዛይንና የሕትመት ድጋፎች የማይሰስት እጁን ይዘረጋል፡፡ ሠዓልያንና ስራዎቻቸውን በጥሞና የሚከታተል፣ የሚያዳምጥ፣ ኃይልና ጉልበት የሚሰጥ፤ የሚጠይቅ ብቻም ሳይሆን የሚያፋጥጥና የሚመረምር  ጥልቀትና ልቀት የሚያጎናጽፍና የሚያበረታ ነፍስ ያለው ሰው ነበር፡፡ ሠዓልያንና ጋለሪዎች አሰራራቸው እንዲዘምን የሚያማክርና የሚደግፍ ነበር፡፡ የክቡር የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ዌብሳይትን ዲዛይን ማድረግና ከ12 ዓመታት በላይ እንዲሰራ ከፍሏል፡፡ ሠዓልያን ስራዎቻቸውን መሸጥ በሚቸገሩባቸው ጊዜያት ከፍሎ በማሰራት (ኮሚሽን በማድረግ) የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ያነሳሳ ነበር፡፡ ደስታ ለሁሉም የሚሞቅ የጠዋት ጸሐይ ነበር፡፡
ደስታ፤ ሰውየው ባጭሩ
ደስታ ማሕደረ፤ ከአባቱ መቶ አለቃ ማሕደረ ደስታ እና ከእናቱ ወ/ሮ ሰናይት መሸሻ ጥር 17፣ 1971 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተወለደ፡፡ የሰው ልጅ ራሱን ለማግኘት በሚያልፍባቸው የአስተዳደግ፣ የአካባቢ፣ የትምሕርትና የሕይወት ጉዞ ውስጥ ደስታ ራሱን በመቅረጽ ሂደት የሚወደውን ሰርቶ ለመኖር፤ በሚሰራውም ሰዎች እንዲደሰቱና ለውጥ እንዲያመጡበት ለማድረግ ብዙ ይታገልና ይጥር ነበር፡፡ ይህም ክቡር የሆነው የሰው ልጅንና ሕይወትን ከመውደድ የመነጨ ነበር፡፡
ደስታ ገና በለጋ ወጣትነቱ ማለትም ከሃያዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ጀምሮ ለሃገራችን የሥነ-ትምህርትም ሆነ የሥነ-ውበት ዘርፎች መሃከል የግራፊክስ ዲዛይን ሙያ በቅጡ በማይታወቅበት ጊዜ ሙያውን በራሱ ተነሳሽነት በመጀመር ለእድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት ሙያተኞች በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት  አንዱ ነው፡፡ ሆኖም ለሚወደው ሙያ መክፈል የነበረበት መስዋዕትነት በስኬት የታጀበ እንዲሆን ብዙ መጣር፣ ብዙ ራስን ማስተማር፣ ብዙ መስጠትንና ብዙ ማካፈልን በመጨመር ለብዙዎች ስኬትና ውጤታማነት በታታሪነት ሲሰራ ኖሯል፡፡ በእርግጥም የሰው ልጅ በዚህች ዓለም ኖሮ ሲያልፍ የሚቀረው ለራሱ ምን ምን እንዳተረፈ ሳይሆን ለሰዎች ምን ምን እንዳበረከተ ነውና የደስታ ሙያዊ አበርክቶቶች ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ ከግለሰብ እስከ ተቋም፤ ከኩባንያዎች እስከ ማሕበራዊ ድርጅቶች፤ ከሃገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፕሮግራሞች ድረስ በመሳተፍ፤ ዓይን-ከፋችና የትኩረት መስህብ እንዲሆኑ ያስቻሉ ስራዎችን መስራትና ለበርካታ የግራፊክ ዲዛይንና ሌሎች ሙያተኞች የስራ ዕድል ሲፈጥር ኖሯል፡፡ ደስታ የግራፊክስ ዲዛይን ሙያ፣ ከሙያ በዘለለ የፕሮፌሽናል ሴክተር ኢንዱስትሪ እንዲሆን ታላቅ ሕልም የነበረውና ለዚህም ሲተጋ የኖረ ሲሆን ያቋቋመውን ዲዛይን ላብን ከቀዳሚዎቹና ከተጽዕኖ ፈጣሪዎቹ ዘንድ ማሰለፍ ችሏል፡፡  
ደስታ በቤተሰቦቹ፣ በጓደኞቹና በስራ አጋሮቹ ልቦና ውስጥ የሚቀሩ ትውስታዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ለምን እንደሚታወሰን ጭምርም ነው፡፡ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር እንደሚለው፤ እሴት ያለው ሕይወት መኖር ባጋጣሚ የሚመጣ፤ አልያም ሁኔታዎች የሚወስኑት ጉዳይ ሳይሆን ራሳችን መርጠን የምንፈጽመው እንደሆነ በተግባር ያሳየ ሙሉ ስብዕና ያለው ሰው ነበር፤ ደስታ፡፡ ምሉዕነቱም ከራሱ ባሻገር ለሌሎች መነሳሳትን በመፍጠር፣ የሰዎች ኑሮና አስተሳሰብ ላይ የጎደለውን ለመሙላት ያለው ቅንነት፣ ደግነትና ተነሳሽነት፣ ሁኔታዎችንና አካባቢውን በቀላሉ በመረዳትና ለችግሮች መፍትሄ ማበጀት መቻሉ፤ ለሚያነሳቸው ወይም ለሚያማክራቸው ግላዊም ሆነ የስራ ጉዳዮች ጥልቀትና ስፋት እንዲሁም ነገሮችን ተርታ በሆነ ሳይሆን ልዩ በሆነ አውታር መመልከት መቻሉ ነው፡፡
ደስታ በግላዊ ሕይወቱም ዘወትር ጠዋት ከቤቱ ሲወጣ ብቻም ሳይሆን ወደ ፈጣሪው ቀና ማለትን የሚያዘወትር በፈጣሪው እምነትና ተስፋን የሚጥል ነበር፡፡ እሱ መንፈሳዊ ጥያቄዎች አልነበሩትም፡፡ ካለው ለሌሎች ማካፈልን የኑሮውና የሕይወቱ መርህ ማድረግ ብቻም ሳይሆን ይኖረውም ነበር፡፡
ለሙዚቃና ለሥነ-ግጥም ልዩ ፍቅር ነበረው ደስታ፡፡ የሰለሞን ደሬሳ አድናቂም ነው፡፡ ለሥነ-ጥበብ በጠቅላላው እንዲሁም ለኢትዮጵያ ዘመንኛ ሥነ-ጥበብና ሥዕል፣ ጥልቅ ፍቅርና ልባዊ ቅርበት የነበረው ሲሆን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት፣ የሃገራችን ሠዓልያንን ሲያበረታ፣ ሲያግዝና የሥዕል ስራዎችን ሲሰበስብ የነበረ የጥበቡ ዓለም እውነተኛ ወዳጅ ነበር፡፡ ለሥነ-ጥበብ የሰጠው ፍቅርና አክብሮት፣ በኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብን የመደገፍ ወይም የፓትሮኔጅ ታሪክ እንዲሁም ሠዓልያን ልቦና ውስጥ ህያው ሆኖ ይኖራልም፡፡ ደስታ ከብዙዎች ተሸሽጎና ከሥነ-ጥበብ ትርዒቶች ራሱን አግልሎና ደብቆ ቢኖርም፣ የፈጠራ ችሎታው ከሙሉ ጊዜ አርቲስትነትና ሠዓሊነት የሚያሰልፈው ነው፡፡ ይህም በቀጣይነት በምንመለከታቸው ስራዎቹ ይፋ የሚሆን ነው፡፡
በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ አንድ ታላቅ ባለሙያና የሥነ-ጥበብ ደጋፊ አጥታለች፡፡
ደስታ ማሕደረ ከባለቤቱ ቅድስት አሰፋ ጋር ለአራት ዓመታት በትዳር የኖረ ሲሆን የማንነቱ አውታር የሆኑት የፍቅር፣ የደግነት፣ ከልብ-የሚፈነቀሉ የደስታ እንዲሁም የሰውኛ ሰናይ ባሕሪያትን ለትዳር ሕይወቱ፣ ለቤተሰቦቹና ዘመድ አዝማዶቹ እንዲሁም ለጓደኞቹና ለማሕበራዊ መስተጋብሮቹ ሲለግስ ኖሯል፡፡
ደስታ ማሕደረ መስከረም 19, 2012 ባልተጠበቀ ቅጽበት ሕይወቱን ቢያጣም፣ በልቦናችንና በልባችን ጠብቀን ልናኖራቸው የሚገቡ እሴቶችን ትቶልን አልፏል፡፡ ምን ማለቴ ነው? እንዲህ አይነቱን ተወርዋሪ ደስታ ብናጣም እንዴት ነው እንዲህ ወይም ሌላ አይነቱን መፍጠር የሚቻለው ለማለት ነው፣ ይህን ሁሉ የምለው፡፡ ያ እስኪሆን ድረስ ግን መርሳት ፍጹም የተከለከለ፣ ደስታ የሆነውን መዘንጋት ነውር በመሆኑ ነው  ይህ ጽሁፍ የተሰናዳው:: ፓፒ ምድርን ቀለል አድርጎ እንደኖራት ሁሉ አሁንም አፈሩ ይቅለለው፡፡ ቸር እንሰንብት!!!


Read 2965 times