Saturday, 12 October 2019 12:20

የከበደ ሚካኤል ዝንጀሮና ኢትዮጵያ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(4 votes)

ደራሲ ከበደ ሚካኤል የፈጠሯት አንድ ዝንጀሮ አለች፡፡ ዝንጀሮዋ እንደ ማንም ዝንጀሮ በጫካ የምትኖር ናት፡፡ ዝንጀሮዎች መኖሪያቸው ባደረጉት ጫካ ውስጥ ችግር ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይታሰብም፣ የከበደ ሚካኤል ዝንጀሮ ግን ክፉ ፈተና ደርሶባታል፡፡ በምታውቀውና ጥርሷን ነቅላ ባደገችበት ጫካ ውስጥ መንገድ ጠፍቷት ስትባክን ውላለች፡፡ መውጫ ፍለጋ ስትንከራተትም፣ አካሏ ክፉኛ በእሾህ ተወግቷል::  ከወጋት እሾህ በላይ አካሏ ውስጥ የተሰገሰገው እሾህ ስቃይዋን አብዝቶታል። እንደ ምንም ጥራ ተጣጥራ ከጫካው  ብትወጣም፣ እንደ ልቧ መንቀሳቀስ አልቻለችም፡፡ በደረሰባት ጉዳት እያቃሰተች ሳለ አንድ ሰው ያገኛታል - ምን ልርዳሽ ሲልም ይጠይቃታል፡፡ ‹‹መጀመሪያ የመቀመጫዬን አውጣልኝና ተቀምጬ ትንፋሽ መሰብሰብ ልቻል፡፡ ከዚያ ሌላውን እኔ ራሴ እነቅለዋለሁ›› ስትል  ነው የመለሰችለት፡፡  
በየዓመቱ በመስከረም የመጨረሻው ሰኞ ላይ፣ የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባቸውን ያካሂዳሉ:: በሕገ መንግሥቱ መሠረትም፣ የወቅቱ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት  የመክፈቻ ንግግር ለሁለቱ ምክር ቤት ተሰብሳቢዎች ያደርጋሉ፡፡ ባለፈው ሰኞ፣ ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ በዚህ ዓመት በመንግሥት ይከናወናሉ የተባሉ ጉዳዮችን ጠቅለል አድርገው ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ በንግግራቸው የመጀመሪያ ክፍል ካተኮሩባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ  ሰላምና መረጋጋት ይገኙባቸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት አገርን ከዳር እዳር የናጠው የማን አለብኝነት እንቅስቃሴ ብዙዎችን ከአካባቢያቸው እንዳፈናቀለ፣ ሀብት ንብረታቸውን እንደነጠቀ፣ ንብረት እንዳወደመ፤ የዜጎችን  ውድ ህይወት እንደቀጠፈ  ይታወቃል::
ምስሉ ከአዕምሯቸው ጓዳ የጠፋ የማይመስለው ፕሬዚዳንቷ፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው እንደነበር፣ ከተፈናቀሉት ውስጥ ብዙዎቹም ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው መመለሳቸውን ጠቁመው፣ ዛሬም አንድ መቶ ሺህ ገደማ ሰዎች መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ዘንድሮ ከዚህ አይነት ችግር የፀዳ ይሆን ዘንድ መንግሥት ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጸል፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበር እያሉ ለጮሁ ወገኖች ተስፋ የሚሰጥ ቃል ነው፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ሰላም በእያንዳንዱ ሰው አዕምሮ ውስጥ የሚኖር ጉዳይ  ነው፡፡ ግን ደግሞ ለሰላም የማይገዛ ሕሊናን፣ ለወንጀል ሥራ የሚዘረጋ እጅን ለፍርድ ማቅረብ የመንግሥት ቀዳሚ ሥራ መሆኑ ሊዘነጋ  አይገባም፡፡  
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት፣ የሥልጣን እርካቡን በረገጠ ማግስት ይሻሻላሉ ብሎ ቃል ከገባባቸው ጉዳዮች መካከል፡- የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚገድቡ ሕጎች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ደግሞ የፀረ ሽብር አዋጁ ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬም አዋጁ ለዜጎች መከሰሻና መንገላቻ ሆኖ እየሠራ ይገኛል፡፡ እስከ አሁን የተሻሻሉት የበጎ አድራጎት አዋጅና የምርጫ ሕግ ሲሆን የፕሬስና የመረጃ ነፃነት ሕግ ሳይነኩ ቀርተዋል፡፡ የብሮድካስት አዋጅም እንዲሁ፡፡
ክብርት ፕሬዚዳንቷ፤ በዚህ ዓመት ከተያዘው ወይም ሊሠራ ከታቀደው ውስጥ ሕጎችን ማሻሻልና አዲስ ሕጎችን የማውጣት ተግባር አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ቃል እንደ ከዚህ ቀደሙ ውሃ በልቶት እንዳይቀር እንፀልያለን። በተለይ በተለይ የጸረ-ሽብር አዋጁና የፕሬስና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፡፡
ሴትየዋ ባሏን አጋድማ ትረግጠዋለች:: መጀመሪያ ላይ “ወንድ ልጅን እንዴት ሴቷ ደበደበችው?” ይባላል  ብሎ በዝምታ ለማሳለፍ ሞከረ፡፡ ዱላው እየበዛ ሲሄድ ‹‹ኧረ ተጋደልን›› ብሎ ጮኸ፡፡ እሷ ግን ቀላል አልነበረችም፤ “ለይ” ስትል አፋጠጠችው፡፡
 ባል ሆዬም፤ ‹‹ገደለችኝ›› ብሎ ጮኸ ይባላል::
መንግሥትም አንዳንድ ነገሮችን መለየት ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ በከፊል ይሸጣል ስለተባለው ኢትዮ-ቴሌኮም ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም፡፡ በከፊል ወደ ግል ይዛወራል እየተባለ፣ በቴሌኮም የሥራ መስክ ሁለት አዳዲስ ተቋማት እንደሚመሰረቱ ፕሬዚዳንቷ ገልፀዋል:: የቴሌ በከፊል መሸጥ ቀረ እንዴ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ለነባሩም ሆነ አዲስ ለሚመጡት የቴሌኮም ድርጅቶች መንግሥት የአመራር ነፃነት ሊሰጣቸውና ያንንም  ሊያከብርላቸው ይገባል፡፡ ይህን ካደረገ በእርግጥም እድገትን ማሳካት  ይቻላል፡፡
አንድ ወይም ሁለት ዓመት ወደ ኋላ ተመልሰን የአንዳንድ ስብሰባዎችን ፍፃሜ ስናይ የምናገኘው ማጠቃለያ፣ ይህ ጉዳይ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካትቶ፣ ለተማሪዎች መቅረብ አለበት የሚል ነው፡፡ እስከማውቀው ድረስም የመማሪያ መጻሕፍት የሚቀየሩት ምርምር ተደርጎና የሚጎድለው ተፈትሾ አይደለም:: ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው እንደሚቋቋም የገለፁት የትምህርትና የምርምር ተቋም “እንኳን ደህና መጣህ” የሚባል ተግባር እንደሆነ አምናለሁ፡፡
እምነቴን የሚፈታተነኝ ስለ መብራት አቅርቦት የተነሳው ጉዳይ ነው፡፡ በየክልሉ የተቋቋሙና በመቋቋም ላይ ያሉ የኢንዱስትሪ ቀበሌዎች (ፓርኮች) አያሌ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ደግሞ ሃያና ሰላሳ ኢንዱስትሪዎችን በውስጣቸው እንደያዙ ይታመናል፡፡ በሌላ በኩል፤ በአጠቃላይ በአገሪቱ ከፍተኛ የሃይል እጥረት መኖሩንም አሳምረን እናውቃለን፡፡ ከዚህ አንጻር፣ ለመብራት የተሰጠው ትኩረት በቂ ሆኖ አልታየኝም ወይም አልተሰማኝም፡፡ ኧረ ይታሰብበት እላለሁ፡፡   
የአንድ አገርን መንግሥት በሌሎች አገራት ሕዝብና መንግሥት ፊት ሞገስ እንዲያገኝ የሚያደርጉት የዲፕሎማቲክ መልዕክተኞቹ ማለትም አምባሳደሮች ወይም ቆንስሎች ናቸው፡፡ በንጉሡ ዘመን (የደርግን አላወቅም) አምባሳደርነት ከቤተ መንግሥት አካባቢ ማራቂያ፣ አንዳንድ ጊዜም እንደ መጦሪያ ሹመት የሚቆጠር ነበር፡፡ ኢሕአዴግም ከዚህ የተለየ ነገር አላመጣም፡፡ የቀድሞ የክልል ፕሬዚዳንቶች የተሸኙት ወደ አምባሳደርነት ነው፡፡ ለአምባሳደርነት የሚመጥኑም ሆነ የማይመጥኑ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይሄ ዓይነቱ አሰራር መታረም ይገባዋል፡፡ ሌሎች አገራት አምባሳደር  የሚመድቡት ተሿሚው የሚሄድበት አገር ቋንቋን፣ ባህልንና ታሪክን ወዘተ አስጠንተው ነው፡፡ ኢትዮጵያስ ቢያንስ ይህን ማድረግ እንዴት
ይሳናታል?
መንግሥት ያሰበውን በአግባቡ የሚፈፅመው፣ ሕገ ደንብ የራሱን አስተዋፅኦ ሊያበረክት የሚችለው አገር አማን ሲሆን  ነው:: መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር ሲችል ነው፡፡ አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ ግን የአቶ ከበደ ሚካኤል ዝንጀሮ ካለችበት ሁኔታ የተለየ አይደለም፡፡ በየቦታው በየምክንያቱ የሚቀሰቀሰው ግርግርና ግጭት፣ ለነገ ማሰብና ማቀድን አዳጋች የሚያደርግ ነው፡፡ ዜጎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው ያለ ሥጋት መንቀሳቀስ ተስኖአቸዋል፡፡ አንዳንድ አካባቢ በመከላከያ ሃይል ነው የሚጠበቀው፡፡ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች ዛሬም በየጎጇቸው በራፍ ላይ ቆመው ስለ ራሳቸው ይጮሀሉ፡፡ አንዳቸውም ወደ መሃል ሲመጡ አይታይም፡፡ በየአካባቢው “አትለውም ወይ” የሚለው የጎበዝ አለቃም  በዝቷል፡፡ ማቁሰል መቋሰል፣ ማብሸቅ መበሻሸቅ ሙያ ሆኗል፡፡ ዛሬ የምንገኘው በዚህ ውስጥ ነው፡፡ ነገስ? ኢትዮጵያ ትንፋሿን ሰብስባ ወደ ፊት ትራመድ ዘንድ ፋታ ትፈልጋለች - እሾህ የመንቀያ!!  

Read 6857 times